
የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ሩሲያ ከሁለተኛው «የዓለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓ ትልቁን ጦርነት ልትከፍት ነው» ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ከቢቢሲ ጋር ቃል መጠይቅ የነበራቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ «አንዳንድ ምልክቶች እንደሚያሳዩት ጦርነቱ በተለያየ መልኩ ጀምሯል»ብለዋል።
የደኅንነት ሰዎች ሩሲያ የዩክሬንን ዋና ከተማ ኪዬቭን መክበብ የሚያስችል ጥቃት ልትሰነዝር እንደሆነ ነግረውናል ብለዋል ቦሪስ።
«ሰዎች መረዳት ያለባቸው ነገር ይህ ጦርነት የሚያስከፍለውን የሰው ዋጋ ነው» ሲሉ አክለዋል።
ሚዩኒክ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዓለም መሪዎች ጋር ስለምድራችን ደኅንነት እየተወያዩ ነው።
የአሜሪካ መንግሥት እንደሚገምተው ከ169 ሺህ እስከ 190 ሺህ የሚገመቱ የሩሲያ ወታደሮች በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ተሰማርተዋል።
አሜሪካ እንደምትለው የሩሲያ ወታደሮች በሩሲያ ብቻ ሳይሆን በቤላሩስ ድንበር በኩልም በተጠንቀቅ ቆመዋል።
ነገር ግን ይህ የአሜሪካ አሃዝ በምዕራባዊ ዩክሬን ያሉ ታጣቂዎችንም የሚያካትት ነው።
ምዕራባውያን ሩሲያ በማንኛውም ጊዜ ዩክሬን ላይ ጥቃት ልትሰነዝር እንደምትችል ሲያስጠነቅቁ ከርመዋል።
ነገር ግን ሩሲያ ይህ የምዕራባውያን ወሬ ውሃ አያነሳም በማለት አጣጥላ ወታደሮቼ ልምምድ እያደረጉ እንጂ ለጦርነት እየተዘጋጁ አይደለም ብላለች።
የሩሲያ ወረራ ሊቀረፍ የሚችል ነው ወይ ተብለው የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ጆንሰን «ያለን መረጃ የሚያሳየው ይህ ሊሆን የማይችል እንደሆነ ነው» ሲሉ መልሰዋል።
«እውነታው የሚያሳየው ሩሲያ ዕቅዷን ለማሳካት ሥራ እንደጀመረች ነው።»
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፤ ሩሲያ ወደ ዩክሬን ለመግባት ያሰበችው በምሥራቅ አቅጣጫ ብቻ ሳይሆን በቤላሩስ በኩልም እንደሆነ ለምዕራባውያን መሪዎች ተናግረዋል።
«እያየን ያለነው ነገር ከ1945 [የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቂያ] በኋላ ትልቁ ጦርነት በአውሮፓ ሊከፈት እንደሚችል የሚጠቁም ነው»ብለዋል ቦሪስ።
«ሰዎች የዩክሬናውያንን ሕይወት መቀጠፍ ብቻ ሳይሆን የወጣት ሩሲያውያንንም ነብስ ሊያስቡ ይገባል።»
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር ጀርመን ውስጥ መክረዋል።
ምንጭ ቢቢሲ
አዲስ ዘመን የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም