በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተላለፈውን አገራዊ ጥሪ ተቀብለው “በታላቁ ጉዞ ወደ አገር ቤት” መርሃ ግብር የመጡ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላትን በአገር ወግ ማዕረግ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበልና ምስጋና ለማቅረብ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል። በሂልተን አዲስ ኢንተርናሽናል ሆቴል ይፋ የተደረገው ይህ መርሃ ግብር ከተባባሪ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ዝግጅቶች መደረጋቸው ታውቋል። ይህንን አስመልክቶ የዝግጅት ክፍላችን አጠቃላይ መሰናዶው ምን እንደሚመስል መግለጫውን ተከታትሎ ከዚህ እንደሚከተለው አቅርቦላችኋል።
አቶ አለማየሁ ጌታቸው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የመሰናዶው ዋናው ዓላማ ከትውልድ አገራቸው ርቀው በዓለም ማእዘናት የሚኖሩ ወቅታዊ የአገራቸው ሁኔታን በመረዳት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ የቆዩና እያበረከቱ ያሉ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች አንድ ሆነው ከጎናችን በመቆም ከተገባበት ጦርነት በአሸናፊነት ለመወጣታችን አንዱ የዲያስፖራ ማህበረሰብ ሚናና አስተዋፅኦ ቀላል ስላልሆነ ምስጋና ማቅረብ ተገቢበመሆኑ ነው። የዲያስፖራው ማህበረሰብ በአገራችን ልማትና አንድነት ላይ የተቃጣውን የከፋፋይ ፖለቲካ ጦርነት እና የኃይል እርምጃ አራማጆችን ሃሳብ በመቃወም ያሳዩት ትብብርና ድጋፍ ከፍተኛ ቦታና ክብር የሚሰጠው ነው። በተለይ በውጪ አገር ሆነው “በቃ!” “ኖ ሞር” ከማለት ጀምሮ በድፍረት ያሳዩት ትግልና ጀግንነት ቀላል እንዳልሆነ መንግስት የሚገነዘበው ነው።
ዳይሬክተሩ እንደሚናገሩት፤ ትግሉን በማቀጣጠል በአገረ መንግስት ግንባታ ልማት በላቀ እንዲደገም ወደ አገር ቤት የመጡትን እንግዶች በአገር ባህል ወግና ስርዓት ደማቅ አቀባበል ማድረግ እንደ ባህላችን የሚጠበቅብን የውዴታ ግዴታ በመሆኑ በሰላም የመጡ እንግዶችን የሰመረ ቆይታ እንዲኖራቸው ለማድረግ የባህልና የስፖርት ሚኒስቴር ከኢስት አፍሪካ ኢንተርቴይመንትና ኤቨንት ኦርጋናይዘር ጋር በመሆን በቂ ዝግጅት አድርጓል።
የተሰናዱት ሁነቶች“ወደ አገር ቤት የመጡትን ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንግዶችን ተቀብለን ባህላቸውን፣ ታሪካቸውን እንዲሁም ሃብቶቻቸውን አውቀውና ተደስተው የሚመለሱባቸው ሁነቶች ተመቻችተው ዝግጅቶችም ተጠናቀዋል” ያሉት ዳይሬክተሩ አቶ አለማየሁ ፤ እንደ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከብዙ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በርካታ ተግባርና ኃላፊነቶችን እየተወጡ እንደሚገኙይናገራሉ። መንግስት ለዲያስፖራው ባደረገው ጥሪ መሰረት ጥሪውን አክብረው ወደ አገራቸው ከዓለም ማእዘናት የመጡ የዲያስፖራ አባላትን እና በአገር ውስጥ የሚገኙ ዘመድ አዝማዶቻቸውን በአንድ ላይ በማሰባሰብ እየተዝናኑ የአገራቸውን ባህላዊ እና ኪነ-ጥበባዊ እንዲሁም እደ-ጥበባዊ እሴቶችን የሚጎበኙበትና እርስ በእርስ የሚተዋወቁበት ልዩ የመዝናኛ መርሃ ግብሮችም ተዘጋጅተዋል።
ይህን ሃሳብ ያመቻቹት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከኢስት አፍሪካ ቢዝነስ ግሩፕ እና ከኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ጋር በመተባበር ነው። በዚህም ለእንግዶች በአገር ባህል ስርዓትና ወግ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ይደረጋል ። የተለያዩ የባህል፣ የኪነ-ጥበብና የስፖርት ዘርፎች፣ ሁነቶች እና ትእይንቶች ይካሄዳሉ ።
ዝግጅቶቹ ከጥር 20 እስከ 22 /2014 በተለያዩ መርሃ ግብሮች የሚከናወኑ ሲሆን ከእነርሱ መካከል የመጀመሪያው ሁሉም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች የሚሳተፉበት የባህል ኤግዚቢሽን በወዳጅነት አደባባይ የሚካሄድ ሲሆን ክልሎቹ ያላቸውን ባህል፣ ኪነ-ጥበብ፣ እደ-ጥበብ እና ሌሎች ባህላዊ እሴቶችን በአውደ ርዕይ ያቀርባሉ ። እንዲሁም በመጀመሪያው የመሰናዶ ፕሮግራም የባህል ሲምፖዚየም በሸራተን አዲስ ይካሄዳል ።
የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ወይዘሮ እንግዳዬ እሸቴ ሁነቱን አስመልክቶ እንዳሉት፤ በአውደ ርዕዩ ላይ በስታር ባክስ የተያዘውን አንድ ሚሊዮን ሰዎችን በአንድ ቀን ውስጥ ቡና በነፃ የማጠጣት የጊነስ ሪኮርድ ለመስበር ያሰበ በመላው የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር በሁሉም የአገሪቱ ቅርንጫፍና ዋናው መሰናዶ በሚደረግበት በወዳጅነት አደባባይ አምስት ሚሊዮን ሰዎችን በነፃ በማጠጣት ክብረ ወሰኑን ለመስበር የሚደረግ ዝግጅት አለ ። ከዚህ በተጨማሪ “ቡናችን ለሚሊዮኖች” የሚለውን መርሃ ግብር ለማድመቅ “ኑ ቡና ጠጡ” በሚል መሪ ቃል አንድ ሺህ ሲኒ በረኮቦት ታላቅ የቡና ጠጡ ስነ-ስርዓት ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች በተገኙበት ይከናወናል። ከእርሱ ጋር ተያይዞ ባህላዊ የገና ጨዋታ፣ የፈረስ ጉግስ፣ የግመል ግልቢያ፣ የቡድን ገመድ ጉተታና ሙዚቃ ይካሄዳል። የሙዚቃ ኮንሰርት ዝግጅትም በወዳጅነት ፓርክ በአንጋፋና ታዋቂ ሙዚቀኞች ይቀርባል።
የእደ-ጥበብ ምርቶች፣ አልባሳት፣ ባህላዊ ምግቦች፣ የስነ-ጽሁፍ ቅርሶች የብሔር ብሔረሰብ ሙዚቃ ዝግጅቶች ይቀርቡበታል። ይህ ሁነት በጥር 21 ቀጥሎ ተመሳሳይ ዝግጅቶች የሚደረጉበት ሲሆን ለታዳሚያንም ክፍት ሆኖ ይቆያል። በሶስተኛው ቀን በሚደረገው መርሃ ግብር ላይ መነሻውንና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ያደረገ የ5 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ከጠዋቱ 12፡30 ሰዓት ጀምሮ ታዋቂ የአገራችን አትሌቶች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና በዝግጅቱ ላይ በሚሳተፉ እንግዶች ይካሄዳል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥር 16/2014