ኢትዮጵያ በአልጄሪያና በግብጽ ክለቦች የሚጫወቱት ሽመልስ በቀለና ሙጂብ ቃሲምን የመሳሰሉ ተጫዋቾች እንዳሏት ይታወቃል። ይህ ግን ኢትዮጵያ እንዳላት አቅምና እንደ ክለቦቹ ደረጃ እዚህ ግባ የማይባል መሆኑ ብዙዎችን ያስማማል።
እነዚህ ተጫዋቾችም ወደ አልጄሪያና ግብጽ ክለቦች ያመሩት ከአገር ውስጥ ክለቦቻቸው ጋር ኮንትራታቸውን ጨርሰው በራሳቸው መንገድ ተስማምተው እንጂ በአለም አቀፍ የተጫዋቾች የዝውውር ገበያ በከፍተኛ ገንዘብ የኢትዮጵያ ክለቦች ሸጠዋቸው አይደለም።
ከዚህ ቀደም እንደ ጌታነህ ከበደና ሳላዲን ሰኢድን የመሳሰሉ ተጫዋቾችም ወደ ግብጽና ደቡብ አፍሪካ ክለቦች ያመሩት በተመሳሳይ መንገድ እንጂ በትልቅ የዝውውር መንገድ አልነበረም። የሃያ አንድ አመቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና የኢትዮጵያ ቡና አጥቂ አቡበከር ናስር ይህን ታሪክ የቀየረ ዝውውር መፈጸሙ ተረጋግጧል።
የአቡበከር የውጪ ዝውውር ጉዳይ በተለይም ወደ ደቡብ አፍሪካው ሃብታም ክለብ ማሚሎዲ ሰንዳውንስ እንደሚያቀና መወራት ከጀመረ ሰንበትበት ብሎ የነበረ ቢሆንም፣ የተጨበጠ ነገር የተሰማው ግን ከትናንት በስቲያ ነው። አቡበከር ከአፍሪካ ዋንጫ መልስ ለሙከራ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀናው የፊፉ የጥር ወር የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ሊጠናቀቅ ከአንድ ሳምንት ያነሰ ጊዜ በቀረው ወቅት እንደመሆኑ ዝውውሩ እክል ሊገጥመው እንደሚችል በብዙዎች ዘንድ ስጋት አድሮ ነበር። በዝውውሩ ጉዳይ የሚነሱ ውዥንብሮችም ይህን ስጋት አጠንክረውት ነበር። ይሁን እንጂ የዝውውር መስኮቱ ሰኞ ሌሊት ከተጠናቀቀ በኋላ በነጋታው ለኢትዮጵያ
እግር ኳስ አዲስ ብስራት ከደቡብ አፍሪካ ተሰምቷል። አቡበከርም ለደቡብ አፍሪካው ከበርቴና የአብሳ ፕሪሚየር ሊግ መሪ ክለብ ሰንዳውንስ ፊርማውን ማኖሩ ተረጋግጧል። የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ ለመሳተፍ ወደ ድሬዳዋ ለመጡ እንግዶች ከትናንት በስቲያ ባዘጋጀው የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ላይ የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ፕሬዘዳንት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ባደረጉት ንግግር፤ አቡበከር ለሰንዳውንስ መፈረሙን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴም ትናንት ከብስራት ስፖርት ጋር ባደረጉት ቆይታ ይህንኑ አረጋግጠዋል። ዝውውሩ የተጫዋቹንም ይሁን የክለቡን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ መፈጸሙን የገለጹት አቶ ገዛኸኝ”በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ትልቅ ዝውውር ተፈጽሟል፣ እጅግ የተሻለና ታሪካዊ ዝውውርም ነው” በማለት ተናግረዋል። ከተጫዋቹ ክፍያና ጥቅማ ጥቅም እንዲሁም ክለቡ ከዝውውሩ የሚያገኘው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን ያስረዱት አቶ ገዛኸኝ፣ የገንዘቡን መጠን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
ይህን ዝውውር ለማሳካት ኢትዮጵያ ቡና ትልቅ ጥረት ማድረጉን ጠቅሰዋል፤ ክለቡ ለአቡበከር በሰጠው የረጅም አመት ኮንትራትም ተጠቃሚ እንደሆነ በማስረዳት ሌሎች የአገር ውስጥ ክለቦች ከዚህ መማር እንዳለባቸው አብራርተዋል። ሰንዳውንስ እንደ ሌሎቹ የአቡበከር ፈላጊ ክለቦች ሁሉ በቀጥታ ሊያስፈርመው ፍላጎት ያሳደረው ከአፍሪካ ዋንጫው በፊት ነበር። ይሁን እንጂ አቡበከር ባለፈው የውድድር አመት የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ አስደናቂ ጊዜ ሲያሳልፍ በሀያ ሁለት ጨዋታ ሃያ ዘጠኝ ግብ ያስቆጠረበትን ብቃት ዘንድሮ መድገም አለመቻሉ ጥርጣሬ እንደፈጠረባቸው አልሸሸጉም።
በእርግጥ በዘንድሮው የውድድር አመት አቡበከር በዘጠኝ ጨዋታ አራት ግቦችን ሲያስቆጥር ሁለቱን በፍጹም ቅጣት ምት መሆኑ ሰንዳውንሶችን ቢያጠራጥር አይፈረድባቸውም። ለዚህም ተጫዋቹን በአፍሪካ ዋንጫ ዳግም አይተው ለመገምገም ወስነዋል። እንደ እድል ሆኖ አቡበከር በአፍሪካ ዋንጫ ግብ ማስቆጠር አልቻለም። ይህም በተጫዋቹ ብቃት ላይ ሌላ ጥርጣሬ እንዲፈጠርባቸው ምክንያት ነበር።
ይሁን እንጂ አቡበከር ዘንድሮ የአምና ብቃቱን መድገም ያልቻለው በብሔራዊ ቡድንም ይሁን በክለቡ አሰልጣኞች አምና የፊት መስመር አጥቂ ከነበረበት ቦታ ተቀይሮ የመስመር አጥቂ እንዲሆን በመደረጉ መሆኑን በማስረዳት ኢትዮጵያ ቡና ሌላ እድል እንዲሰጠው ትልቅ ጥረት ማድረጉን ከአቶ ገዛኸኝ ቃለመጠይቅ መረዳት ይቻላል። ሰንዳውንስም በዚህ መሰረት ነው ለአቡበከር የሙከራ እድል ሰጥቶ ወደ ደቡብ አፍሪካ የጠራው።
አቡበከር በሰንዳውንስ በነበረው የአንድ ሳምንት የሙከራ ጊዜ በሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ ሁለት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል የክለቡን ቀልብ መግዛትና ማሳመን ችሏል።
ሰንዳውንሶችም ተጫዋቹ እንዲያመልጣቸው ስላልፈለጉ በመጨረሻ ሰአት የቻሉትን ሁሉ ጥረት አድርገው ፊርማውን ሊያኖሩ ችለዋል። ይሁን እንጂ በደቡብ አፍሪካ ሊግ አንድ ክለብ ከአምስት በላይ የውጭ አገር ተጫዋቾችን መያዝ ስለማይችልና ሰንዳውንስም ኮንትራት ያላቸው አምስት የውጪ አገር ተጫዋቾች ስላሉት ሌላ መላ መዘየድ ነበረባቸው። በዚህም አቡበከርን አስፈርመው እስከ መጪው ሰኔ ድረስ አቡበከርን ለኢትዮጵያ ቡና በውሰት መስጠትን አማራጭ አድርገዋል።
በዚህም መሰረት በመጪው ሰኔ አቡበከር በይፋ የማሜሎዲ ሰንዳውንስ ንብረት መሆኑ ይረጋገጣል። የአቡበከር የተሳካ ዝውውር ከእድሜው አኳያ ጠንክሮ መስራት ከተቻለ ምንም ነገር ማሳካት እንደሚቻል ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በተለይም ለታዳጊዎች ትልቅ ትምህርት የሚሰጥና ተነሳሽነትን የሚጨምር እንደሚሆን የብዙዎች እምነት ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 26/2014