የአፍሪካ አገራት ጠንካራ የመሰረተ ልማት ትስስር ያልዘረጉ በመሆናቸው የኢኮኖሚ መስተጋብራቸው በዛው ልክ ዝቅተኛ መሆኑን ጥናቶች ያመላክታሉ። ለዚህ ማሳያም በአህጉራችን አፍሪካ በአገራት መካከል ያለው የንግድ አጋርነት ከ19 በመቶ ያልዘለለ የእርስ በእርስ ግብይት መፈጸማቸው ይጠቀሳል። በተቃራኒው ጠንካራ መሰረተ ልማት የዘረጉት አውሮፓውያን አገራት መካከል ያለው የእርስ በእርስ ግብይታቸው 70 በመቶ የሚደርስ ሲሆን፤ በኤዥያ አህጉር በአገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ ደግሞ 52 በመቶ የሚደርስ ው።
ከአለም ማህበረሰብ 16 በመቶ የምትሸፍነው አፍሪካ ግን በአህጉሩ ውስጥ የኢኮኖሚ ትስስር ብቻ ሳይሆን የአለም አቀፍ የንግድ ተሳትፏዋ ከ2 ነጥብ 6 በመቶ ያልዘለለ ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህም አፍሪካውያን እርስ በእርስ ተሳስረው ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም መፍጠር እየቻሉ፤ በጋራ ተሳስሮ ከመስራት ይልቅ በተናጠል ጎዞ እየዳከሩ መንገዳቸው ከድጡ ወደማጡ እንደሆነባቸው የሚያሳይ ነው።
ከዚህ አኳያ ደካማ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እና ትስስር ውጤት የአፍሪካን ምርታማነት 40 በመቶ እንደቀነሰው የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ። እንዲሁም በ54 የአፍሪካ አገራት ተፈርሞ ወደ ስራ የገባው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት የአህጉሪቱን አገራት የእርስ በእርስ የንግድ ልውውጥ 40 በመቶ በላይ ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል። ነገር ግን በአህጉሪቱ በቂ መሰረተ ልማት ካልተዘረጋ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነቱ የታሰበውን ያህል ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችል ምሁራን ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይ ከሰሃራ በታች ያሉ የአህጉሪቱ ክፍል ደግሞ በመሰረተ ልማት ትስስሩ እጅጉን የተጎዳ ስለመሆኑ ይገለጻል። እናም የአህጉሪቱን የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ለማሻሻል የአፍሪካ ህብረት ከተለያዩ የአለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት ጋር በመሆን እየሰራ ቢሆንም፤ በቂ ባልሆነ የገንዘብ አቅርቦትና የፕሮጀክት አፈጻጸም ችግር ምክንያት በተፈለገው ልክ የአህጉሪቷን መሰረተ ልማት ማሟላት አልቻለም። አፍሪካ በሚፈለገው ልክ በኢኮኖሚው ላለመዋሃዷና በኢንቨስትመንቱ ላለመተሳሰሯ ደግሞ አንዱና ዋነኛው መክንያት በአህጉሪቱ በቂ የመሰረተ ልማት ትስስር አለመዘርጋቱ ነው።
ይሁን እንጂ በአህጉሪቱ አገራት ያላቸውን ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስር ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር የተለያዩ ተስፋ ሰጭ ፕሮጀክቶችን አከናውነዋል። እያከናወኑም ይገኛሉ። ከነዚህ መካከል የምስራቅ አፍሪካና አካባቢውን የንግድ ትስስር ያሳድጋል ተብሎ የታመነበት የላፕሴት ፕሮጀክት አንዱ ነው። ይህ በቻይናው ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ በመታገዝ በኢትዮጵያ፣ በኬንያና በደቡብ ሱዳን የተጀመረው ቀጠናዊ የጋራ ግዙፍ የመሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክት ውጤት ማሳየት ጀምሯል። ፕሮጀክቱ ከኬንያው ላሙ ወደብ ተነስቶ ሶስቱን አገራት በኢኮኖሚ የሚያስተሳስር ሲሆን የአፍሪካ ህብረት እ.ኤ.አ በ2063 የተዋሃደችና የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የያዘው እቅድ አካል ነው።
የምስራቅ አፍሪካና አካባቢውን የንግድ ትስስር ያሳድጋል ተብሎ የታመነበት ፕሮጀክቱ ላሙ ወደብ፣ ደቡብ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ትራንስፖርት ኮሪዶር (ላፕሴት) በሚል ይታወቃል። ላፕሴት በምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ እና ብዙ ተስፋ የተጣለበት የመሠረተ ልማት ግንባታ ሲሆን፤ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳንን የሚያገናኝ ፕሮጀክት ነው። የመሰረተ ልማት ዝርጋታው ትልሙ የምስራቅ አፍሪካንና የአካባቢውን የንግድ ትስስር በማቀላጠፍ በአፍሪካ በስፋት ባልተለመደ መልኩ የጋራ ኢኮኖሚያዊ እድገትን የሚያመጣ እንደሚሆን ይጠበቃል። ተመጋጋቢ የሆነ ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ትስስር በመዘርጋት አህጉራዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር ለታቀደው እቅድ እርሾም ነው።
የላፕሴት ፕሮጀክት ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገራት ጋር ምን ያህል እንደሚያስተሳስራት፣ ያለው የኢኮኖሚ ጠቀሜታ እና የፕሮጀክቱን አፈጻጸም በተመለከተ ከሰሞኑ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት፤ የላፕሴት ፕሮጀክት በኬንያ የሚገኘው የላሙ የባህር ወደብን መሰረት አድርጎ ሶስቱን ሀገራት (ኢትዮጵያን፣ ኬኒያንና ደቡብ ሱዳንን) በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር የተዋቀረ ግዙፍ ቀጣናዊ ፕሮጀክት ነው።
ፕሮጀክቱ የላሙ ወደብን ማዕከል በማድረግ ሶስቱ አገራትን በመንገድ መሰረተ ልማት ለማስተሳሰር አቅዶ ይነሳ እንጂ፤ በሶስቱ አገራት መካከል የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ትስስርን፤ ሦስቱን ሃገራት የሚያገናኙ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የባቡር መስመር መሰረተ ልማት ግንባታን፤ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ዝርጋታ ፕሮጀክትን፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን እና ሌሎች የቀጣናውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ይበልጥ የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ይከናወናሉ ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ሁሉንም አገራት በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርጉና የአህጉሪቱን ኢኮኖሚያዊ ውህደት የሚያሳልጥ እንደሆነ ሚኒስትሯ ገልጸው፤ በዋናነት በአገራቱ መካከል የንግድ ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር ፕሮጀክቱ የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል። እንደዚሁም በአገራቱ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች የተመረቱ ምርቶችን ወጪና ጊዜን በቆጠበ መልኩ ወደ ውጭ በመላክ ከዘርፉ ማግኝት የሚገባቸውን የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ ያስችላል። እንዲሁም በአገራቱ መካከል በሚፈጠረው የገበያ ትስስር ሂደት ውስጥ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ከፍተኛ የስራ ዕድል የሚፈጥር ይሆናል። በሌላ በኩል አገራችን ኢትዮጵያ የባህር በር እንደሌላት ይታወቃል። ስለዚህ ፕሮጀክቱ አማራጭ ወደብ እንዲኖራት ያስችላታል።
የፕሮጀክቱ አፈጻጸም በተመለከተ ለአብነት በኢትዮጵያና በኬንያ የተለያዩ ተግባራቶች እየተከናወኑ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል ። በኬንያ የላሙ ወደብ ግንባታ እየተፋጠነ ይገኛል። ወደቡ እስከ 32 የሚደርሱ ግዙፍ መርከቦችን በአንዴ ማስተናገድ የሚችል አቅም ያለው ነው። በወደቡም ሶስት የመርከቦች ማቆያ ሥራ እየተፋጠነ ሲሆን፤ የመጀመሪያው የመርከቦች ማቆያ ሥራ ግንባታ ተጠናቋል። ሁለተኛውና ሶስተኛው የመርከቦች ማቆያ ሥራው በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል። ይህም አንዱ እና ዋነኛው የፕሮጀክቱ አፈጻጸም በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እንደሚገኝ የሚያመላክት ነው። ስለዚህ በላሙ ወደብ ሦስት የመርከቦች ማቆያ ሥራ እየተፋጠነ መሆኑ፤ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው።
የላሙ ወደብ ልማት የአካባቢው አገሮችን ኢኮኖሚ ለማስተሳሰር አስፈላጊ በመሆኑ ኢትዮጵያ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት ተግታ እንደምትሰራ ሚኒስትሯ ይናገራሉ። በኢትዮጵያ በኩል ያለው የፕሮጀክቱን አፈጻጸም በተመለከተ የሞጆ ሞያሌ መንገድ ግንባታ ተጠናቋል። ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ለእግረኛ ከመንገድ በታች እና በላይ 45 መተላለፊያ ያሉት ሲሆን በአጠቃላይ 202 ኪ.ሜትር የፍጥነት መንገድ የጎን ስፋቱ 32 ሜትር ነው ። የመንገዱ አጠቃላይ ወሰን 90 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፤ ይህም በቀጣይ ለሚኖረው የማስፋፋት ስራ በቂ ቦታ እንዲኖር የሚያስችል ይሆናል።
እንዲሁም የጉምሩክ ስራውን የሚያቀለው የአንድ መስኮት አገልግሎት ግንባታ እንዲሁ ተጠናቆ ስራ ጀምሯል። ይህም በኢትዮጵያ በኩል የፕሮጀክቱ አፈጻጸም በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይና አገሪቱ ለፕሮጀክቱ ያላትን ቁርጠኛ አቋም የሚያመላክት ነው።
በጥቅሉ ባሳለፍነው ክረምት ደግሞ የፕሮጀክቱን ሂደት በጋራ ሶስቱ ሀገራት መምራት የሚችሉበትና ስራውን ማፋጠን የሚያስችላቸው የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ መስርቶ ወደ ተግባር ለመግባት የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈርሟል። ይህም አገራቱ ፕሮጀክቱን ተደጋግፈው ወደ ፊት ለማስኬድ እና ውጤታማ ለማድረግ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
ምንም እንኳን የምስራቅ አፍሪካ አገራት የመሳሪያ ድምጽ የማይጠፋበት፣ የእርስ በእርስ ጦርነት የነገሰበት፣ በአሸባሪ ቡድን የሚታመሱ እና ቀጠናው ካለው ጂኦፖለቲካዊ ፋይዳ አኳያ ኃያላን አገራት የሚራኮቱበት ቢሆንም ቅሉ፤ የቀጣናው አገራት የመሰረተ ልማት ትስስር እና የንግድ ግንኙነት ጠንካራ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
ለአብነት የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር፣ የውሃ ቧንቧ እና የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ዝርጋታ የሁለቱን አገራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሰረተ ልማቶች ናቸው። የባቡር መስመር ዝርጋታው ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ወደብ ወጪና ጊዜዋን ቆጥባ ከውጭ ምርት እንድታስገባ ያስችላታል። በአንጻሩ ደግሞ ጅቡቲ ከኢትዮጵያ በተመጣጣኝ ዋጋ የኤሌክትሪክ ኃይል እያገኘች ትገኛለች።
ከዚህ ባሻገር ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ግብፅና ሱዳን በተመጣጣኝ ዋጋ የኤሌክትሪክ የኃይል አቅርቦት ከማግኘታቸው ባለፈ የህዳሴው ግድብ የወንዙን ሥነ ምህዳራዊ ሁኔታ መጠበቅ ስለሚችል በየወቅቱ የሚዋዥቀውን የወንዙን የውኃ መጠን በማስተካከል ዓመቱን ሙሉ በታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት የተመጣጠነ የውሃ ፍሰት እንዲኖረው ያደርጋል። የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ግድባቸው በደለል እንዳይሞላም ያስችላል። በአንጻሩ ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት በተመጣጣኝ ዋጋ ከምታቀርበው የኃይል አቅርቦት የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ያስችላታል።
በአጠቃላይ የምስራቅ አፍሪካ እና አካባቢው አገራት በተለይ በመንገድ መሰረተ ልማት የተሳሰሩ ናቸው። ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያገናኟት በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች በመገንባት ላይ ይገኛሉ። አንዳንዶቹም የመንገድ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ስራ የገቡ ሲሆን፤ ከእነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል አፍሪካን የማስተሳሰር ዓላማ ያነገበው የላፕሴት ፕሮጀክት አካል የሆነው እና ከግብጽ በኢትዮጵያ አድርጎ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚዘረገው መንገድ አካል የሆነው የሞጆ ሀዋሳ ሞያሌ መንገድ ተጠቃሽ ነው። ከግብጽ ተነስቶ በኢትዮጵያ፣ በኬንያና በታንዛኒያ አድርጎ እስከ ደቡብ አፍሪካ የሚዘልቀው ይህ መንገድ በሀገራት መካከል አቻ ግንኙነቶች እንዲስፋፉ የሚያደርግ መሆኑንም ነው ምሁራን የሚናገሩት።
የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጠንካራ የሆነ የንግድ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፤ ለአብነት ኬንያ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳ ጠንካራ ግንኙነት ነው ያላቸው። ይህ መንገድ ኢትዮጵያን ከኬንያ ጋር ሲያገናኝ፤ በዚያው ኢትዮጵያን ከዩጋንዳም ጋር ያገናኛል ማለት ነው። በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከታንዛኒያ ጋርም በቀላሉ ለመገናኘት እድል ይሰጣል። ሌሎች ሀገራት ጋርም ለመገናኘት እድል ይፈጥራል። እስከ ደቡብ አፍሪካ ካሉ ሀገራት ጋር ለመገናኘት ሰፊ እድል ይኖራል። ይህም ኢትዮጵያን ከሌሎች ሀገራት ጋር ለማገናኘት ሰፊ እድሎችን የሚፈጥር እንደሆነ ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።
አፍሪካውያን የ2063 ግቦችን አስቀምጠው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። ፖለቲካዊ ውህደት፣መልካም አስተዳደር፤ ሰላምና ደህንነት፣ ባህል ፣ልማት ፣ዕድገት ከግቦቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ። የመጀመሪያው አስር ዓመት ዕቅድም የባቡር ትራንስፖርት ፣ ነፃ የንግድ ቀጣና፣ ጦርነትን ማስቆም የመሳሰሉትን ማሳካት ናቸው። ግቦቹን ለማሳካትና የአፍሪካን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በዋነኛነት በመሰረተ ልማት መተሳሰር ወሳኝነት አለው። ይሄም ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራ ነው ።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ጥር 28 ቀን 2014 ዓ.ም