ኢትዮጵያ ሶስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ራሷ አሰናድታ ያስቀረችው ከዛሬ ስልሳ ዓመት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 13 ቀን 1954 ዓ.ም ነበር። የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተመሰረተው በ1949 ዓ.ም የካቲት ወር ላይ ነው። መስራቾቹም ግብጽ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ ነበሩ። በወቅቱ ኢትዮጵያን በመወከል በስብሰባው ላይ ታድመው የነበሩት የኢትዮጵያ ስፖርት አባት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ እና ሌተናል ኮሎኔል ገበየው ዱቤ ነበሩ። ፌዴሬሽኑ በተመሰረተበት ዓመት በሱዳን በተካሄደው የመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ አትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ተሳታፊዎች ነበሩ።
ከመስራቾቹ አንዷ የነበረችው ኢትዮጵያ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ዋንጫውን ከፍ ማድረግ ከቻሉት አገሮች ተርታ ትጠቀሳለች። ሶስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅታ በወርቃማ ትውልዷ ለመጀመሪያ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ በመሆን ዋንጫውን ማስቀረት ችላለች። ሰላሳ ሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሆነን የሶስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብቸኛ ድል በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችን እንደሚከተለው አስታወስን።
በወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያረፈው እቴጌ ጣይቱ ሆቴል ነው፡፡ ሶስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማካሄድ የወሰደው ጊዜ አንድ ሳምንት ብቻ ነው። ውድድሩ በተጀመረበት የመክፈቻ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥር 6 ቀን 1954 ዓ.ም በግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ቱኒዝያ ላይ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ለፍጻሜ አለፈ። ግቦቹን ያስቆጠሩትም ሉቺያኖ ቫሳሎ፣ ግርማ ዘለቀና መንግስቱ ወርቁ ነበሩ። በሌላኛው ምድብ ግብጽ ዩጋንዳን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ በፍጻሜው የኢትዮጵያ ተፋላሚ መሆኗን አረጋገጠች።
ጥር 11 ቀን 2011 ዓ.ም በታተመው አዲስ ማለዳ ቅጽ 1 ቁጥር 11 ላይ የሰፈረ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ግብጽ ከአምስት ዓመታት በፊት በ1949 ዓ.ም የተደረገውን የመጀመሪያውን የአፍሪካ ዋንጫ ያነሳችው ኢትዮጵያን 4 ለ 0 በማሸነፍ ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት በዚህ ምክንያት ያደረባቸው ቁጭት ከሁለቱ አገራት ባላንጣነት ጋር ተዳምሮ የፍጻሜ ጨዋታውን ለማሸነፍ የጋለ ስሜት ውስጥ ገብተው ነበር።
የአዲስ አበባ ስታዲየም በ25 ሺ ተመልካቾች ጢም ብሎ ሞልቶ ግጥሚያው ተጀመረ። ለፍጻሜ ጨዋታው ኢትዮጵያ ያሰለፈቻቸው ተጫዋቾች ጊላ ሚካኤል ተስፋ ማርያም፣ ክፍሎም አርአያ፣ አስመላሽ በርሔ ፣ በርሔ ጎይቶም ፣ አዋድ መሐመድ፣ ተስፋዬ ገብረ መድኅን ፣ ግርማ ዘለቀ፣ መንግሥቱ ወርቁ፣ ሉቻኖ ቫሳሎ ፣ ኢታሎ ቫሳሎና ጌታቸው ወልዴ ሲሆኑ ተጠባባቂዎች ደግሞ ተክሌ ኪዳኔ ፣ ጌታቸው መኩሪያ፣ እስማኤል ጊሪሌ፣ ብርሃኔ አስፋው፣ ኃይሌ ተስፋ ጋብርና ነፀረ ወልደሥላሴ ነበሩ። ይድነቃቸው ተሰማ በዋና አሰልጣኝነት ፀሐየ ባሕረና አዳሙ ዓለሙ በረዳትነት ቡድኑን ሲመሩ ጥላሁን እሸቴ ደግሞ የብሔራዊ ቡድኑ ወጌሻ ነበሩ።
ጨዋታው በተጀመረ 35ኛው ደቂቃ ላይ ግብጽ በአብዱልፈታ በደዊ አማካኝነት ግብ አስቆጥራ ስታዲየሙ ጸጥ ረጭ እንዲል አደረገች። በ74ኛው ደቂቃ ግርማ ዘለቀን ቀይሮ የገባው ተክሌ ኪዳኔ ግብ አስቆጥሮ ኢትዮጵያን አቻ አደረገ። ነገር ግን ከሽርፍራፊ ሰከንዶች በኋላ በደዊ ሁለተኛ ግብ በማስቆጠሩ ደስታው ወደ ውጥረት ተቀየረ።
ከደቂቃዎች ቆይታ በኋላ ሉቻኖ ቫሳሎ የአቻነቷን ግብ ከመረብ አሳረፈ። ይህችን የአቻነት ግብ መንግስቱ ወርቁ እንዳስቆጠረ የሚገልጹ የታሪክ ሰነዶችም አሉ። ጨዋታው በዚህ መልኩ ቀጥሎ መደበኛ ጊዜው በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ።
የተጨማሪ ሰዓት ጨዋታው ተጀምሮ በ101ኛው ደቂቃ ላይ ግብጾች የፈጸሙትን የመከላከል ስህተት ተጠቅሞ ሉቻኖ ቫሳሎ ለራሱ ሁለተኛውን ለኢትዮጵያ 3ኛውን ግብ አስቆጠረ። በጨዋታው 117ኛ ደቂቃ ላይም አራተኛውንና የመጨረሻውን ግብ መንግስቱ ወርቁ ሲያስቆጥር በአዲስ አበባ ስታድየም ታድሞ የነበረው ተመልካች በደስታ ዘለለ። በዚህ መልኩ ኢትዮጵያ እስከ ዛሬም መድገም የተሳናትን የ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ባለድል ሆነች።
ብቸኛው ዋንጫ ከተገኘ ስልሳ ዓመታት ቢቆጠሩም ለእግር ኳስ የተለየ ፍቅር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ዳግም የአፍሪካ ዋንጫውን የማንሳት ህልማቸውን እውን የሚያደርግ ብሔራዊ ቡድን አላገኙም።
በዚህ ታላቅ መድረክ የዋንጫ ክብር ቀርቶ ተሳትፎ እንኳን ብርቅ ሆኖ ሊቢያ እኤአ 1982 ላይ ካስተናገደችው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ ኢትዮጵያ ወደ መድረኩ ለመመለስ ሰላሳ አንድ ዓመት ጠብቃለች። እኤአ በ2013 ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችው ውድድር በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እየተመራ ወደ መድረኩ የተመለሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ትልቅ መነቃቃት ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ዳግም ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለመመለስ ስምንት ዓመታትን ፈጅቷል።
በዚህም በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመሩት ዋልያዎቹ በካሜሩን እየተካሄደ በሚገኘው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያን ለአስራ አንደኛ ጊዜ እንድትሳተፍ አስችለዋል። ሃያ አራት አገራት ለመጀመሪያ ጊዜ እየተሳተፉበት በሚገኘው በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ዋልያዎቹ በኬፕቨርዴ 1ለ0፣ በካሜሩን 4ለ1 ተሸንፈውና ከቡርኪናፋሶ ጋር 1ለ1 ተለያይተው ባለፈው ሰኞ የአፍሪካ ዋንጫ ጉዟቸውን እንደ ደመደሙ ይታወቃል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 16/2014