ኢትዮጵያ በታላላቅ የእግር ኳስ መድረኮች መሳተፍ ባልቻለችባቸውና ብትሳተፍም ስኬታማ ባልሆነችባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ አንድ ጀግና ምንጊዜም ስሟን ከፍ አድርጎ ያስጠራል። ይህ ሰው ኢትዮጵያውያን በእግር ኳሱ ውድቀት የሚቆጩትን ያህል መጽናኛም ጭምር ነው።
ኢትዮጵያውያን በአለም ዋንጫና በኦሊምፒክ መድረኮች ብሔራዊ ቡድናቸውን በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ለማየት ባይታደሉም አንድ ተወካይ አያጡም።
ባምላክ ተሰማ ወዬሳ፣ ባለፉት በርካታ አመታት የኢትዮጵያን የእግር ኳስ ዳኝነት ሙያ ወደ አንድ ደረጃ ያሸጋገረው ይህ ሰው ዛሬ በሚጠናቀቀው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ ከነበረው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ይልቅ መነጋገሪያና አገሩን ያስጠራ ጀግና ሆኗል።
ኢንተርናሽናል አልቢትር ባምላክ ተሰማ በተለይም ከትናንት በስቲያ ምሽት በሴኔጋልና በቡርኪናፋሶ መካከል የተካሄደውን የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ በአስደናቂ ብቃት የመራበት መንገድ በበርካታ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጭምር ሙገሳን አስገኝቶለታል።
ባምላክ ለዳኞች እጅግ ከባድ ከሚባሉ ጨዋታዎች አንዱ የሆነውን የረቡእ ምሽት የአፍሪካ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ፍልሚያ በሚደንቅ ሁኔታ ተቆጣጥሮ ከመምራቱም በላይ አዳጋች የሆኑ ውሳኔዎችን የተወጣበትና የቪኤአር አጠቃቀሙ በአለም የስፖርት ቤተሰብ እንዲመሰገን አድርጎታል።
ዴይሊ ሜልን የመሳሰሉ የእንግሊዝ ዝነኛ የሚዲያ አውታሮችም ባምላክ ጨዋታውን የመራበትን መንገድ በማድነቅ እንግሊዛውያን ዳኞች ከእሱ ትምህርት መውሰድ እንዳለባቸው ጽፈዋል።
በእርግጥ የአርባ አንድ ዓመቱ ኢትዮጵያዊ አርቢትር በዚህ ጨዋታ ሙገሳ ይዥጎድጎድለት እንጂ በእግር ኳስ ዳኝነቱ ባለፉት አመታት ተመሳሳይ ታሪኮችን በታላላቅ መድረኮች ሲሰራ ነበር።
በእግር ኳስ ዳኝነት የ18 ዓመታት ልምድ ያካበተና በፊፋ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛነት ከ11 ዓመት በፊት የተመዘገበ ነው፡፡ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ የተለያዩ የእግር ኳስ ውድድሮችን በብቃት መርቷል።
የዘንድሮውን ሳይጨምር በ3 የአፍሪካ ዋንጫዎች 7 ግጥሚያዎችን ሲያጫውት፤ በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ከ3 የዋንጫ ጨዋታዎች በላይ መምራት ችሏል። ባምላክ ከዚህ ቀደም በ3 የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ በዋና ዳኝነት ሲሰራ 8 የአፍሪካ ዋንጫ ግጥሚያዎችን አጫውቷል፡፡
በ32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ግብፅ ላይ ከመራው የዋንጫ ጨዋታ በፊት ኢትዮጵያን በውድድሩ ላይ በብቃት በመወከል ለመላው ኢትዮጵያውያን ኩራት ለመሆን የበቃው፤ ሁለት የምድብ ጨዋታዎች፤ 1 የሩብ ፍፃሜ እና 1 የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎችን በዋና ዳኝነት በመምራት ነበር፡፡
ሁለቱ የምድብ ጨዋታዎች ቱኒዚያ ከአንጎላ 1 እኩል እንዲሁም ካሜሮን ከጋና 0ለ0 የተለያዩባቸው ጨዋታዎች ሲሆኑ፤ በሩብ ፍፃሜ ደግሞ አይቬሪኮስት ከአልጄሪያ ተገናኝተው በመለያ ምት አልጄሪያ 5ለ4 ያሸነፈችበትን እንዲሁም በግማሽ ፍጻሜ ሴኔጋል ቱኒዚያን በተጨማሪ ክፍለጊዜ 1ለ0 ያሸነፈችበት ጨዋታዎች ናቸው፡፡
በተጨማሪ በ2015 እኤአ በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ አንድ ጨዋታ እንዲሁም በ2017 እኤአ በ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሁለት ጨዋታዎችንም መርቷል፡፡ ከአፍሪካ ዋንጫ በተጨማሪ በካፍ የአፍሪካ ክለቦችቻምፒዮንስ ሊግ 21 ፤ በአፍሪካ ዞን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ 8 ፤ በፊፋ ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ 2 ፤በካፍ ሱፐር ካፕ 1 ፤ በፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ 1 እንዲሁም በአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ 2 ጨዋታዎችን በዋና ዳኝነት አጫውቷል፡፡
በአፍሪካ የክለቦች ውድድር 3 የዋንጫ ጨዋታዎችን በዋና ዳኝነት ለመምራት የበቃ ሲሆን እነሱም በአፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ በ2016/ 17 አልአሃሊ ከዋይዳድኤሲ፤ በ2017 /18 ኤስፔራንስ ከአልአሃሊ እንዲሁም በአፍሪካ ክለቦች ሱፕር ካፕ በ2018 /19 ኤስፔራንስ ከራጃ ካዛብላንካ ያደረጓቸው ወሳኝ ፍልሚያዎች ባምላክ ተሰማ በብቃት ከመራቸው ታላላቅ ጨዋታዎች በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው።
ባምላክ በ2017/18 የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ የመራበት ወቅት በዳኝነት ህይወቱ ፈታኙ ነበር። በወቅቱ ሁለተኛውን የመልስ ጨዋታ እንዲመራ ካፍ ሲመርጠው የመጀመሪያው ዙር ስህተትን አብሮ እንዲያርም ጭምር ነበር ።
የመጀመሪያውን ዙር ጨዋታ በወቅቱ በመሩት ዋና ዳኛ አልጀሪያዊው መኸዲ ሸሪፍ አማካኝነት ካፍ ከፍተኛ ውግዘት ውስጥ ወድቆ ጫና የሚቋቋም ዋና ዳኛ ይፈለግ ነበር።
የተሻሩ ፣ መፅደቅ የሚገባቸውና የታለፉ ውሳኔዎች የመልሱን የፍፃሜ ጨዋታ ይበልጥ ተጠባቂ አደረጉት። በወቅቱ የአል አህሊው አሰልጣኝ ፓትሪስ ካቴሮን ከመገናኛ ብዙሀን ጋር ተፋጠው አንድ ጥያቄ ቀረበላቸው “ስለተመደበው ዋና ዳኛ ምን ይላሉ?” ተባሉ። መልሳቸው አጪር ነበር “ በኢትዮጵያዊው ዋና ዳኛ ሙሉ እምነት አለኝ “ ።
ዋልያዎቹ ባለፈው ዓለም ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው መሳተፍ ባይችሉም፤ ሁለት ኢትዮጵያውያን ዳኞች ግን በሙያቸው የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን በመዳኘት አገራቸውን በዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ወክለዋል። ከእነዚህም መካከል አንዱ ባምላክ ተሰማ ነበር።
በወቅቱ በሩሲያው 2018 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን እንዲመሩ ከተመረጡ 6 አፍሪካዊያን ዳኞች መካከልም አንዱ ነበር። ይህም ከ48 ዓመታት በኋላ የአለም ዋንጫ ጨዋታን የመራ ኢትዮጵያዊ ዳኛ አድርጎታል። በሜክስኮ የዓለም ዋንጫ ላይ ስዩም ታረቀኝ የሚባሉ ኢትዮጵያዊ ዳኛ ተሳታፊ እንደነበሩ ይታወቃል።
ባምላክ ተሰማ ባለፈው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክም ጨዋታዎችን እንዲመራ ተመርጦ አገሩን ማኩራቱ ይታወቃል። በፈረንጆች 2017 ዓመት በካፍ የዓመቱ ምርጥ ዳኛ በእጩነት ውስጥ መካተቱም አይዘነጋም።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 27/2014