የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና የኢትዮጵያ ቡና ክለብ የአጥቂ መስመር ወጣት ተጫዋች አቡበከር ናስር በተለይም ባለፈው አመት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አስደናቂ ብቃት ማሳየቱን ተከትሎ ከአገር ውጪ ያሉ በርካታ ክለቦች ባለፈው ግንቦት ተጫዋቹን ለማስፈረም ፍላጎት ማሳየታቸው ይታወቃል።
ይሁን እንጂ በወቅቱ ክለቡ ኢትዮጵያ ቡና ለየትኛውም ክለብ ጥያቄ ፈጥኖ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ቆም ብሎ ነገሮችን ለማጤን በመወሰኑ የትኛውም ዝውውር ሳይሳካ ቀርቷል።
የኢትዮጵያ ቡና የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ በወቅቱ ‹‹የአቡበከርን የተሻለ ደረጃ መድረስና ዕድገቱን እንፈልጋለን። ይህ ልጅ ወደ አውሮፓ ወይም ወደ ተሻለ ክለብ ሄዶ እንዲጫወት እንፈልጋለን።
ዞሮ ዞሮ ለልጁም ዕድገት ለአገርም ጥቅም እንዲሁም ለክለቡ ትልቅ ክብር እና ስም ነው። የሚመጡትን ጥያቄዎች ቁጭ ብለን በማየት ለእኛም ለእሱም ጠቃሚ የሆነ ውሳኔ እንወስናለን። ከዚህ ወጭ በአሉባልታ እና በወሬ የሚሆን ነገር እንደሌለ እንዲታወቅ እንፈልጋለን›› በማለት ተናግረዋል፡፡
የ2013 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክስተት የሆነው የኢትዮጵያ ቡና አጥቂ አቡበከር ናስር በሃያ ሶስት ጨዋታ ሃያ ዘጠኝ ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ የሊጉን ከፍተኛ ግብ የማስቆጠር ክብረወሰን ከጌታነህ ከበደ መረከቡ ይታወቃል።
አቡበከር ባለፉት አመታት ግብ በናፈቃቸው የሸገር ደርቢ ጨዋታዎች ጭምር በቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በአንድ ጨዋታ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ሐትሪክ (ሶስታ) በመስራት አስደናቂ ብቃት አሳይቷል።
በአጠቃላይ በውድድር አመቱ አራት ጊዜ ሐትሪክ መስራት የቻለው አቡበከር የኮከብ ግብ አግቢነትን እንዲሁም የኮከብ ተጫዋችነትን ሽልማት ማሸነፍ ችሏል። ይሁን እንጂ በዘንድሮው የውድድር አመት በሊጉ የአምናውን ብቃት መድገም አልቻለም።
እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ ዋንጫም አቡበከር የዋልያዎቹ የፊት መስመር ተሰላፊ ቢሆንም በውድድሩ ግብ ሳያስቆጥር ከካሜሩን ተመልሷል። አቡበከር ከካሜሩን ከተመለሰ ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን የተዳፈነ የሚመስለው ከአገር ውጪ ባሉ ክለቦች የመጫወት ህልሙና የውጪ ክለቦች ጥያቄ ዳግም ነብስ ዘርቷል።
አቡበከር ከአፍሪካ ዋንጫ ቆይታው በኋላ የደቡብ አፍሪካው ጠንካራ ክለብ ማሚሎዲ ሰንዳውንስ ቀልብ አርፎበታል። የደቡብ አፍሪካን ሊግ በ19 ጨዋታ በ44 ነጥብ እየመራ የሚገኘው ማሚሎዲ ሰንዳውንስ በጥር ወር የዝውውር መስኮት አቡበከር ናስርን ለማስፈረም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረገው ድርድር አቡበከርን ለማስፈረም ለሙከራ ጠርቶታል።
ይህንንም ተከትሎ ከቀናት በፊት አቡበከር ወደ ደቡብ አፍሪካ አቅንቷል። በሙከራው ጊዜ የትራንስፖት እና ደቡብ አፍሪካ በሚቆይበትም ጊዜ ሙሉ ወጪውን ክለቡ የሚችል መሆኑን የኢትዮጵያ ቡና ክለብ አስታውቋል።
አቡበክር ደቡብ አፍሪካ ከደረሰ በኋላ ከክለቡ ጋር ልምምድ የሰራ ሲሆን፣ የሙከራ ጊዜውን በወዳጅነት ጨዋታዎች በማካሄድ በቀጣይ ከክለቡ ጋር የሚኖረውን ቆይታ ይወስናል ተብሎ ይጠበቃል። በቅርብ የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙትም አቡበከር በሙከራ ጊዜው አስደናቂ ብቃት በማሳየት ማሚሎዲ ሰንዳውንስን የመቀላቀል ሰፊ እድል አለው።
ይህም በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ተጠቁሟል። አቡበከር ይህን ማሳካት ከቻለም በካፍ ፕሬዚዳንት እና ባለሀብት ፓትሪስ ሞሶፔ ባለቤትነት የሚመራው ማሚሎዲ ሰንዳውንስ ክለብ አካል በመሆን በቀጣይ የእግር ኳስ ህይወቱ አዲስ ምእራፍ የሚከፍት ይሆናል።
ካለፈው አመት የውድድር አጋማሽ ጀምሮ የደቡብና ሰሜን አፍሪካ ክለቦች ይህን ወጣት ኮከብ የግላቸው ለማድረግ ጥያቄ ቢያቀርቡም አቡበከር ከነበረበት ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ፉክክር አንፃር ሳይሳካ ቀርቷል።
የውድድር አመቱ ከተጠናቀቀ በኋላም የአፍሪካ አገራትን ጨምሮ የምስራቅ አውሮፓና የኤዥያ አገራት ተጫዋቹን ለማስፈረም ግልፅ በሆነ ደብዳቤና በተለያዩ የመገናኛ መንገዶች ለኢትዮጵያ ቡና ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበር ይታወሳል። እያቀረቡ ይገኛሉ፡ ፡
ባለፈው ጥር የዝውውር መስኮትም የአልጀሪያ ክለብ አቡበከርን ማስፈረም ፈልጎ ሳይሳካ ቀርቷል። የደቡብ አፍሪካው ክለብ ካይዘር ቺፍ፣ በጆርጅያ የመጀመሪያ ዲቪዚየን እየተሳተፈ የሚገኘው ዲላ ጎሪ እግር ኳስ ክለብ አቡበከርን የግላቸው ለማድረግ ፍላጎት ከነበራቸው ክለቦች መካከል ይጠቀሳሉ።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 20/2014