የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን /ዋልያዎቹ/ ከስምንት አመት በኋላ በተካፈሉበት የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ከምድባቸው ሳያልፉ ቀርተዋል። ከውድድሩ አዘጋጅ ካሜሩን፣ ቡርኪና ፋሶና ኬፕቨርዴ ጋር በምድብ አንድ የተደለደሉት ዋልያዎቹ ሁለት ጨዋታዎችን በሽንፈት አንዱን ደግሞ በአቻ ውጤት አጠናቀው በአንድ ነጥብና ሁለት ግቦች ከውድድሩ በጊዜ ተሰናብተዋል።
የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስብስብ ከውድድሩ አስቀድሞም በአማካኝ ወጣት ተጫዋቾችን በብዛት የያዘና በመድረኩ ልምድ የሌለው እንደሆነ በተደጋጋሚ ተነግሯል። ዋልያዎቹ ሃያ አራት አገራት ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፉበት የአፍሪካ ዋንጫ ከምድባቸው ጥሩ ሦስተኛ ሆነው ለማለፍ እንኳን የተሳናቸው በዋናነት በልምድ ማነስ ምክንያት ነው ተብሎ ይጠቀሳል። አሰልጣኝ ውበቱ አባተም ዋልያዎቹ የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገው ከቡርኪናፋሶ ጋር አንድ ለአንድ ከተለያዩበት ጨዋታ በኋላ የቡድኑ ችግር የልምድ ማነስ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ይህም በአጭር ጊዜ የሚስተካከል እንዳልሆነና ጊዜ እንደሚያስፈልግ መናገራቸው ይታወሳል።
በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ዋልያዎቹ ልምድ የሌላቸውና ወጣቶች መሆናቸው በዚህ አፍሪካ ዋንጫ ዋጋ እንዳስከፈላቸው ቢስማሙም፤ ይህ የልምድ ጉዳይ እንዴት እንደሚቀረፍ አሳሳቢ መሆኑን አስተያየት ይሰጣሉ። በተለይም በኢትዮጵያ እግር ኳስ እንዲህ አይነት ውጤቶች ከተመዘገቡ በኋላ ነባሩ አሰልጣኝ ተሰናብቶ አዲስ አሰልጣኝ የሚቀጠርበት ልማድ ችግሩን ለመቀረፉ ተግባር ሁልጊዜም እንቅፋት እንደሚሆን ይታመናል። ምክንያቱም ነባሩ አሰልጣኝ ተሰናብቶ አዲስ ሲመጣ በራሱ አስተሳሰብና የእግር ኳስ ፍልስፍና መሰረት አዲስ ቡድን ለመገንባት አዳዲስ ተጫዋቾችን መምረጡ አይቀርም። ይህም የዋልያዎቹን ስብስብ ሁልጊዜም አዲስና ልምድ የሌለው እንዲሆን አስገድዶታል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝና በአሁኑ ወቅት የፕሪሚየር ሊጉን ክለብ ሃዲያ ሆሳዕናን እያሰለጠኑ የሚገኙት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ፤ ከአሁኑ የዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ አብዛኞቹ ተጫዋቾች ወጣት መሆናቸውን ይናገራሉ። ከቀድሞዎቹ ብሔራዊ ቡድኖች አንጻር የአሁኑ የዋልያዎቹ ስብስብ ብዙ ወጣቶችን እንዳካተተ የሚናገሩት አሰልጣኝ አሸናፊ፣ እንደማንኛውም የሥራ አለም ተጫዋቾቹ መጀመሪያና ከአመታት በኋላ ልምድ ሲያካብቱ የሚኖራቸው አቅምና ብቃት እንደሚለያይ ያምናሉ። ከዚህ አኳያ እነዚህ ተጫዋቾች ልምድ ቢያካብቱ የተሻለ ነገር ሊያሳዩ እንደሚችሉም ይናገራሉ።
እነዚህ ተጫዋቾች ልምድ አካብተው ወደ ፊት የተሻለ ነገር እንዲያሳዩ ውጤት በተበላሸ ቁጥር አሰልጣኝ መቀየር ስህተት መሆኑን ለአዲስ ዘመን አስተያየት የሰጡት አሰልጣኝ አሸናፊ፣ የአሁኑ ብሔራዊ ቡድን ከአሰልጣኝ አብረሃም መብራቱ አንስቶ እየተገነባ የመጣና በአሰልጣኝ ውበቱ አባተም የቡድኑ ግንባታ እንደቀጠለ ያብራራሉ። ወደፊትም ይህ የቡድን ግንባታ እንዲቀጥልና ተጫዋቾቹም ልምድ አግኝተው የተሻለ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን እንዲፈጠር አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከቡድኑ ጋር መቀጠል እንዳለባቸው ያስረዳሉ።
አስልጣኝ አሸናፊ ይህ ካልሆነ ግን አዲስ አሰልጣኝ ሲመጣ የነበሩትን ተጫዋቾች ቢያንስ ሃምሳ በመቶ መቀየሩ እንደማይቀር እምነታቸው ነው። “አሰልጣኝ ውበቱ ቢቀጥል የቡድኑ ግንባታም ይቀጥላል፤ ይሄ የእኔ አመለካከትና እንደዜጋም ይመለከተኛል ብዬ የማምንበት ነው” ያሉት አሰልጣኝ አሸናፊ፣ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚም፣ አሰልጣኝ ከማሰናበቱ በፊት ቆም ብሎ ማሰብ እንዳለበት ይጠቁማሉ።
እንደ አሰልጣኙ ገለጻ፣ ፌዴሬሽኑ ለአሰልጣኝ ውበቱ የተሻለ ጥቅም ሰጥቶ ሊያቆየው ይገባል፣ እንደ አገራችን ክለቦች የአንድ አመትና ከዚያ ያነሰ የኮንትራት ጊዜ ለብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ መስጠት አገርን አይጠቅምም።
የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ የአምናው ቻምፒዮን ፋሲል ከነማ አሰልጣኝና የቀድሞ የዋልያዎቹ ምክትል አሰልጣኝ ስዩም ከበደም ውጤት በተቀያየረ ቁጥር አሰልጣኝ መቀየር አያስፈልግም በሚለው ሃሳብ ይስማማሉ፡ ፡ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ቀርቶ በክለብ ደረጃም ውጤት ሲጠፋ አሰልጣኝ የማሰናበት ልማድ ተገቢ እንዳልሆነም ይናገራሉ፡፡
አንድ አሰልጣኝ ቡድኑን ገንብቶ ለተሻለ ውጤት ለማብቃት ቢያንስ የአንድ ኦሊምፒክ እድሜ (አራት ዓመት) ሊሰጠው እንደሚገባ የገለፁት አሰልጣኝ ስዩም፣ ውጤትን መሰረት አድርጎ አሰልጣኝ ለመቀየር ውሳኔ ላይ ከመድረስ በፊት ሰከን ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል ነው የሚሉት፡፡
አሰልጣኝ ስዩም ብሔራዊ ቡድኑን በቀጣይ ዓመታት የተሻለና ጠንካራ አድርጎ ለመገንባት ከልምድ ማነስ ባሻገር ሌሎች በርካታ ስራዎችን ጊዜ ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግም ያምናሉ፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ አሁን ያሉበትን በርካታ ክፍተቶች በአግባቡ አጢኖ በእያንዳንዱ የቴክኒክና የአካል ብቃት ጉዳይ ላይ ጠንካራ ሥራ መስራት እንደሚያስፈልግም ይናገራሉ፡፡ በተለይም የዋልያዎቹ ስብስብ በቴክኒክ ረገድ ጥሩ አቅም እንዳለው የሚነገረውን ጉዳይ አጠንክሮ ያሉባቸውን ክፍተቶች በምን መልኩ ማስተካከል ይቻላል በሚለው ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 14/2014