የአገር አፍራሽና አሸባሪውን ቡድን ህልም ለማምከን በተካሄደው የህልውና ዘመቻ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ታላቅ ተጋድሎ አድርገዋል። የትግራይን ሕዝብ ምሽግ በማድረግ በርካታ ጥፋቶችን ያደረሰው አሸባሪው ትህነግ በትግሉ አቅሙን እንዲያውቅና ዳር እንዲይዝ መላው ሕዝብ አኩሪ ተጋድሎ እያደረገ ይገኛል።
ሸብርተኛ ቡድኑ በከፈተው ጦርነት ንፁሃንን ሰለባ ከማድረጉም በላይ ዘመን በተለይም በአፋርና አማራ ሕዝቦች ላይ የማይረሳ ጠባሳን አድርሷል። ቡድኑ ከወራት በፊት በደረሰበት ጠንካራ ዱላ እያፈገፈገ በወረራ ከያዛቸው ቦታዎች ተጠራርጎ ለመውጣትም በቅቷል።
ነገር ግን አሸባሪው ቡድን በወሎና በአፋር ክልል በቆየባቸው ጥቂት ወራት ያጠፋቸው ጥፋቶች ዛሬም በሚሊየን የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎችን በችግርና በሰቆቃ ውስጥ እንዲኖሩ አድርጓቸው ይገኛል። አሸባሪው ቡድን ያደረሰው ሰብዓዊ፤ ቁሳዊና ኢኮኖሚያዊ ውድመት እንዲህ በቀላሉ በአንድ ጀምበር ወደ ነበረበት ሊመለስ ካለመቻሉ ባሻገር፤ አሁን ባለው የመንግስት ውሱን አቅም ብቻ የሚሞከርም አይደለም።
ይህንን ሀቅ በመረዳት ችግሩ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ መላው ኢትዮጵያውያን ለችግር የተዳረጉ ዜጎችን ለመታደግ የአቅማቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል። እኛም ለዛሬው የሀገርኛ አምዳችን የአዲስ አበባ አማራ ወጣቶች ማህበር በዚህ ረገድ የሰራቸውንና እየሰራቸው ያለውን ስራዎች ለማሰቃኘት ወደናል።
የማህበሩ ፕሬዚዳንትና የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ወጣት ዘነበ በለጠ በማህበሩ የተሰሩ ስራዎችን አስመልክቶ እንደሚከተለው ገልጾልናል። የአዲስ አበባ አማራ ወጣቶች ማህበር ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ወጣቶችን ከማንቃትና ከማደራጀት ባለፈ በርካታ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ሲሰጥ ቆይቷል።
ከዓመት በፊትም በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚደረገው የህልውና ዘመቻ ትብብርና ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባ መንግስት ካወጀበት ጊዜ አንስቶ፤ የማህበሩ አባላት እንደ ግለሰብ፤ ማህበሩም እንደ ማህበር አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በተለይም ወራሪው አሸባሪ ቡድን በአፋርና አማራ ክልልች ሰርጎ በመግባት በርካታ ንጹሃን ዜጎችን ለችግር ከዳረገና ንብረት ካወደማ በኋላ፤ እነዚህን ጥፋቶች ወደ ነበሩበት ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ማህበሩ የትኛውም ጊዜ በተለየ በርካታ ስራዎች አከናውኗል እያከናወነም ይገኛል።
ማህበሩ የድጋፍና ትብብር ስራዎቹን ማከናወን የጀመረው የደረሰውን ችግር እንደማንኛውም ዜጋ ከተመለከተና የመንግስትን ጥሪ ከሰማ በኋላ ከአባላቱ ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ ነበር። በውይይቱም ከሁሉም በፊት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የሚጠበቅበትን ለመስራት ከስምምነት ላይ ይደርሳል። በዚህም መሰረት እንዳጠቃላይ በኢኮኖሚው ዘርፍ ከህልውና ዘመቻው በኋላ አንድ መቶ ስልሳ ሁለት ሚሊየን ብር የሚገመት የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ ችሏል።
እነዚህ ሰብዓዊ ድጋፎችም በቀዳሚነት ተደራሽ የተደረጉት ተፈናቅለው በየመጠለያው በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ነው። ለእነዚህ ዜጎች ሲቀርቡላቸው የነበሩት ነገሮችም፤ ለእለት ፍላጎት መሟላት ያለባቸውና ለምግብነት የሚውሉ ፓስታ፤ መኮሮኒ፤ ዱቄት፤ ስንዴ፤ ሩዝ፤ ጤፍ ያሉት ናቸው። እንዲሁም ከቁሳቁስ የምግብ ማብሰያ የመአድ ቤት እቃዎች፤ ፍራሽ፤ ብርድልብስና አንሶላ ይገኙበታል። ለህጻናትና ለሴቶች ደግሞ የንጽህና መጠበቂያና የመሳሰሉት ናቸው።
ይህንን ለማዳረስ በተደረገው እንቅስቃሴም፣ በተለይ በአዲስ አበባ «ሁለት ያለው አንድ ይስጥ» በሚል መሪ ቃል በተደረገው የልብስና ቁሳቁስ ድጋፍ ማሰባሰብ መርሃ ግብር በርካታ ዜጎች በመተባበራቸው በርካታ ድጋፎችን ለተፈናቃዮች ማድረስ ተችሏል። እንደሚታወቀው በአገሪቱ በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር የተዳረጉ የማህበረሰብ ክፍሎች በርካታ ናቸው።
እነዚህን በሙሉ ማዳረስ በአንድ ማህበር የሚቻል አይደለም። በመሆኑም ማህበሩ እስካሁን ድጋፉን ሲያደርግ የነበረው በጦርነቱ የከፋ ችግር የደረሰባቸው በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ፤ ዋግህምራ፤ በሰሜን ጎንደር፤ በደቡብ ጎንደር በተለይ እብናት በሚባለው አካባቢና በሰሜን ሸዋ ግንባር ነው።
በአፋር ክልልም በተመሳሳይ የቁሳቁስ ድጋፎች ለሶስት ዙር ያህል ተደርገዋል። ድጋፎቹ የተሰባሰቡትም በአዲስ አበባ ከተማ ስር ከሚገኙ አስራ አንድ ክፍለ ከተሞች ውስጥ ባሉ አንድ መቶ ሃያ ሶስት ወረዳዎች ነው።
ማህበሩ በእነዚህ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ባለው መዋቅር ካሰባሰበው መካከል የስምንቱ ክፍለ ከተሞች ያስተባበሩት ወደ አማራ ክልል፡፡ እንዲሁም የሶስቱ ክፍለ ከተሞች ደግሞ ወደ አፋር ክልል ተልከዋል። ድጋፎቹ በሙሉ የተደረጉት ደግሞ የማህበሩ አመራሮችና አባላት በአካል በተገኙበት ቦታው ድረስ በመሄድ ነው።
ይህ የተደረገበት ዋነኛ ምክንያትም የሚደረጉት ድጋፎች ከቁሳዊ ጥቅማቸው ባለፈ ተፈናቅለው ለመጡትና በከፍተኛ ችግር ውስጥ ለሚገኙት ዜጎች “አብረናችሁ ነን፤ ከጎናችሁ እንቆማለን” በማለት ወገን እንዳላቸው እንዲሰማቸው የአብሮነት መንፈስ ለመፍጠር ታስቦ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ማህበሩ ከሰራቸው ስራዎች መካከል ወቅታዊውን አገራዊ ጥሪ በመቀበል ወጣቱ የአገር መከላከያ ሰራዊትን እንዲቀላቀል ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
አሸባሪው ሕወሓት በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ እርምጃ ወስዶ በአገሪቱ ትልቅ ችግርና ውጥረት በተከሰተበት ወቅት የመንግስትን ጥሪ ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊቱን ሲቀላቀል የነበረው ወጣት ቁጥር በሚጠበቀው ደረጃ በቂ አልነበረም።
ወራሪውን ኃይል ለመመከት መሰልጠንና መታጠቅ እንዳለባቸው ያምኑ የነበሩ ወጣቶችም በመጀመሪያው ዙር ተቀዳሚ መዳረሻቸው ያደርጉ የነበረው መከላከያ ሰራዊቱን መቀላቀል ሳይሆን ሚሊሻውንና ፋኖን ነበር። በመሆኑም ማህበሩ ይህንን ክፍተት በመገምገም ለሁለተኛ ዙር ምልመላ ባደረገው ከፍተኛ ወጣቱን የማንቃትና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የማስገንዘብ እንቅስቃሴ የነበረውን ሁኔታ መቀየር ችሏል።
በዚህም በሁለተኛው ዙር 40ሺ የሚደርሱ ወጣቶች የመከላከያ ሰራዊቱንና የሚሊሻና ፋኖ ኃይልን እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ችሏል። ይህ ቅስቀሳ የተደረገውና ወጣቱንም ማሰባሰብ የተቻለው በክልሉና በመላው አዲስ አበባ በተሰሩ ስራዎች ነው። እነዚህ ስራዎች ሲሰሩም የማህበሩ አባላት ወጣቱን ከማንቃትና ለአገሩ አንድነት መከበርና ለሕዝቡ ነጻነት እንዲታገል ከመቀስቀስ ባለፈ በተግባርም የአርአያነት ስራቸውን ሲወጡ ነበር።
በዚህም የማህበሩ አባላት የሆኑ አንድ ሺህ ሁለት መቶ አምሳ ወጣቶች በደብረ ማርቆስ የአማራ ልዩ ኃይል ማሰልጠኛ ተቋም ከአዲስ አበባ ሄደው እንዲገቡና ስልጠና ወስደው አገራቸውን እንዲታደጉ ለማድረግ በቅቷል። ከእነዚህ ወጣቶች መካከል አብዛኛዎቹ በጎንደር ግንባር ከፍተኛ መስዋእትነት በመክፈል አገራቸውን መታደግ ችለዋል። በዚህ የጦርነት ግንባርም ከወጣቶቹ መካከል የቆሰሉት በአሁኑ ወቅት በጦር ኃይሎችና በቤላ ማገገሚያ ህክምናቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ። ማህበሩም በማገገሚያ ማእከላቱ በመገኘት ለወጣቶቹ ሞራልን ጨምሮ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እያደረገላቸው ይገኛል።
በሌላ በኩል ማህበሩ እያከናወናቸው ባሉ እንቅስቃሴዎች በአሸባሪው ቡድን የጠፉና የወደሙ የመንግስት፤ የድርጅትና የግለሰብ ንብረቶችን በማየትና በመለየት የመመዝገብና የመሰነድ ስራዎች ተሰርተዋል። እነዚህ ስራዎች የተከናወኑትም በአንድ ወገን በቀጣይ ማህበሩ የቻለውን በአቅሙ ለመደገፍ ዝግጅት ለማድረግ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተሰበሰበውንና እየተሰበሰቡ ያሉትን መረጃዎች በመውሰድ ማንኛውንም ድጋፍ ለማድረግ የሚፈልግ አካል በቀላሉ ድጋፉን ተደራሽ ለማድረግ እንዲያስችለው ታስቦ ነው።
ወጣት ዘነበ በአሁኑ ወቅት በመሰራት ላይ ያሉትንና በቀጣይም በማህበሩ ሊሰሩ የታቀዱትን ስራዎች እንደሚከተለው ያብራራቸዋል። በአማራና አፋር ክልሎች በርካታ ዜጎች ንብረቶቻቸው ወድመዋል።
ቤታቸው ፈርሷል፤ ከብቶቻቸው ተነድተውባቸዋል። ባጠቃላይም እነዚህ ንጹሀን ዜጎች በአሸባሪው ቡድን ጥሪት አልባ እንዲሆኑ ተደርጓል። በመሆኑም ማህበሩ በቅርቡ በአጣዬ፣ በሸዋ ሮቢትና ደብረ ሲና ድረስ በአካል ሄዶ በማየትና የሚያስፈልገውን ነገር በመለየት አቅም በፈቀደ ባለሀብቶችን በማስተባበር ድጋፍ ማድረግ ጀምሯል። ከእነዚህም መካከል በደብረሲና ከተማ ሙሉ ለሙሉ የወደመ አንድ የህጻናት ቤተ መጻህፍት በማህበሩ በኩል ግንባታው የተጀመረ ሲሆን በቅርቡም ተጠናቆና ግብአት ተሟልቶለት ወደ ስራ የሚገባ ይሆናል።
በተጨማሪ ከወለጋ/ነቀምትና የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው የመጡና በደብረ ብርሃን በመጠለያ ካምፕ ውስጥ ከአስር ወር በላይ የቆዩ የአማራ ክልል ተወላጆች አሉ። ማህበሩም ለእነዚህ በችግር ውስጥ ላሉ ዜጎች የእለት ፍጆታ እቃዎች እንዲደርሳቸው እያደረገ ይገኛል።
በተመሳሳይ አዲስ አበባ ተፈናቅለው ለመጡም ፍራሽ የምግብ ማብሰያና መሰል ቁሳቁሶች እንዲደርሳቸው በማድረግ የእለት ችግሮቻቻውን ለመቅረፍ በመስራት ላይ ነው። በሌላ በኩል የህልውና ዘመቻው ያልተጠናቀቀ በመሆኑና የመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ከሚያስፈልገው መካከል አንዱ መሆኑን ማህበሩ ያምናል።
በመሆኑም ማህበሩ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ከመገንዘብ ባለፈ በተመሳሰይ መንግስትም የድጋፍ ጥሪ በማቅረቡ በቅርቡ ስምንት ኤፍ ኤስ አር ሙሉ የተለያዩ ቁሳቁሶችንና ሶስት መኪና ሙሉ ውሃ ማድረስ ተችሏል።
ህብረተሰቡን በማንቃት ረገድም ማህበሩ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። ከእነዚህም መካከል በህልውና ዘመቻው ሚናችን ምን መሆን አለበት በማለት ችግሩ የተወሰኑ ብሄሮች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊ መሆኑን እንዲረዳ በተለያዩ መድረኮች ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የማንቃት ስራዎች ተሰርተዋል።
እነዚህ ስራዎች የተሰሩትም ከኦሮሚያ ክልል ወጣቶች ማህበርና ከደቡብ ክልል ወጣቶች ማህበር ጋር በመሆን በትብብር ነው። የዚህ አይነቱ የትብብር እንቅስቃሴ በቀጣይም በሌሎቹ ክልሎች ከሚገኙ ወጣቶችና የወጣቶች ማህበራት ጋር የሚከናወን ይሆናል።
ዛሬም ከዚህ ሁሉ ጥፋት በኋላ ሕወሓት የጦርነት ጉሰማውን እስካሁን አላቆመም። ይልቁንም ትንኮሳውንና ንጹሃን ዜጎችን ማንገላታቱን ቀጥሏል ያለው ወጣት ዘነበ በቀጣይ ከማህበሩ አባላትም ሆነ ከመላው ወጣት የሚጠበቀውን እንደሚከተለው ተናግሯል። ወጣቶች በየትኛውም ቦታ በምንም አይነት የኑሮ ደረጃ ላይ ቢሆኑ የፈለጉትን ሊያሳኩ የሚችሉት አገር ስትኖርና አገር ሰላም ስትሆን ነው።
በመሆኑም ለአገር ሉአላዊነትና ለሕዝቦች ነጻነት ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል። ለአገር ነጻነትና ለሕዝቦች መስዋእትነት መክፈል ማለት ደግሞ የግድ በግንባር ተገኝቶ ጥይት ተኩሶ ጠላትን መግደል አይደለም።
ማንኛውም ወጣት ባለበት ሆኖ በአቅሙ አገሩን መጠበቅ፣ ወገኑን መንከባከብና መታደግ ይችላል። ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ በማድረግ፤ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ፤ በአገር መልካም ገጽታ ግንባታዎች ተግባር በመሳተፍ፤ አገሩን ከጥፋት መታደግ ይኖርበታል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ጥር 20/2014