ስለ ወጣትነት የምናውቀውን፣ የሚሰማንን፣ የምናየውንና የምንሆነውን (ወይም የሆነውን) እንፃፈው ቢባል ያለ ምንም ጥርጥር ቃላት ያጥሩናል፤ ቋንቋው ሁሉ ውሱን ሆኖ ምናልባት የሌሎች ነገሮችን እገዛ ሊፈልግ ይችላል። ማለትም ወጣትነት እንዲህ በቀላሉ ሊገለፅ የሚችል ማንነት ወይም ጽንሰ ሀሳብ አይደለም።
«ወጣት የነብር ጣት» የሚል ፖለቲካ ተኮር አገላለፅ አለ። ብዙ ጊዜም በከፍተኛ ባለ ስልጣናት አንደበት ሳይቀር ሲነገር ይሰማል። በተለይ በሶሻሊስት ሥርዓተ ማህበር ውስጥ ይህ ዓይነቱ አገላለፅ የሥርዓቱ የደም ስር እስኪመስል ድረስ ይዘወተራል። የመዝወተሩን ያህል ግን ስለ መተግበሩ ማረጋገጫ የለም። (ምንም ሆነ ምን ግን፣ ኢትዮጵያ 70 በመቶ ያህሉ ሕዝቧ ወጣት መሆኑን፤ ይህንን የሚያክል ቁጥር ያለው የሥራ ኃይል ይዛ ደግሞ በችግር መኖሯን ልብ ማለት፤ ለጊዜውም በቅንፍ አስቀምጦ ማለፍ ያስፈልጋል።)
ወጣትነት ለሠራበት ሀብት ነው፤ ለተማረበት እውቀት ነው፤ ለተጠቀመበት መሣሪያ ነው፤ ላወቀበት ብልሀትና ስልት ነው። በአግባቡ ለቆመበት የሕይወቱ መሠረት ነው። ባጭሩ ለልባም ሰው፣ ወርቃማው የዕድሜ ክልል የሆነው ወጣትነት ሁሉንም ነገር ነው ማለት ይቻላል።
ወጣትነት ከሌሎች የእድሜ እርከኖች ሁሉ አንድ ሰው በስነ ልቦና፣ በአስተሳሰብ፣ በማህበራዊነት (ደረጃው)፣ በተሳትፎ ወዘተ ለየት ብሎ የሚታይበት የእድሜ እርከን ሲሆን፤ በአካል፣ በስነ አእምሮ፣ በስሜት፣ በባህርይ፣ በፍላጎት፣ በመስተጋብር ወዘተ ለየት ያለ ሁኔታ የሚታይበት መሆኑም በበርካታ ጥናቶች የተረጋገጠ ሲሆን በሕይወት ውስጥም ለማንም ግልፅ በሆነ መንገድ የሚስተዋል ጉዳይ ነው።
እየተነጋገርን ያለነው ከጤናማ ሁኔታ አኳያ ነውና ምናልባት (በተለያዩ ምክንያቶች) ይህ፣ ከላይ የገለፅነው ሀሳብ የማይገልፃቸው ወጣት አባላት ካሉ ጉዳዩ በሌላ መንገድ ሊስተናገድ የሚችል መሆኑን መግለፅ ይገባል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ «ወጣት» በማለት ጊዜውን በአግባቡ የሚጠቀመውን፤ ከራሱም አልፎ ለሌሎች የሚተርፈውን፤ የሱ ተቃራኒ ከሆነውና ጊዜውን ቅርጥፍ አድርጎ ከሚበላው ጋር በአንድ ቋት ውስጥ ከትቶ ማወደስም ሆነ አለማወደስ ተገቢ ባለመሆኑ ነው።
ይህ ከላይ የተሰጠው መንደርደሪያ፣ የአምዱ ተከታታዮች እንደሚያውቁት፣ ወደ አንድ መሠረታዊ ጉዳይ፤ በተለይም አንድ ለሌሎች ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ሰብዕናን ወደ ፊት ማምጣት ላይ ያተኮረ ፕሮግራም እንደሆነ ይገነዘባሉ። በመሆኑም ዛሬ ከአንድ ታታሪ፣ ቀናና ራእይ ያለው ወጣት ጋር ቆይታ እናደርጋለን።
ታሪኩ ፈይሳ ይባላል። ታታሪና ባለ ራእይ ወጣት ነው። ታሪኩ ተወልዶ ያደገው እዚሁ አዲስ አበባ አካባቢ፣ ቡራዩ ሲሆን፤ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮም ኑሮውን ያደረገው እዚሁ አካባቢ ነው። ታሪኩን በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግረነው የሰጠንን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋልና አብረን እንዝለቅ።
ስሜ ታሪኩ ፈይሳ ይባላል። ተወልጄ ያደኩት እዚሁ ቡራዩ ነው። እድሜዬ 26 ሲሆን አሁን በቋሚነት ሥራዬ ሊስትሮነት ነው። በእሱው ነው የምተዳደረው። ዋና ሥራዬ እሱ ነው ማለት ነው።
በዚሁ በሊስትሮነት ሥራዬ እኔን ጨምሮ አምስት ቤተሰቦችን አስተዳድራለሁ። ሁለት ወንድሞች፣ አንድ እህትና አቅመ ደካማ እናቴን የምደግፈው እኔ ነኝ።
እናቴ ያማታል፤ እኔ ነኝ ይህንኑ ሥራ እየሠራሁ የምደግፋት። ወንድሞቼንና እህቴ (የ7ኛ፣ 10ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው) የማስተምራቸው እኔ ነኝ። እኔ በችግር ምክንያት ትምህርቴን ከ8ኛ ክፍል ባቆምም እነሱ መማር ስላለባቸውና እንደ እኔ ማቋረጥ ስለሌለባቸው እያስተማርኳቸው ነው።
ምንም እንኳን እንደ ሌላው የሥራ ዘርፍ ገቢው ትልቅ ባይሆንም የሊስትሮነት ሥራ ጥሩ ነው። ሞራል ያለው ሥራ ነው። ከሰው ያስተዋውቃል፤ ከሰው ያግባባል። በእርግጥ ሥራው አንዳንዴ እንደ አየሩ ሁኔታ ነው፤ ይለዋወጣል፤ አንዳንዴ ይቀዘቅዛል። እኔ ግን የራሴ ደንበኞች ስላሉኝ እየመጡ ያሠሩኛል። ሁሌም እኔ ጋር እየመጡ ነው ጫማቸውን የሚያስጠርጉት። በዚህ ምክንያት እኔ ብዙ ጊዜ አልጎዳም።
ሥራው ጥሩ ነበር፤ ግን ምን ያደርጋል ቀለም በጣም ነው የተወደደው። በእርግጥ ምንም ያልተወደደ፤ ያልጨመረ ነገር ባይኖርም የቀለም መወደድ አንዱ ችግራችን ነው። ስለዚህ ሰዉ የማስጠረግ ልምዱ ከድሮው ቀንሷል። የደንበኞች ቁጥር ለመቀነሱም አንዱ ምክንያት ነው ማለት ነው። እንደዚያም ሆኖ ጥሩ ነው። እዚህ (አስኮ መኪና ተራ ማለቱ ነው) በአግባቡ ከሠራ በቀን ቁርስ፣ ምሳ ተችሎ እስከ 100 ብር ተይዞ ይገባል።
ወጣት ታሪኩ ፈይሳ በዚሁ በሊስትሮነት ሥራው ይተዳደርና ቤተሰቡንም ያግዝ እንጂ ጊዜና ጉልበቱን ለሊስትሮነት ሥራው፣ ለራሱና ለቤተሰቡ ብቻ አይደለም የሚያውለው። ይህንንም በተመለከተ የሚከተለውን ይነግረናል።
እኔ በፈተጥሮዬ ሰው መርዳት፤ በሰብአዊ ተግባር ላይ መሰማራት፣ ሰብአዊ አገልግሎት መስጠት በጣም ደስ ይለኛል። የተጎዱ፣ የተቸገሩ … ሳይ ዝም ማለት ደስ አይለኝም። ወደ ፊትም ቢሆን አቅመ ደካሞችን፣ ደጋፊ የሌላቸው ሕፃናትን ብረዳ ደስ ይለኛል። በመሆኑም በወረዳ ደረጃ እንቀሳቀሳለሁ። በተለያዩ ሥራዎች ውስጥ ያለ ምንም ዓይነት ጥቅምና ክፍያ አገልግሎት እሰጣለሁ።
የምሳተፍባቸው ሥራዎች የተለያዩ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ ሰላምና ፀጥታ፣ ደም ልገሳ፣ በጎ አድራጎት፣ ማደራጀት እና የመሳሰሉት ይገኙበታል።
ሰላምና ፀጥታን በተመለከተ ማታ ማታ ሮንድ ከመዞር ጀምሮ የተለያዩ ፀጥታን የተመለከቱ ሥራዎችን እሠራለሁ። አካባቢው ድንበር (የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን መጋጠሚያ) አካባቢ እንደ መሆኑ መጠን ጥንቃቄን፣ ተናቦ መስራትን ይጠይቃልና ያንን ሁሉ እንሠራለን። ፀጉረ ልውጥ ሲያጋጥም ተመካክረን ያንን ችግር እንፈታለን።
የሕዝባዊ ሰራዊት ስልጠና ወስጄ በአመራርነት እየሠራሁ እገኛለሁ። በአሁኑ ሰዓት 27 ሰዎችን በስሬ የያዝኩ መቶ መሪ ነኝ። ቅድም እንዳልኩት አካባቢው የሁለት ክልሎች መገናኛ ድንበር ከመሆኑ አኳያ ብዙ ነገር አለ። የሰላም ጉዳይ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚፈልግ ከመሆኑም አኳያ ፀጥታና ሰላም ላይ መሰማራቱ ተገቢ ሆኖ ስላገኘሁት በዚያ መሳተፌ ደስ ይለኛል። አብረውኝ የሚሠሩትም ደስተኞች ናቸው፤ ደስ እያላቸው ነው የሚሠሩት።
በጎ አድራጎትን (የበጎ ፈቃድ ሥራ)ን በተመለከተም ብዙ ሥራዎችን እየሠራሁ ነው የቆየሁት። አሁንም አላቆምኩም። ባስፈለገበት ጊዜና ቦታ ሁሉ እሠራለሁ። ከ«አልጋ አከራይ ማህበር» ጋር በመሆን አልጋ አከራዮችን (አልጋ አለ እያሉ ለተከራይ የሚያስተዋውቁትን) እና ከ«ሊስትሮ ማህበር» ጋር በመሆን ሊስትሮዎችን በየሙያቸው በማደራጀት፤ እያንዳንዱ በነፍስ ወከፍ በቀን አንድ ብር ተቀማጭ እንዲያደርግ በማድረግ ደብተርና እስክሪፕቶ መግዛት ለማይችሉ የአካባቢያችን ተማሪዎች ደብተርና እስክሪፕቶ እና ሌላ የሚያስፈልጓቸውን የትምህርት ቁሳቁሶችን እንገዛላቸዋለን።
አመት በዓል ሲመጣ ችግረኞችን፣ የታመሙ ሰዎችን እንጠይቅበታለን። በገንዘባችን ገዝተን፣ ከአካባቢው ሆቴሎች ምግብ እየጠየቅን በመሰብሰብ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች እየሰበሰብን ምሳ እናበላለን።
አንድ «ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው» የሚል ነገር አለ። ትክክል ነው። እኛ ሀብታሞች አይደለንም። ግን እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች እንደ አቅማችን እንረዳለን። ይህ ማለት ደግሞ ሰው በቻለው ሁሉ ሰውን መርዳት ይችላል ማለት ነውና አባባሉ ትክክል ነው።
የአቅመ ደካሞችን ቤት ከመሥራት እስከ ማደስ ያሉ ሥራዎችን ሁሉ እንሠራለን። ይህን ሁሉ የምናደርገው ያለ ምንም ክፍያ ነው። ከመንፈሳዊ እርካታና የዜግነት ግዴታን ከመወጣት አኳያ ብቻ ነው የምንሠራው። ይህንን ሁሉ ስንሠራ ሊስትሮ ነን ብለን ወደ ሥራችን በማተኮር አይደለም፤ ማህበራዊ አገልግሎት የመስጠት ግዴታ ስላለብን ሥራችንን አቁመን ነው የምንሠራው። በዚህ ተግባር ደግሞ እኔ የማስተባብራቸው ሁሉም ደስተኞች ናቸው። በፍቅር ነው የምንሠራው።
ሁለ ገቡ ወጣት ታሪኩ ፈይሳ ከወረዳ አመራሮች ጋር ያለውን ግንኙነት፤ መግባባትና በተለያዩ ሥራዎች አብሯቸው የመሳተፉን ጉዳይ በተመለከተም እንዲህ ሲል ነበር ያጫወተን።
የደም ልገሳውም ሆነ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ፤ ወይም የበጎ አድራጎቱም ሆነ የሰላምና ፀጥታው ሥራ ያው ወረዳው በሚያውቀው ሁኔታ ነው የሚሠራው። ማለትም ከወረዳው ጋር ነው አብረን የምንሠራው። ሁሉንም ሥራዎቻችንን የወረዳው አስተዳደር ያውቀዋል።
ከወረዳው አስተዳደር ጋር በምንሠራበት ጊዜም እንደ የአካባቢው የሊስትሮዎች ማህበር አስተባባሪነቴ ከወረዳው ጋር በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ እሰጣለሁ። ለምሳሌ አልጋ አከራዮችንና ሊስትሮዎችን አደራጅተን ወደ አንድ እራሱን ወደ ቻለ የሥራ ዘርፍ እናስገባቸው የሚል ሀሳብ በተደጋጋሚ አቅርቤ ጉዳዩንም አስረድቻለሁ። በእርግጥ እስካሁን ምንም ዓይነት ምላሽ አልተገኘም። መልስ የመስጠት ችግር አለ። ግን ጥያቄውን በተገቢ ጥያቄነቱ ተቀብለውታል።
ሌላው እነዚህ ሕዝባዊ አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች ድጋፍና እውቅና ማግኘት ይገባቸዋል። ዝም ሊባሉ አይገባም። በእርግጥ የምስክር ወረቀት እንሰጣለን የሚል ነገር ይሰማል። ጥሩ ነው። ምንም ሆነ ምን ግን፣ በማንኛውም መንገድ ይሁን እውቅና መስጠት ያስፈልጋል።
«አሁን ሊስትሮ ነህ፤ የምትተዳደረውም በእሱው ነው። የወደፊት እቅድህስ ምንድን ነው፣ በምን ዓይነት ሥራ ላይ ተሰማርተህ መሥራት ትፈልጋለህ፣ ወይስ በዚሁ መቀጠል?» ለሚለው የጋዜጠኛው ጥያቄም ወጣት ታሪኩ እንደሚከተለው ይናገራል።
እኔ መነሻ ገንዘብ ቢኖረኝ፣ ወይም የሚያግዘኝ፣ የሚደግፈኝ፤ የሚያሠራኝም አካል ቢኖር መሰማራት የምፈልገው በንግድ ሥራ ላይ ነው። መነገድ ነው የምፈልገው። ነግጄ እራሴን ችዬ፣ ቤተሰቦቼንም መርዳትና የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ ማድረግ ነው የምፈልገው። የወረዳው መስተዳድርም አንድ ነገር፣ የቀበሌ ቤት እንኳን ቢሰጠኝና ከግለሰብ ኪራይ ቤት ብድን እራሱ አንድ ትልቅ ነገር ነው። አንድ ክፍል ቤት እንኳን ባገኝ ቀላል አይደለም፤ በቂዬ ነው። እነዚህ ቢሟሉልኝ የበለጠ ሠርቼ እራሴንም ሆነ ሌላውን መርዳት እችላለሁ። ሁኔታዎች ቢመቻቹልኝ በሥራም፣ በችግርም በሌላም ምክንያት ያቋረጥኩትን ትምህርቴንም የመቀጠል ፍላጎት አለኝ።
በመጨረሻም ለእድሜ እኩዮችህ፣ ባጠቃላይም ለወጣቱ የምታስተላልፈው መልእክት ካለህ ማስተላለፍ ትችላለህ።
እሺ። በእርግጥ ለወጣቱ የማስተላልፈው መልእክት አለ። ለወጣቱ የማስተላለፈው መልእክት በመጀመሪያ ደረጃ ሥራ ክቡር መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። ሥራ መምረጥ ተገቢ እንዳልሆነና ያገኙትን፣ የሚችሉትን ሁሉ መሥራትና መለወጥ ያስፈልጋል። በሱስ መጠመድና ጎዳና ላይ መውደቅ ሊቆም ይገባዋል። ይህ በምንም ዓይነት ሁኔታ ቢሆን ተገቢ አይደለም። የሀብታም ልጅ ሁሉ ሳይቀር በሱስ ምክንያት ጎዳና ወጥቶ ከቤተሰቡ ተነጥሎ ማየት ያሳዝናልና ይህ ሁሉ ሊሆን አይገባውም። አንዳንድ ወገኖች (ተቋማት ማለቱ ነው) እነዚህን ወጣቶች እየሰበሰቡ ሊያርሟቸውና አሰልጥነው ወደ ሥራ ሊያሰማሯቸው ይገባል።
በአጠቃላይ ወጣቱም ሰውን መርዳት፣ በጎ አድራጎትና የሰላምና ፀጥታ ሥራ ላይ በመሰማራት ሕዝቡን ማገልገል አለበት። ይህን ሁሉም ወጣት ማድረግ አለበት እላለሁ። እኛም ታሪኩ ለወጣቶች ያስተላለፈውን ምክር እነሆ እያልን ለዛሬ በዚህ ተሰናበትን።
ግርማ መንግሥቴ