ልጆች እንዴት ናችሁ? ሰላም ነው? ለዛሬ ይዤላችሁ የመጣሁትን እንግዳ እንዴት እንዳገኘሁት ልንገራችሁና ይህ ጎበዝ ልጅ ምን እንደሚሰራ አብረን እናነባለን።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ በሰላም የሕጻናት መንደር ጋር በመተባበር ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል! በሚል መሪ ቃል የንባብ ሳምንት፣ ዓለም አቀፍ የሕጻናት ቀን፣ የመጽሐፍት አውደ ርዕይና አውደ ውይይት መርሐ ግብር በቅርቡ አካሄዶ ነበር። በእለቱ ከተጋበዙ ታላላቅ እንግዶች መካከል “የአውሮፕላን በረራ ምስጢሮች” መጽሐፍ ጸሐፊ ታዳጊ ቅዱስ የሸዋስም አንዱ ነበር።
አይገርማችሁም ልጆች ይህ ልጅ ገና በለጋ እድሜው የክብር እንግዳ ሆኖ በመጋበዝ የሕይወት ተሞክሮውን ለሌሎች ሲያካፍል? ልጆቼ ህልማችሁን አውቃችሁ ህልማችሁ ጋር የሚያደርሰውን ትክክለኛ መንገድ ከመረጣችሁ እንደ ቅዱስ ከታላላቆች እኩል የክብር እንግዳ የማትሆኑበት ምክንያት አይኖርም።
ልጆች ቅዱስ በመድረኩ ላይ ስለሰራውና ስለራሱ እንዲህ ሲል ተናግሯል በትዕግስት አንብቡ እሺ! መልካም ቆይታ። ቅዱስ የሽዋስ የአቡነ ጎርጎሪዮስ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ገና በህፃንነት እድሜው አውሮፕላንን
ሲመለከት እንዴት መብራር ቻለ? በሚል ውስጡ ጥያቄ ይፈጠርበት ነበር። ይህንኑ ለእናትና ለአባቱ ጥያቄ ያቀርብ ነበር።
ጥያቄውን የተረዱት ወላጆቹ ስለ አውሮፕላን “የበረራ ሚስጢሮች” የሚናገሩ መፃህፍትን በማቅረብ ኢንተርኔት እንዲመለከትና በተለያየ መልኩ ስለዚህ ጉዳይ እውቀት ያላቸውን ሰዎች በማገናኘት ስለአውሮፕላን በረራ ሚስጢሮች ያሉትን ጥያቄዎች ለመመለሰ ይሞከር ነበር። የመፅሐፉ ሀሳብ በልጅነቱ የቀረቡ ጥያቄዎችንና መልሶቻቸውን፤ ከተለያዩ በሙያው ውስጥ ካሉ ሰዎች መልስ ሲያገኝ የፃፈው በመሆኑ በመፅሐፍ እንዲታተም አድርጎታል።
የአስራ አራት አመቱ ልጅ ቅዱስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጥረቱን አይቶ አየር መንገዱን ያስጎበኘው ሲሆን ሽልማትም ሰጥቶታል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህን ያደረገው ልጁ ሲያድግ በድርጅቱ ውስጥ ሰራተኛ መሆኑ እንደማይቀር ለራሱ ቃል ገብቶለት ነው።
በእለቱ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ ለሰላም የሕጻናት መንደር መስራች ለወይዘሮ ጸሐይ ሮስሊ የተበረከቱ በብር 85 ሺህ የፈጁ በቁጥር 1100 መጻሕፍት የተበረከተ ሲሆን ቅዱስም መፅሃፉን ለሰላም ህፃናት መንደር መሰራች፤ ለኤጀንሲው ሀላፊዎች በወቅቱ ለነበሩ ትላልቅ ሰዎች በስጦታ አበርከቶ ነበር። ቅዱስ ከህፃንነት እድሜው አንስቶ እስከ አስራ አራት አመት እድሜው ያሳለፈውን የሕይወት ተሞክሮ ለታዳሚው በስፋት ያቀርበ ሲሆን ለታዳጊው ከኤጀንሲው የተዘጋጀ የምስክር ወረቀት እና የተለያዩ ይዘት ያላቸው መጽሐፍት ተበርክቶለታል፡፡
ልጆቼ ቅዱስ ጎበዝ ነው አይደል? ታዳጊው በአሁኑ ሰዓት ሁለተኛውን በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተፃፈ መጽሐፍ እየፃፈ እንደሆነ ተናግሯል። መጽሐፉ ስለ አውሮፕላን ዲዛይን እድገቶች የሚያብራራ መጽሐፍ ነው።
ልጆች መጽሐፍትን ለመጻፍ የቻለው ብዙ ስለሚያነብ እንደሆነ ቅዱስ ተናግሯል። ስለዚህ ለማወቅ የፈለጋችሁትን ዕውቀት በሙሉ ማወቅ የምትችሉት መጽሐፍ በማንበብ ነውና ጎበዝ አንባቢ ለመሆን መጠንከር አለባችሁ። ቅዱስም በማንበብ ብዙ እውቀት ማግኘት ትችላላችሁ ብሏችኋል። ልጆች የቅዱስን ምክር ሰምታችሁ አንብቡ! በርቱ! ጠንከሩ እሺ!። መልካም ጊዜ ይሁንላችሁ።
አሥመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን የካቲት 20 /2014