ወጣት ሲሀም አየለ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው እዚሁ አዲስ አበባ ሲሆን ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርቷን ያጠናቀቀችው «ናዝሬት ስኩል» ተብሎ በሚታወቀው ሴት ተማሪዎች ብቻ በሚማሩበት ትምህርት ቤት ነው።
የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስ እና ኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ ተቀብላለች። ወጣት ሲሀም ሁለት ወንድሞችና ሁለት እህቶች አሏት። ለወላጆቿ አምስተኛና የመጨረሻ ልጅም ነች። የመጨረሻ ልጅ በመሆኗ ምክንያት አባቷ በጣም ያቀርቧትና ነፃነት ይሰጧት እንደበር ታወሳለች። ከቤት ውስጥ ሥራና ከማንኛውም ጫና ነፃ ሆና ትምህርቷ ላይ ትኩረት እንድታደርግና ሙሉ በሙሉ በራስ የመተማመን መንፈስ እንድታዳብር ያደርጉ እንደነበርም ትገልፃለች።
አባታቸው ለሦስቱም ሴቶች ልጆቻቸው እንዲህ ዓይነቱን ነፃነት ቢሰጡም ለእሷ የሚያደርጉት ላቅ ያለና የተለየ እንደነበረም ታስታውሳለች። ከታዳጊነት ዕድሜ ዘመኗ እስከ አሁን ከልቦለድ ጀምሮ ስለ አገርና ሕዝብ አስተዳደር፣ ስለውጪ ግንኙነቶች፣ ስለድህነት፣ ስለኢኮኖሚና የተለያዩ ጉዳዮች የሚተርኩ መጻሕፍትን ለማንበብ ሰፊ ዕድል የሰጣት መሆኑንም ትጠቅሳለች።
ደፋር እንድትሆንና ከሰዎች ጋር የተሻለ ግንኙነት እንዲኖራት ማድረግ አስችሏታል። ሲሀም እንደአዲስ ተመራቂዎች የሥራ ዕድል በማጣት አልተንገላታችም፡፡ ሲሀም ሥራ ማግኘት የቻለችው ገና የሁለተኛ ዓመት ዩኒቨርቲቲ ተማሪ ሆና ነው። ገና በለጋ ዕድሜዋ አፍሪካንና አውሮፓን ጨምሮ ስድስት የሚሆኑ የውጭ አገራትን በመጎብኘት ያካበተችውን ሙያ ተግባር ላይ አውላለች፡፡
ሲሀም በአሁኑ ወቅት ወጣቶችን ለሥራ ብቁ እና ተመራጭ እንዲሆኑ ስልጠና በመስጠት ትታወቃለች። ሲሀም በአሁኑ ወቅት የኢንፎ ማይንድ ሶሉሽንስ አክሲዮን ማህበር ውስጥ በፕሮግራም ዳይሬክተርነት እየሠራች ትገኛለች። ፕሮጀክቱ ዋና ትኩረቱ ያደረገው ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ለሚወጡ ተማሪዎች የሥራ ቅጥር ዕድል እንዲያገኙ ማመቻቸት ነው።
በዚህ ፕሮጀክት ከሚሠሩት 50 ሠራተኞች መካከልም 90 በመቶ ያህሉ ሴቶች ናቸው፡፡ በአገራችን እየተስፋፋ የመጣው ሥራ አጥነት የዜጎችን በተለይም የሴት ተመራቂ ወጣቶችን ሥራ የማግኘት ዕድል እንዳጠበበው የተረዳችው ወጣቷ ሲሀም ተመራቂ ተማሪዎች ለሥራ የሚያዘጋጃቸውን ስልጠና መስጠት የጀመረችውም እነዚህን ክፍተቶች ከለየች በኋላ ነው። እንደጥናቷ ሴት ተመራቂ ተማሪዎች ፈጥነው ሥራ የማያገኙባቸው ምክንያቶች ፈርጀ ብዙ ሲሆኑ አንዱና ዋነኛው መረጃ እንደልብ ማግኘት አለመቻል ነው።
ሁለተኛው በዚህ ምክንያት በቂ የሥራ ዕድል አለመኖር ሲሆን ሦስተኛው ዕድሉን ቢያገኙም የሥራ ቦታው ርቀት ያለው መሆኑ ነው። ‹‹ሥራ ሊገኝባቸው የሚችሉ አማራጮችን አለማወቅ ሴቶች ሥራ እንዳያገኙ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ ነው›› የምትለው ሲሀም አንድ ተመራቂ ተማሪ ሥራ ለመፈለግ በትንሹ በቀን 20 ብር እንደሚያወጣ ከሦስት ዓመት በፊት የተጠና ጥናት ትጠቅሳለች። አማራጮቹን ቢያውቁም እንኳን ከትራንስፖርት ሣንቲም ጀምሮ ተሯሩጠው ሊፈልጉበት የሚያስችል ጥሪት በማጣትም ሥራ የማያገኙበት ሁኔታ እንዳለም ትገልፃለች።
ሲሀም ለሴት ተመራቂዎች እንዲሁም ለወጣቶች ሥራ ማጣት ምክንያት ናቸው ካለቻቸው ውስጥ ደፍሮ አለመሞከር፣ በራስ አለመተማመን፣ በዚህ የተነሳ በሥራ ፈተና ቃለ መጠይቅ ወቅት መፍራትና ለተጠየቁት ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ አለመስጠት፣ በኢኮኖሚም ሆነ ልምድ በማጣት ለአለባበሳቸው በሚፈለገው ልክ ዝግጅት አድርገው ለቃለመጠየቅ አለመቅረብ እንደሆነ ታብራራለች። ችግሮቹን ለመፍታት የመረጃ መረብ በመፍጠር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች። ይህ ይዛ የመጣችው ዕድል ጾታ ሳይለይ ሁሉንም ተመራቂ ተማሪ ተጠቃሚ የሚያደርግ ከመሆኑም
በላይ ለሴት ተመራቂዎች የተለየ ትኩረት ይሰጣል። ትኩረቱ ከዚህ ቀደም ወጣቶች የትምህርት ዕድል አለማግኘታቸውንና አሁን ላይ ቢያገኙም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደረጃ ተደራሽነቱ ዝቅተኛ መሆኑ፤ በዚህ ሁኔታ ለመመረቅ የበቁትን ደግፎ ማውጣት ግድ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ነው። ይህን መሠረት በማድረግም ተመራቂዎች ከመመረቃቸው በፊትና በኋላ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ የሚያስችሉ የተለያዩ ስልጠናዎች እንዲወስዱ ማድረግ ከተግባራቱ ቀዳሚው ነው።
ድርጅቱ ወደ ሥራ ከገባ ጀምሮም ለ100 ሺህ ያህል ተመራቂ ተማሪዎች ስልጠናዎችን ሰጥቷል። እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ ሴት አመራሮችን ከመፍጠር ጋር ተያይዞ ሊደርሽፕ (የአመራርነት) ስልጠና የሚሰጥበት መሪ የተሰኘ ፕሮጀክትም አለው፡፡ መሪ ሥራውን የጀመረው በፈረንጆቹ 2018 ሲሆን ከኢርያን ሶሉሽንስ / Earyan Solutions/ ጋር በትብብር የሚሠራ ፕሮጀክት ነው። በ30 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ሴት ተማሪዎች በየዓመቱ በስልጠናው የሚሳተፉ ሲሆን እስከ አሁን ባለው መረጃ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ተጠቃሚ ሆነውበታል።
ሆኖም ፕሮጀክቱ አዲስ አበባ ላይ የተወሰነ በመሆኑ በክልል እንዲሰፋ እየተሠራም ይገኛል። ‹‹ለአንድ ቤተሰብ ልጆቹን አስተምሮ ማስመረቅ፤ ተመርቆም ሥራ በመያዝ ራሳቸውን ሲችሉ ማየት ትልቅ ስኬት ነው›› የምትለው ሲሀም የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሳለች በዩኒቨርሲቲው የወሰደችው የሥራ ፈጠራ ክህሎት ስልጠና ከራሷ አልፋ ለሌሎች ወጣቶች ሥራ ማስገኘት የሚያስችል ተግባር መሠማራት እንዳስቻላትም ትናገራለች። ሲሀም እሷ በናዝሬት ስኩል የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን አጠናቅቃና ጥሩ ውጤት አምጥታ ወደ ዩኒቨርሲቲ በምትገባበት ወቅት ወንድምና እህቶቿ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሥራ ባለማግኘታቸው በፍለጋ ይንከራተቱ ነበር። በአእምሮዋ ለምን የሚል ጥያቄ የፈጠረባት ሲሀም ከዩኒቨርሲቲ ተመርቃ በምትወጣበት ሰዓት ምን ልትሆን እንደምትችልም ስጋት ተሰምቷት ነበር፡፡
ስትገባ የመረጠችው ፖለቲካል ሳይንስ እና ኢንተርናሽናል ሪሌሽን ሥራ ሊያስገኝላት መቻል አለመቻሉን ሳታውቅ መምረጧ ያሳስባትም ነበር። ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ ለዚህ የሚረዳ ምክር ወይም ዝግጅት እያገኙ መምጣት ይገባ እንደነበር የተገነዘበችውም በዚያን ወቅት ነበር፡፡
ሲሀም የፖለቲካል ሳይንስ መስክን የመረጠችው 11ኛ ክፍል እያለች የተለያዩ መጽሐፍቶችን በማንበቧ ሲሆን ይሄና የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ መሆኗ አገርና ሕዝብ እንዴት እንደሚተዳደር፣ የሕዝብ ደህንነትስ እንዴት እንደሚጠበቅ የሚለውን በጥልቀት እንድትመረምር አድርጓታል።
የበለጠ በኢኮኖሚና በቢዝነስ ጉዳዮች ላይ እንድታተኩርም አስችሏታል።
በተጨማሪም በትምህርት ስኬታማ እንድትሆንና የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሆና የወሰደችውን የሥራ ክህሎት ስልጠና በመጠቀም ወደ ሥራ ዓለም ፈጥና እንድትገባ አግዟታል። ያለፈችበትን መንገድ ሁሉም ተመራቂ ወጣቶች በተለይም ተመራቂ ሴቶች እንዲጠቀሙበት አብዝታም ትፈልግ ነበር።
ተማሪዎቹን በማብቃት ለሥራ የሚያዘጋጅ ስልጠና ላይ ትኩረት አድርጋ የምትሠራውም ለዚህ እንደሆነ ትናገራለች። ሲሀም አሁን በምትሰጠው ስልጠና ሴቶች የበለጠ ተሳታፊ እንዲሆኑ ብዙ ጥረት በማድረግም ትታወቃለች።
ወደ መቐለ ዩኒቨርሲቲ በመሄድ ለተማሪዎች የቅድመ ሥራ ላይ ሥልጠና ሰጥታ ነበር። በዚህ ስልጠና ከተሳተፉት ሁለት ሺህ ተማሪዎች መካከል ሴቶቹ አምስት እንኳን አይሞሉም ነበር።
«ገርሞኝ ሴት ተማሪዎቹ የት እንዳሉ ጠየቅኩ» ትላለች። ስለ ስልጠናው መረጃ ያላቸው አለመሆኑና ዶርም መሆናቸው ሲነገራት፤ ወዲያው መረጃ አግኝተው የመጡት ሴት ተማሪዎችን በየአቅጣጫው በማሰማራት ዶርም ለቀሩት ሴት ተማሪዎች መረጃውን በማድረስ ቀስቅሰው እንዲያመጧቸው አደረገች።
ከዚህ በኋላም በርካታ ሴቶች በስልጠናው ለመሳተፍ ችለዋል። ሲሀም የምትሰጠው ስልጠና ከስልክና ኮምፒዩተር ጀምሮ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ያካትታል። ሁሉም ተመራቂ ተማሪዎች እንደተመረቁ ሥራ ከማያገኙባቸው ምክንያቶች አንዱ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክህሎታቸው ላይ ክፍተት በመኖሩ ነው። ይህ ክፍተት ሴቶች በኢኮኖሚ ተጽእኖ ስለሚደርስባቸው ይበልጥ የሰፋ ነው። ስማርት ስልክ እንኳን የሌላቸው ብዙ ናቸው። ያላቸውም አጠቃቀሙን አያውቁትም።
በአምስቱ ዓመት ቆይታዋ እዚህ ላይ ሁሉ ትኩረት አድርጋ በመሥራት በሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ለሥራ ብቁ አድርጋለች። የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ሲቋቋምም የመንግሥትና የግል ቀጣሪ ድርጅቶች የተመራቂ ተማሪዎች በተለይም የሴት ተመራቂዎች ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝና በልዩ መርሐ ግብር እንዲታገዝ የበኩሏን አስተዋፅኦ አድርጋለች።
ሲሀም እንደምትለው ወጣቶችን ማብቃት አገርን መገንባት ነው። በተለይ ደግሞ ሴቶችን ማብቃት ማኅበረሰብን ማሳደግ ነው። ሴት ወጣቶች የቅድመ ሥራ ስልጠና መውሰድና ደፍረው ወደ ውድድር መግባት አለባቸው ስትል ምክሯን ለግሳለች።
ደፍረው የሄዱትን ሴቶች አብነት በማድረግም በቀጣሪ ድርጅቶች ዘንድ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ብቃት ያላቸውና ውጤታማ በመሆናቸው በእጅጉ ተፈላጊ እንደሆኑ ትገልፃለች። አብዛኞቹ ቀጣሪ ድርጅቶች ይሄንኑ እንደሚመሰክሩላቸውና ሴት ሠራተኞችን እንዲልኩላቸው የሚጠይቁም በርካቶች መሆናቸውን ትናገራለች።
በመሆኑም አዲስ ተመራቂ ተማሪዎች ከምርቃት በኋላ ለሥራ ቅጥር ከመሄዳቸው በፊት ዘመኑን የሚመጥን አቅም መገንባት እና መደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ከዚህ ተሞክሮ መቅሰም ይቻላል የሚል ምክረ ሃሳብ በመስጠት የዛሬ ጽሑፋችንን እዚህ ላይ አበቃን። መልካም ሰንበት!::
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን የካቲት 18 /2014