ልጆችን ቀጥቶ ማሳደግ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ማሕበራዊ እሴታችን ነው። ወላጆች ልጆቻቸውን በውጉ አሳድገው ለቁም ነገር የማብቃት ኃላፊነታቸውን በተለያዩ መንገዶች ይወጣሉ። እያንዳንዱ ወላጅ ልጆቹ ጥሩ ስብዕና እንዲላበሱ በሚመስለው መንገድ ይቀርጻቸዋል። ከሚፈለገው መስመር ሲወጡ ደግሞ ይገስጻቸዋል፤ በዚያም ካልተመለሱ ይቀጣቸዋል። ይህ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ያለፈበት ወግና ሥርዓት ነው።
አንዳንድ ጊዜ ግን ወላጆች ንዴታቸውን መቆጣጠር ሲያቅታቸው እንኳን በአብራክ ክፋይ ላይ በማንም ላይ ሊደረግ የማይችል የጭካኔ ብትር በልጆቻቸው ላይ እያሳረፉ ለከፋ ችግር ሲዳርጓቸው እንመለከታለን፡፡
የትኛውም የአካል ክፍላችን ሲጎድል መሉዕነት አይሰማንም። በተለይም ሠርተን ለማደር ከቦታ ቦታ የምንቀሳቀስበት የእግራችን ጉዳት በሕይወታችን ላይ የሚገጥመንን ፈተና የበለጠ ያከብድብናል። ጉዳቱ የደረሰብን በቤተሰብ በተለይም በወላጅ አባታችን መሆኑን ስናስብ ደግሞ ማመን ያቅተናል። ግራ በተጋባ ስሜት ውስጥ ሆነን የሕይወት ዘመናችንን እናሳልፋለን። ምንም ይሁን ምን ጉዳቱ ያሳደረብንን ተጽዕኖ ተቋቁመን ቀጣይ ሕይወታችንን ለመምራት ከመጣር ውጭ አማራጭ አይኖረንም።
የዛሬዋ እንግዳችን እንዲህ አይነት ታሪክ ካላቸው ሰዎች አንዷ ነች።ወጣት አስናቀች ዘገየ ትባላለች። ወጣቷ በአምስት ዓመቷ አባቷ ባደረሰባት ግርፋት ሁለት እግሮቿ ተጎድተው ለአካል ጉዳተኝነት የተዳረገች ነች።የትናንቷ ብላቴና የአሁኗ ወጣት በእናቷ ድጋፍና እንክብካቤ በርካታ መከራዎችን አልፋ የራሷን ሕይወት መኖር ብትጀምርም ዛሬም ድረስ በወላጅ ቅጣት ምክንያት የደረሰባትን አካል ጉዳተኝነት ተቋቁማ ራሷን ችላ ለመኖር ጥረት ታደርጋለች።አዲስ ዘመን ጋዜጣ የወጣቷ የሕይወት ታሪክና ተሞክሮ ለሌሎች ትምህርት እንዲሆን በማሰብ እንደሚከተለው አቅርቧል።
ወጣቷ እንዳጫወተችን ተወልዳ ያደገችው ባሌ ክፍለ አገር ጋሰራ ወረዳ ጉራንዳ ጊዮርጊስ በሚሰኘው አነስተኛ መንደር ነው። ጉዳቱ የደረሰባት የዚሁ መንደር ነዋሪ በነበሩት እናትና አባቷ ፀብ ምክንያት ነው።
ሁሉም ምሽቶች የእናትና አባቷ ፀብ ያልተለያቸውና በጭቅጭቅና ንትርክ የሚያልፉ ቢሆንም ለእሷ እንደዚያች ምሽት የሕይወት ዘመንዋን ሙሉ ያጨለመው ክስተት አልነበረም።
የፀቡ መንስኤ የአራት ወር ነፍሰ ጡር የነበረችው እናቷ እስዋን ለአባቷ ጥላ መጥፋት በማሰቧ የተከሰተ አለመግባባት ነበር። እናቷ እንዲህ አይነት ውሳኔ የወሰነችው ነጋ ጠባ የሚደርስባትን ጭቅጭቅና ዱላ ለመሸሸ ነበር።ሃሳቡ የእናቷ ብቻ አልነበረም።የባለቤቷ እህትም የሚደርስባትን ዱላ ለመገላገል ያላት የመጨረሻ አማራጭ ቤቱን ትቶ መጥፋት እንደሆነ ትመክራት እንደነበር አስናቀች ትናገራለች።
ሆኖም ይህ ሃሳብ በአማቷ /በአስናቀች አባት እናት/ ዘንድ ጥሩ ትርጉም አልተሰጠውም ነበር። አብስላ የምታበላው፣ ቡና የምታፈላለት፣ የምትንከባከበውና ቤቱን ሞቅ ደመቅ አድርጋ የምትጠብቀው ሚስቱ ልጃቸውን ጥላው መሄዷ (ልጃቸው ሚስቱን ማጣቱ) የበለጠ እንደሚጎዳው ያስባል። እንደአስናቀች አባባል አያቷ እናቷ ላይ የሚደርስባት በደል አልታያቸውም ነበር።
‹‹አሁን ሳስበው እናቴ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ሳያውቁት ቀርተው ሳይሆን የእናት አንጀት ሆኖባቸው ክርስቶስ ለሥጋው አደላ እንደሚባለው ለልጃቸው አድልተዋል›› ትላለች ወጣቷ።
እናም አያቷ /የአባቷ እናት/ ይሄን የልጃቸውንና የልጃቸውን ሚሰት ምክር ሰምተው ዝም ማለት ስላልፈለጉ ቀኑን ሙሉ ሲብሰለሰሉ ውለው ማታ ለልጃቸው ይነግሩታል።
‹‹አባቴ ከሥራ ሲመጣ ጠብቀውም ሚስትህ ልጅህን እኔ ጋር ጥላልህ ጠፍታ ልትሄድ ነው›› ብለው ይነግሩታል።በዚሁ ምክንያትም ምሽት ላይ ‹‹ልጄን ለእናቴ ጥለሽ ልትጠፊ ነው›› በማለት አባቷ በር ዘግቶ እናቷን ይደበድባል።ድብደባው የፀናባትና የአራት ወር ቅሪት የነበረችው እናቷ መሬት ላይ ትዘረራለች።
ይሄኔ ብላላቴናዋ አስናቀች ያለማቋረጥ ታለቅሳለች። ዝም እንድትል አባቷ ቢያስፈራራትም ጩኽቷን አላቆም ትላልች። በዚህ የተበሳጨው አባቷ ይገርፋታል። በመጠጥ ሞቅታ ታጅቦ የተፈፀመው ግርፋት ህፃን የሚቀጣበት ወግ አልነበረምና አስናቀችም እንደ እናቷ ራሷን ስታ ትወድቃለች። አባት እናትና ልጁን እወደቁበት ትቶ እናቱ ዘንድ ሄዶ ያድራል። እሷና እናቷ ግን እዛው የወደቁበት ቦታ ያነጋሉ።
ማለዳ እናት ከወደቀችበት ተጣጥራ በመነሳት አስናቀችን ለአባቷ ቤተሰቦች ሰጥታ በቅርበት ወደሚገኙት ቤተሰቦቿ ጋር ትሄዳለች። ብዙም ሳትቆይ በሦስተኛው ቀን የአስናቀች የአባቷ ዘመዶች አስናቀች በፀና ታማለች ብለው ለእናቷ መልክተኛ ይልካሉ። እናቷ ወይዘሮ ትዕግስት ሙሉጌታ ስትከንፍ ትሄዳለች።
ሆኖም እንደ ልቧ ወዲያ ወዲህ በማለት ትቦርቅ የነበረችው ልጇ መቆምም ሆነ መቀመጥ ተስኗት ታገኛታለች። በኋላ ወደ ህክምና ስትወስዳት ሐኪም ጭንቅላቷ ውስጥ ደም መፍሰሱን ይነግራታል።አስናቀች ሁኔታውን ከእናቷ እንደተረዳችው በወቅቱ መናገር አቁማለች፤ ሰውነቷ ክፉኛ ያተኩስ ነበር ፤ ሁለቱም እግሮቿም እብጠት ጀምረዋል።
አንድ ጊዜ በወጌሻ ሌላ ጊዜም በህክምና እርዳታ ቢደረግላትም ከህመሟ መዳን ይሳናታል።ፈጥና ጥሩ ሕክምና አላገኘችም ነበር።በዚህ የተነሳ ጉዳቱ ስር እየሰደደ ሄደ።
ወላጅ እናቷ በአምስት ዓመቷ አሁን ወደ ምትኖርበት አዲስ አበባ ከተማ አስናቀችን ይዛት ትመጣለች።እናቷ በችግር ውስጥ ሆናም ቢሆን ልታሳክማት ሞከረች ግን አልሆነም።ህክምና እየሞከረች ለብዙ ዓመታት ስትሰቃይ ቆይታለች። እናቷም ለሁለት አሥርት ዓመታት ደክማላታለች።የጤናዋ ጉዳይ ግን መሻሻል አልቻለም።
‹‹የእናቴን ድካምና ልፋት የሚገልጸው ቃል የለም፤ ከእኔ ጋር ፍዳዋን አይታለች›› ትላለች አስናቀች።እናቷ እርሷን ለማሳከም አስር ዓመት በሰው ቤት ሠርታለች።
‹‹እኔ የአካል ጉደተኛ መሆኔን ሲያዩ አንፈልግም። መቅጠራችንን ትተነዋል ይሏት ነበር። በዚህ የተነሳ ለእኔ ብላ እጅግ ዝቅ ባለ ዋጋ ቀጥረው እንዲያሰሯት ሁሉ ለምና ታውቃለች›› ብላናለችም አስናቀች። ብቻ ወጣቷ እንዳወጋችን እናቷ ለእሷ ብላ ያልወጣችው ያልወረደችው የለም፤ ያልሞከረችው የሥራ ዓይነት አልነበረም።
‹‹በዚህ ላይ እያደኩ ስመጣና ክብደቴ ሲጨምር ተሸክማ ሆስፒታል ልታመላልሰኝ ባለመቻሏ እጅግ ታዝን ነበር። እግሬ እየተንዘላዘለ ትሸከመኝ ነበር›› ስትል የእናቷን መንገላታት ታስታውሳለች። በወቅቱ የእናቷ ወንድም አጎቷ በሸክም ይረዳት እንደነበርም ታክላለች። ‹‹እናቴ ለኔ ያልሆነችው የለም›› የምትለው ወጣቷ ፈትላ ጋቢ አሰርታ፣ ዳንቴል ሰርታ፣ ትኩስ ምግቦችን አብስላ በመሸጥ እቁብ እየጣለች እንዳሳከመቻትም ነግራናለች።
አስናቀች እንዳወጋችን እናቷ አካል ጉዳተኛ ልጆችን የሚደግፉትን ቲሻየር ሆምን ያገኘቻቸው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጊቢ ውስጥ እሷን ስታሳክም በነበረበት ወቅት ነው። ቲሻየር ሆምም ነፃ ሕክምና እንድታገኝ በማድግ እናቷን ከሕክምና ወጪና ከሌሎች ከእሷ የእግር ጉዳት ጋር ከሚደርስባት እንግልትና ውጣ ውረድ አሳርፈዋታል። በኋላም እራሳቸው ጋር ወስደው ሲያኖሯት እናቷ እንደ ልቧም ሥራ መሥራት ጀመረች።
‹‹በዚህ ሁኔታ ሁለቱንም እግሬን በቀዶ ጥገና ታከምኩ። የተጣመመውም ተቃናልኝ። ጫማም በልኬ ተሰራልኝና አደረኩ። በሁለት ክራንች እየታገዝኩ በእግሮቼ ቆሜ መሄድ ቻልኩ›› ብላናለች ወጣት አስናቀች የሕክምናውን የመጨረሻ ውጤት ስትገልፅልን። ሕክምናው ሲጠናቀቅ ከቲሻየር ሆም ወጣች። የሚያደርግላት ድጋፍም ቆመ። ሆኖም ከሕክምናው ጎን ለጎን በእናቷ ጥረት ትማር የነበረውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አጠናቅቃ በአይ.ሲ.ቲ ለመመረቅ በቅታለች።
‹‹እናቴ ትምህርቴን እስከ ፕሮፌሰርነት እንድቀጥል ትፈልጋለች›› የምትለው አስናቀች ሆኖም በዲፕሎማ በተመረቀችበት በአይ.ሲ.ቲ የሙያ መስክ ሥራ ልትቀጠር ባለመቻሏ ተስፋ መቁረጥዋንም አጫውታናለች። በእናቷ ጉትጎታና እራሷ ባላት የመማር ፍላጎት ትምህርት የመቀጠል ዕቅድ አላት። ሥራ ያላገኘችበትንና በዲፕሎማ የተመረቀችበትን የአይ.ሲ.ቲውን ሙያ ትምህርት መስክ ሥራ በሚገኝበት በአካውንቲንግ ትምህርት መስክ ወደ ዲግሪ ለማሳደግ አስባለች።
ይህ እቅዷ አሁንም የእናቷን ድጋፍ የሚፈልግ ነው። እናቷ እሷን በሚያስፈልጋት ጊዜ ሁሉ ለመደገፍ ዝግጁ ብትሆንም የሚመቻትን ቤት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ማግኘት ይከብዳታል።
አዲስ አበባ በእርሷ ደረጃ የምትፈልጋት አንድ ክፍል ቤት የኪራይ ዋጋዋ አራት ሺ ብር ነው።በዚህ ላይ የደላላ ይከፈላል፤ የመብራትና ውሃም ለብቻ ይታሰባል።ይህን የሚያደርግ አቅም አይኖራትም።
እንዲህ አይነት ዋጋ ቢከፈልባቸውም መፀዳ ጃቸው እሷ ልትጠቀምባቸው የሚያስችሏት አይደሉም። አብዛኛዎቹ መሬት ላይ ቁጭ ተብሎ ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ ናቸው። በዚህ ላይ የጋራም ናቸው። እኔ በእንዲህ ዓይነቶቹ መፀዳጃዎች መጠቀም አልችልም። ለመፀዳዳት ስፈልግ እናቴ የግድ ከአጠገቤ መኖር አለባት›› ትላለች።
አስናቀች በአሁኑ ወቅት በዚሁ በቤት ውድነትና ምቹ ያለመሆን እንዲሁም በሥራ እጦት ምክንያት ሰርክ አጠገቧ በመገኘት ከማፀዳዳት ጀምሮ ድጋፍ ከምታደርግላትና ‹ብቸኛዋ ደጋፊ› ከምትላት ወላጅ እናቷ ተለይታ ጎባ ከተማ ውስጥ ሄዳ ለመኖር ተገድዳለች። ‹‹ጎባ እንደ አዲስ አበባ ከተማ ቤት ውድ አይደለም። እንደ አቅም ቤት አግኝቶ መኖር ይቻላል›› የምትለው አስናቀች ጎዳና ዳር ቡና እያፈላች በመሸጥ በወር ከሶስት መቶ እስከ አራት መቶ የአቅሟን ቤት ኪራይ እየከፈለች መኖሯን አውግታናለች።
ሆኖም ዋነኛ የገቢ ምንጯ ‹ቡና ጠጡ› እንደመሆኑ ገቢው አሁን በምኖርበት ሁኔታ ያዛልቀኛል ብላ አታምንም። ምክንያቱ ደግሞ አንዳንድ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሥራውን እሷ በመሥራቷ ያላቸው አመለካከት የተዛባ መሆኑ ነው። በክራንች እየተንቀሳቀሱ መሥራቱ ስለማያመቻት በየመቀመጫው እየዞረች ቡናውን የምታድልና ሳንቲም የምትቀበል አንዲት ልጅ ብትቀጥርም አንዳንዶቹ ሰዎች ሥራውን በመሥራቷ ደስተኛ አለመሆናቸውን ትናገራለች።
‹‹እኔን ሲያዩ በጣም የሚደነግጡ በርካቶች ናቸው ትላለች።የዚያኑ ያህል የሚያበረታቷት አይጠፉም። አዝነውና ጉዳቷ ተሰምቷቸው አይዞሽ የሚሏት፤ እንዲህ ብታደርጊ እያሉ ምክር የሚለግሷትም ብዙ ናቸው።
አስናቀች እናቷ አጠገብ ሆና ብትሰራ ትመርጣለች፤ እናቷም ብትሆን ግድ ሆኖባት እንጂ ልጇ ከአጠገቧ እንድትለያት አትፈልግም። ቢቻላትና ፈጣሪ ቢፈቅድ የሚያስፈልጋትን ድጋፍ ሁሉ እያደረገችላት ዘወትር ከእሷ አጠገብ ሳትለይ ብትኖር ትመርጣለች። ለዚህ ብላ የምታደርጋቸውም ጥረቶች አሉ።
የደረሰብኝ የእግር ጉዳት ማስታወቂያ በወጣ ቁጥር እንደልብ አንቀሳቅሶ ሥራ ለመፈለግ ስለማያስችለኝ በየመሥሪያ ቤቱ የምታመለክትልኝ እናቴ ናት›› አስናቀች በ18 ዓመቷ የወለደቻትን የሰባት ዓመት ልጇን እናቷ ወስዳ እያሳደገችላት እንዳለችም ትናገራለች። ልጅቱን ያገኘችውን በመሥራት የተሻለ የግል ትምህርት ቤት በማስገባት ሁለተኛ ክፍል እንዳደረሰችላትም ገልፃልናለች። ሰርክ ቤት የምትከራየውም ህፃንዋን ከትምህርት ቤት ማምጣትና ማድረስ በሚያስችላት አመቺ አቅራቢያ ነው።
ወጣት አስናቀች እሷም ከእናቷና ከልጇ አጠገብ ሆና የመኖርና ሥራ የመሥራት ብርቱ ፍላጎትና ምኞት እንዳላትም ነግራናለች። ከእናቷ አጠገብ ሆና ቀን እየሰራች ማታ ዲግሪዋን በአካውንቲንግ ትምህርት የመቀጠል ራዕይዋንም አጫውታናለች። ሆኖም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አሁን ድረስ ይሄን ራዕይዋን ማሳካት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ አልተፈጠረላትም።በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩም ሆነ ቤት የመስጠት ኃላፊነት ያለባቸው ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች የወጣቷን ጉዳትና ራሷን ለመቻል የምታደርገውን የመፍጨርጨር ጥረት ከግንዛቤ በማስገባት ድጋፍ የሚያደርግላት አካል እንዲኖር ተመኘን።ቸር እንሰንብት፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2014