ሥራና ሠራተኛ የሚገናኙባቸው አጋጣሚዎች ድንገተኛ ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንዶች እንኖርበታለን ብለው ባላሰቡት ሥራ ህይወታቸውን ይመራሉ፤ ብዙ አስበው፤ ብዙ ሞክረው አንዱ ላይ ይወድቃሉ። የዛሬው እንግዳችን እራሳቸውን አሸንፈው ለመኖር ሲሉ የተለያዩ የጉልበት ሥራዎችን ሞክረዋል።
በአጋጣሚ የለመዱትን ሥራ መተዳዳሪያ አድርገው ቤተሰብ መስርተው ህይወታቸውን እየመሩ ይገኛል። ባለታሪኩ ከሸንበቆ የተለያዩ የቤት ቁሳቁሶችን እየሠሩ በመሸጥ በሚያገኟት ገቢ ስድስት የቤተሰብ አባላትን የሚያስተዳድሩ ናቸው። ሙያውን የለመዱት እዚሁ አዲስ አበባ ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ ወንዞች ዳርቻ በሚገኙ አንዳንድ መኖሪያ ቤቶች የሚበቅለውን ሸንበቆ እየገዙ ቁሳቁስ ሠርተው ለገበያ በማቅረብ ሃያ አምስት አመታትን ያሳለፉና ዛሬም በዚሁ ሥራ ላይ ያሉ ናቸው። የባለታሪኩ የሥራ እይታ፣ ትጋትና ጥረት አስተማሪ በመሆኑ አዲስ ዘመን ጋዜጣ እንግዳ ሊያደርጋቸው ወዷል። አቶ ዲነካ ሳኒ ይባላሉ።
ተወልደው ያደጉት በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ጉንችሬ ወረዳ ነው። በልጅነታቸው እንደ አካባቢው የሥራ ባህል ከብቶችን በመጠበቅና ጉልበት በማይጠይቁ የግብርና ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ቤተሰቦቻቸውን እያገዙ አድገዋል። የቤተሰቦቻቸው ቁጥር ሰፊ በመሆኑ ከግብርና የሚያገኟት ገቢ ከዓመት እስከ ዓመት የምታደርስ አልነበረችም።
ሌላው ቀርቶ ቆጮ ለማምረት የሚያስችል በቂ የእንሰት ተክል እንኳን እንዳልነበራቸው ይናገራሉ። ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ እንደነበር የሚገልጹት የያኔው ታዳጊ ዲነካ የቤተሰቦቻቸው ጥገኛ ከመሆን የራሳቸውን ሥራ ሠርቶ ለመኖር በማሰብ እልፍ ሲልም ተቸግረው የሚኖሩትን ወላጆቻቸውን ለመርዳት በሚል ነበር ገና በልጅነታቸው የትውልድ መንደራቸውን ትተው የተሰደዱት። ይህ የሆነው ከዛሬ አርባ አራት ዓመት በፊት ነበር። እድሜው ለሥራ የደረሰ አብዛኛው የጉራጌ ማህበረሰብ ከአካባቢው ርቆ በመሄድ ሠርቶ መኖርን ባህሉ ያደረገ በመሆኑ ዲነካም የታላላቆቻቸውን ዱካ ተከትለው ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ።
እንደእርሳቸው አባባል ያኔ አዲስ አበባ እንደአሁኑ ሰው፣ ተሽከርካሪና ፎቅ አልበዛባትም ነበር። እንደዚያም ሆና ዳኒካን ፈትናቸዋለች። አዲስ አበባ ሠርቶ የሚታደርባት ከተማ መሆኗን እንጂ ግራ የምታጋባ መሆኗን አልሰሙም ነበር። በተለይም ሥራ የጀመሩት መርካቶ አካባቢ በመሆኑ ሠርቶ መኖር ሳይሆን ገብቶ መውጣት እንኳ ያስቸግራቸው እንደነበር ይግልጻሉ።
የእለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን በሚያደርጉት መሯሯጥ ቀስ በቀስ መግቢያና መውጫዋን ማጥናት ይጀምራሉ። ጠዋት ወጥተው ማታ መግባቱን ቢለማመዱትም ከእለት ጉርስ የሚተርፍ ጥቅም ማግኘት አልቻሉም። በዚህም ላይ የመርካቶ ሁከትና ግርግር ምቾት አልሰጣቸውም።
በዚህ የተነሳ ሌላ ሥራ ማፈላለግ ይጀምራሉ። ዳኒካ በአንድ ሆቴል ውስጥ በአስተናጋጅነት ተቀጥረው መሥራት ይጀምራሉ። ያኔ የሆቴል አስተናጋጆች እንደአሁኑ በፈረቃ የሚሠሩበት ዘመን ባለመሆኑ ወር እስከ ወር ዓመት እስከ ዓመት ያለዕረፍት መሥራታቸውን ይቀጥላሉ።
በሆቴል ውስጥ በአስተናጋጅነት ለዓመታት ሲሠሩ በመሃል የመስቀል በዓል ሲደርስ ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ ለጥቂት ቀናት ፈቃድ ጠይቀው ይሄዳሉ እንጂ አንድም ቀን የእረፍት ሰዓት ተሰጥቷቸው አያውቁም። እንደ አሁኑ ለአስተናጋጆች ቲፕ የመስጠት ባህልም አልነበረም። እንደውም አንዳንዴ ሂሳብ ሲጎድልባቸው ከደመወዛቸው ይቆረጥባቸው እንደነበር ይናገራሉ።
ምግብና መኝታ ተችሏቸው ለአመታት በወር ከ30 እስከ 50 ብር እየተከፈላቸው ይሠሩ ነበር። ከዚያም በኋላ በአሥር ብር የደመወዝ ማሻሻያ ተደርጎላቸው ከአስተናጋጅነት ወደ ድራፍት ቀጂነትና ባሬስታነት ይቀይራሉ፤ ነገር ግን ህይወታቸውን መቀየር አልቻሉም። አሁንም ሌላ ሥራ መሞከር ስለነበረባቸው ከሆቴል ሥራ ለቅቀው በግለሰብ ቤት ጥበቃ ተቀጥረው መሥራት ይጀምራሉ ።
ከአሥር ዓመት በላይ የተለያዩ ሥራዎችን እየቀያየሩ ቢሠሩም ሕይወታቸውን የሚቀይር ነገር እንዳላገኙ ይናገራሉ። ግን የመስቀል በዓል በደረሰ ቁጥር የአቅማቸውን ቋጥረው እየሄዱ ቤተሰቦቻቸውን ሳይጠይቁ ቀርተው አያውቁም።
አንድ ወቅት ከሸንበቆ የተሠሩ ቁሳቁሶችን እያዞሩ የሚሸጡ የአካባቢያቸውን ሰዎች ድንገት ያገኟቸውና ስለገቢያቸው ይጠይቋቸዋል። ዲነካ በወር የሚያገኙትን እነርሱ በሳምንት ውስጥ ሊያገኙ እንደሚችሉ ይነግሯቸዋል።
ዲነካ የእነርሱን ሙያ የመልመድ ፍላጎት ያድርባቸውና እንዲያስጠጓቸው ይጠይቋቸዋል። ሰዎቹ የሚሠሯቸውን ቁሳቁስ እያዞረ የሚሸጥላቸውና የጉልበት ሥራዎችን የሚያግዛቸው ሰው ይፈልጉ ስለነበር ፈቃደኝነታቸውን ይገልጹላቸዋል። በወር ከሚያገኙት የተሻለ ገንዘብ ሊከፍሏቸው እንደሚችሉ ይነግሯቸዋል። ዲነካ ሳያቅማሙ የጥበቃውን ሥራ ትተው ከሰዎቹ ጋር መዋል ይጀምራሉ። የሚበሉትን እየበሉ በሚያድሩበት እያደሩ ለሚሠሩት የጉልበት ሥራ ተገቢው ክፍያ እየተከፈላቸው ህይወትን በሌላ መንገድ መሞከራቸውን ቀጠሉ።
የእርሳቸው የሥራ ድርሻ ከተለያዩ አካባቢዎች ሙያተኞቹ የሚገዙትን ሸንበቆ አጓጉዘው ሥራው ቦታ ማድረስና እየሰነጠቁ፣ እየፋቁና በሚፈለገው ልክ እየቆረጡ ለሚሠሩት ሰዎች ማቀበል ነበር። አንዳንድ ጊዜ የተመረቱትን ቁሳቁስ እያዞሩ ይሸጣሉ። አንዳንድ ጊዜም ሙያተኞቹ የሚሠሩትን እያዩ ይሠሩ ነበር። በዚህ አጋጣሚም ሙያውን የመለማመድ እድል ያገኛሉ።
ከአሠሪዎቻቸው ባልተናነሰ የሸንበቆ ቁሳቁሶችን የማምረቱን ሙያ ይካኑታል። ዲነካ ሙሉ ጊዜያቸውን በሥራ ላይ እያዋሉ ሙያውን በደንብ ከተለማመዱ በኋላ ራሳቸውን ችለው ሸንበቆ እየገዙ ቁሳቁሶችን በመሥራት እየሸጡ ገቢ ወደ ማግኘት ይሸጋገራሉ። የቀን ገቢያቸውንም ያሻሽላሉ።
ቤት ተከራይቶ የመኖር አቅምም ያገኛሉ። ከዚህ በኋላ ትዳር የመመስረት ፍላጎት ያድርባቸውና የአገራቸውን ልጅ አግብተው መኖር ይጀምራሉ። ባለቤታቸው በወቅቱ ሥራ አልነበራቸውም ። ኋላ ግን የአዲስ አበባን ኑሮ ለማሸነፍ ሲሉ ከአገር ቤት ወደ አዲስ አበባ ቆጮ በማምጣት እየሸጡ ኑሯቸውን ለመደጎም ጥረት ያደርጉ ነበር።
ሁለቱም በየፊናቸው ተሯሩጠው በሚያገኙት ገቢ የቤት እቃ አሟልተው ሲኖሩ ከዓመት በኋላ ልጅ ይወለዳል። የልጆች ቁጥር አንድ ሁለት እያለ አምስት ይርሳል። ባለቤታቸው የቤት እመቤት ሆነው ልጆችን በማሳደግ ብቻ ይወሰናሉ። በአንድ በኩል የቤተሰብ ቁጥር እየጨመረ መሄድ በሌላ በኩል የኑሮ ውድነቱ መባባስ ኑሯቸውን አዳጋች ያርገዋል።
ዲነካና ባለቤታቸው ከወለዷቸው አምስት ልጆች አንዱ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለያቸውም የተቀሩትን አራት ልጆቻቸውን ለማስተማር ፈታኝ የህይወት ውጣ ውረድ አሳልፈዋል። የቀበሌ ቤት ከማግኘታቸው በፊት አብዛኛውን ህይወታቸውን በኪራይ ቤት ማሳለፋቸውን ይናገራሉ። በየጊዜው ልጆችን ይዞ ከአንዱ ቤት ወደ ሌላ ቤት፤ ከአንድ ሰፈር ሌላ ሰፈር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አሰልቺ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ሰፈር በመቀያየራቸው ምክንያት ሎጆቻቸው ትምህርታቸውን ለማቋረጥ የተገደዱበት አጋጣሚ መኖሩንም ይገልጻሉ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የመኖሪያ ቤት ጥያቄያቸው ተመልሶላቸዋል። የካ ክፍለ ከተማ ቀበሌ ስድስት በአነስተኛ የቀበሌ ቤት ውስጥ መኖር ጀምረዋል። የአስቤዛ፣ የአልባሳትና የልጆቻቸውን የትምህርት ቤት ወጪ እየሸፈኑ ኑሮን በመታገል ላይ ናቸው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የተማሪዎች ምገባ መርሀ ግብርን ተግባራዊ ካደረገ ወዲህ በመለስተኛ ደረጃ የሚማሩት የሁለት ልጆቻቸው ጉዳይ እፎይታ እንደሰጣቸው ይናገራሉ። ባለቤታቸውም በተማሪዎች ምገባ ሥራ እድል ስለተከፈተላቸው አሁን ከቤት እመቤትነት ወደ ሠራተኝነት ተሸጋግረዋል።
ዲነካ እንደሚናገሩት ባለቤታቸው ሥራ ይዘው ባይረዷቸውና የሁለቱ ልጆቻቸውን የትምህርት ቤትና የምግብ ወጪ ከተማ አስተዳደሩ ባይሸፈንላቸው ኑሮን መቋቋም አይችሉም ነበር። ሌሎቹን ልጆቻቸውንም የኮሌጅ ወጪያቸውን ሸፍነው ማስተማር አይችሉም ነበር። ዲነካ አንዳንድ ቀናትን የሚያሳልፉት ለቁሳቁስ መሥሪያ የሚያገለግለውን ሸንበቆ በመፈለግ ነው። ሸንበቆ በአዲስ አበባ አንዳንድ ቦታዎች ላይ በተወሰነ መልኩ ይገኛል።
ወንዝ ዳርቻ የሚኖሩ ግለሰቦች እንደ አጥርና እንደ ጥላ የሚጠቀሙት ተክል ለእነ ዲነካ መተዳደሪያቸው ስለሆነ በሚገኝበት መንደር እየሄዱ ግዢ ይፈጽማሉ። በአንድ ጊዜ ቢያንስ ለአንድ ወር የሚበቃቸውን ሸንበቆ ገዝተው ማስቀመጥ አለባቸው። ስለዚህ በተወሰነ ጊዜ ሥራቸውን አቋርጠው ሸንበቆ የሚገኝበትን ሥፍራ ያስሳሉ። ፍለጋ በሚወጡባቸው ጊዜያት ረዥም የእግር ጉዞ ያደርጋሉ። በሸንበቆ ፍለጋ የሁለትና የሶስት ቀን ገቢ የሚያጡበት አጋጣሚም አለ።
ብዙ ጊዜ ፍለጋ የሚያደርጉት ወንዞች ባሉባቸው አካባቢዎች ነው። በተለይም የቀበና እና የግንፍሌ ወንዞችን ተከትሎ በአንዳንድ ሰዎች ቤት ስለሚገኝ በር እያንኳኩ ይጠይቃሉ። ሰዎችን እንዲሸጡላቸው ማግባባቱም እራሱን የቻለ ፈተና እንደሚሆንባቸው ይናገራሉ። እርሳቸው ሥራ እንደጀመሩ አካባቢ አንድ የሸንበቆ ዘንግ ከሃያ አምስት ሳንቲም ባልበለጠ ይገዙ ነበር። እዚያው ሸንበቆውን በገዙበት አካባቢ ቁጭ ብለው በመሥራት ምርታቸውን እዚያው ይሸጡ ነበር። አሁን ግን የሸንበቆው ዋጋ ጨምሯል። የሥራ ቦታቸውም በአንድ ቦታ ተወስኗል። አንድ ዘንግ ሸንበቆ ከሁለት እስከ ሶስት ብር ይገዛሉ። የትራንስፖርት ዋጋ ላለማውጣት ከቅርብም ይግዙ ከሩቅ የሚሠሩበት አደዋ ድልድይ ድረስ በሸክማቸው ያደርሳሉ።
ማለዳ ከቤታቸው ወጥተው አድዋ ድልድይ አጠገብ ቁጭ ብለው የተለያዩ ቁሳቁሶችን እየሠሩ እግረ መንገዳቸውንም እየሸጡ ይውላሉ። የዳቦ ቅርጫት፣ የአትክልት ማስቀመጫ፣ የልብስ ማስቀመጫ፣ ዘንቢል፣ የህጻናት አልጋ፣ ጫማ መደርደሪያ፣ የውሻ መተኛ እና ሌሎችንም ቁሳቁሶችን እየሠሩ ይሸጣሉ።
በቀን ከመቶ እስከ ሁለት መቶ ብር ገቢ ያገኛሉ። ምሳቸውን አንባሻ በልተው እጃቸው ላይ ባለው ገንዘብ አስቤዛ ገዘትው ማታ ወደ ቤታቸው ይገባሉ። አንዳንድ ጊዜም የሸንበቆውን ቁርጥራጭና ፍቅፋቂ ለማገዶ እንዲተርፋቸው ማታ ወደ ቤታቸው ሲገቡ ተሸክመው ይሄዳሉ። በበጋ ወቅት የዲነካ የእለት ተእለት የኑሮ ገጽታ እንዲህ አይነት መልክ ያለው ነው።
በክረምት ወራቶች ግን እጅግ እንደሚፈተኑ ይናገራሉ። በክረምት ወቅት ዝናብ ላይ ቁጭ ብለው መሥራት ስለማይችሉና የሚገዟቸው ሰዎች እንቅስቃሴም ስለሚገታ ገቢያቸው ያሽቆለቁላል። ለልጆቻቸው ዳቦ የሚገዙበት ገንዘብ ያጡበት አጋጣሚ እንደነበር ያስታውሳሉ። ይነስም ይብዛም ከገቢያቸው አንጻር ከክረምት ይልቅ የበጋው ጸሃይ ቢወርድባቸው ይመርጣሉ።
ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ ሌላ ፈተና ገጥሟቸዋል። እርሳቸው የሚያመርቷቸውን ምርቶች በፕላስቲክ እያመረቱ ለገበያ የሚቀርቡ ፋብሪካዎች እየተበራከቱ በመምጣታቸው በገቢያቸው ላይ ተፅዕኖ እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ። በጥራትም በዋጋም ተመራጭ ለመሆን ጠንክረው እየሠሩ ናቸው።
ዲነካ አሁን ትልቁ ፍላጎታቸው የሥራ ቦታ ማግኘት ነው። ቤት ተከራይተው እንዳይሠሩ ገቢያቸው የቤት ኪራዩን የሚሸፍንላቸው አይደለም። ለሃያ አምስት ዓመታት ጸሃይና ዝናብ እየተፈራረቁባቸው መንገድ ዳር ተቀምጠው ሠርተዋል። አሁን አሁን በአቅማቸው መድከምና በሰውነታቸው መሳሳት ምክንያት መቋቋም እያቃታቸው እንደመጣ ይናገራሉ።
ዲነካ ሙያቸው በስልጠና እና በገንዘብ ቢደገፍ ቄንጠኛና ጠንካራ የቤት ቁሳቁሶችን ከሸንበቆ ማምረት ይቻል ነበር ይላሉ። በተለይም የሚመለከተው አካል የመሥሪያ ቦታ ቢሰጣቸው ሙያቸውን ለወጣቶች በማካፈል የሥራ እድል መፍጠር እንደሚችሉ ይናገራሉ። በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚበቅለውንና ያለ አግባብ የሚባክነውን የሸንበቆ ምርት በአግባቡ ጥቅም ላይ የማዋል እድልም ይፈጠራል ብለዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን የካቲት 12 /2014