የምንጊዜም የቦክስ ስፖርት ንጉሱ መሐመድ አሊ የዓለም የቦክስ ቻምፒዮንና ታላቅ የቡጢ ተፋላሚ ብቻ አልነበረም።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፤ የጥቁር ሕዝቦች ሰንደቅ፤ በመላው ዓለም በስፖርትና በታላቅ ስብዕና ተምሳሌትም ጭምር ነው። ብዙዎችን ቦክስ ስፖርት ሳይሆን የጥጋበኞች ድብድብ አድርገው ከመሳል አስተሳሰብ አውጥቶ የቦክስን ስፖርት ጥበባዊ ገፅታ በማላበስ ተወዳጅና አሁን ላይ በዓለማችን በአንድ ጊዜ በርካታ ሚሊየን ዶላሮች የሚያሳቅፍ ግንባር ቀደም ስፖርት እንዲሆን ተፅዕኖውን አሳርፏል።
ሙዚቀኛም ሆኖ ለሂፕ ሆፕና ራፕ የሙዚቃ ስልቶች ጉልህ ሚና ተጫውቷል። በቦክስ ስፖርት ታሪክ የምንጊዜም ምርጥ ቦክሰኛ የተባለውም በተለያዩ የቡጢ ፍልሚያዎች ዘመን የማይሽራቸው ገድሎችን በማስመዝገብ ነው። መሐመድ አሊ የቦክስ ጓንቱን ሰቅሎ ስፖርቱን በቃኝ ብሎ ከተሰናበተ ከሦስት ዓመታት በኋላ እኤአ በ1984 ከስፖርቱ ልምድ ጋር በተያያዘ ፓርኪንሰንስ በተባለ በሽታ ተያዘ።
ለሰላሳ ሁለት ዓመታት ከዚህ ህመሙ ጋር ሲታገል ቆይቶ ከአምስት ዓመት በፊት በሰባ አራት ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
የጥቁር ሕዝቦች ወር በሆነው የካቲት መሐመድን አለማስታወስ አይቻልምና በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችን ከብዙ በጥቂቱ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል። መሐመድ አሊ ወደ ቦክስ ሕይወት የመጣበት አጋጣሚ አስገራሚ ነው። የአስራ ሁለት ዓመት ልጅ በነበረበት ወቅት ብስክሌቱ ተሰርቆበት በሊውስቪል ኬንታኪ ለሚገኝ ጆ ማርቲን ለተባለ ፖሊስ አመለከተ። «የሰረቀኝን ባገኘው ልክ አገባው ነበር» ብሎም ምሬቱን ይገልፃል።
የቦክስ አሰልጣኝ የነበረው ፖሊስ ትንሹን መሐመድ ራሱን እንዴት ከጥቃት መከላከል መማር እንዳለበት መከረው። የተወሰኑ ስልጣናዎችን ሲወስድ ቆይቶም ብስክሌቱ ከተሰረቀች ከስድስት ሳምንታት በኋላ በሰፈሩ በአንድ አማተር የቦክስ ግጥሚያ ላይ ተሳተፈና በነጥብ አሸናፊ መሆን ቻለ። ይህች አጋጣሚም በዓለም በገነነበት ስፖርት የመሰረት ድንጋይ ነች።
መሐመድ የትውልድ ስሙ ካሴስ ክሌይ ቢሆንም፣ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ባሮችን ነፃ ለማውጣት በታገሉ ታላቅ ሰው መታሰቢያነት የወጣለት ስም ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ከባድ ሚዛን ቻምፒዮን ከሆበኋላ በማግስቱ ስሙን ለመቀየር ወሰነ። የነፃነት ታጋዩን ማልኮለም ኤክስ ከጎኑ አድርጎ በሰጠው መግለጫ «ዘ ኔሽን ኦፍ ኢስላም» የተባለውን ተቋም መቀላቀሉን በማሳወቅ የባርያ ስም ይለው የነበረውን ካሴስ ክሌይ በመቀየር በቀድሞ ስሙ ላለመጠራት ወሰነ።
በወቅቱ «ኔሽን ኦፍ ኢስላምን» ይመራ የነበረው ኤልጅያህ መሃመድ እኤአ በ1964 ላይ መሐመድ አሊ የሚለውን ስም ካወጣለት በኋላ እሱን በማፅደቅ እስከ ሕይወት ዘመኑ መጨረሻ ተጠራበት። ለ21 ዓመታት በፕሮፌሽናል ቦክሰኛነት በርካታ የቡጢ ፍልሚያዎችን ከአሜሪካ እስከ አፍሪካ እንዲሁም ሌሎች ዓለማት ላይ የተፋለመው መሐመድ አሊ ለሦስት ጊዜ የዓለም ከባድ ሚዛን ቻምፒዮን ሆኗል። ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም የከባድ ሚዛን ቻምፒዮን ለመሆን የበቃውም የ22 ዓመት ወጣት እያለ ነው። ዓለም አቀፍ ደረጃ ባላቸው ፕሮፌሽናል የቦክስ ግጥሚያዎች ላይ 61 ጊዜ ተሳትፎ 56ቱን ማሸነፍም ችሏል።
ከነዚህ ድሎቹም 37 ያህሉን ተጋጣሚዎቹን በበቃኝ በመዘረር ነው። አስገራሚው ነገር በ31 ተከታታይ የቦክስ ግጥሚያዎች ሳይሸንፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሸነፈው የክፍለ ዘመኑ ምርጥ ፍልሚያ በተባለው ግጥሚያ በጆ ፍሬዘር ነበር። በፕሮፌሽናል የቦክሰኛነት ዘመኑም ሽንፈትን የቀመሰው 5 ጊዜ ብቻ ነው።
የመጨረሻው ፍልሚያም እኤአ በ1981 ከትሬቨር ቤሪቢክ ጋር በማድረግ ስፖርቱን በቃኝ ብሏል። አሜሪካ በቬትናም በ1970ዎቹ መጀመሪያ ያደረገችውን ጦርነት በመቃወሙ ለ3 ዓመታት ከፕሮፌሽናል ቦክስ ውድድሮች ታግዶ የቆየው መሐመድ አሊ እገዳው በተጣለበት ወቅት ከ10 የማያንሱ የዓለም ከባድ ሚዛን ቻምፒዮናዎች ባያመልጡት አሁን ካሉት የበለጠ በርካታ ክብሮችን መጎናፀፍ ይችል ነበር። በዚህም ከ80 ሚሊየን ዶላር በላይ ሀብት ማፍራት
ችሏል። ለዚህም ሀብቱ ምንጭ ስፖርቱን ከተሰናበተ ወዲህ ግንባር ቀደም ተዋናዮቹ ስሙንና ምስሉን የሚጠቀሙ ከ40 በላይ ኩባንያዎች ናቸው።
ታሪካዊው ኢትዮጵያዊ አትሌት አበበ ቢቂላ በ196o የሮም ኦሊምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ ለጥቁር ሕዝቦች የመጀመሪያውን የማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ሲያስመዘግብ መሐመድ አሊም በቦክስ የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቆ ነበር። ሁለቱ ታሪካዊ የጥቁር ሕዝቦች ከዋክብት ፊርማቸውን ተለዋውጠውም ነበር። ይሁንና መሐመድ አሊ ይህን የወርቅ ሜዳልያውን ለአገሩ ከማበርከት ይልቅ በሊውስ ቪል ግዛት በሚገኘው የኦሃዮ ወንዝ ጨምሮታል።
ሜዳልያውን ለአሜሪካና ለትውልድ ከተማው ሊውስ ቪል ቢቀዳጅም ለጥቁሮች በርገር የመግዛት መብት ባለመኖሩ ተቃውሞውን ለመግለፅ ነበር ይህን እርምጃ የወሰደው። በ1996 አገሩ አሜሪካ ባስተናገደችው የአትላንታ ኦሊምፒክ ችቦውን እንዲለኩስ ከመደረጉ ባሻገር ወንዝ የጨመረው የወርቅ ሜዳልያ ምትክ ሌላ ሜዳሊያ በአንገቱ ተጠልቆለታል።
በ1970 የዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ መታሰቢያ ሽልማት የተቀበለው መሐመድ አሊ፤ የዓለም አቀፋዊ ወዳጅነት ተምሳሌት ሆኖም ያውቃል። የተባበሩት መንግስታት የሰላም መልዕክተኛ ሆኖም ከ1998 እስከ 2008 በታዳጊ አገራት በመዘዋወር አገልግሏል።
መሐመድ አሊ በንግግር ችሎታው፤ በልዩ የግጥም ስንኞቹም ተወዳጅነት ያተረፈ ነው። «በማይሞት እምነትና ፍቅር የተሻለ ዓለም መፍጠር እንደሚቻል አሳይቶናል። ሁሌም ቻምፒዮን ነው»። በማለት በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ባራክ ኦባማ በመሐመድ ስርዓተ ቀብር ላይ ተናግረዋል። በርካታ የዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪና ታላላቅ ሰዎችም ተገኝተው መሐመድን ወደማይመለስበት ሸኝተውታል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 20 /2014