
• መስቀል አደባባይን በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎች በሕጋዊ መንገድ ይፈታሉ
አዲስ አበባ፡- የለውጥ ኃይሉ ለሃይማኖት ያለው አተያይ የተዛባ እንደሆነ መልክ ለማስያዝ የሚደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም መንግሥት ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በትብብር እየሠራ ይገኛል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
መስቀል አደባባይን በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎችን በሕጋዊና ሠላማዊ መንገድ ከተማ አስተዳደሩ እንደሚፈታ ከንቲባዋ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ ጉባዔ ማጠናቀቂያ ትናንት ሲደረግ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ2014ዓ.ም የግማሽ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርትን አስመልክቶ ከምክር ቤቱ ለተነሳላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡
በወቅቱ ከሃይማኖትና ከመንግሥት ግንኙነት አንጻር ከለውጡ ጋር ተያይዞ የለውጥ ኃይሉ ለሃይማኖት ያለው አተያይ የተዛባ እንደሆነ መልክ ለማስያዝ የሚደረጉ ጥረቶች አሉ፤ ይሁንና መንግሥት ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በትብብር የሚያከናውነውን ሥራ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።
የመንግሥትና የሃይማኖትን ግንኙነትን በተመለከተ አንዳንድ ሰዎች ያላቸው ዕይታ የተሳሳተ ቢሆንም፤ መንግሥት ግን ከሃይማኖት ተቋማት ጋር የልማትና የሠላም ሥራዎችን ጨምሮ በትብብር እየሠራ ይገኛል ብለዋል። በሰላምና ጸጥታ እንዲሁም በልማት ጉዳዮች ላይ በጋራ የመስራት ልምዱ እንደቀጠለ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ከዚህ የመንግሥት ጥረት ባለፈ ግን ስናገለግል የመንግሥትን ኃላፊነትና ሃይማኖታችንን በተመለከተ መስመራችንን መጠበቅ አለብን፡፡ ነገር ግን በራሳችን ፍላጎትና ትህትና ዝቅ ብለን ማክበር እንችላለን። ከዚህ አንጻር ግን ችግር ሲፈጠር የመሪዎችን ስም እየጠቀሱ ከሚከተሉት ኃይማኖት ጋር ጉዳዩን ማያያዝ ስህተት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሰዎች የትኛውንም ዕምነት በነጻነት የመከተል ነጻነት እንዳላቸውና ይህ ነጻነት በየትኛውም አካል መከበር መቻል እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
ሕዝቡን ለማገልገል የተቀበሉትን ሥልጣንና ኃላፊነት ለሚያምኑበት ዕምነት አሊያም ለሌላ ፍላጎት እንዲውል ማድረግ እንደማይገባም ገልጸዋል፡፡
መስቀል አደባባይን በተመለከተ ምላሽ የሰጡት ከንቲባ አዳነች፤ በምላሻቸውም የመስቀል አደባባይን ጉዳይ አስመልክቶ የሚነሱ ጥያቄዎችን በሕጋዊና ሠላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባ የመንግሥትም አቋም መሆኑን ገልጸዋል።
“ኢትዮጵያ ውስጥ መስቀል አደባባይ ከተሰራበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያሉትን ልምዶችና ሰነዶችን በእርጋታ በመመልከት እንዲሁም ለሌላ ፖለቲካ ፍጆታ መጠቀም ሳያስፈልግ ማየት ይገባናል። የብሔር ጉዳይም ሳይታከልበት የተወለድንበትና የተገኘንበት አካባቢ ነው የሚለውን መመዘኛ ሳናደርግ እንዲሁም የምንከተለው ዕምነት መመዘኛ ሳይሆን፣ ጉዳዩን ከአባቶችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ጋር በሕጋዊ መንገድ መፍታት ይገባል” ብለዋል፡፡
እንደ ከንቲባዋ ገለጻ፤ መረጃዎች ላይ ተመርኩዞ መወያየት፣ መረጃና ማስረጃ እንዲሁም ስለ አደባባይ በተመለከተ ዓለም አቀፍና የኢትዮጵያን ልምድ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም መንግሥት ትብብርን ማዕከል ባደረገ መልኩ ግንኙነት በመፍጠር አብረን መፍታት እንችላለን የሚል አቋም አለው፡፡
ከዚህ ባሻገር ከወይብላ ማርያም ጋር ተያይዞ በጥምቀት በዓል ሰሞን በተፈጠረ ችግር የሰው ሕይወት መጥፋት እንዳልነበረበት፣ ታቦትም ደጅ ማደር እንዳልነበረበት ገልጸው፤ ሁኔታውን የሚመለከተው የጸጥታ አካል እየመረመረው መሆኑን ገልጸዋል። ችግር በተፈጠረ ጊዜ ወደ ግጭት በማምራት የሰው ሕይወት እንዲጠፋ የማድረግ አዝማሚያን መግታት እንደሚገባም አሳስበው፤ ትክክለኛውን ጥፋተኛ ወደ ሕግ ማቅረብ ሲቻል እንዲህ ዓይነት ችግሮች እንዳይደገሙ ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል።
ከንቲባዋ ከከተማዋ ሠላምና ጸጥታ ጋር ተያይዞ ጠንካራና ራሱን የቻለ የፖሊስ አደረጃጀት ሪፎርም እየተደረገ እንደሆነ ገልጸው፤ ይህም የሕብረተሰቡን የደህንነት ስጋት እንደሚቀነስ በሰጡት ምላሽ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር የአመራር ስምሪት አድሎአዊነት የተሞላበት ነው ተብሎ በምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄና አስተያየት፤ አመራር የሚሰማራው በአንጻራዊ ብቃት፣ ሥነ ምግባር፣ የትምህርት ዝግጅት፣ የሥራ ተነሳሽነትና ውጤታማነት እንዲሁም ስብጥርን መሠረት በማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ችግሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ነገር ግን ሆን ተብሎ የሚፈጠሩ አድልኦ እንደሌለ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የቤት እጦት ችግርን ለመፍታት አዳዲስ ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ እንዳለና ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞም የሸማች ማሕበራትን አቅም ከማሳደግ ጀምሮ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነም ገልጸዋል።
ሦስተኛው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ ጉባዔ ከየካቲት 3 እስከ የካቲት 4 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ለሁለት ቀናት ተካሂዷል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2014