የሐምሌ ወር ከተጋመሰ ጥቂት ቀናት አልፈዋል። ወቅቱን የጠበቀው ከባድ ዝናብ ቀኑን ሙሉ ሲያውርደው ውሏል። አካባቢው ጭቃና ድጥ ሆኖ እግረኞችን ለመራመድ እየፈተነ ነው። በስሱ ብልጭ የምትለው ጸሀይ አፍታ ሳትቆይ በቀን ጨለማ ትዋጣለች። ዝናቡን ተከትሎ ሽው የሚለው ነፋስና ብርድ በርካቶችን ያንቀጠቅጣል።
በቢሾፍቱ ሰማይ ስር የነገሰው ሐምሌ ያለአንዳች ከልካይ እንዳሻው እየናኘ ነው። በዣንጥላና የክረምት ልብስ የሚታዩ በርካቶች ለወቅቱ አየር ያሰቡበት ይመስላል። ጠዋት ማታ ጊዜውን ለመቋቋም ተዘጋጅተው ይውላሉ።
የምሽት ቀጠሮ
ባልና ሚስቱ ምሽት ላይ ሊገናኙ ቀጠሮ ይዘዋል። አልፎ አልፎ ለብቻ ማሳለፍ በፈለጉ ጊዜ ተቃጥረው ከአንድ ሰፍራ ያመሻሉ፤ አንዳንዴ ደግሞ በቀን ተገናኝተው የልባቸውን ሲያወጉ ይቆያሉ። ይህ ዓይነቱ ልምድ ለእነሱም ሆነ ለሌላው ተመልካች አዲስ ሆኖ አያውቅም።
ጥንዶቹ ችግር ክፍተታቸውን የሚፈቱት በጥልቅ ተወያይተው ዳር የሚያደርሱት ፣ በእንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ነው። አንዳንዴ በንግግር ሳይግባቡ ፣በሀሳብ ሳይጣመሩ ወደቤት ይገባሉ። አባወራው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያመጣው አዲስ ባህሪ ለሁለቱም ሰላም ማጣት ምክንያት እየሆነ ነው። በየምክንያቱ ነገር እያነሳ ይጨቃጨቃል። ምክንያትና ሰበብ እየፈለገ ክፉ ይናገራል። ባስ ባለ ጊዜም ቡጢ ለመሰንዘር እጆቹ ፈጣን ናቸው። ሚስት ከዚህ ልማዱ እንዲቆጠብ ስትጥር ቆይታለች። በቀላሉ ችግሩ ባይፈታም ለጊዜው ነገር በርዶ በመካከላቸው ሰላም ይወርዳል። ለባልና ሚስቱ ሰላም ማጣት ምክንያት የሆነው በመካከላቸው የተፈጠረው ጥርጣሬ ነው፤ አባወራው ባለቤቱን ማመን ከተወ ከራርሟል። ሚስቱ ሁሌም ከሌላ ወንድ ጋር እንደምትማግጥ ይሰማዋል።
ይህን ሰበብ አድርጎም በየምክንያቱ ሲጣላት፣ሲጠራጠራት ቆይቷል። ሚስቱ በመካከላቸው የሆነውን እውነት ለመደበቅ ትጥራለች። ጉዳያቸውን ሌሎች ሰምተው እንዳይታዘቡ የማታደርገው የለም። ድምጹ ከፍ እንዳይል ቃሉ እንዳይሰማ፣ ንግግሩ እንዳይጎድፍ ትጠነቀቃለች፤ያም ሆኖ ድርጊቱ ከአቅም በላይ ሆኖ ችግሩ ይገዝፋል። ባልና ሚስት ቤት ውስጥ ከማውራት፣ልጆች ፊት ከመጨቃጨቅ ፣እየተዝናኑ መወያየት የተሻለ መሆኑን አምነዋል፤ በዚህ ምክንያትም ችግራቸውን ከደጅ አስቀምጠው፣የውስጣቸቸውን ተነጋግረው ወደቤት ይገባሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ ልማድ እያዋጣቸው አይደለም። ንግግሩ ቂም አጭሮ፣መወያየቱ ሆድ አስብሶ ወደቤት ይመልሳቸው ይዟል።
ቅድመ-ታሪክ
የጥንዶቹ ትዳር ሀያ ሁለት ዓመታት አስቆጥሯል። በነዚህ ዓመታት መሀል የተገኙት ሁለት ልጆች በወላጆቻቸው እንክብካቤ አድገዋል። ትናንት ባልና ሚስቱን የሚያውቁ ብዙዎች የትዳራቸውን መልካምነት ይመሰክራሉ። ሁሉም ዓመታትን በፍቅር አልፈው ሁለት ልጆቻቸውን በፍቅር ማሳደጋቸውን ያወሳሉ። በመካከላቸው የተገኙት አንዲት ሴትና አንድ ወንድ ልጅ ፣የመኖራቸው ትርጉም፣የትዳራቸው ምልክት ሆነው ህይወታቸውን አሙቀዋል፤እስከዛሬ በወላጆቻቸው መኖር ተስፋ የሚያደርጉት ልጆች የነገውን ማንነት በእነሱ መኖር ሊገነቡ ያለአንዳች ሀሳብ ኖረዋል።
ጥንዶቹ የዕድሜያቸውን ግማሽ በቢሾፍቱ ደብረዘይት ከተማ ገፍተዋል። ዓመታትንም እርስ በእርስ ሲተሳሰቡ ‹‹አንተ ትብስ፣አንቺ›› ሲባባሉ ነበር። ሁለቱም ከሀያ ዓመታት በፊት የነበረውን የፍቅር ጊዜ አይዘነጉትም። የዛኔ እስኪገናኙ ፣ተያይተው እስኪያወጉ ቀኑ ያጥራቸው ነበር።
ይህ ፍቅር ዕድሜ ገዝቶ በትዳር ከተጣመሩ በኋላም በዚህ ስሜት ቀጥለዋል። የቤቱ የመጀመሪያ ልጅ የአስራ አራት ዓመት ታዳጊ ናት። ጥንዶቹ የአራት ዓመቱን ወንድ ልጃቸውን እስኪያገኙ የበኩር ልጃቸውን እንደ ዓይን ብሌን ይቆጥሯት ነበር። አሁንም ቢሆን ለሴት ልጃቸው የተለየ ፍቅር ይለግሳሉ። ልጅቷ ከፍ ማለት ከጀመረች ወዲህ የእናት አባቷን አለመግባባት እያስተዋለች ነው። ጠዋት ማታ ሲጨቃጨቁ ሲጣሉ እያየች ይጨንቃታል።
በእሷ አቅም ማስታረቅና ማስማማት አትችልም። ችግሩን እያየች ትታዘባለች። እናት አባቷ እንደቀድሞው ተስማምተው ቢኖሩላት ደስታዋ ነው።
ሐምሌ 14 ቀን 2009 ዓም
ትንሽዋ ልጅ ትምህርት ቤት ውላ ስትመለስ ወላጆቿን በቤት አላገኘችም። በግቢው ያለው የአራት ዓመቱ ታናሽ ወንድሟ ብቻ ነበር። የት እንደሄዱ ደጋግማ አሰበች። ውላ ስትገባ በተለይ እናቷን ማጣት አትፈልግም። ከቤት ስትደርሰ የወላጅነቷን ፍቅር እንድትለግሳት ትሻለች። እሷም ብትሆን የትምህርት ቆይታዋን፣ ከቀን ውሎዋ እያዛመደች ማውራቱን ልምድ አድርጋለች።
ምሽቱ እየገፋ ነው። ወቅቱን ተከትሎ ማጉረምረም የጀመረው የሐምሌ ዝናብ ‹‹መጣሁ›› ማለት ጀምሯል። በነጎድጓድ ታጅቦ ‹‹ብልጭ›› የሚለው መብረቅ ምሽቱን አክብዶታል። አሁን በቤቱ ያሉት ሁለት ልጆች ከቀድሞ ይልቅ ፍርሀት ይሰማቸው ይዟል። እስከሁን ወላጆቻቸው ወደቤት አልገቡም። የአራት ዓመቱ ህጻን ዕንቅልፍ እያዳፋው ነው። ወላጆቹን እያሰበ ደጁን ሲያይ አምሽቷል። የአስራ አራት ዓመቷ ታዳጊ ይበልጥ ጨንቋታል። በዚህ ክረምትና ጨለማ እናት አባት ቤታቸውን ትተው ደጅ ማምሸታቸው ሊገባት አልቻለም።
ደጁን እያየች ኮሽታ ታዳምጣለች። ኮቴ ትለያለች። አዲስ ነገር የለም። ሰአቱን ደጋግማ ቃኘችው ። አሁን ከምሽቱ አራት ሰአት ማለት ጀምሯል። ከቀድሞው ይበልጥ ተደናገጠች። ወላጆቿ እስከዚህን ሰአት ያለአንዳች ምክንያት እንደማይቆዩ ገባት። ከቀኑ ስምንት ሰአት ጀምሮ ከቤት የወጡት ባልና ሚስት እስካሁን አልተመለሱም። ጉዳያቸው ለመዝናናት መሆኑን አውቃለች።
ጊዜ ፈጅተው እስካሁን መቆየታቸው ግን ለበጎ አይመስልም። ልጅቷ ሁኔታው ቢያስደነግጣት የእጅ ስልኳን አንስታ ወደእነሱ መስመር መደወለች ያዘች። ስልኩ ጥቂት እንደጠራ ተነሳ ። ልጅቷ የስልኩን ምላሽ ከማግኘቷ አስቀድሞ ሀይለኛ ጫጫታና ሁካታ ከጆሮዋ ደረሰ። ደምቆ የሚሰማው የሙዚቃ ድምጽ የወላጆቿን መገኛ ጠቆማት። ድምጹን ለማሸነፍ ስልኩን ከጆሮዋ አስጠግታ ለመናገር ሞከረች። ስልኩን ያነሳው አባቷ ነው ። ልጅቷ እየደጋገመች የት እንደሆኑ ጠየቀች። የአባቷ ድምጽ ፈጣንና አጭር ነበር። እንደሚያመሹና እንዲተኙ ተናግሮ ስልኩን ከጆሮዋ ጠረቀመው። ልጅቷ የአባቷን ትዕዛዝ ተቀብላ እንዳለው አልተኛችም ። አሁንም ደጁን እያደመጠች ጥበቃዋን ቀጠለች። ኮቴ እየለየች፣ድምጽ እየጠበቀች ከምሽቱ ታገለች፤አሁንም በዓይኖቿ የሚንከባለለው ዕንቅልፍ ደጋግሞ እየፈተናት ነው።
እናት አባቷ ከደጅ ሆነው አልጋን ማየት አልፈቀደችም። እያንቀላፋች፣እየባነነች፣እየተነሳች፣እየቆመች ጥበቃዋን ቀጠለች። አሁን ቀድሞ ከደወለችበት ሰአት የበለጠ ምሽቱ ገፍቷል። ሌሊቱ ጭር እያለ የሰዎች ድምጽ መጥፋት ጀምሯል። ከሰፈሩ ውሾች ጩኸት በቀር በአካባቢው የሚሰማ ድምጽ የለም። በጣራው ላይ መሰማት የጀመረው ዝናብ ለመኝታ ይበልጥ ይፈትናል። ጊዜው የዕንቅልፍ ሰአት ነው። ምሽቱ ከክረምቱ ተጣምሮ መክበድ ጀምሯል። ልጅቷ አሁንም እናት አባቷን እየጠበቀች ነው።
ሰአቷን ደጋግማ ታያለች። ከደወለችበት ጊዜ የሁለት ሰአት ጭማሪ ታክሏል። አሁን ከሌሊቱ ሰባት ሰአት ማለት ጀምሯል። የግቢው ነዋሪ በጣፋጭ ዕንቀልፍ ውስጥ ነው። አሁንም የጥንዶቹ መድረሰ እየተሰማ አይደለም። አካባቢው ጸጥ ፣ ጭር እንዳለ ሌሊቱ መገስገስ ይዟል። የባለትዳሮቹ ጎጆ ገርበብ ብሎ መምጣታቸውን ይጠብቃል። አዲስ ነገር የለም።
ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት…
አሁንጊዜው ከሌሊቱ ስምንት ሰአት ሆኗል። በዚህ ሰዓት ይበልጥ ጭርታው ይጨምራል። ዕንቅልፉ ይበረታል። በአካባቢው ድንገት የተሰማው ድምጽ ግን የብዘዎችን ጆሮ አነቃ። የተኙትን ነፍሶች ቀሰቀሰ። ድምጹ አስደንጋጭና የሚረብሽ ነበር። ይህ ድምጽ ከሌሎች ይልቅ ለታዳጊዋ ተማሪ ይበልጥ ቅርብ ሆነ። እየሰማች ያለው ጩኸትና ሲቃ በእርግጠኝነት የእናቷ ነው።
ድምጹን ተከትሎ የሚሰማው ሀይለ ቃል የአባቷ መሆኑ አልጠፋትም። ልጅቷ ከነበረችበት የድካም ስሜት ነቅታ ከግቢው በመውጣት ፈጥና ሮጠች። በእርግጥም አባቷ እናቷን እየደበደባትና በጭካኔ እያሰቃያት ነበር። ታዳጊዋ ሜላት በእናት አባቷ መሀል እየሆነ ያለውን እውነት በቀላሉ ማመን አልቻለችም።
ድቅድቁ ጨለማ የእናቷን ግልጽ ጉዳት አልደበቃትም። የልጅነት መንፈሷ በደል ስቃይዋን ለማየት አላገዳትም። እናቷ ሁለት ዓይኖቿ ከእይታ ተጋርደው ደጋግማ እየጮኸች ነው። ጠጋ ብላ የከፋ ጉዳቷን አስተዋለች። እንደገመተችው ሆኗል። ሁለቱም ዓይኖቿ በማይታመን ድርጊት ተጎድተው ደም ያነባሉ።
እየጮኸች፣ እያለቀሰች ልትቀርባት ሞከረች። አባቷ ይህን እንድትሞክረው አልፈቀደላትም። የውሃ መውረጃ ቦይ ውስጥ የወደቀችው እናት በባሏ ጸጉሯ እየተጎተተ በድንጋይ ትወገራለች። አባወራው ከወደቀችበት ጭቃ እያነሳና እየጣለ ያንገላታታል። ለማገዶ ከተከመረው እንጨት አንዱን መዞ በጭካኔ ይደበድባታል። ወይዘሮዋ በደከመ ድምጽ ‹‹ እባክህ ተወኝ፣ይበቃሀል፣ እያለች ትማጸናለች። ሰውዬው ልመናዋን በሰማ ቁጥር እልሁ ይጨምራል፣ንዴቱ ያይላል፣በዓይኑ የሚዞረውን የቅናት ስሜት እየታገለ በባለቤቱ ላይ ጥቃቱን ይጨምራል።
እየደጋገመ ‹‹ከማን ዋልሽ ፣ከማን ታየሽ›› የሚለው ሰው ለጥያቄው ፈጣን ምላሽ ባለማግኘቱ ብስጭቱ እየጨመረ መሰንዘሩን ያጠነክራል። በድንገቴው ጩኸት የተቀሰቀሱ ጎረቤቶች ጆሯቸውን ጥለው ያዳምጣሉ። እየሰሙት ያለው የስቃይ ድምጽ የወይዘሮዋ መሆኑን አምነዋል ። ባለቤቷ አቶ ብሩክ በዚህ ውድቅት ሚስቱን እየደበደበ ማሰቃየቱ አልገባቸውም።
ካሉበት ወጥተው ለመገላገል አልደፈሩም፤አብዛኞቹ የሚሰሙትን ፈታኝ ድምጽ እያዳመጡ ሁኔታውን ይከታተላሉ። የባልና ሚስቱ ልጅ ሜላት ከውሃ መውረጃው ቱቦ ወድቃ አበሳ የምታይ እናቷን መታደግ አልሆነላትም። በእሷ አቅም እንደአውሬ እየሆነ ያለውን አባቷን መገላገል የሚቻላት አይደለም። በቀረበች ቁጥር በአባቷ ቁጣ ትባረራለች። አሁን ያላት አማራጭ በልጅነት ድምጽዋ ሀይል ጨምራ መጮህና እርዳታ መጠየቅ ብቻ ነው። ሜላት በጣር ላይ ያለችውን እናቷን እያየች ጩኸቷን አቀለጠችው።
ይህኔ ድምጽ የሰሙ ጎረቤቶች ከያሉበት ብቅ ማለት ጀመሩ። ሁኔታውን ያስተዋለው አባወራ ነገሩ ብሶ ሰው ከመብዛቱ በፊት ሚስቱን እየጎተተ ወደቤት አስገባት። እየተጎተተች የገባችው ወይዘሮ ከአልጋ ተወርውራ ዳግም ጥቃት ማስተናገድ ያዘች፤በያዘው ዱላ መላ ሰውነቷን የሚያገላብጠው ባል በሚያደርገው ሁሉ አልረካም። ዓይኖቿን አጥፍቶ ፣አካሏን ሰባብሮ አንገቷን ለመውጋት ስለት መፈለግ ያዘ። ለጊዜው በእጁ የገባውን ትልቅ ማንኪያ ከአንገቷ አሳርፎ እንደፈለገው አደረገ። የመጣውን ሁሉ ያለአንዳች መታገል የምትቀበለው እማወራ ጨካኙን ጉልበተኛ ልትከላከለው አልቻለችም፤ የልጆቿ አባት፣ዓመታትን በትዳር የዘለቀው ግማሽ አካሏ እያደረሰባት ባለው ከባድ ጉዳት እየተዳከመች ነው። ትንፋሽና ሀይሏ እየቀነሰ መምጣቱን የተረዳው አቶ ብሩክ ለጊዜው ከድብደባው ጋብ ብሎ ማሰብ ጀመረ። አሁን ራሱን ለማሳረፍ መተኛት ይኖርበታል፡፤ ሜላት በደም ርሳ ከአልጋ የተኛችውን እናቷን ከአንገቷ ጨርቅ አንጥፋ ደግፋት ቆየች።
እናት በልጇ እገዛ ብቻ መቆየት አልቻለችም ። ከአልጋው ድንገት ተንሸራታ ወደቀች። የመውደቅ ድምጽ የሰማው አባወራ ከተኛበት ተነስቶ ከመሬት ያገኛትን ሚስቱን ወደአልጋው መለሰ። በዚህ ጊዜ ባለቤቱ ትንፋሻዋ እያጠረ፣አካሏ እየደከመ ነበር።
ሊነጋ ሲል…
የጭንቁ ሌሊት አብቅቶ የንጋት ጊዜው ቀርቧል። አንገቷን ደግፋ የተቀመጠችው ሜላት የእናቷ ትንፋሽ እያጠረ መሆኑ ገብቷታል። በፍራቻ የአባቷን አይን እያስተዋለች የሚሆነውን ትጠብቃለች። ወፎች ሲንጫጩ ሁሉ ነገር ተጠናቀቀ፡፤ስቃይና በደል ያስተናገደችው መከረኛዋ ወይዘሮ ትንፋሽ በህቅታ ተቋጨ። ህይወቷ ማለፉን ያወቀው አባወራ በማለዳው አዲስ ዘዴ አቀናበረ፤ ባለቤቱ በደም ግፊት ማረፏን ለወዳጅ ዘመድ ተናግሮ ለቅሶ ሊቀመጥ ተዘጋጀ ፤የቅርቡን ጨምሮ የሩቅ ወዳጅ ዘመድ የወይዘሮዋን ድንገቴ ሞት ቢሰማ ከያለበት ደርሶ ግቢውን አጨናነቀው። ለቅሶው ፣ ሀዘኑ በረታ። ገና በጠዋቱ ለወንድሙ ደውሎ የሚስቱን ሞት ሲያረዳው ወደእሱ ሲመጣ የሬሳ ሳጥን እንዲገዛ በመንገር ነበር።
ወንድሙ በሰማው ጉዳይ ቢደናገጥም ወይዘሮዋ ድንገት ወድቃ ሞተች ያለውን ሰበብ ሊቀበለው አልቻለም። ገብቶ ካያት በኋላም በጥርጣሬና ባለማመን ስሜት ሆኖ ሲጨናነቅ ቆየ። የሌሊቱን ስቃይና ጩኸት ሲያዳምጡ ያደሩት ጎረቤቶች በአባወራው የፈጠራ ወሬ ተናደዋል። ባለቤቱ የሞተችው በደረሰባት ከባድ የድብደባ ጥቃት መሆኑን አውቀውም ለፖሊስ ጠቁመዋል። በድንገቴው ሞት የተደናገጡ የአካባቢው ሰዎች በሀዘን ደረታቸውን ደቁ። ከልብ አዝነው አነቡ፣አምርረው አለቀሱ።
የፖሊስ ምርመራ…
የወንጀሉ መፈጸም ጥቆማ የደረሰው ፖሊስ የወይዘሮዋን መሞት ፈጽሞ ያለመኑ ሰዎችን በመረጃ ይዞ በአባወራው ላይ የምርመራ ሂደቱን ጀመረ። የሟች እስከሬን ከመቀበሩ በፊት ደርሶም ተገቢውን ምርመራ አካሄደ ።
በትክክልም ሟች ከሰአታት በፊት ከባድ የሚባል ጥቃት ደርሶባታል። ተጠርጣሪው ጥያቄ ሲቀርብለት ማመን አልፈለገም። ባለቤቱ ወድቃ መሞቷን በማስረዳት ድርጊቱን ለመካድ ሞከረ። አልተሳካለትም። ጉዳዩን የያዘው የቢሾፍቱ ከተማ ወንጀል መርማሪ ምክትል ኢንስፔክተር ታሪኩ ወራቲ በመስቀለኛ ጥያቄ እያዋዛ እውነቱን እንዲናገር ጠበቀው። ግለሰቡ ምርጫ አልነበረውም። በልጆቹ እናት ላይ በቅናት መንፈስ ተነሳስቶ የግድያ ወንጀል ስለመፈጸሙ አመነ።
ውሳኔ…
ዓመታትን በትዳር አብራው ያሳለፈችውን የልጆቹን እናት በጭካኔ በገደለው ግለሰብ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት የተሰየመው ፍርድ ቤት ተከሳሹ ጥፋተኛ መሆኑን በማስረጃዎች አረጋግጧል። ህዳር 15 ቀን 2012 ዓ.ም በዋለው ችሎትም ግለሰቡ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የዕድሜ ልክ አስራት እንዲቀጣ ሲል ውሳኔውን አሳልፏል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን የካቲት 12 /2014