አንዳንዴ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑና ሊነጣጠሉ የማይችሉ ጉዳዮች፣ ወይም አካላት ሲነጣጠሉ ይታያሉ። ከእነሱም ሁለቱ ትምህርት ቤት እና ቤተ መጻሕፍት ናቸው። እነዚህ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ የሆኑ አካላት በምንም መንገድ ሊለያዩ የሚችሉ፤ እንዱ ካለ አንዱ ሊቆም የሚችል አይደለም።
በመሆኑም ሁለቱ እኩል ተፈላላጊዎች ናቸው። እንደ መነሻ ከታሪክ እንጀምር። ከታሪክ አኳያ «በአራተኛው ክፍለ ዘመን ዓክልበ. የመጀመሪያው የግሪክ ክፍት ቤተ መጻሕፍት ተብሎ የሚጠራው በሄርኩለስ ተከፈተ።
በሦስተኛው ክፍለ ዘመን ዓክልበ. የጥንት መጻሕፍት ትልቅ ማዕከል ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባውን አሌክሳንድሪያን መሠረተ።» «ቤተ-መጻሕፍት ምን እንደሆኑ እና ያለ እነርሱ ምንም ማድረግ እንደማይቻል» የሚያስረዳ አንድ ጽሑፍ ውስጥ ደግሞ፤ «የቤተ-መጻሕፍት ባህል ታሪክ የኅብረተሰብ ታሪክ እና ባህል አካል ነው።
በዓለም ላይ በጣም ጥንታዊ የሆኑት ቤተ-መጻሕፍት የሱመር ሥነ-ጽሑፍ የመጀመሪያዎቹ የሸክላ ካታሎጎች፣ የአሹርባኒፓል ቤተ መጻሕፍት፣ በግብፅ ውስጥ ያለው የኢድፉ ቤተ መቅደስ ቤተ መጻሕፍት ነበሩ።
በአቴንስ ውስጥ ትላልቅ የግል ቤተመጻሕፍት በዩሪፒድስ፣ ፕላቶ፣ አሪስቶትል፣ ዴሞስቴንስ፣ ዩክሊድ፣ ዩቲዴመስ የተያዙ ነበሩ። የመጀመሪያው የሕዝብ የግሪክ ቤተ መጻሕፍት በአቴንስ በፓሲስትራተስ ተመሠረተ። የዓለም ስምንተኛው ድንቅ – የአሌክሳንድሪያ ቤተ መጻሕፍት – ከ700,000 በላይ በእጅ የተፃፉ መጻሕፍትን ያካተተ ነበር» የሚል ሰፍሮ እናገኛለን። ወደ እኛም ስንመጣ አፄ ቴዎድሮስ ዘመናዊ ቤተ መጻሕፍት ማደራጀታቸውን፤ የተጀመረውም በእሳቸው ዘመነ መንግሥት መሆኑን ከታሪክ እንረዳለን። እንዲህ እንዲህ እያልን መሄድ እንችላለን። ግን የዚህ ጽሑፍ ዐቢይ አላማ የቤተ መጻሕፍትን ታሪካዊ አመጣጥ ማጥናት ባለመሆኑ ወደ እዚያ ጎራ አንልም።
አሁን ባለው ሁኔታ በአፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ አስር ቤተ መጻሕፍት አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት አብርኈት ቤተ መጻሕፍት በአራት ወለሎች ተከፍሎ በውስጡ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን መጻሕፍት የሚይዝ መደርደርያ የተገጠመለት፤ ከ240ሺህ በላይ የሚሆኑ ወረቀት አልባ መጻሕፍትና 300ሺህ ጥናታዊ ጽሑፎች የያዘ፤ የሕፃናት ማንበብያ ስፍራን ጨምሮ የአይነ ስውራን ማንበቢያ ቦታና የብሬል መጻሕፍት የሚገኙበት፤ አምፊ ትያትር እና መጫዎቻ ስፍራዎች፤ እንዲሁም ከ120 በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ መመገቢያ ካፌ፣ ስምንት የመጻሕፍትና ተጓዳኝ አገልግሎት መስጫ ሱቆች የሚገኙበት አዲሱ ቤተ መጻሕፍት ይገነባና ይደራጅ ዘንድ ያስፈለገው ከተማ ለማድመቅ ሳይሆን አንድ እራሱን የቻለ የእውቀት ምንጭ በመሆኑ ነው። በመሆኑም አገራችን አንድ አውራ ቤተ መጻሕፍት አፈራች ማለት ነው።
ሌላስ? በሌላ በኩል «ዓለማ’ቀፍ ዲጂታል ቤተ መጻሕፍትን ለመክፈት ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ አገር ሆና ተመርጣለች» ሲል የአማራ ክልል መገናኛ ብዙኃን (ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲን ጠቅሶ ባቀረበው) ዜና (ሚያዝያ 17/2010 ዓ.ም)እና በዜናው ስር «ቤተ መጻሕፍቱ በሰባት የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የተዘጋጁ የተለያዩ መጻሕፍት እንዲሁም ለእረፍት ጊዜ ንባብ የሚሆኑና በሦስት የአፍሪካ ቋንቋዎች የተፃፉ የታሪክ መጻሕፍት ይኖሩታል። በአሜሪካ፣ ኖርዌይ፣ እንግሊዝና ሌሎች አገራት ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው ዓለማ’ቀፉ ጥምረት በኢትዮጵያ የሚከፍተው ይኸው ቤተ መጻሕፍት ሕፃናትና ወጣቶች ደረጃቸውን የጠበቁ መጻሕፍት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።
በኢትዮጵያ የተመረጡት ሰባቱ ቋንቋዎች አማርኛ፣ ትግርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ሶማሊኛ፣ ሲዳምኛ፣ ወላይትኛ እና ሀዲይኛ መሆናቸው ታውቋል፡ ፡» በሚል የሰፈረውን ማንበብም ለአገራችን አንድ እርምጃ ወደ ፊት መሄድ አንድ ማሳያ ነው። እዚህ ብቻ አይደለም። አሜሪካ የሚኖሩ
ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ መረጃ … እንዳይርቁ በማሰብ እዚያው አሜሪካ «ዲ.ሲ. የሕዝብ መጻሕፍት ቤት» ተከፍቶ ቀልጣፋ አገልግሎት ይሰጣል። «ቀልጣፋ» እንል ዘንድ ያስገደደን ደግሞ «በዋሽንግተን ዲ.ሲ. የሚኖሩ፣ የሚሠሩ ወይም የሚማሩ ከሆነ የዲ.ሲ. የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ካርድ በማንኛውም ቦታ ወይም በdclibrary.org ማግኘት ይችላሉ። በተጨማሪም ካርዱን በሚከተሉት ግዛቶች ወይም ከተሞች፣ አሌክሳንድርያ፣ አርሊንግተን፣ ፌር ፋክስ፣ ፍሬድሪክ፣ ላውደን፣ ሞንትጋሞሪ፣ ፕሪንስ ጆርጅስ ወይም ፕሪንስ ዊልያም ማግኘት ይችላሉ።» የሚለው ሲሆን፤ በስሩም 25 የሰፈር ቤተመጻሕፍት እና ማዕከላዊ ቤተመጻሕፍት ይገኛሉ።
በቤተ መጻሕፍቱ ንባብን የሚያበረታቱ፣ ዲጂታል ዜግነት፣ ጠንካራ ማህበረሰቦች፣ የአካባቢ ታሪክ እና ባህልን የሚያበረታቱ አገልግሎቶች፣ መጣጥፎች እና መርሀ-ግብሮችን ለወጣቶች እና ለአዋቂዎች የDCPL ድጋፍ ይሰጣል። የቤተመጻሕፍት አካባቢዎች ነፃ ዋይፋይ፣ ነፃ የኮምፒዩተር፣ የፕሪንተር አገልግሎቶች፣ የማህበረሰብ መሰብሰቢያ ክፍል ቦታዎች እና የመጻሕፍት፣ መጽሔት፣ ጋዜጣዎች፣ ዲቪዲዎች እና ተጨማሪ ነገሮች የሚሰጡ ስለመሆኑ ሁሉ ከይፋዊ ድረ ገፁ መረዳት ይቻላል። ይህንን ሁሉ እዚህ መደርደር ያስፈለገው እኛ የቱ ጋር ነው ያለነው? ብለን እንድንጠይቅና እራሳችንን እንድንፈትሽ በማሰብ ነው።
ምናልባት ቢያስፏጨው … እንዲል ገጣሚው። እየተነጋገርንበት ካለነው ርእሰ ጉዳይ አኳያ «ለመሆኑ እኛ የት ጋር ነው ያለነው?» የሚለውን ፈታኝ ጥያቄ አንስተን እንወያይ ብንል ደስ ባለን ነበር። ያን ማድረግ ባለመቻሉ ተገቢ ምንጮችን ጠቅሰን አንዳንድ ሀሳቦችን እናንሳ። ትምህርት ሚኒስቴር በዚህ ባለፈው ወር መገባደጃ ላይ ሰፋ ያለና የወቅቱን የትምህርት ተቋማትን ወቅታዊ ይዞታ የሚመለከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶ ነበር። ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ ከሰጡት መግለጫ መረዳት የተቻለውም አሁን ካሉት የትምህርት ተቋማት ደረጃቸውን የጠበቁ የማግኘቱ ጉዳይ የነጠፈ መሆኑን ነው።
መግለጫው እንዲህ ያሰፍረዋል፤ «በኢትዮጵያ 48 ሺህ ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም ደረጃቸውን የጠበቁት 0 ነጥብ 01 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው። በአጠቃላይም ስድስት ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው ደረጃ አራት ላይ የሚገኙት። እነሱም ቢሆኑ የሚያስተምሯቸው ልጆች 12ኛ ክፍልን ሳይፈተኑ ነው ወደ ውጭ አገራት ለመሄድ ልባቸው የሚነሳሳው። ስለዚህም ኢትዮጵያ ደረጃቸውን የጠበቁ የአካልና የአዕምሮ ማበልጸጊያ ትምህርት ቤቶች ያስፈልጓታል። […] 99 በመቶዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች የሚማሩት ከደረጃቸው በታች በሆኑና በምንም ዓይነት መስፈርት ትምህርት ቤት ሊያሰኛቸው የሚችል ደረጃ በሌላቸው ተቋማት ውስጥ ነው። በእንደዚህ ዓይነት ተቋማት ውስጥ የተማሩ ወጣቶች መጨረሻቸው ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም።
ስለዚህም ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች እንዲኖሩንና ሕፃናት አስፈላጊውን የአካልና የአዕምሮ ማዳበሪያ እንዲያገኙ ማድረግ ከእኛ ይጠበቃል። ለዚህም በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችል ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶችን እንደ አዲስ መገንባት» ያስፈልጋል። በቃ፣ ይሄው ነው። ከዚህ የሚኒስትሩ መግለጫ ተነስቶ በየተቋማቱ ያሉና የሌሉ፤ ያሟሉና ያላሟሉ ወዘተ ቤተ መጻሕፍትን መረዳት ለማንም አይከብድምና በዚሁ እንለፈው። ታኅሣሥ 14 ቀን 2014 አ.ም በሆቴል ዴሊ ኦፖል የተካሄደን የሙያና ቴክኒክ ትምህርት ዘርፉን የገመገመ፤ የተሻለ ሥራ አፈፃፀም ላሳዩትም እውቅና የሰጠ መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር።
በመድረኩም የተለያዩ ጥናቶች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፣ በጥናቶቹም ከተነሱት አንዱ በየተቋማቱ ያሉት ቤተ መጻሕፍት ጉዳይ ነበር። በጥናቶቹ ላይ እንደ ተገለፀው አንድ ትምህርት ቤት ቤተመጻሕፍት ሊኖረው ይገባል የሚለው አይደለም ዋናው ነገር፤ ይህ የታወቀና ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ለውይይት የሚቀርብ አይደለምና ነው።
በጥናቶቹ እንደተገለፀው አንድ የትምህርት ተቋም ቤተ መጻሕፍት ቢያንስ የተቋሙን ማህበረሰብ 25 በመቶውን በአንድ ጊዜ መያዝ መቻል አለበት። ይህን መያዝ ያልቻለ ቤተ መጻሕፍት እንዳለ አይቆጠርምና ከደረጃ በታች በመሆኑ ተቋሙን ሳይቀር ይዞ ሊሰናበት ይችላል። እዚህ ላይ አንድ ጉዳይን ልብ ማለት ያስፈልጋል። እሱም ቤተ መጻሕፍት የሚያስፈልጉት ለትምህርት ተቋማትና ተማሪዎች ብቻ እንዳልሆነ፤ ቤተ መጻሕፍት የማያስፈልገው ሰው እንደሌለ ልብ ማለት ተገቢ ነው።
ጥናቱ ይህን ይበል እንጂ ከነ አካቴውም እንኳን ቤተ መጻሕፍቱ ቃሉም በግቢያቸው የሌላቸው ተቋማት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። መድረኩን ያዘጋጀው አዲስ አበባ መስተዳድር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን እንደገለፀውም ደረጃቸው ከ40 በመቶ በታች የሆኑ ኮሌጆች በቀጥታ እንዲዘጉ ተወስኗል።
ይህ የተረጋገጠና ከግለሰብ አስተያየት የፀዳ መረጃ በመሆኑ እዚህ ተጠቀምንበት እንጂ የየግል ምልከታና ትዝብታችንን እናክልበት ብንል እንደ አገር ያለንበት ሁኔታና ይዞታ እሚያሳፍር ነው የሚሆነው። ሁሉ ነገር የጨበጣ በሆነበት፣ ሱፐርቫይዘር ሲመጣ ከአንዱ ኮሌጅ ወደ ሌላው መጻሕፍት እየተጫኑ የሚዘዋወሩበት ወዘተ አሠራር ሁሉ እንደነበር አይተናል፤ ሰምተናልም። ተማሪዎች «ገንዘብ አዋጡና ከእንቶኔ ቤተ መጻሕፍት የተለያዩ መጻሕፍትን ፎቶ ኮፒ እናደርግላችሁና እቤታችሁ ታነባላችሁ።» ይል የነበረ ኮሌጅ መሀል ፒያሳ እንደነበር ይህ ፀሐፊ አሳምሮ ያውቃል።
አንድ ሳይፈቀድለት ናዝሬት ላይ ካምፓስ የከፈተ ሀብታም ባለ ኮሌጅ የሱፐር ቪዥን ባለሙያዎች እንደሚመጡ ሲነገረው አዲስ አበባ ካለው ካምፓስ መጻሕፍት አጓጉዙ የናዝሬቱን «ቼክ ፖይንት» እንዳለፈና ከአመታት በኋላ እንደተነቃበት (እርምጃ ይወሰድ አይወሰድ አላውቅም) የአንድ ሰሞን የመገናኛ ብዙኃን የዜና ርእስ ነበር።
እዚህ አገር በእውቀትና ትውልድ ላይ እዚህ ድረስ ነው የሚቀለደው። ከኢፌዴሪ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው «ዕውቀትን ሊያስገኙ የሚችሉ ሃብቶች» ተብለው ከተዘረዘሩት 1ኛው (በተቋማት ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉ ሃብቶች) እና 3ኛው (የተለያዩ ጽንሰ ሀሳብ ያላቸው መጻሕፍት) ሁሉንም ተቋማት የሚመለከቱ ቢሆንም በተለይ የትምህርት ተቋማትን፤ በተለይም ቤተ መጻሕፍትን በቀጥታ የሚመለከቱ ናቸው፤ ጉዳዩ የዋዛ አይደለም።
ኮሚሽኑ ከአዲስ ዘመን ጋር በትብብር በሚያዘጋጀው ጽሑፍ «የዕውቀት ሥራ አመራር ሥርዓት» በሚል ርእስ ስር በርካታ ጽሑፎችን ማስነበቡን የሚገልፅ ሲሆን ለዛሬ በጠቀስነው ጽሑፍ ግን የበለጠ ክብደት ተሰጥቷቸው የተገኙት፤ በዕውቀት ሥራ አመራር ዙሪያ የተቋሙን ነባራዊ ሁኔታ ግምገማ ማካሄድ፣ ዕውቀትን መፍጠርና ማደራጀት፣ የዕውቀት ኦዲት ትንተና ማካሄድ (በተቋሙ ምን ዕውቀት አለ?፣ ምን ዕውቀት ይጎድላል?፣ ዕውቀቱን የሚፈልገው ማነው?፣ ዕውቀቱ እንዴት ይጠቅማል?)፣ ዕውቀት የሚደራጅበትን ተግባር ማከናወን፣ የዕውቀት ሥራ አመራር አደረጃጀትን መፍጠር እና የመሳሰሉት ናቸው። እንደተቋሙ ብያኔ እውቀት ይሸጋገራል።
ሽግግሩም በሁለት (ውስጣዊ እና ውጫዊ) የሚከፈል ሲሆን፤ «ውስጣዊ ዕውቀትን ወደ ውጫዊ ዕውቀት መቀየር / Externalization/ ይህ ማለት፣ በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ያለን ዕውቀት በማውጣትና ውጫዊ ዕውቀት በማድረግ፣ አደራጅቶ ሌሎችም እንዲጠቀሙበት ማስቻል ነው።» ከላይ ያሰፈርነውን ምን ያህል ከቤተ መጻሕፍት ጋር አያይዞ መተርጎም እንደተቻለ ባናውቅም አንድ የማይካድ እውነት ቢኖር ጉዳዩ በቀጥታ የተያያዘ መሆኑ ነው። (ለነገሩ ስለ ቤተ መጻሕፍት አነሳን እንጂ የአሁኑ ዘመን ትምህርት ቤቶች «ምሳ መመገቢያ» ታዛ እንጂ የስፖርት ማዝወተሪያስ አላቸው እንዴ??) በአንድ ወቅት ሰርጌቪች የተባሉ ሩሲያዊ እንደተናገሩት ምንም እንኳን የትምህርት ተቋማት ቢጠፉም የመጽሐፍ ማከማቻዎች በትክክል ከተደራጁ ባህሉ በእውነቱ ሊታደስ ይችላል።
የቤተ መጻሕፍት አስፈላጊነት የት ድረስ እንደሆነ ያመላከተ ነውና ለጥቅስ ቢበቃ አይገርምም። ባጠቃላይ፣ የቤተ መጻሕፍትን አስፈላጊነት ያልተገነዘበ ሰው አለ ለማለት ይቸግራል።
ይሁን እንጂ ያውቃሉ የተባሉትም እሚሠሩትን ያውቁታል ለማለት እያስቸገረ ይገኛል። ዘመኑ በየፎቁ ላይ ኮሌጅ፣ ዩኒቨርሲቲ … መክፈት ሙዝ ልጦ የመግመጥ ያህል የቀለለበት ጊዜ ነው። ባጭሩ የትምህርት ተቋማትን ያለ ቤተ መጻሕፍት ማሰብ ዓሣን ከባሕር ውጪ በሕይወት እንዲኖር የመመኘት ያህል ቂልነት ነውና እውቀትን የማደራጀት ሥራ ቢሠራ፤ ለመጪው ትውልድም (ያለፈውማ አልፏል) ቢታሰብለት ለማለት ነው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጥር 16/2014