አዲስ አበባ፡- ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው 33 ቢሊዮን 986 ሚሊዮን 693 ሺህ 730 ብር የተጨማሪ በጀት ጥያቄ ረቂቅ በምክር ቤቱ አባላት ዘንድ ጥያቄ አስነሳ። ምክር ቤቱ ትናንት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 26ኛ መደበኛ ስብሰባውን ሲያካሄድ፤ ከዓለም አቀፍ ማህበር ግማሹን በዕርዳታና ቀሪውን በብድር የተገኘውን 33 ነጥብ 99 ቢሊዮን ብር በጀት ጥያቄ ለምክር ቤቱ የቀረበ ሲሆን፤ አባላቱ ብድሩ ከአገሪቱ ፖሊሲ ጋር አይጣጣም፤ ግልጽነት ይጎድለዋል እና ሌሎች ጥያቄዎችን አንስተዋል። የምክር ቤቱ አባላት ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል በብድር መጥቶ እንዲጸድቅ የተጠየቀው በጀት ለህዝብና ቤት ቆጠራ የሚውል ነው።
የቆጠራ ኮሚሽኑ ባለፈው ጊዜያት ከነበረው የተዓማኒነትና የአሠራር ችግር ተነስቶ ሪፎርም ባልተደረገበት ሁኔታ ቆጠራ ማካሄድም ሆነ በጀት መመደብ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ ገንዘብ ሲረጭ አሁን ያለውን የ10 ነጥብ 9 በመቶ ግሽበት በማሳደግ የዜጎችን የኑሮ ውድነት ያባብሳል።
በዓመቱ መጀመሪያ ላይ የጸደቀው በጀት ጉድለት አለው። ይህን ጉድለት መሙላት እየተገባ ተጨማሪ መጽደቅ የለበትም። የአገሪቱ ፖሊሲ ከውጭ የሚገኝ ብድር ለካፒታል እንደሚውል ያስቀምጣል። አሁኑ የተገኘው ብድር የሚውለው ለመደበኛ እንደሆነ ያመላክታል፤ ይህ ከአገሪቱ ፖሊሲ ጋር ይጋጫልም ብለዋል። የምክር ቤቱ አባላት የተወሰነው ተጨማሪ በጀት የሚጸድቀው ለመጠባበቂያ እንደሆነም ገልጸዋል።
ገንዘቡ ለምን እንደሚውል ዝርዝር ማብራሪያ ሳይታወቅ ተጨማሪ በጀት ማጽደቅ አይገባም። ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ኪሊ-ቱሉ ካፒ የወርቅ ማዕድን ማውጫ መንገድና የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋት በዓመቱ መጀመሪያ በበጀት መያዝ ሲገባው ሳይያዝ አሁን ላይ በጀት መጠየቁ አግባበ አይደለም በማለት በደንብ መጠናትን መመርመር እንዳለበትም አመላክተዋል።
አባላቱ እነዚህና ሌሎች ጥያቄዎችን ከነሱ በኋላ ምክር ቤቱ ረቂቁን ለዝርዝር ዕይታ ለገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል። ምክር ቤቱ ከዚህ በተጨማሪ የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎችን ብዜት በገንዘብ መደግፍን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን ረቂቅ አዋጅ፣ በጅቡቲና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገውን የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነት፣ በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለሴቶች ንግድ ሥራ ፈጠራ ብቃት ማሳደጊያ ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የብድር ስምምነት፣ በኢትዮጵያና በጣሊያን ለአነስተኛና መካከለኛ ከተሞች ሳኒቴሽን እንዲሁም ለዘላቂና አካታች የግብርና ምርት እሴት ሰንሰለት ዕድገት ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2011
በአጎናፍር ገዛኽኝ