አዲስ አበባ፦ በቀጣይ ሁለት ዓመታት ይገነባሉ የተባሉት ሦስት አዳዲስ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሰመራ፣ በአይሻና በአሶሳ ከተማ የሚገነቡ መሆናቸውን አቶ አማረ አስግዶም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተናግረዋል።
ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የሚገነቡት ጆብ ኮምፓክት የሚል ስያሜ ባለው ፈንድ ሲሆን፤ በዚህ ፈንድ የዓለም ባንክ፤የአውሮፓ ህብረትና ሌሎች አጋር ድርጅቶችም ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። አጠቃላይ እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቁት እነዚሁ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታቸው በቅርቡ የሚጀመር መሆኑንም አስረድተዋል።
በአሁን ወቅት በኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን እጅ የሚገኝና ወደፊት ለሚፈጠሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት የሚውል 12 ሺህ ሄክታር መሬት በመሬት ባንክ ተይዞ በፕላን ተከልሎ ርክክብ የተደረገ ሲሆን፤ ከዚሁ ውስጥም ሦስት ሺህ ሄክታሩ ካሳ ተከፍሎበት ወደ ልማት የገባ ነው ብለዋል። ቀሪው ዘጠኝ ሺህ ሄክታር መሬት ደግሞ በሂደት በኮርፖሬሽኑ አቅምም ይሁን በግል የማልማት ፍላጎት ሲኖር በቅደም ተከተል ከመሬት ባንክ እየወጣ የሚለማ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማትና ማስፋፋት ከመንግሥት አቅም ጋር የሚያያዝ ቢሆንም የከተሞችንና የክልሎችን ተሳትፎም ይጠይቃል ያሉት አቶ አማረ፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገነቡባቸው ክልሎችና ከተሞች ከፌዴራል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር የፀጥታ፤ የወሰን ማስከበር፤ የመሬት ልየታና የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
አቶ ዑመር አህመድ የአሶሳ ከተማ ከንቲባም እንደተናገሩት፤ በቀጣይ ግንባታ ከሚጀመርባቸው አዳዲስ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል አንዱ የአሶሳ ከተማ እንደመሆኑ፤ ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ተግባራዊነት እየሠራን እንገኛለን ብለዋል። በዚህም የመሬት ልየታ መከናወናቸውንና የተለየውን ቦታ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለማስገባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከሰላም አንጻር አሶሳ ከተማ በአሁን ወቅት ሰላሟ የተረጋጋና ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2011
በፍሬህይወት አወቀ