ከሃያ ሁለት ዓመታት በፊት ሲጀመር የኢትዮጵያን የማህበረሰብ አቀፍ ስፖርት ለማነቃቃትና የጎዳና ላይ ውድድሮችን ባህል ለማዳበር ነበር። ዛሬ ላይ ግን ከጎዳና ላይ የሩጫ ውድድርነት አልፎ ለአገር እያበረከተ ያለው ውለታ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ።
በኢትዮጵያ ጀግናና የቁርጥ ቀን ልጅ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ መስራችነት የተጀመረው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ዋናውንና በአዲስ አበባ በየዓመቱ የሚካሄደውን የአሥር ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች በሚያዘጋጃቸው መሰል ውድድሮች አገርን በታላላቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች ማስጠራት የቻሉ ብርቅዬ አትሌቶችን ፈልፍሎ በማውጣት ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ያበረከተውን አስተዋፅኦ የማይገነዘበው አይኖርም።
ከዚህ ጎን ለጎን ከውድድሩ ከሚገኘው ገቢ ቀንሶ ለረድዔት ተቋማት ማቋደሱም አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው እውነታ ነው፡፡ አልፎ ተርፎም የስፖርት ቱሪዝምን በኢትዮጵያ በማነቃቃት የተጫወተው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ከአገር ውስጥ ስመጥር አትሌቶች ባሻገር የሌሎች አገራት ከዋክብት አትሌቶች በተወዳዳሪነትም ይሁን በተጋባዥነት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አድማቂ ከመሆን አልፈው ውድድሩ አንድ የቱሪስት መስህብ እንዲሆን ማስቻሉ ነጋሪ አያሻውም። ይህም በአፍሪካ ትልቁ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር እንዲሆን ከማስቻሉም በላይ በዓለም ታላላቅ ከሚባሉ አሥር የጎዳና ላይ ውድድሮች አንዱ ሆኖ እንዲመረጥ አድርጎታል።
ይህ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ባለፉት በርካታ ዓመታት ለኢትዮጵያ ካበረከተው መልካም ነገር ጥቂቱና ሁሉም የሚያውቀው ነው። ዛሬ ግን ይህ ታላቅ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ከዚህ ቀደም በተለየ መልኩ ለአገር አንድ ውለታ ውሏል። ኢትዮጵያ ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር ተገዳ በገባችበት ጦርነት ከዲፕሎማሲው ጋር በተያያዘ ፈተና እንደ ገጠማት ይታወቃል።
አሜሪካን ጨምሮ በርካቶቹ የምዕራባውያን አገራትም ያላቸውን የፈረጠመ የገንዘብ አቅም እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነት ያላቸው መገናኛ ብዙሃኖቻቸውን ተጠቅመው የኢትዮጵያን ስምና ገፅታ በማጠልሸት አሁንም ድረስ እየሰሩ ናቸው።
በተለይም እነዚህ አገራት ኢትዮጵያ ሰላሟ በእጅጉ የተናጋና የጦርነት ቀጠና እንደሆነች አስመስለው የአፍሪካ መዲና ከሆነችው አዲስ አበባ ጭምር ዜጎቻቸውን ለማስወጣት ሲጥሩ እንደነበር አይዘነጋም።
ይህም የተሳሳተ መረጃ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት በሚያስቡ የሌሎች አገራት ዜጎችና ቱሪስቶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ግልፅ ነው። የሌሎች አገራት ዜጎችና ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት አገሪቱ ሰላም መሆኗንና ለደህንነታቸው የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ በተለያያ ዘዴ ሊያጣሩ ይችላሉ።
ከነዚህም ዘዴዎች አንዱ የአደባባይ በዓሎች ሲሆኑ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዚህ ረገድ የሚጫወተው ሚና የተለየ ቦታ ይሰጠዋል።
ይህንን ሚናውንም ከትናንት በስቲያ በአግባቡ ተወጥቶ በተግባር ማሳየት ችሏል። መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ያደረገው ሃያ አንደኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከትናንት በስቲያ ሲካሄድ በኢትዮጵያ መገለጫ አረንጓዴ፣ቢጫና ቀይ የመሮጫ ካኒቴራዎች ያሸበረቁ ሃያ አምስት ሺህ ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ ምዕራባውያን እንደሚያሟርቱት ሰላም ያጣች የጦርነት ቀጠና እንዳልሆነች አስመስክረዋል።
ከፀጥታ ስጋት ጋር በተያያዘ ስሟን በማጉደፍ በቅርቡ በመዲናዋ የሚካሄደውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔን እንድትነጠቅ የሚንቀዠቀዡ አካላትም እጃቸውና አፋቸውን እንዲሰበስቡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከትናንት በስቲያ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያስተላለፈው መልዕክት ትልቅ ነው። ለዚህም በአገሪቱ ሰላም እንደሌለ ለሌሎች ለማሳመን ዘወትር ጥረት የሚያደርጉት ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጭምር እየመረራቸውም ቢሆን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሰላም ተካሂዶ መጠናቀቁን ለመዘገብ እንደተገደዱ ማየት ይቻላል።
በውድድሩ ተካፋይ የነበሩ በርካታ የውጪ አገር ዜጎችም በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎቻቸው በታላቁ ሩጫ ሲደሰቱና ሲዝናኑ እንጂ አንዳች እንከን ገጠመን ብለው ያስተላለፉት መልዕክትና የለጠፉት ፎቶ ግራፍ የለም። ይህም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አገር የዲፕሎማሲ ችግር ውስጥ በገባችበት ወቅት ራሱን ችሎ ትልቅ የገፅታ ግንባታና የማይተመን የዲፕሎማሲ ስኬት እንዳስመዘገበ ሊያስቆጥረው ይችላል።
ከዚህ ቀደም በመሪዎች ደረጃ ባልተለመደ መልኩም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ትኩረት ሰጥተው መልዕክት እንዲያስተላልፉ ያደረጋቸው ታላቁ ሩጫ ከስፖርታዊ ኩነትነቱ አልፎ በሰላም፣ በአንድነት፣ በወንድማማችነት እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ እንዲሁም የኢትዮጵያ መገለጫ መሆኑ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በማህበራዊ ገፃቸው ከትናንት በስቲያ ባስተላለፉት መልዕክት ‹‹ባለፉት ሃያ ዓመታት ታላቁ ሩጫ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ማሰባሰብ ችሏል፤ በዓመት አንዴ ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ አብሮነት ልባቸውን እንዲሰጡ አድርጓል። በሐይማኖታዊ በዓላት አብረው መሆን ያልቻሉ ዜጎች በታላቁ ሩጫ ተቃቅፈው ይሮጣሉ፤ በብሔረሰባዊ መሰባሰቦች አንድ ላይ መሆን ያልቻሉ ሕዝቦች ታላቁ ሩጫን ጠብቀው ይገናኛሉ።›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
‹‹ ኃይሌን በታላቁ ሩጫ ስናመሰግነው ዝግጅቱ ለአትሌቲክስ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ አኳያ ብቻ ሳይሆን፥ ኢትዮጵያዊ መሰባሰብን፣ ኢትዮጵያዊ ትስስርን፣ ኢትዮጵያዊ መቀራረብን የምንፈጥርበት፤ በብሔር፣ በቋንቋና በሐይማኖት የማንታጠርበት፣ የሁላችንም የሆነ ታላቅ ዝግጅትን ስላስጀመረልን ጭምር ነው›› ብለዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 17/2014