የ አፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ለ33ኛ ጊዜ በካሜሩን አስተናጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል። በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንም ከካሜሩን፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኬፕ ቨርዴ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ተደልድሎ ከምድቡ ሳያልፍ ከውድድሩ በጊዜ ተሰናብቷል።
ስለአፍሪካ ዋንጫ ሲነሳ በ‹‹የአፍሪካ እግር ኳስ አባት››ትነት የሚታወቁት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ አብረው መታወሳቸው ግድ ነው።
ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ አንድ ለእናቱ የሆነውን የአፍሪካ ዋንጫዋን (1954) ስታሸንፍ የቡድኑ አሠልጣኝ እርሳቸው ነበሩ። ኢትዮጵያ ዋንጫውን ያሸነፈችው ደግሞ ከ60 ዓመታት በፊት፣ በዚሁ ሰሞን፣ ጥር 13 ቀን 1954 ዓ.ም ነበር።
አቶ ይድነቃቸው እግር ኳስን ተጫውተዋል … አሠልጥነዋል … መርተዋል። አመራርነታቸው ደግሞ ከኢትዮጵያም የተሻገረ ነበር። በእነዚህ እግር ኳሳዊ ተግባራት ሁሉ ወርቃማ ስኬቶችን ተጎናፅፈዋል።
ዛሬ ይህን መሰል ደማቅ ታሪክ መፃፍ የቻሉትን የአንጋፋውን የስፖርት ሰው የይድነቃቸው ተሰማን ታሪክ በጥቂቱ እንመለከታለን። ይድነቃቸው ተሰማ መስከረም 1 ቀን 1914 ዓ.ም ጅማ ከተማ ውስጥ ተወለደ። አባቱ የበርካታ ሙያዎች ባለቤት የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ሲሆኑ እናቱ ደግሞ ወይዘሮ ሙላቷ ገብረሥላሴ ይባላሉ።
አዝማሪ፣ ባለቅኔ፣ ቀራፂ፣ ሰዓሊ፣ ነጋዴ፣ መኪና አሽከርካሪ (የመጀመሪያው ባለ መንጃ ፈቃድ)፣ መካኒክ፣ ፖለቲከኛ፣ ፎቶ አንሺ … የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ፤ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ፣ በልጅ ኢያሱ፣ በንግሥት ዘውዲቱና በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥታት ስመ ጥር ሰው ነበሩ።
በተለይ በልጅ ኢያሱ ዘመን ጉልህ ፖለቲካዊ ተሣትፎ ነበራቸው። ከዚህ በተጨማሪም ለልጅ ኢያሱም የተለየ አክብሮት ስለነበራቸውና አብዛኛው በአዲስ አበባ ከተማ የነበረው የመሐል አገሩ መኳንንት ልጅ ኢያሱን ከሥልጣን ለማውረድ በተሰለፈ ጊዜ ሁሉ ነጋድራስ ተሰማ ግን የልጅ ኢያሱ ታማኝ ባለሟል ሆነው እስከ መጨረሻው ድረስ በመዝለቃቸው ልጅ ኢያሱ ከሥልጣናቸው ተሽረው ዘውዲቱ ምኒልክ ንግሥት፤ ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን ደግሞ አልጋ ወራሽ ሆነው በተሾሙበት ወቅት በቀልድ አዋቂነታቸውም ተደናቂ የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ፣ በግዞት ወደ ጅማ ተወስደው ነበር።
ይድነቃቸው የተወለደውም በዚህ ወቅት ነበር። ይድነቃቸው እንደማንኛውም የዘመኑ ልጆች እድሜው ለትምህርት ሲደርስ የቄስ ትምህርት ቤት ገብቶ የመጽሐፍ ቅዱስ እና የአማርኛ ቋንቋ ትምህርትን ተምሯል። የፈረንሳይኛ ትምህርትን ደግሞ በአሊያንስ፣ በዳግማዊ ምኒልክና በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤቶች ተከታትሏል።
በወቅቱም ለእግር ኳስ፣ ለብስክሌትና ለሩጫ ስፖርቶች ልዩ ፍቅር ነበረው። ብስክሌቱንና ሩጫውን ባይገፋበትም እግር ኳሱን ግን በተጨዋችነት፣ በአሠልጣኝነትና በኋላም በአመራርነት እስከ ሕይወቱ ፍፃሜ ቀጥሎበት ዛሬም ድረስ ስሙን ማስጠራት የቻለበት ሙያ ሆኖለታል። ገና በስምንት ዓመቱ የትምህርት ቤቱ የሕፃናት እግር ኳስ ቡድንን በአምበልነት እየመራ ተጫውቷል።
በ1924 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴና የስዊድኑ ንጉሥ ልጅ በተገኙበት መድረክ ይድነቃቸውና የትምህርት ቤት ጓደኞቹ የስፖርት ትርዒት አቅርበው ሽልማት ተቀብለዋል።
ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ይድነቃቸው ወደ ኢጣሊያ ሚሲዮን ትምህርት ቤት በመግባት በወቅቱ ለአገር ተወላጆች (ለኢትዮጵያዊያን) ይሰጥ የነበረውን ትምህርት አጠናቋል። ይድነቃቸው በ1928 ዓ.ም ወደ ፈረንሳይ ለመሄድ ከተመረጡት ሁለት ጎበዝ ተማሪዎች መካከል አንዱ በመሆን ዝግጅቱን አጠናቅቆ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያ በፋሺስት ኢጣሊያ በመወረሯ ምክንያት የፈረንሳዩ ጉዞው ሳይሳካ ቀረ።
በስምንት ዓመት እድሜው የስፖርት ዓለም ተሳትፎን የጀመረው ይድነቃቸው፣ በ14 ዓመቱ የአራዳ ልጆች የነበሩት አየለ አትናሽ እና ጆርጅ ዱካስ የመሰረቱትን የዛሬውን ‹‹ቅዱስ ጊዮርጊስ›› የእግር ኳስ ቡድንን ተቀላቀለ። በወቅቱም እነይድነቃቸው ጨዋታዎችን ሲያደርጉ የግብ አግዳሚና ቋሚ እንጨቶችን ተሸክመው በየቦታው ይንከራተቱ ነበር። የግብ አግዳሚና ቋሚዎችን በቋሚነት መትከል ደግሞ የሚሞከር አልነበረም።
ሌላው ሁሉ ይቅርና ‹‹ሳር ታበላሻላችሁ›› በሚል የሚደርስባቸው ተቃውሞ እንኳ ከባድ ነበር። ይድነቃቸው ለ23 ዓመታት ያህል ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተሰልፎ በመጫወት ለክለቡ ለረጅም ዓመታት በመጫወት/ በመሰለፍ እስካሁን ድረስ ባለ ክብረወሰን ነው። ከይድነቃቸው በመቀጠል ለቅዱስ ጊዮርጊሥ ለብዙ ጊዜያት የተጫወተው ለ16 ዓመታት ያህል ቡድኑን ያገለገለው
ዝነኛው ተጫዋች መንግሥቱ ወርቁ ነው።
በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ይታተም የነበረውና ‹‹የሮማ ብርሃን›› የተሰኘው ጋዜጣ በወቅቱ ቅዱስ ጊዮርጊሥ ከስድስት ኪሎ ቡድን ጋር ያደረገውን ጨዋታ በዘገበበት ጽሑፉ የይድነቃቸውን ብቃት እንዲህ ሲል ገልፆት ነበር… «… ነገር ግን ስድስት ኪሎዎች ምንም እንኳ በራቸውን አጠንክረው ይዘው ቢጫወቱም ኳሲቱ ዙራ ዙራ ከዚያው ከይድነቃቸው እግር ገባችና ይድነቃቸው እንደልማዱ ኳሲቱን ይዞ ከፊት ያገኘውን ልጅ ሁሉ እያሳለፈና እያስዘለለ ሲሮጥ ኳሲቱ በገዛ እጅዋ የምትሮጥ እንጂ እሱ በእግሩ የምትነዳ አትመስልም ነበር …» ይድነቃቸው ቅዱስ ጊዮርጊሥ ክለብ በቆየባቸው ዓመታት ከተጨዋችነት በተጨማሪ አሠልጣኝ ሆኖም አገልግሏል። በአንድ የውድድር ዘመን ለክለቡ 43 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። ይህ ስኬትም ይድነቃቸውን እስካሁን ድረስ ባለ ክብረወሰን አድርጎታል።
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ተሰልፎ ተጫውቷል። ይድነቃቸው የተጨዋችነት ዘመኑን ካጠናቀቀ በኋላ ወደ አሠልጣኝነት በመሸጋገር የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንን መርቷል። ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ አንድ ለእናቱ የሆነውን የአፍሪካ ዋንጫዋን (1954) ስታሸንፍ የቡድኑ አሠልጣኝ ይድነቃቸው ነበር።
ኢትዮጵያ ባለ ድል የሆነችበት የሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር የውድድሩ ከፍተኛ/ኮከብ ግብ አስቆጣሪዎችም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበሉ ሉቺያኖ ቫሳሎ እና የግብፁ አብደልፋታህ በደዊ ሲሆኑ እያንዳንዳቸው ሦስት ግቦችን አስቆጥረዋል።
የውድደሩ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ የተመረጠው ደግሞ ዝነኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቹ መንግሥቱ ወርቁ ነበር።
ይድነቃቸው ተሰማ ከተጨዋችነትና ከአሠልጣኝነታቸው ባሻገር ታላላቅ ተግባራትን ያከናወኑትና ታዋቂነትን ያተረፉት የስፖርት ማኅበራትን በማደራጀትና በመምራት ነው። የኢትዮጵያ ስፖርት ጽሕፈት ቤትን አቋቁመው ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በዘመናዊ መልኩ ለማደራጀት ጥረዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሲመሰረትም አስተዋፅኦዋቸው እጅግ የጎላ ነበር።
በወቅቱም የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ ሆነው ተመርጠው ነበር። በ1949 ዓ.ም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) አህጉራዊ ውክልና ኖሮት በዓለም እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (FIFA) ውስጥ እንዲሳተፍ ታቀደ። ኮንፌዴሬሽኑ በየካቲት 1949 ዓ.ም በካርቱም ከተማ ተመሠረተ። በምስረታ ስብሰባው ላይም አቶ ይድነቃቸው ኢትዮጵያን በመወከል ተገኙ።
በወቅቱ የተሻለ አቅም የነበረውን ፌዴሬሽን የመሠረተችው ግብጽ የማህበሩን ጽሕፈት ቤት ወደ ካይሮ ከተማ እንዲዛወር አድርጋ ግብፃዊው ኢንጂኔር አብደልአዚዝ አብደላ ሳሌም የመጀመሪያው የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾሙ።
ከመስራቾቹ በመቀጠልም ደቡብ አፍሪካ እና ሌሎች አገራት ታዳጊውን ተቋም በአባልነት ተቀላቀሉ። ከድርጅቱ ምስረታ ጀርባ የይድነቃቸው ሚና የጎላ ነበር። የኮንፌዴሬሽኑን መተዳደሪያ ደንብ በመቅረጽ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበራቸው። ይድነቃቸው ይህንኑ ኮንፌዴሬሽን፣ እ.አ.አ ከ1964-72 በምክትል ፕሬዚዳንትነት፣ ከ1972-1987 ደግሞ በፕሬዚዳንትነት መርተውታል።
ይድነቃቸው በደቡብ አፍሪካ ይካሄድ በነበረው የአፓርታይድ ስርዓት ላይ በሚያሳዩት ተቃውሞም ይታወቁ ነበር። የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ሲጀመር የደቡብ አፍሪካ እግርኳስ ማህበር ‹‹ … ‹ሁሉም ጥቁር› አልያም ‹ሁሉም ነጭ› የሆኑ ተጫዋቾች እንጂ በምንም አይነት ሁኔታ ‹ከሁለቱም የተዋሀደ› ቡድን ወደ ውድድሩ አልክም …›› ማለቱን ተከትሎ ይድነቃቸውን ጨምሮ ብዙ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች የእኩልነት መብት ተሟጋቾች ደቡብ አፍሪካ ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን እንድትገለል ጫና በማሳደራቸው እ.አ.አ በ1958 ካፍ (CAF) ደቡብ አፍሪካን ከአባልነት አገዳት።
በወቅቱ የይድነቃቸው የሥራ ባልደረባና የካፍ ተወካይ የነበሩት አብድልሐሊም መሐመድ ደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ፖለቲካዊ ስርዓቷን በስፖርት ውስጥ እንዲንሰራፋ በማድረጓ ካፍ ከአባልነት ሲያግዳት በይድነቃቸው የማያወላውል ጽኑ አቋም ምክንያት እንደነበር መስክረዋል።
ከቅኝ ግዛት ተላቅቀው ነፃነታቸውን የሚጎናፀፉ የአፍሪካና እስያ አገራት ቁጥር መጨመር ዘረኝነትን የተከተለ አሠራርን የሚተገብሩ አገራት ከዓለም አቀፉም ሆነ ከአህጉራዊ ማኅበራት እንዲታገዱ ጫና ማሳደሩን አጠናከረው።
ይህም በወቅቱ ለዘረኛ አሠራሮች ጥብቅና ቆመው የነበሩ የፊፋ (FIFA) አመራሮችን ከፍተኛ ጫና ውስጥ ከተታቸው። ከአፍሪካ፣ እስያ፣ ደቡብ አሜሪካ እና ሶቭየት ኅብረት በተገኘ ሰፊ ድጋፍና በጊዜው የካፍ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ይድነቃቸው መሪነት የፊፋ ምክር ቤት ደቡብ አፍሪካ ላይ በድጋሚ የእገዳ ውሳኔ አሳለፈ። በዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ የነበረው የአፍሪካዊያን ኮታ እንዲስተካከል እነ አቶ ይድነቃቸው በፅናት መከራከራቸውንም ቀጠሉ።
የወቅቱ የፊፋ ፕሬዚዳንት የነበሩት ስታንሊ ሮውስ ‹‹ … ብዙ ሰዎች ተጨባጭ ያልሆነ ሀሳብ እንደሆነ ያምናሉ። ለምሳሌ እንደ እንግሊዝ ያለች እግር ኳስ የተጀመረባትና ምስረታውን ያደራጀች አገር ወይም ደግሞ ሰፊ ልምድ ያላቸው፣ በፊፋ ምስረታ ወቅት ትልቅ ድርሻ የነበራቸው፤ እንዲሁም በዓለም እግር ኳስ ጉዳዮች ላይ በሚነሱ ችግሮች ተጽእኖ የሚያሳድሩ ጣልያንና ፈረንሳይን የመሳሰሉት አገሮች ከአፍሪካና እስያ ከሚመጡ አገሮች ጋር እኩል ድምፅ የመስጠት መብት መኖር የለበትም …›› ብለው አስተያየት ሰጡ።
አቶ ይድነቀቻውም በዚህ የሮውስ የማን አለብኝነት አመለካከት ተገርመው ‹‹… ምንም እንኳ ለፊፋ መመስረት የተወሰኑ አህጉራት በተቋሙ የእድገት ሒደት ውስጥ በሀሳብ፣ በቁሳቁስና በገንዘብ ረገድ ያበረከቱትን የተሻለ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ብንረዳም እኛ የምንጠብቀው ግን ተቋሙ አለማቀፋዊ ድርጅት የመሆኑን ያህል በዴሞክራሲያዊ አሠራር የሁሉንም አባል አገራት መብቶች በተመሳሳይ ሁኔታ የሚያስከብር እንዲሆን ነው።
ስለዚህም አሠራሩ በህጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ የዓለም እግር ኳስን ጥቅምና አንድነትን በዘላቂነት የሚከተል፤ እንዲሁም በፊፋ ወስጥ ያሉት አባላት በሚያድግ ሚዛናዊ ውክልና እንዲሳተፉ መደረግ አለበት …›› ሲሉ ሞገቱ። አቶ ይድነቃቸው ለ‹‹አንድ አገር-አንድ ድምጽ›› መርህ ከመታገላቸውና ስኬታማ ከመሆናቸውም በላይ በሮውስ አመራር የዓለም ዋንጫ አውሮፓን ማዕከል ባደረገው ንፍቀክበብ ብቻ ተወስኖ እንዳይዘልቅና ለሌሎች አህጉራትም እንዲዳረስ ረጃጅምና ተከታታይ የደብዳቤ ግንኙነቶችን ከሮውስ ጋር በማድረግ አፍሪካ የቀጥታ ተሳትፎ ኮታ ኖሯት እግር ኳሷ እንዲበረታታና እንዲያድግ ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል። በዚህም ስኬታማ ነበሩ።
የአፍሪካን እግር ኳስ ጥቅምና ፍላጎት በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስጠበቅ ረገድ የአቶ ይድነቃቸው ሚና እየጎለበተ ሄዶ ኃላፊነታቸውም ጨመረ። እ.አ.አ በ1966 ዓ.ም. የፊፋ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል፣ በ1967 የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ፤ እንዲሁም በ1972 ዓ.ም የካፍ ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾሙ።
በአንደበተ ርቱዕነታቸው የሚታወቁት አቶ ይድነቃቸው ከጥሩ አማርኛ ተናጋሪነታቸው በተጨማሪ እንግሊዘኛን፣ ፈረንሳይኛን እና ጣልያንኛን በጥሩ ሁኔታ መናገር መቻላቸው በዓለም አቀፍ ስፖርት አስተዳደር መድረኮች ውስጥ ያለውን ውስብስቡን ፖለቲካ በአፍሪካ የእንግሊዘኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ተናጋሪ ማዕዘናት በተሟላ ክሂሎት ለማሰስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቶላቸዋል።
እ.አ.አ በ1974 ብራዚላዊው ዥያን-ማሪ ፎስቲን ጎድፍሮይድ ጆኣዎ ዴ ሀቨላንጅ (‹‹ጆ ሀቨላንጅ››) የፊፋ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ። ወቅቱ አቶ ይድነቃቸው የካፍ ፕሬዚዳንት ሆነው ማገልገል የጀመሩበት ጊዜ ነበር።
አፍሪካም በ1960ዎቹ ስትታገልላቸው ለነበሩት አላማዎቿ ግልጽ ድጋፍ የሚያደርግ የእግር ኳስ መሪን እ.አ.አ በ1970ዎቹ አጋማሽ አገኘች። ካፍ ቀደም ሲል ከፊፋ ጋር ባለመስማማቱ ይፈጠሩ የነበሩ ከውድድሮች ራስን የማግለል እና ከባለሥልጣናቱ ጋር የሚደረጉ እልህ አስጨራሽ ትግሎች ቀርተው የአፍሪካን ግቦች ማሳካት ተጀመረ።
እ.አ.አ በ1974 በፍራንክፈርት በተካሄደው የፊፋ ስብሰባ ላይ የጎሳ፣ የዘር እና የሐይማኖት መድልዎን በአገሩ ውስጥ የሚያሰፍን ማንኛውም የፊፋ አባል አገር ከዚህ ድርጊቱ የማይታቀብ ከሆነ ፈጣን የእገዳ ውሳኔ እንዲተላለፍበት ካፍ ሐሳብ አቀረበ።
ደቡብ አፍሪካም ከፊፋ አባልነቷ ተባረረች። በዓለም ዋንጫ የሚሳተፉ የአፍሪካ ተወካዮች ቁጥርም አደገ። አቶ ይድነቃቸው በካፍና በፊፋ ውስጥ ከነበራቸው የሥራ ኃላፊነት በተጨማሪ የአፍሪካ ስፖርት ኮንፌዴሬሽኖች ኅብረት ፕሬዚዳንት፣ የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች የክብር ፕሬዚዳንት እንዲሁም የአፍሪካ ስፖርት ጠቅላይ ምክር ቤት እና የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (IOC) አባል ሆነውም አገልግለዋል።
ከሦስት አሥርት ዓመታት በፊት ጋዜጠኞች ለወቅቱ የፊፋ ፕሬዚዳንት ጆ ሀቨላንጅ ‹‹ከእርስዎ በኋላ የፊፋ ፕሬዚዳንት ማን ይሆናል? እርስዎን የሚተካው ማነው?›› ብለው ሲጠይቋቸው ባጭር ቋንቋ ‹‹ሚስተር ተሰማ ነዋ!›› በማለት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ለቦታው እንደሚመጥኑ ተናግረው ነበር።
ሃቨላንጅ ያለምክንያት አልነበረም እኚህን ታላቅ አፍሪካዊ የስፖርትና የኦሊምፒክ ግንባር ቀደም መሪን ለትልቁ የኃላፊነት ቦታ ያጯቸው። አቶ ይድነቃቸው የኢትዮጵያን ዘመናዊ ስፖርት ያደራጁ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ትክክለኛ መስመር ያስያዙ፣ ለአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም ለብሔራዊ ኢሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር ህልውና የተጉ፣ ልዩ ልዩ ሕጎችንና መተዳደሪያ ደንቦችን በአማርኛ ያዘጋጁና ለአፍሪካም የተረፉ ታላቅ ሰው ናቸው።
አቶ ይድነቃቸው ተሰማ፣ ዘርንና ሀይማኖትን መሠረት ያደረገን የስፖርት ክለቦች አደረጃጀትን በጥብቅ ያወግዙና ይቃወሙ ነበር። ከዚህ ባሻገር በስፖርታዊ ክንውኖች ወቅት የሲጋራና የአልኮል ምርቶች በስታዲየሞች አካባቢዎች እንዳይተዋወቁ በፅናት ይከራከሩም ነበር።
ታዲያ ሃቨላንጅ ያኔ አቶ ይድነቃቸውን ለፊፋ ፕሬዚዳንትነት ሲያስቧቸው ለጥቆማቸው አክብሮታቸውን የገለፁት ታላቁ ኢትዮጵያዊ፣ በጤና እክል ምክንያት እጩነቱን ለመቀበል እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።
የበርካታ ሪከርዶች ባለቤት የሆኑት አቶ ይድነቃቸው፤ ከውጭ አገራት መንግሥታት ሳይቀር ብዙ ዋንጫዎችን፣ ሜዳሊያዎችንና ሌሎች ሽልማቶችን አግኝተዋል። በእርግጥ አቶ ይድነቃቸው የአፍሪካ እግር ኳስ የወደፊት አቅጣጫን በሚመለከት ከፍተኛ የሆነ ሀሳብ ነበራቸው።
እ.አ.አ በ1974 ዓ.ም በተካሄደው የካፍ ስብሰባ ላይ ‹‹ … በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ አፍሪካ አንድ እና የማትከፋፈል መሆኗን በማረጋገጥ፣ የአፍሪካን አንድነት ለማስጠበቅ በጋራ እንድንሰራ፣ በእግር ኳሳችን እና በአጠቃላይ የኑሮ ገጽታችን ላይ የተንሰራፋውን ባዕድ አምልኮ፣ ጎሰኝነትና ሌሎች የምንገለልባቸውን ነገሮች በሙሉ እንድናወግዝ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ …›› በማለት ተናግረው ነበር።
ከኢትዮጵያም አልፈው የአፍሪካ የስፖርት አባት በመባል የሚታወቁት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ነሐሴ 13 ቀን 1979 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
አቶ ይድነቃቸው በረጅሙ የማስተዳደር ሥራ ዘመናቸው የሚታወሱት በሜዳ ውስጥም ሆነ ከሜዳ ውጪ ፍትህን ለማስፈን በጽናት ባካሄዱት ትግል ነው። ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ አስተዳደር ስልታቸውም በልዩነት የሚጠቀስ ሆኖ የሚኖር ነው።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥር 18/2014