በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው የፓን አፍሪካ የትምህርት ቤቶች የእግር ኳስ ውድድር ፍፃሜውን አግኝቷል። በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ በሁለቱም ጾታ ተሳታፊ መሆኗ የሚታወቅ ሲሆን ፣ ኢትዮጵያን የወከሉት ትምህርት ቤቶች በሴቶች 3ኛ በወንዶች ደግሞ 4ኛ ሆነው አጠናቀዋል።
ኢትዮጵያን በታዳጊ ሴቶች ውድድር የወከሉት የዲላ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሲሆኑ በታዳጊ ወንዶች የተሳተፉት ከኦሮሚያ ክልል የአዋሮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ናቸው።
የዲላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በመጀመሪያው ቀን የነበሯቸውን ሁለት ጨዋታዎች በድል አጠናቀዋል፤ ይህም ውጤት የደረጃ ፉክክር ውስጥ አስገብቷቸዋል። በደረጃው ጨዋታም ከቤኒን አሸንፎ የመጣው ቡድን በአዘጋጇ አገር በመለያ ምት 4ለ3 በመሸነፍ 3ኛ ሆኖ ውድድሩን አጠናቋል።
በውድድሩ መጀመሪያ ጨዋታዎች በወንዶች አስተናጋጇ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን የገጠመችው ኢትዮጵያ 2-1 ስታሸንፍ በሴቶች ሴኔጋልን 2-0 በማሸነፍ ነበር ውድድሩን የጀመሩት። በቀጣዩ ጨዋታም በወንዶች ኢትዮጵያ ቤኒንን 1-0 ስታሸንፍ በሴቶችም በተመሳሳይ ቤኒንን 2-1 ማሸነፍ ችላለች።
በታዳጊ ወንዶች የተሳተፉት የአዋሮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በሞሮኮ አቻቸው 2ለ1 ተሸንፈው በውድድሩ ሶስተኛ ሆኖ የማጠናቀቅ ዕድላቸውን አጥተዋል።
አበረታች ውጤት ያስመዘገበውን የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ባለፈው ሰኞ ምሽት ወደ አገሩ የተመለሰ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ አቶ ባሕሩ ጥላሁንና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ አሊሚራ መሐመድ እንዲሁም የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ተወካዮች በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል አድርገውለታል።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2014