ሰሞኑን ሰፈሩ በተለየ ሽታ ታውኳል።በመጠኑ ሽው ሲል የቆየው ጠረን አሁን ላይ እየባሰበት ነው። እንግዳው ጉዳይ ለአፍንጫቸው የሚደርስ ሁሉ ፈጥነው አፋቸውን ይሸፍናሉ።ከአቅማቸው በላይ የሆነ አንዳንዶች ጥቂት እንኳን መታገስ አልቻሉም።ለውስጣቸው የሚደርሰው እንግዳ ነገር እየተናነቀ ይፈታተናቸው ይዟል።
በሰፈሩ አንዳንዴ ቆሻሻ ሲጣልና ንጽህና ሲጠፋ ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ ይኖራል።እንደሰሞኑ ዓይነት የከፋ ሽታ ግን ሰንብቶበት አያውቀውም።የችግሩ መላ ማጣት ያስጨነቃቸው ነዋሪዎች እርስ በእርስ ማውራት ጀምረዋል።ይህ ለጤና ያልተመቸ አዲስ ነገር መፍትሄ እንደሚያሻው እያወጉ ነው።
ጥቂት ቆይቶ መንደርተኛው የራሱን መላ ምት መስጠት ጀመረ።ሽታው የሚመጣው ከወዴት ነው? የሚለውን ለማወቅም መመራመሩን ያዘ።አንዳንዶች ከቱቦው ሊሆን እንደሚችል ተናገሩ።ሌሎች ደግሞ ክምር ቆሻሻ ነው ሲሉ ገመቱ።ሁሉም ሀሳቡን በየመልኩ እያዋጣ ሰነዘረ፣ በግምት መላምቱ ተወያየ ። መፍትሄው ፈጥኖ አልተገኘም።ፍንጭ አልታየም።
ነፋሻማው አየር ካለበት እያነሳ ለየሁሉም አፍንጫ የሚያደርሰው ክፉ ሽታ ነዋሪውን እንዳወከው ሰነበተ።አንድ ቀን ግን ድንገት ሽታው ተወግዶ ሰላማዊ ዕለት ሆኖ ዋለ።ይህ አጋጣሚ እንዴት እንደሆነ አልታወቀም።ክፉው ሽታ መጥፋቱ፣ ንጹህ አየር መተካቱ እፎይታ የሰጠው ነዋሪ ለምክንያቱ ቦታ የሰጠው አይመስልም።
ቀናት ተቆጠሩ።የተከሰተው ክፉ ሽታና የተከተለው ወሬ በአንድ አልከረሙም።ጉዳዩ ተረስቶ የቀድሞው ሕይወት ቀጥሏል።አንድ ማለዳ አንድ ሰው በሰፈሩ መሀል ሲራመድ ባዕድ ሽታ ለአፍንጫው ደረሰ።ሰውየው ይህን ሽታ ደግሞ ለማስታወስ አልዘገየም።ከቀናት በፊት በአፍንጫው ሽው ሲል መክረሙ ትውስ አለው።
ሰውዬው ሽታው ወደመጣበት አቅጣጫ እያመላከተ በስፍራው ለተገኙት ጥያቄ አቀረበ።በአካባቢው የቆመው ወጣት ለመልሱ ፈጥኖ ምላሽ ሠጠው።የዛሬው ሽታ የውሻው ሞት መሆኑን ነግሮ የቀበረበትን ቦታ አሳየው።ጎረቤቱ ፊቱን እንደከሰከሰ ቦታውን ተጠይፎት አለፈ።
ወጣቱ የእጁን አካፋ ከመሬቱ እያመቻቸ አፈሩን መደልደል ቀጠለ።ከቀናት በፊት የሞተ ውሻውን ከመጣል መቅበር መፈለጉን እያወራ ነው።አንዳንዶች ለውሻው መቅበሪያ ያዘጋጀውን ጉድጓድ በመገረም አስተዋሉት።አካባቢውን በክፉ ሽታ ማወኩ አልተመቻቸውም።
የግቢው ሰዎች እያደር ሽታው ቢብሳቸው እርስ በእርስ አወጉ።አሁንም ይህ ጉዳይ የሰፈሩ ጠንቅ እየሆነ ነው።ሽታው ጠፋ ሲባል እየተመለሰ በርካቶችን አበሳጭቷል።ብዘዎች በወጣቱ ምላሽ እውነቱን አውቀዋል።የክፉ ሽታው ምንጭ የውሻው ሞት መሆኑ ገብቷቸዋል።
ወጣቱ የጎረቤቶቹ ሁኔታ ሰላም ነስቶታል።በየቀኑ ስለሸታው መከሰት ደጋግመው ማውራታቸው እያናደደው ነው።እሱ የሞተ ውሻውን አፈር አልብሶ ቀብሯል።በላዩ የከባድ መኪና ጎማ ጭኖ አፈሩን ደልድሏል።አሁን በየምክንያቱ መነሳቱ አልተመቸውም።አንዳንዶች ከቀናት በፊት ግቢውን ሲያጸዳ እንደነበር አስታውሰው ቆሻሻ ሰብስቦ ማቃጠሉ ትዝ አላቸው። ይህን ሲያስቡ የውሻው ከጉድጓድ የመቀበር ምክንያቱ ገባቸው።
ዮዲት …
ዮዲት በሐዋሳ ከተማ ከአንዲት ወይዘሮ ቤት ተከራይታ ትኖራለች።ራሷን ለማሳደር ኑሮዋን ለመምራት ውሎዋ የመስተንግዶ ሥራ ነው።ተቀጥራ በምትሠራበት ሆቴል ወር ጠብቃ የምትወስደው ደመወዝ ለሚያሻት ወጪ በቅቷት አያውቅም።
ወጣቷ ጎዶሎዋን ሞልታ የልቧን ለማድረስ ተጨማሪ ገቢን ትሻለች።እንዲህ ይሆን ዘንድ የሰፋ ምርጫ የላትም።በትምህርት ያለመግፋቷ ሥራ እንዳትመርጥ አግዷታል።ገንዘብ አግኝታ ገቢዋን ለመጨመር ያላት ዕድል አንድ ብቻ ነው።ከመንገድ ቆሞ ራስን መነገድ።ወንዶችን ቀርቦ ገንዘብን መቁጠር።
ዮዲት የቀን ድካሟን አጠናቃ የምሽቱን ስትጀምር አለባበሷ ይቀየራል።አነጋገር አረማመዷ ከወትሮው ይለያል።በቀይ መብራት ከሚያብዱት ቡና ቤቶች አመሻሽታ ከአስፓልቱ ዳር ስትቆም ተመልካቿ ይበዛል።በአጭር ቀሚሷ፣ በረዥም ጫማዋ ከወዲያ ወዲህ ስትል ዓይኖቿ ይቃብዛሉ።መላ ሰውነቷ ደንበኛን ስቦ ገንዘብ ለማምጣት የድርሻውን ይወጣል።
አንዳንዴ እንዲህ ሆና ሲቀናት ገንዘብ ይዛ ትገባለች።አንዳንዴ ደግሞ እንዳሰበችው ሳይሆን ቀርቶ በእጅጉ ትከፋለች።‹‹ደንበኞቼ…›› የምትላቸው ሴትነቷን በጉልበታቸው ተጠቅመው ያባርሯታል፣ ይገፏታል።ሌሎች ከተስማሙት ቀንሰው፣ ያላሰበችውን ጥቂት ብር ይወረውሩላታል።ሲሻቸው ሰድበው፣ ደብድበው ይሸኟታል።
ዮዲት እንዲህ ሆና ለመኖር ከብርድና ጨለማው ጋር ስቃይ መከራን ትቀበላለች።ዕንባን ከሳቅ ኀዘን ከደስታ ትጋራለች።ያም ሆኖ ከሁሉም ያላት ሕይወት ሰላማዊ ነው።ከአከራይና ጎረቤቶቿ ጋር ተግባብታ ተስማምታ ታድራለች።ዮዲት ለጎረቤቶቿ በክፉ ደጉ ትደርሳለች።ሁሉን እንደዓመሉ አቻችላ ለማደርም መልካምነቷ ይጎላል።
ጎረቤቶቿ ስለእሷ መተዳደሪያ የሚያውቁት የሆቴል መስተንግዶ መሆኑን ነው።ሁሌም ምሽት ላይ ቤቷ እንደማትኖር ያያሉ።ይህን እውነት የተቀበሉት ግን ከሥራ ባህሪው አዛምደው ብቻ ነው።በግቢው ከሚኖሩት ጥቂቶቹ በምሽት ከመንገድ ስትቆም አይተዋል።
አቤል…
አቤል መኮንን ሀዋሳ ከተማ መናኸሪያ ከተባለው ሰፈር ይኖራል።ልጅነቱን ከወላጆቹ ፍቅር አግኝቶ፣ በቤተሰቡ ተከቦ አድጓል።ዕድሜው ከፍ ሲል ግን አብሮት ያደገው ደስታ ራቀው።ወላጆቹ ፍቅር አጥተው መጨቃጨቅ፣ መነታረክ ያዙ።አለመግባባታቸው ሰፍቶ ሰላማቸው ቢጠፋ ሊለያዩ ወሰኑ።ይህ እውነት ለአቤል ከባድ መርዶ ሆነ።
የእናት አባቱ በፍቺ መለያየት ሰላም የነሳው ወጣት ፍቅርና ደስታ ራቀው።የትናንቱን መልካም ሕይወት ሲያስብ የዛሬው ማንነት አስጠላው።ሲጎረምስ ወጣትነቱን በምቾት አልተቀበለውም።ጫትና ሲጋራ መጠጥና ስካር መለያው ሆነ።በወላጆቹ የሆነውን ለመርሳት በአልኮል ብርጭቆ መደበቅ ጀመረ።በቤተሰቦቹ ቤት እየኖረ የጋራዥ ሙያን ተማረ።የሚያገኘው ገንዘብ አያንሰውም።
ሥራ ላይ ሲሆን ጫት፣ ከሲጋራው እየሳበ ካሻው ሴት ጋር ይዝናናል።በቅርብ የሚያውቁት ስለመጠጥና ጫቱ እያነሱ ይመክሩታል።እሱ ስለዚህ ጉዳይ መስማት አይፈልግም።አጥብቀው ሲጠይቁት በወላጆቹ ያሳብባል።በእነሱ መለያየት ወጣትነቱ መባከኑን፣ ሱሰኛ መሆኑን ይናገራል።
የካቲት 12 ቀን 2009 ዓ.ም…
አቤል በዚህ ቀን እንደወትሮው ከሥራ ውሏል።ሁሌም እንደሚያደርገው ጎራ ወደሚልበት ቡና ቤት ለመሄድ እያሰበ ነው።ይህን ሲያስብ የኪሱን አቅም ይፈትሻል፤ ለመጠጡ፣ አለፍ ሲልም ለሌላ መዝናኛ የሚሆን ገንዘብ እንዳለው ማወቅ አለበት።
ወደ ስፍራው ሲደርስ ምሽቱ ገፍቶ ነበር፤ የቡናቤቱ ሳቅ ጨዋታ እንደወትሮው ደርቶ ሁሉም በስፍራው አለ።ቦታ ይዞ የሚጠጣውን እንዳዘዘ በዓይኖቹ ማማተር ያዘ።ከሚያስተናግዱት እየነጠለ ማማረጥ ቀጠለ።ለምሽቱ ቀልቡ ያረፈባት ሴት አልነበረችም።
አቤል ወደቤት ሊሄድ ተነሳ።ብቻውን ማደር አልፈለገም።መንገዱ ጭር ማለት ጀምሯል።በየጠርዙ ለቆሙ ሴቶች የመሸ አይመስልም።አላፊ አግዳሚውን እያማተሩ ጠያቂያቸውን ይናፍቃሉ።አቤል ዓይኖቹ አላረፉም።ከወዲያ ወዲህ እያለ ሰው መፈለግ ይዟል።አጋጣሚ ሆኖ ከአንዲት ወጣት ጋር ተያዩ።ሳይነጋገሩ ለመግባባት አልቸገራቸውም።
ዮዲት አስተያየቱን አይታ አጠገቡ ደረሰች።ከጎኗ የቆሙ የምሽት ሴቶች አቤልን ተከትላ ስትሄድ የቅናት በሚመስል አስተያየት ገላመጧት።ጥቂት ቆይቶ የጋራ ወሬ ጀመሩ።አቤል ሌሊቱን ከእሷ ጋር ማሳለፍ ፈልጓል።ዮዲትን የሚወስዳት ወደ ሆቴል አይደለም።መኖሪያ ቤቱ ካለው መኝታ ቤቱ ነው። መራመድ ሲጀምሩ ሰዓቱ ገፍቶ ነበር።
አቤል ወደ ቤት ይዟት ሲገባ ከወንድሞቹ መጠንቀቅ ይኖርበታል። ድርጊቱን ካዩበት ወቀሳና ቁጣውን አይችለውም።ዮዲት ለአዳር እሱን ከመከተሏ በፊት በሂሳብ ተነጋግራለች።እሱም ያለችውን ቆጥሮ ሊከፍላት ተስማምቷል።
ወደ ቤት ሲዘልቁ አቤል ዮዲትን ደጋግሞ አስጠነቀቀ።አንዳች ድምጽ ብታሰማ፣ ጮክ ብላ ብታወራ እንደማይፈቅድ ነገራት።ይህን ካደረገች ቤተሰቦቹ ይሰማሉ።ከሰሙ ችግር ይመጣል።ዮዲት በአቤል ቃል ተስማማች።ሌሊቱን በጋራ አሳልፈው መንጋት ሲጀምር አቤል ከመኝታው ፈጥኖ ተነሳ።ልክ እንደማታው ዮዲት በስውር እንድትወጣ ፈልጓል።ያላትን አልተቃወመችም።ይህን ከማድረጓ በፊት ከእሱ የምትፈልገው ገንዘብ አለ።ማታ ያላትን አስታውሳ ገንዘቡን እንዲሰጣት እጇን ዘረጋች።
አቤል ዮዲት የጠየቀችውን በወጉ ሰምቷል።ከኪሱ ገብቶ ብሩን አወጣ።በእጇ ሲያኖረው ዮዲት ፈጥና መቁጠር ጀመረች።ያላትና የሰጣት ገንዘብ ፈጽሞ አይገናኝም።ኮስተር ብላ ማታ ሊሰጣት ቃል የገባውን ብር ጠየቀችው።አቤል ቃሏን ሲሰማ ንዴት ያዘው።የሰጣት ብር በቂ እንደሆነ ሊያስረዳት ሞከረ፤ አልተግባቡም።
ከቆይታ በኋላ አቤል ዮዲትን አንቆ ሶፋው ላይ ጣላት።አንገቷን ይዞ ሲታገላት ትንፋሽዋ እያጠረ ነበር።እየተፍጨረጨረች እንዲተዋት ተማጸነችው።እሷን ለመስማት አልታገሰም።እንደወደቀች ዞር ብሎ አስተዋላት።አትናገርም፤ ትንፋሽ የላትም።ያለመንቀሳቀሷ ቢያሰጋው ቀረብ ብሎ አያት።በሕይወት እንደሌለች ሲረዳ በድንጋጤ ደነዘዘ።
አቤል በዮዲት ላይ በሩን ዘግቶ ሊወጣ ሲል ወንድሙን አገኘው።በሰበብ አታሎ ከስፍራው አራቀው።ተመልሶ ሲገባ አንዳች ለውጥ አልነበረም።አስከሬኑን ከሶፋው አንስቶ ተሸከመው።ወደመኝታ ቤቱ አስገብቶም የአልጋውን ፍራሽ ጠቀለለ።ርብራቡን አንስቶ ከስር ሲያስተኛው የሆነውን እንደሚደብቅለት ተረዳ።ለጊዜው በእፎይታ ተንፍሶ በሩን ቆልፎ ወጣ።
አንድ ቀኝ ሙሉ ከአልጋው ስር የተኛው አስከሬን ማንም ሳያየው ዋለ።በጥብቅ የተቆለፈው በር በማንም አልተከፈተም።አቤል ምስጢሩን ደብቆ ከራሱ ሲሟገት ውሏል።ከሥራ ሲመለስ ምን ማድረግ እንዳለበት እያሰበ ነው።ቢጨንቀውም መፍትሄውን ማምጣት አለበት።ማንም ሳያየው አስከሬኑን ከቤት ማውጣት ግድ ይለዋል።
ሟች ከእሱ ያለመታየቷ ከጥርጣሬ እንደሚያርቀው ተማምኗል።አሁን መጨከን፣ መጀገን አለበት።ይህን እያሰበ ቀጣዩን መሸሸጊያ መቃኘት ያዘ።ያሰበው ሁሉ ሚዛን አልደፋ አለው።በድንገት ግን በግቢው ያለአንዳች ሥራ የተጣለው አሮጌ ፍሪጅ ትውስ አለው።ፈጥኖ ከመቀመጫው ተነሳ።ዝቅ ብሎም የአልጋውን ስር አስከሬን አስተዋለው።አንድ ሙሉቀን የቆየው አካል ማበጥ፣ መቀየር ጀምሯል።
በምንጣፍ ጠቅልሎ አስከሬኑን ከፍሪጁ ሲያስገባ ማንም ያየው አልነበረም።አሁን አቤል አስከሬኑን ካለበት አርቆ ጥቂት እፎይታ አግኝቷል።ውሎ ሲያድር የአካባቢው በክፉ ሽታ መናወጥ ግን ስጋቱን ጨምሮ ያስጨንቀው ይዟል።አቤል የሽታው ትኩረት መሳብ ዕንቅልፍ ነሳው።አሁንም የሽታው የመነሻ ምንጭ አልታወቀም።ይህ መሆኑ ለማሰቢያ ጊዜ ሰጥቶ መላ እያስፈለገው ነው።
አዲስ መላ…
ከቀናት በኋላ አቤል የአዕምሮውን አዲስ ዘዴ ሊጠቀምበት ወሰነ።አገር ምድሩን ካናወጠው ክፉ ሽታ ለመራቅ ያለው ምርጫ አንድ ብቻ ሆኗል።አሁንም አስከሬኑን ብቻውን ከፍሪጁ ያወጣል።ጨለማን ተገን አድርጎም ያሰበውን ይፈጽማል።ዕቅዱን ሲፈጽም ማንም እንዳላየው አረጋግጧል።አስቀድሞ በቆፈረው ጉድጓድ የሚመልሰውን አፈር አዘጋጅቶ ወደ ፍሪጁ ተመለሰ።
ቀናት የቆጠረው በድን አካል ክፉኛ ተቀይሯል፤ ጥቅሉን ምንጣፍ በጥንቃቄ ተሸክሞ ወዳዘጋጀው ቦታ አደረሰው።አስቀድሞ በቆፈረው ጉድጓድ አጋድሞ አፈሩን መለሰበት።ማግስቱን በቦታው ያለፉ ሰዎች ቦታ የቀየረውን ሽታ እየጠቆሙ ምንነቱን ጠየቁ።አቤል አፈሩን በአካፋው እየመለሰ የሞተውን ውሻ እየቀበረ መሆኑን ተናገረ።
አሁንም የግቢው ጉምጉምታ ቀጥሏል።ለጊዜው እንደመጥፋት ያለው ሽታ እፎይታ የሰጠው ነዋሪ በሌላ ርዕስ ተጠምዷል።አቤል ውሻውን በግቢው መቅበሩ ለብዙዎች አልተመቸም።ይህ በሆነበት ሳምንት የተከሰተው አስደንጋጭ ክስተት አካባቢውን ክፉኛ አስደንግጦ የፖሊስ ኃይልን አስጠራ።
የፖሊስ ምርመራ…
የከተማው ፖሊስ ድንገቴውን ጥቆማ ሰምቶ ከስፍራው ሲደርሰ የሆነውን እውነት አረጋገጠ።አቤል ውሻዬን ቀበርኩበት ካለው ጉድጓድ የአንዲት ሴት ግማሽ አካል በጎረቤት ውሻ ተጎትቶ ወጥቷል።ፖሊስ ስፍራውን ከቦ ከወገብ በታች ባገኘው የሴት አካል ላይ ምርመራውን ቀጠለ።ቀሪውን ክፍል ለማውጣትም ቁፋሮውን አካሄደ።ሙሉ አካል እንደተገኘ ፖሊስ ወደግቢው ዘልቆ አሮጌውን ፍሪጅ ፈተሸ።በተለየ ክፉ ሽታ ተናውጧል።በትክክልም የሟች አስከሬን በቦታው ቆይቷል።
ፖሊስ በቂ መረጃዎችን ይዞ ተጠርጣሪውን ማሰስ ጀመረ።ማንነቱን ለማወቅ አልቸገረውም።የፍተሻ ትዕዛዝ ይዞ ወደ እነ አቤል ቤት ያመራው ቡድን ከደጁ ደርሶ በራፉን አንኳኳ።የግቢውን ቤቶች እየፈተሸ ወደ አንድ ክፍል አመራ።በሩ በቁልፍ ተዘግቷል።ከመዝጊያው ጀርባ ያለው ጠረን ይረብሻል።ፖሊስ በሩ እንዲከፈት ጠየቀ።ክፍሉ የአቤል መኝታ ቤት መሆኑን የጠቆሙት ቤተሰቦች ስልክ እንዲደወልለት ፈቀዱ።ቁጥሮች በተደጋጋሚ ተመቱ።
አቤል ጥሪውን ተቀብሎ እየመጣ መሆኑን ተናገረ።በታሰበው ሰዓት በስፍራው ያልደረሰው ወጣት ሳይመጣ ሰዓታት ተቆጠሩ።ፖሊስን ጨምሮ ትዕግስታቸው ያለቀው ቤተሰቦች በሩ እንዲሰበር ተባበሩ።የታሰበው ሆነ።ፖሊስ የመኝታ ክፍሉን ሰበረ።ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ከባዱ ሽታ አፍንጫቸውን አጠነው።እንደምንም ተቋቁመው ወደ ውስጥ አለፉ።
አልጋው ላይ ብርድ ልብስ ሥርዓት የለውም።ርብራቡ በከፊል መታየቱን ያስተዋለው ፖሊስ ዝቅ ብሎ ስሩን ፈተሸ።ሲፈለግ የነበረው አቤል ትልቅ ሳንጃ ይዞ በጀርባው ተንጋሏል።እንደምንም አወጡት።ምርመራውን የያዘው ምክትል ኢንስፔክተር በየነ ባልቻ ቃሉን በአግባቡ ተቀበለ።አቤል ወንጀሉን እንደፈጸመ አልካደም።ራሱን ሊያጠፋ እንደነበር አልደበቀም።
ውሳኔ…
የኅዳር 14 ቀን 2010 ዓ. ም በችሎቱ የተሰየመው የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድቤት በተከሳሹ ላይ የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት በቀጠሮው ተገኝቷል።በዕለቱ በሰጠው ውሳኔም ግለሰቡ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአስራ ስምንት ዓመት ጽኑ እስራት ይቀጣልኝ ሲል ወስኗል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጥር 28 ቀን 2014 ዓ.ም