ቤንች ማጂ ዞን ሚዛን አማን ከተማ። ዕለቱን በየጉዳያቸው ሲሮጡ የዋሉ ነዋሪዎች ምሽቱን ወደቤት መመለስ ይዘዋል። የነሐሴ ወር መጨረሻ ነው። ዝናቡ ‹‹መጣሁ›› እያለ ያስፈራራል። ጭቃው ለጉዞ አዳግቶ እግርን እየያዘ ነው። ዝናብ ሲያርሳቸው የከረሙ ዕጽዋት ልምላሜን ለብሰው እጅብ ማለት ጀምረዋል። አሁን የበጋው አቧራ የለም። በየስፍራው የክረምቱ በረከት እየፈሰሰ ነው።
ከአዲስ ከተማ አካባቢ ነዋሪዎች አብዛኞቹ ጀንበር ሳትጠልቅ በጊዜ ገብተዋል። የመንደሩ አካል የሆነው የሚሊኒየም ሰፈርም በርካቶችን እንደያዘ በዝምታው ዘልቋል። ጊዜው ምሽቱ እየደረሰበት ነው። አልፎ አልፎ የሚያልፉት እግረኞች ፈጠን እያሉ መራመድ ጀምረዋል። ሰዓቱ ገፍቶ ምሽት ሶስት ሰዓት እያመለከተ ነው። ቁጥቋጦ የወረሰውን መንገድ አቋርጠው የሚያልፉ እግረኞች የጨለማውን መንገድ በጥንቃቄ እየተራመዱ ያወጋሉ።
ከደቂቃዎች በኋላ ከየግቢያቸው ደርሰው በሰላምታ ይለያያሉ። ክረምቱ ከጨለማው ተዳምሮ ለእግር መንገድ ያሰጋል። ከፊት የሚታይ ቁጥቋጦ ሁሉ የቆመ ሰው መስሎ ያሰደነግጣል። እንዲህ አይነቱን መንደር ለብቻ ማቋረጥ አስፈሪና አዳጋች ነው። መንገደኞቹ ይህ ሁሉ ያሳሰባቸው አይመስልም።
ሰፈሩን አልፈው፣ መንደሩን አቋርጠው፣ ወዳሰቡት ተቃርበዋል። ድንገት ግን ጨዋታቸውን ከሚያቋርጥ፣ እርምጃቸውን ከሚገታ እውነታ ላይ ዓይናቸው አረፈ። ሁሉም ባዩት ጉዳይ ተደናግጠው ተፋጠጡ። ጨለማ ያልገታው፣ ምሽቱ ያልደበቀው አስደንጋጭ ክስተት ከፊታቸው ተጋረጠ።
የልጅ ተስፋ …
በልጃቸው የወደፊት ሕይወት ታላቅ ተስፋን የሰነቁ ወላጆች ጠዋት ማታ አርቀው ያስባሉ። መኮንን ልጃቸው እነሱ ካለፉበት አስቸጋሪ ሕይወት መንገድ ልቆ እንዲሻገርላቸው ይሻሉ። በወጉ ካስተማሩት ለራሱ ይበጃል፤ ለአገር ለወገኑ ይጠቅማል። ይህ እውነት በጠዋቱ የገባቸው እናት አባት ልጃቸው ትምህርት ቤት እንዲሄድ ከቀለም እንዲዋደድ ፈቀዱ። በህጻንነት ዕድሜው ለትምህርት እጁን የሰጠው መኮንን ነገን በተሻለ ዓለም መቀበል እንዳለበት ሲነገረው አደገ። የእሱንና የወላጆቹን ህልም ዕውን ለማድረግ ትጋቱን ያለአንዳች ስንፍና አሳየ። ጠዋት ማታ ደብተሩን ይዞ ለጥናት ባዘነ።
ይህ ልፋቱ ፍሬ እንዲይዝ፣ ተስፋ እንዲያጭር በትምህርቱ ጎበዘ። አንደኛ ደረጃን ተሻግሮ ወደቀጣዩ ሲያልፍ መኮንን የትምህርት ጠቀሜታን ይበልጥ አውቆት ነበር። እሱ ትምህርቱን ሲጨርሰ ብዙ ዕቅዶችን ወጥኗል። ከራሱ አልፎ ለወላጆቹ፣ ከእነሱ ተርፎ ለአካባቢውና ለአገሩ ይበጃል።
ይህ ይሳካ ዘንድም ዛሬን መትጋትና መልፋት ይኖርበታል። መኮንን በየደረሰበት ክፍል የሚይዘው ውጤት ስለነገው ማንነቱ አመላካች ሆነ። አብሮት ያደገው በጎነት መለያው ሆኖ ቀጠለ። ለወላጆቹ ይታዘዛል። ለጎረቤቶች ይላካል። የአካባቢው ተወዳጅና ተፈላጊ ልጅ ነው። በየቀኑ የራሱንና የቤተሰቡን ህልም ለማሳካት ይሮጣል። ወላጆቹ በእሱ ላይ ያሣደሩት ዕምነት የተለየ ሆኗል። ወጥቶ በገባ ቁጥር መልካም ውጤት ከሚሹት ዓይኖች ጋር ይፋጠጣል። ከትምህርት ውሎ ሲገባ ጉልበቱን አይሰስትም። እንደልጅነቱ የታዘዘውን ይፈጽማል። እንደአቅሙ የቻለውን ያደርጋል። ሁሌም በጎነቱን ከሚያውቁ ወዳጅ ዘመዶች ምስጋንን እንደተቸረ ነው። ስለነገው በጎን ከሚያስቡለት፣ ደጉን ከሚመኙለት ሁሉ ዝቅ ብሎ ይመረቃል። መኮንን አሁንም ትጋት ላይ ነው።
በጥሩ ውጤት እየተሻገረ ትምህርቱን ቀጥሏል። ከእሱ መልካም ፍሬን የሚሹ ወላጆቹን ፍላጎት አልዘነጋም። የታሰበውን አሳክቶ ቤተሰቡን ማስደሰት ይሻል። በትምህርቱ ልቆ ለእኩዮቹ፣ ለሰፈሩ አርአያ መሆን ይፈልጋል። ተወዳጁ ተማሪ በትምህርቱ እየበረታ ገሰገሰ። አሁን የማትሪክ ፈተና የሚወስድበት ጊዜ ላይ ነው። ይህ ወቅት ለሰነቀው ዓላማ ወሳኝነት አለው።
ማትሪክ እንደተፈተነ ውጤቱን በጉጉት ጠበቀ። ወላጆቹ ዛሬም ከጎኑ ናቸው። ያሰበውን ሊያሳኩለት፣ ከፈለገው ግብ ሊያደርሱት እንዳሰቡለት ያውቃል። ቤተሰቦቹ እስካሁን በጥረቱ የተጓዘውን ልጃቸውን አስበው የተሻለውን መንገድ አቀዱለት።
ስለቀናውና ተወዳጁ ልጃቸው የማይሆኑት የለም። እስከዛሬ ከሆኑለት በላይ ሊያደርጉለት አስበዋል። እስከዛሬ በጥረቱ የተጓዘው ልጃቸው በጅማሬው ሊቀጥል ይገባዋል። መኮንን ተከታዩን የኮሌጅ ትምህርት ለመማር እየተዘጋጀ ነው። ለዚህ ደግሞ በቂ ገንዘብና አቅም ያስፈልገዋል። መኮንን ከጓደኞቹ ሳያንስ፣ ከእጁ ሳያጎድል እንዲማር እናት አባቱ በሬያቸውን፣ መሬታቸውን ሸጠዋል። ልጃቸው የኮሌጅ ተማሪ ይሆን ዘንድ ዛሬም የአቅማቸውን ያደርጋሉ። ተወዳጁ ተማሪ በወላጆቹ በረከት የኮሌጅ ትምህርቱን ቀጠለ። ዛሬም የፍላጎቱን ሊሞሉ አቅማቸውን ያሟጠጡ እናት አባቱን ውለታ አልዘነጋም። አሁንም በዓላማው መበርታት አለበት። ከታሰበው ከታቀደው መድረስ ግድ ይለዋል።
ስኬት …
የታሰበው አልቀረም። መኮንንና የልጅነት ህልሙ በገሀድ ተገናኙ። ለራሱና ለወላጆቹ ነባር ዕቅድ ሆኖ የኖረው እውነት ከስኬት ሲደርሰ ወላጆች የልባቸው ሞላ። የሚሳሱለት ልጃቸው የኮሌጅ ትምህርቱን አጠናቆ ጉልበታቸውን ሳመ። ወዳጅ ዘመድ፣ ጓደኛ ጎረቤት ምስጋናውን ቸረው። መኮንን ትምህርቱን አጠናቆ ስራ ጀመረ። ከኮሌጅ የተመረቀበትን ፎቶግራፍ ከግድግዳቸው የሰቀሉት ወላጆች የነገውን መልካም መንገድ እያሰቡ ብሩህ ተስፋን ሰነቁ።
አሁን የልጃቸውን ፍላጎት ሞልተዋል። መኮንን የሰው እጅ ሳያይ፣ ከሌሎች ሳያንስ ተምሮ ተመርቋል። ለዚህ እንዲበቃ ሀብት ጥሪታቸውን ትተዋል። ለዓላማው እንዲደርስ ጥቅማቸውን አሳልፈዋል። እንዲህ በማድረጋቸው ተቆጭተው አያውቁም። መኮንን ሁሌም የሚወዱት፣ የሚኮሩበት ልጃቸው ነው።
የሰው ፍቅር …
የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪ ለመኮንን የተለየ አክብሮት አለው፡ ትንሽ ትልቁን የሚያከብረው ወጣት በስራው ብርቱና ጠንካራ ነው። ዘወትር ከቤተክርስቲያን እየተገኘ ያገለግላል። በሰፈር መንደሩ ብቅ ባለ ጊዜ ተወዳጁን ወጣት በፍቅር የሚከበው ይበዛል። በየቤቱ እየዞረ ሰላምታና ፍቅርን የሚቸረው መኮንን ከወላጆቹ ያላነሰ ለአካባቢው ሰው በፍቅር ይገዛል።
ዛሬም እንደትናንቱ ታዛዥና ትሁት ነው። አሁንም እንደቀድሞው ታላላቆቹን እያከበረ ታናናሾቹን ይመራል። ሁሉም ይወዳል፤ ያከበርዋልም። ለሰፈሩ ብርቅና ድንቅ የሆነው ወጣት ሰው የመርዳት ልበ ቀናነት ከእርሱ ጋር ቀጥሏል።
ነሐሴ 28 ቀን 2010 ዓም
ኮንን ጥቂት አመሻሽቶ ወደቤት ለመሄድ አስቧል። መኖሪያው ከከተማው ወጣ ያለ ነው። መንደራቸው ለመድረስ ‹‹ሚሊኒየም›› የተባለውን አካባቢ አቋርጦ በእግሩ ማለፍ ይኖርበታል። ሰፈሩ በጊዜ ጭር ይላል። አካባቢው በጨለማና ቁጥቋጦው ይለያል። መኮንን ሁሌም በዚህ መንገድ ብቻውን ለመመላለስ አዲስ አይደለም። ቦታውን ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ስጋት ገብቶት አያውቅም።
ጥቂት አለፍ ብሎ ከሰፈሩ ሲገባ በፍቅር የሚቃኙት፣ በጉጉት የሚጠብቁት ዓይኖች ይቀበሉታል። ዕለቱን በዕምነት አገልግሎት ያሳለፈው ወጣት ሰዓቱ እየገፋ ጨለማው እየበረታ ሲሄድ ወደቤቱ ለመሄድ የመንገዱን አቅጣጫ ጀመረ። መብራት ያለበትን ጎዳና አልፎ ወደመታጠፊያው ሲያመራ አካባቢው እንደወትሮው ጨልሞ ነበር። ራመድ እያለ ወደፊት ገሰገሰ። ዛሬም እንደወትሮው ከልቡ የገባ ስጋት የለም። ቤት ደርሶ ስለሚያደርገው እያሰበ ነው። ስለነገውም እያቀደ ይራመዳል።
ድንገቴዎቹ እጆች…
መኮንን በጨለማው እየተጓዘ፣ ፈጥኖ እየተራመደ ከራሱ ማውጋቱን ይዟል። መንገዱን ከማጋመሱ በፊት ኮቴ የሰማ መሰለው። ፈጥኖ ዞር ከማለቱ ከበስተኋላው ከባድ እጆች ሲያርፉበት ተሰማው። በልጅነት አቅሙ እየታገለ ራሱን ለማዳን ሞከረ። አጥብቀው ከያዙት አራት ጠንካራ እጆች ሊያመልጥ አልቻለም።
ተሰፋ አልቆረጠም። የአቅሙን እየታገለ መከላከል ያዘ። አልሆነለትም። ፈርጣማዎቹ ክንዶች ከአቅሙ በላይ ሆኑበት። መኮንን ድንገቴዎቹ ጨካኞች ያሰቡትን ፈጽመው ከመሬት እስኪያጋድሙት በጨለማው ውስጥ የሁለት ሰዎች አካል እየታየው ነበር። ሰዎቹ ከእጃቸው የወደቀውን የጨለማ ሲሳይ ቁልቁል እያስተዋሉ ከኪሶቹ ገቡ። እጆቻቸው ከአንደኛው ኪስ ስድስት መቶ ብር፣ ከሌላው ደግሞ አንድ የሞባይል ቀፎ አቀበሏቸው። አሁን ግዳዩ ቀንቷቸዋል። በእግሮቻቸው ስር ስለወደቀው ወጣት ደንታ አልሰጣቸውም። እንደዋዛ ተራምደውት ወደመጡበት ተመለሱ።
ምሸት ሶስት ሰዓት…
በጨለማው መንገድ እያወጉ ሰፈሩን የሚያቋርጡት መንገደኞች ድንገት ባዩት እውነት ተደናግጠዋል። ከፊት ለፊታቸው ድፍት ብሎ የወደቀው በትክክልም የሰው አካል መሆኑን አውቀዋል። ሰዎቹ ጠጋ ብለው የወደቀውን ወጣት አስተዋሉት። ማንነቱ ፈጽሞ አልጠፋቸውም።
ይህን ሲያውቁ ትንፋሹን ሊያዳምጡ ተጠጉት። ወዲያው ተስፋ ቆረጡ። መኮንን በሕይወት አልነበረም። መንገደኞቹ ጊዜ አላጠፉም። ፈጥነው ፖሊስ ዘንድ ደወሉ። ጥሪው የደረሰው የከተማው ፖሊስ ከስፍራው ሲደርስ አልዘገየም። ከተባለው ስፍራ አስፈላጊውን ቡድን አደራጅቶ ተገኘ።
የፖሊስ ምርመራ…
ፖሊስ ከስፍራው ደርሶ የሟችን አስከሬን ከማንሳቱ በፊት ተገቢውን ምርመራ አጠናቀቀ።የሟቹ ወጣት ሕይወት በሰው እጅ ማለፉን በመረዳቱ በአካባቢው መረጃዎችን ማሰባሰብ ያዘ። ወደሚዛን ቴፒ ሆስፒታል የተላከው የሟች አስከሬን የምርመራ ውጤት ወጣቱ በሰዎች ጥቃት ስለመገደሉ አመላካች ነበር። ፖሊስ ምርመራውን አጠናክሮ ቀጠለ።
በስፍራው የሚያውቁትን ነዋሪዎች እየጠየቀ፣ የሚጠረጥሩት ይኖር እንደሆን አጣራ። ማናቸውም በሟች ላይ ጨክኖ እጁን ያነሳል የሚሉት ተጠርጣሪ እንደማይኖር አረጋገጡለት። ውሳኔ… ፖሊስ ያገኘውን መረጃ ሳይንቅ አሰሳውን በስፋት ቀጠለ።
ተስፋ ሳይቆርጥ፣ ሳይዘናጋ በፍለጋው ባተለ። በከባድ ሐዘን ውሰጥ የከረመው የከተማው ነዋሪ በሆነው ክስተት በተፈጸመው ወንጀል ልቡ ተሰብሯል። የመኮንን መልካምነት የሚያውቁ፣ ጨዋነቱን የሚመሰክሩ ሁሉ ሀዘናቸው በረታ። ለቅሷቸው መረረ። አብዛኞቹ ሕይወቱን የቀጠፉትን ጨካኞች ከእጃቸው ሊያስገቡ ጠዋት ማታ ባተሉ። መኮንን መልካም ወጣት ነበር። ትንሽ ትልቁን አክባሪ፣ ለታላቆቹ ታዛዥ፣ ለዕምነቱ አዳሪ ሆኖ ቆይቷል። ራሱን ለማሸነፍ ቤተሰቦቹን ለማስደሰት ያልሆነው የለም።
ህልሙ ዕውን ሆኖ ሙሉ ሰው ከሆነ ጥቂት ጊዜው ነበር። ይህን ደግ ወጣት ማን ገድሎ እንደጣለው ያለመታወቁ በሁሉም ዘንድ ቁጭትና ንዴት እየቀሰቀሰ ነው። መኮንንን ማን ገደለው? ይህ ወሳኝ ጥያቄ የፖሊስ ብቻ አልሆነም።
መልስ አልባው እውነት የከተማው ነዋሪም ድብቅ ሚስጥር እንደሆነ ዘልቋል። ፖሊስ የወንጀሉን የሚስጥር ቋጠሮ ለመፍታት ሌት ተቀን እየባዘነ ነው። ቡድን አደራጅቶ፣ ኃላፊነት አደላድሎ፣ በየቀኑ ይመክራል። የአካባቢው ሰዎች ዘወትር አብረውት ናቸው። የጠረጠሩትን ይጠቁማሉ። የታዘዙትን ይፈጽማሉ። የወጣቱ ጉዳይ ‹‹ደም አልባ›› ሆኖ እንዳይቀር በየአቅጣጫው ይሮጣሉ።
የወንጀል ድርጊት ከሕዝብ ዓይንና ጆሮ እንደማይደበቅ የሚያውቀው ፖሊስ አሁንም ከሚመለከታቸው ጋር መምከሩን ቀጥሏል። ተጠርጣሪዎቹ ከከተማው ውጭ እንደማይሆኑ በማሳመንም የማፈላለጉን ስልት ለነዋሪዎች አጋርቷል። በእልህና ቁጭት ሁሉም በየበኩሉ በሚሮጥበት አጋጣሚ ድንገት አንድ ፍንጭ ስለመገኘቱ ተሰማ። በወንጀል ድርጊቱ ይኖሩበታል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ስም ታወቀ።
ፖሊስ የሰዎቹን ማንነት አጣርቶ ይገኙበታል ከተባለ ስፍራ ደረሰ። አንደኛው ተጠርጣሪ ወንጀሉ በተፈጸመ ሰሞን ከአካባቢው መጥፋቱን ደረሰበት። ፖሊስ የመገኛውን ጫፍ ለማግኘት እግር በእግር አሰሳውን ቀጠለ። የሚፈልገውን ሚስጥር አላጣውም። ግለሰቡ ወደ ጋምቤላ ክልል መጥፋቱ መረጃዎች ደረሱት። ግለሰቡን ለመያዝ ከክልሉ ፖሊስ ጋር መቀናጀት የጀመረው ፖሊስ ‹‹ሚጢ›› ከተባለ ወረዳ እንደሚኖር አወቀ። የፍርድ ቤት መያዣ ትዕዛዝ በማሟላት ተፈላጊውን በእጁ ለማስገባት አልዘገየም። የቤንች ማጂ ዞን ፖሊስ አባላት አንደኛውን ተጠርጣሪ በእጃቸው ካስገቡ በኋላ ሁለተኛውን ለመያዝ መረጃዎችን አሰሱ።
ሁለተኛውን ተፈላጊ ለመያዝ ፖሊስ ያደረገው ጥረት ተሳካለት። ግለሰቡ ከዞኑ ከተማ ወጥቶ ለማምለጥ በሙከራ ላይ ሳለ ከካቴናው ቀለበት አስገባው። ተጠርጣሪዎች ከፖሊስ በግንባር ቀርበው ቃላቸውን ሰጡ። ወጣቱን ለመግደል ምክንያት የሆናቸው የዝርፊያ ወንጀል ለመፈጸም ማሰባቸው እንደሆነ አልሸሸጉም።
የቤንች ማጂ ዞን ፖሊስ መምሪያ የስራ ሂደት መሪ ምክትል ኢንስፔክተር ስንታየሁ ማሞ የተጠርጣሪዎች ሙሉ ቃል በወንጀል መዝገብ ሰፍሮ በፊርማቸው እንዲያረጋገጥ አደረጉ። ግለሰቦቹ ስለድርጊቱ የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል በእማኞች ፊት አስነብበው በራሳቸው ፊርማ አረጋገጡ። የከተማው ነዋሪ የግለሰቦቹን መያዝ ሲሰማ ደስታውን በዕንባው ገለጸ።
ለገንዘብና ሞባይል ስርቆት ሲባል በግፍና ጭካኔ የወጣቱን ሕይወት የቀጠፉ ግለሰቦች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠየቁ። ለአገርና ወገን ታላቅ ተስፋ የነበረውን ወጣት ህልም ያመከኑ ተጠርጣሪዎች ፍትህ በአግባቡ ዕውን ይሆን ዘንድም ተመኙ።
ውሳኔ…
የቤንች ማጂ አካባቢ ፍርድ ቤት በሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ተጠናክሮ የመጣለትን መዝገብ መርምሮ አጠናቋል። ከፖሊስና ዓቃቤ ህግ ለችሎቱ በደረሱት ማስረጃዎች ተመስርቶም የተጠርጣሪዎችን ጥፋተኝነት በአግባቡ አረጋግጧል።
ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ባስተላለፈው ብይንም አንደኛ ተከሳሽ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአስራ ስምንት ዓመት ጽኑ እስራት፣ እንዲሁም ሁለተኛ ተከሳሽ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአስራ ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት ይቀጣ ሲል ወስኗል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጥር 21/2014