የባልና ሚስቱ ትዳር ሰላም ከራቀው ቆይቷል። ጥንዶቹ ጠዋት ማታ ይጨቃጨቃሉ። በየቀኑ ይጣላሉ። ዓመታትን በተሻገረው አብሮነት የተገኙት ሁለት ልጆች በእናት አባታቸው ጠብ መሸማቀቅ ልምዳቸው ሆኗል። ወይዘሮዋ አሁን ላይ እየቆረጠች ነው። በየቀኑ ከመጣላትና ከመጨቃጨቅ ባሏን መፍታት እንደሚሻል ታስባለች።
አንዳንዴ ደግሞ ‹‹ሁሉን ትተሸ ጥፊ›› የሚል ስሜት ይፈትናታል። መለስ ብላ ግን ሌላ ታስባለች። እንዲህ ካደረገች ሁለት ልጆቿ ይጎዳሉ። የለፋችበት፣ ዕድሜ፣ ጉልበቷን የከለፈለችበት ትዳር መና ይቀራል። እሷ ብትርቅ አባወራዋ ሌላ ሚስት ያገባል። እሷ ከቤት ብትወጣ ልጆቿ በእንጀራ እናት እጅ ይወድቃሉ። ያቀናችው ጎጆ፣ የለፋችበት ቤት በሌላ ሴት ይወረሳል።
ሰላም ያጣው ትዳር አሁንም ያለመፍትሄ ቀጥሏል። የባልና ሚስቱ ጠብ በመኮራረፍ ቀናትን እየተሻገረ ቅያሜን አዳብሯል። በየጊዜው ለሽምግልና የሚገቡ ዘመዶች ሙከራ ፈጽሞ አልተሳካም። ሰዎቹ የጥንዶቹ ሰላም ውሎ ሳያድር በመክሰሙ ተቸግረዋል። ለማስማማት፣ አስታርቆ አንድ ለማድረግ የለፉበት ሕይወት መልኩን ቀይሯል። ፍቅር ጠፍቶ፣ መተሳሳብ ይሉት ርቆ፣ በክፉ መተያያት ከተተካ ውሎ አድሯል።
ከዕለታት በአንዱ ቀን የባልና ሚስቱ ጠብና ጭቅጭቅ ከወትሮው ተለየ። እንደዋዛ የተነሳው አለመግባባት ተባብሶም ዱላና ቡጢ ተመዘዘ። ይህኔ ወይዘሮዋ ከልብ ተከፋች። እስከዛሬ ቤቴን፣ ትዳሬን ስትል የቆየችበት እህል ውሀ ሊቋጭ መድረሱ ገባት። ከዚህ በኋላ ከባለቤቷ ጋር በአንድ ጣራ ማደሩ፣ በትዳር መቀጠሉ፣ አልታይ፣ አልዋጥልሽ ቢላት አሻግራ አሰበች።
ወይዘሮዋ በትዳር ቆይታዋ ያፈራቻቸውን ሁለት ልጆች ደጋግማ አየቻቸው። ሁለቱም ህጻናትና ለስራ ያልደረሱ ናቸው። መለስ ብላ ራሷን አጤነች። ሕይወቷ አደጋ ላይ ነው። ዛሬን ልተወው ብትል፣ ነገን ማለፍ የሚያስችል ዕድል የለም። ሁሉም አማራጭ የሚያዋጣ አልሆን አላት ።
ድንገቴው ሀሳብ …
ከቀናት በአንዱ ቀን ማልዳ የወጣችው ወይዘሮ ተመልሳ ላትመጣ፣ ቤቴን ትዳሬን ላትል ከውሳኔ ደረሰች። አሁን ሁለቱ ልጆቿ ከአባታቸው ጋር መሆን ይችላሉ። እሷ ግን ለራሷ ሰላምና ጤና ስትል አገር መንደሩን መልቀቅ አለባት። ዕቅዷን መላልሳ ማሰብ አላስፈለጋትም። ሳታወላውል ቆረጠች።
ወይዘሮዋ የልቧን ውጥን ለመፈጸም፣ ከሰላሟ ጥግ ለመድረስ በልጆቿ ጨከነች። ቤት ጎጇዋን፣ ትዳር ሕይወቷን ትታ ከመኖሪያዋ ራቀች። ምስራቅ ሀረርጌ፣ ኮምቦልቻ ወረዳ፣ ለጋሀማ ቀበሌን ትታ አካባቢዋን ስትለቅ በውሳኔዋ እንደጸናች ነበር።
አሁን ቤት ይሉት ኑሮ፣ ትዳር ይባል ሕይወት ወደ ኋላ ቀርቷል። ወይዘሮዋ ሰላም ያጣችበትን ጎጆ ዘግታ፣ ቤት ንብረቷን ትታ፣ ልጆቿን አራግፋ እግሯ ወደመራት እየተጓዘች ነው። በእንግድነት ያረፈችበት ከተማ ለጊዜው ያሳለፈችውን ውጣ ውረድ አስረሳት።
ወይዘሮዋ ራሷን ለአዲስ ሕይወት አዘጋጀች። ሁሉን ትታ፣ ሰላሟን መምረጧ ልክ እንደነበር ለራሷ ነገረችው። ውስጧን እፎይታ ተሰማው። ውሳኔዋ ትክክል እንደሆነ ገባት።
ከጊዜያት በኋላ…
ማረፊያዋን በአወዳይ ከተማ ያደረገችው ወይዘሮ ከትውልድ መንደሯ ርቃ ሌላ ሕይወት ከጀመረች ቀናት ተቆጥረዋል። ሁሌም በዓይኖቿ ውል የሚሉባት ህጻናት ልጆቿ ናፍቆት እያሳቃያት ነው። ያም ሆኖ ከቀድሞው፣ የአሁኑ ኑሮ የተሻለ እንደሆነ አውቃለች። በከተማው ዋል አደር ስትል ከአንዳንዶች መተዋወቋ፣ ከብዙዎች መግባባቷ መልካም ሆኖላታል ።
ወይዘሮዋ አንድ ቀን ድንገት ካገኘችው ጎልማሳ ጋር ቅርበቷ በረታ። በተገናኙ ቁጥር ወሬ ጨዋታቸው ተለየ። ከሌሎች አስበልጣ የቀረበችውን ሰው በቀላሉ አልራቀችውም። የውስጧን እውነት፣ ያሳለፈችውን ሀቅ አንድም ሳይቀር አወራችው። ሰውዬው የወይዘሮዋን ታሪክ ጊዜ ወስዶ ማድመጡ በብሶተኛዋ ሴት ዓይኖች አስወደደው። እሷ አድማጭ በማግኘቷ ብቸኝነቷን ረሳች። ለሰውዬው በልቧ ልዩ ቦታ ሰጠችው።
ውሎ አድሮ የወይዘሮዋና የሰውዬው ቅርበት ከሌሎች ተለየ። ብቸኝነትና ባይተዋርነቷን ያወቀላትን ጎልማሳ ከልቧ ወደደችው አመነችው። ጥቂት ቆይቶ የ‹‹አብረን እንኑር›› ፍላጎት ተከተለ። ያለማወላወል ተስማማች። ያጣችውን ትዳር፣ የጎደለባትን ቀሪ ሕይወት ከእሱ ተጣምራ ልትሞላው ወሰነች።
አዲስ ህይወት…
አሁን ወይዘሮዋና ሰውዬው በአንድ መኖር ጀምረዋል። ሰፈርተኛው ከግለሰቡ ጋር የምትኖረውን ሴት ስትወጣ ስትገባ ያያታል። ከዓይን እይታ የዘለለ ቅርበት የላቸውምና ሰላም ተባብለው አያውቁም። ሰውዬውም ቢሆን ለጎረቤቶቹ አብራው ስለምትኖረው ሴት ተናግሮ አያውቅም። ቀርቦ የጠየቀው ማንም የለምና አብሮነቱ ከእሷ ብቻ ሆኗል።
ሰውዬውን በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች ባህርይውን አያጡትም። እሱ እስከዛሬ ሕይወቱን ከብዙ ሴቶች አጣምሯል። ከአብዛኞቹ ጋር ግን በሰላም አልዘለቀም። አብረውት የቆዩ ሴቶች ሁሉ ዕንባቸውን ሲያዘሩ፣ ጩኸታቸውን ሲያሰሙ ነበር። መንደርተኛው ሰውዬውን በእጅጉ ሲፈራው ኖሯል። እስካሁን ከእሱ ቀርቦ የሚግባባም ሆነ ሰላም የሚለው አልታየም።
ወይዘሮዋ ይሁን ብላ በገባችበት ሕይወት ግራ መጋባት ይዛለች። ትናንት ጥላው የመጣችው ታሪክ ዛሬ መልኩን ቀይሮ ስለቆያት እየተጨነቀች ነው። ይህን ችግሯን ቀርባ የምታዋየው፤ መፍትሄ የምትጠይቀው፤ ወዳጅ ዘመድ የለም። ጠዋት ማታ በክፉ ባህርይው እየተሳቀቀች ኑሮን መግፋት ይዛለች።
ሁሌም ምሽት መንደሩን አቋርጦ የሚሰማው ኃይለ-ቃል ጥቂት ቆይቶ በሴት ጩኸት ይታጀባል። ይህ አይነቱ ድምጽ ለአካባቢው ነዋሪ አዲስ ሆኖ አያውቅም። ጩኸቱ ዛሬ በዚህች ሴት ድምጽ ይሰማ እንጂ ከዚህ ቀድሞ በሌሎች ጭምር ይታወቃል።
ከሰውዬው መኖሪያ የተለመደው የሴት ጩኸት በተሰማ ቁጥር መንደርተኛው ቤቱን ዘግቶ ያዳምጣል። እንዲህ ከማድረግ የዘለለ ሊገላግል የሚወጣ አይገኝም። ነዋሪው ምሽትም ሆነ ሲነጋ ምን ሆናችሁ? ማለትን ሞክሮት አያውቅም። ሁሌም የማታው ሰዓት በሴቶች ጩኸት ደምቆ በሰውዬው ኃይለ-ቃል ይደመደማል። በጎረቤት ዝምታ ተውጦ፣ በተለመደው ሹክሹታ ይነጋል።
አንዳንዶች ሰውዬው በሚፈጽመው የጉልበት ጥቃት በጥቂት ሴቶች ስለመከሰሱ ያውቃሉ። በሌላ ቀን ተመሳሳይ ድርጊት ሲያዩ ግን ለማስቆም ሞክረው አያውቁም። ሁሉም ሰፈርተኛ የሰውየውን ድርጊት የጎሪጥ እያየ በፍርሀት ይሸማቀቃል፤ በጥርጣሬ እያስተዋለ በቸልተኝነት ያልፋል።
ምሽት በመጣ ቁጥር ከሰውየው ቤት የሚሰማውን የሴት ጨኸት የመንደሩ ሰው ለምዶታል። አሁንም ብዙዎች በሚሰሙት ድምጽ ይጨነቃሉ። ያም ሆኖ የለመፍትሄ ብዙ ለሊቶች ተቆጥረዋል። የረባ ንግግርም ሆነ የአንገት ሰላምታ በሌለበት፣ የሴትዬዋን ችግር ቀርቦ የጠየቀ አልተገኝም።
ሰውዬው ገብቶ በወጣ ቁጥር በፍርሀት የሚያስተውለው ሰፈርተኛ የቀድሞውን ተመሳሳይ ታሪክ አይረሳም። ለፖሊስ ብንናገር፣ ለሕግ ብናሳውቅ ችግር ይገጥመናል ሲል ያስባል። ከዚህ ቀደም ታስሮ በዋስ ተፈትቷል። በዚህ ሳቢያ ነዋሪው የሰማውን እንዳልሰማ፣ ያየውን እንዳለየ ሆኖ ቀናት ተቆጥረዋል።
ያልተለመደው ዝምታ…
ሰሞኑን ከወትሮው በተለየ በጥንዶቹ ቤት ዝምታ ነግሷል። ምሽቱን እንደቀድሞው ጩኸትና ጭቅጭቅ አይሰማም። የሰወዬው ኃይለ-ቃል ጨለማውን ጥሶ ከጆሮ አይደርስም። አጋጣሚው እፎይታን የፈጠረለት ሰፈርተኛ ባገኘው ዝምታ ሰላሙን ወስዶ ዕንቅልፉን ተኝቷል።
አሁን በጥንዶቹ መሀል ፍቅር የሰፈነ ይመስላል። ሰውዬው ከቤቱ ወጥቶ ሲመለስ በተለየ መረጋጋት ነው። እንደቀድሞው ከሴትየዋ ጋር ሲጨቃጨቅ አይሰማም። እሷም ብትሆን ዝምታን መርጣ ሰላም ካገኘች ቀናት አልፈዋል። አብሯት ያለው ሰው ምሽት ላይ እየደበደበ አያስጮሀትም፣ አያስለቅሳትም።
ሰፈርተኛውን የጎሪጥ የሚያስተውለው ጎልማሳ አሁንም ማንም እንዲያናግር፣ እንዲቀርበው አይሻም ። በተለይ ሰሞኑን ከበር ቆሞ ላይ ታቹን መቃኘት ይዟል። ዞር ብሎ ለሚያየው ደግሞ ምላሹ የከፋ ነው። ግልምጫና መኮሳተሩ ከማንም አያስጠጋም። አስተያየቱ ያስፈራል። ሰውን ሁሉ የሚያምን፣ የሚጠጋ አይመስልም። እይታው ጥርጣሬን ተላብሷል። ዓይኖቹ ከላይ ታች እየቃበዙ አሻግረው ይቃኛሉ። እርምጃው በጥንቃቄ ሆኗል።
አሁን የጥንዶቹ ድምጽ ብቻ ሳይሆን ዱካቸው ጭምር ጠፍቷል። እንደወትሮው በአንድ ሲወጡ ሲገቡ አይታይም። ምሽቱን ሰንጥቆ የሚወጣው ድምጻቸው በዝምታ ከተተካ ሁለት ወራት ተቆጥረዋል። መስኮቱ እንደተከረቸመ ነው። የተዘጋው በርም ሳይከፈት ከርሟል።
የአካባቢው ዝምታ ከሰዎቹ መጥፋት ተዳምሮ ሰፈርተኛውን እያነጋገረ ነው። ከተዘጋው በር አጠገብ ዝር ያለ የለም። ስለእነሱ መጥፋት፣ ስለድምጻቸው አለመሰማት፣ ከማውራት የዘለለ ወደ ሕግ ያለፈ፣ ለሚመለከተው የጠቆመ አልተገኘም።
ቤት ተከራዩ…
አንድ ቀን ረፋድ አካባቢ የተገኘ ቤት ፈላጊ ከመንደሩ ደርሶ የሚከራይ ቤት ይኖር እንደሆን ጠየቀ። ፍላጎቱን ያወቁ አንዳንዶች ጥቂት አመንትተው ይበጀዋል ያሉትን መኖሪያ ጠቆሙት። የተጠቆመው ቤት ያለሰው ተዘግቶ ወራት አስቆጥሯል። የነበረበት ተከራይ ‹‹እዚህ ሄድኩ›› ሳይል ከአካባቢው ጠፍቷል። በውስጡ የረባ ዕቃ እንደሌለው የሚያውቁት አከራዮች ቤቱን ለፈላጊዎች ሊያከራዩት ወስነዋል።
ሰውዬው መንደሩን አቋርጦ ወደ ተጠቆመው ቤት አመራ። ከቤቱ ባለቤቶች ተገናኝቶም ጥቂት ቆሞ አወራ። ቤቱ ባለ ሁለት ክፍል እንደሆነ ተነግሮታል። አዲሱ ተከራይ ቁልፉን ተቀብሎ ቤቱን መክፈት ጀመረ። ወደ ውሰጥ አልፎ ውስጡን ከመቃኘቱ ለአፍንጫው የሚከብድ ክፉ ሽታ ሰነፈጠው።
ተከራዩ እንደምንም ውስጡን ተቆጣጥሮ ወደ ሁለተኛው ክፍል ለማለፍ መራመድ ጀመረ። እየሸተተው ያለውን ጉዳይ በቀላሉ መታገል አልቻለም። ውስጡን እየተናነቀው፣ ሆዱን እየጓጎጠው ወደ ውስጥ አለፈ። የተመለከተውን እውነት ፈጽሞ ማመን አልቻለም። ዓይኖቹ እንደፈጠጡ ልቡን ደግፎ ቆመ።
ሰውዬው ያየውን እንዳላየ አድርጎ ቤቱን እንደወደደው ተናገረ። ተመልሶ እደሚመጣ ቃል ገብቶም ከአካባቢው ሊወጣ ፈጠነ። በፊቱ የተለየ ምልክት ባለመታየቱ ምን ሆንክ? እያለ ጥያቄ ያበዛባት አልነበረም። ከሰፈሩ እንደወጣ እግሮቹ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ፈጠኑ። በስፍራው ደርሶ ሁኔታውን ሲናገር የፖሊሶች ጆሮዎች ነቁ። እግሮቻቸው ወደ ተባለው ስፍራ ሊደርሱ ከእነርሱ ሲተባበሩ አልዘገዩም። ጠቋሚውን ተከትሎ የተጓዘው የፖሊስ ሀይል በመንደሩ ደርሶ ቤቱን ከፍቶ ገባ።
ፖሊሶቹ የመጀመሪያውን ክፍል አልፈው ወደ ውስጥ ሲገቡ ከባድና ለአፍንጫ የሚሰነፍጥ ሽታ ተቀበላቸው። ጥቂት እንደተራመዱ ከወለሉ ያዩትን አውነት ሊቀበሉት አልቻሉም። አንድ የሴት የሚመስል አካል ከመሬት ተጋድሟል። ጠጋ ብለው ለማረጋገጥ ሞከሩ መፈራረስ ከጀመረ ወራት ማስቆጠሩ ገባቸው።
ፖሊስ አተኩሮ ለማየት በእጅጉ የሚከብደውን እውነት በማስረጃዎች ማረጋገጥ ግድ ብሎታል። በስፍራው ያለውን ጩኸትና ለቅሶ አረጋግቶ መረጃዎችን አሰባሰበ። አጋጣሚ ሆኖ ከወራት በፊት በቤቱ የነበረውን ግለሰብ አጠገቡ ቆሞ ሁኔታውን ሲቃኝ አገኘው። ሰውዬውን ከእጁ አስገብቶ ሌላ ተከራይ ናት የተባለችን ጎረቤት አስከትሎ ወደ ፖሊስ ጣቢያ አመራ።
የክትትልና የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ ስለወንጀሉ ማጣራት ተጀመረ። ምክትል ሳጂን እቴነሽ በጋሻው ለተጠርጣሪው ጥያቄቸውን በጥንቃቄ አቀረቡ። ሰውዬው የሆነውን አንድ በአንድ መናገር ጀመረ። ከሁለት ወራት በፊት አብራው የነበረችውን ሴት በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏታል። ሴትየዋ ከባሏ ሸሽታ ከእሱ ጋር ለቀናት የቆየች የልጆች እናት ነበረች።
ሰውዬው መሞቷን እንዳወቀ ለወራት በር ዘግቶባት አካባቢውን በጥርጣሬ ሲቃኝ ቆይቷል። የእሱ ሀሳብ አካሏ ፈራርሶ አስኪያበቃ ከደሙ ንጹህ መስሎ መጠበቅና ሕይወቱን መቀጠል ነበር። እስካሁንም የወንጀሉን ዱካ የማጥፋት ውጥኑን ማንም ሳያውቅ ሁለት ወራትን አስቆጥሯል ። በዕለቱ በስፍራው የተገኘውም የሚሆነውን ለማየትና ለማረጋገጥ ነበር ።
ፖሊስ የሟች ስም ወይዘሮ አይሻ ኑር መባሉን አረጋግጧል። ከየት እንደመጣች ለማወቅም ፈዲስ፣ አወዳይና ድሬዳዋ ከተሞችን በፍለጋ ሲያስስ ከርሟል። የሟች አስከሬን ወደ አዲስ አበባ ተልኮ ውጤቱ እንደመጣ ፖሊስ ከዐቃቤ ሕግ ተባብሮ የክስ ሂደቱን ቀጠለ።
ውሳኔ…
ጥር 27 ቀን 2011 ዓም በርካቶችን ዕንባ ሲያራጭ የከረመው የግድያ ወንጀል በዚህ ቀን በፍትህ ሊዳኝ ጊዜው ደርሷል። አሳዛኙን ታሪክ የሰሙና የተመለከቱ ሁሉ ከችሎቱ ተገኝተዋል። ዳኞች የክስ መዝገቡን አጣርተው ተከሳሹ ጥፋተኛ መሆኑን አረጋግጠዋል። በዕለቱ የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድቤቱ በሰጠው የመጨረሻ ውሳኔም ግለሰቡ በዕምነት የተጠጋችውን ወይዘሮ በጭካኔ በመግደሉና ተጠያቂ ላለመሆን አስከሬኗን በድብቅ በማኖሩ የሞት ቅጣት ይወሰንበት ሲል ብይን ሰጥቷል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2014