ሕይወት መልከ ብዙ ናት። አስደሳቹንም ሆነ አሳዛኙን የሰው ልጅ ገፅታ ቁልጭ አድርጋ ታሳያለች። በሕይወት መንገድ አንዱ ሲደሰት ሌላኛው ያዝናል። አንዱ ሲያገኝ ሌላኛው ያጣል። አንዱ ሲታመም ሌላኛው ይድናል። አንዱ ሲወለድ ሌላኛው ይሞታል። ሁለት ተቃራኒ ክስተቶችን የምታስተናግድ በመሆኗም ነው ሕይወት መንታ ገፅታ አላት የሚባለው።
እያንዳንዱ የሰው ልጅ ይህችን ምድር ሲቀላቀል የሚያስተናግደው የሕይወትን መንታ ገፅታ ነው። ወድቆ መነሳት፣ አግኝቶ ማጣት፣ ታሞ መዳን አልያም መሞት፤ በሰው ልጅ የሕይወት ኡደት ውስጥ የሚፈራረቁ ክስተቶች ናቸው። ዋናው ጥያቄ ግን እያንዳዱ ሰው እነዚህን ክስተቶች ተቀብሎ የሚያስተናግደበት መንገድ ለየቅል መሆኑ ነው።
አንዳንድ ሰዎች በሕይወታቸው የሚገጥማቸውን ማንኛውንም ፈተና ተቋቁመው ወደፊት ሲራመዱ ሌሎች ደግሞ በጥቂት ነገር ቅስማቸው ተሰብሮ ከመንገድ ይቀራሉ። ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ደግሞ በሕይወት የሚገጥማቸው ፈተና በእጅጉ ከባድና ተደጋጋሚ ቢሆንም እስከ ሕይወታቸው ፍፃሜ ድረስ ፈተናውን ተጋፍጠው ነጋቸውን ብሩህ ለማድረግ ይፍጨረጨራሉ። ከዚህ በተቃራኒ ብዙዎች በረባ ባልረባው ፈተና ሁሉ እየወደቁ ራሳቸውን ረግመው ለገጠማቸው ፈተና እጅ ሰጥተው ቁጭ የሚሉም አሉ። የአርባ አልያም የሰማንያ ቀን እድሌ ነው በማለት ፈጣሪያቸውን የሚያማርሩም አይጠፉም።
እንግዲህ የሰው ልጅ ወደዚች ምድር ከመጣ በኋላ ጥሮ ግሮ እንዲበላ በፈጣሪው ታዟል። እናም ሁሉም ሰው የፈጣሪውን ፍርድ ተቀብሎ ሕይወቱን ለማቆየት ሲል ሌት ተቀን ይለፋል። የሚለፋውም አንድም የራሱን ሁለትም የቤተሰቡን ህልውና ለማቆየት ሲል ነው።
በቀደመው ግዜ ሰዎች ገንዘብ ለማግኘት ብዙ መልፋት ይጠበቅባቸዋል። አብዛኛዎቹ ሥራዎችም ከጉልበት ጋር የሚያያዙ በመሆናቸው ልፋትንና ድካምን ይጠይቃሉ። ሆኖም በግዜ ሂደት ሥራ በዘመናዊ ማሽነሪዎችና በቴክኖሎጂ እየተደገፈ በመምጣቱ ሰዎች ቀደም ሲል ሲያወጡት የነበረው ድካም እየተቃለለ መጥቷል።
እንዲያም ሆኖ ታዲያ ዘመኑ ብዙ መልፋትን ባይጠይቅ እንኳን ብልሃትን በተከተለ መልኩ ሰርቶ ለማግኘት ጭንቅላትን በሚገባ ማሰራትና አዳዲስ የሥራ ፈጠራን ይዞ ብቅ ማለትን የሚያስገድድ እየሆነ መጥቷል። እንደ ቀደመው ዘመን ብዙ ጉልበት አውጥቶ ገንዘብ ከማግኘት ይልቅ በብልሀት ሰርቶ የተሻለ ማትረፍ የዘመኑ አዋጭ አሰራር ሆኗል።
የኢትዮጵያም ኢኮኖሚያዊ እድገት ምንም እንኳን ሌሎች አደጉ ከሚባሉት አገራት ጋር የሚስተካከል ባይሆንም በሉላዊነት አለም ወደ ትንሽ መንደርነት እየተቀየረች በመምጣቷ ከዚህ በብልሃት ሰርቶ ትርፍ የማግኘት እውነታ ያመለጠ አይደለም።
በእርግጥ በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች በተለይ ደግሞ በአምራች ኢንዱስትሪውና ኮንስትራክሽን ዘርፉ በርካቶች ጉልበታቸውን አፍሰው ይሰራሉ። ይሁንና የሚያገኙት ገቢ ከሚያወጡት ጉልበት አንፃር ተመጣጣኝ ነው ለማለት አያስደፍርም። እነዚህ ሰዎች እንዲህ የሚለፉት ታዲያ ህይታቸውን ለማቆየት እንጂ መቼም ለማትረፍ አይደለም።
አንዳንዱ ትንሽ ሰርቶ ብዙ ማትረፍ የሚሆንለት አለ። ሌላው ደግሞ ብዙ ለፍቶ ጠብ የማይለለት አለ። ዞሮ ዞሮ ግን አካሄዱ ቢለያይም በሁለቱም ጎራ ለመኖር የሚደረግ ጥረት እንዳለ ያሳያል። ምንም ካለመስራት ብዙ ለፍቶ ጥቂት ማገኘት ግን ሁሉንም ያስማማል።
ዛሬ ላይ የኑሮ ውድነቱ ሰማይ ነክቷል። ራስን ለማቆየት አንድ ሥራ ብቻ መስራት በቂ አልሆነም። የተሻለ ገቢ ለማግኘት ብዙ ከመልፋት በዘለለ ብዙ ማሰብ፣ ሥራ መፍጠርና በብልሀት መሥራት የግድ ብሏል። እንዲያም ሆኖ ግን የሰው እጅ ላለማየትና ኑሮን ለማሸነፍ ተፍጨርጭረው የእለት ጉርሳቸውን የሚሞሉ አልጠፉም። የወይዘሮ ሌሊሴ ቀጄላ ሕይወትም ከዚህ የተለየ አይደለም።
ወይዘሮ ሌሊሴ ውልደቷም ሆነ እድገቷ እዚህ አዲስ አበባ አይደለም። የሕይወት መስመር አስገድዷት አዲስ አበባ አመጣት እንጂ ውልደቷም ሆነ እድገቷ ወለጋ ሌቃ ዱለቻ ነው። ትምህርት ቤት ገብታ የመማር እድል ባታገኘም አፈር ፈጭታ የልጅነት ግዜያዋን ያሳለፈችው በዚችው ሌቃ ዱለቻ በተባለች አነስተኛ የገጠር መንደር ነው።
በዚች መንደር ከእድሜ አቻዎቿ ጋር ቦርቃ ተጫውታለች። እንደብዙዎቹ የገጠር ልጆች ውሃ በእንስራ በመቅዳት፣ የከብቶች አዛባ በመሰብሰብና ቡና በማፍላት ቤተሰቧቿን በሥራ አግዛለች። እንዳለመታደል ሆኖ ግን የቀለም ትምህርት ለመማር አልታደለችም።
ትምህርት የመማር ፍላጎት በውስጧ ቢኖርም ፍላጎቷን ማሳካት አልቻለችም። ትምህርት ደህና ሰንብት ብላ ውሃ አጣጯን አግኝታ አገባች። አብረው መኖር ጀመሩ። ጤፍና ቡና ከባለቤቷ ጋር ሲነግዱ ቆዩ። ኑሮ ግን ቀላል አልሆነላቸውም። ሕይወትም አልጋ በአልጋ ሊሆንላቸው አልቻለም። እርሱ እዛው ሰርተን እንለወጥ ሲል እርሷ ግን ልቧ ወደ አዲስ አበባ ሸፈተ። ወለጋ ላይ ሆና አዲስ አበባን ገነት አድርጋ ሳለቻት።
እናም ኑሮን ለማሸነፍ ብለው ወደ አዲስ አበባ ኮበለሉ። አዲስ አበባ ግን እንዲህ በዋዛ አለተቀበለቻቸውም። አዲስ አበባ ኑሮዋን ላወቀባት ሳትሰስት የምትሰጥ ላላወቀባት ደግሞ የምተነፍግ ከተማ ናት።
ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ባለቤቷ ለግዜው የካቲት 12 ሆስፒታል በጥበቃ ሰራተኝነት ተቀጠረ። በዚህ መሀል እርሷ ነፍሰጡር ነበረችና ሴት ልጅ ወለደች። እርሱ ሰርቶ በሚያገኘው ገቢ ብቻ መተዳደር ግን አልቻሉም። ሥራ ፈለገች፤ ልጅ ይዛ እርሷን የሚያሰራ ጠፋ። ያላት ብቸኛ አማርጭ ልመና ነውና የአንድ አመት ልጇን ይዛ ጎዳና ላይ ወጣች።
በየጎዳናው እየተዘዋወረች መለመኗን ተያያዘቸው። የሁለቱ ጥንዶች ሕይወት በዚህ መልኩ ለሦስት አመታት ዘለቀ። እንዲህም ሆኖ እርሱ በጥበቃ ሥራ እርሷ ደግሞ በልመና ኑሮን መገፋት አልቻሉም። በልመና የምታገኛት ገቢ ከእለት ጉርሷና ከልጇ ወጪ ልትሻገር አልቻለችም። ለቤት ኪራይ የሚያወጡት ወጪም ኑሮን ለመቋቋም አላስቻላቸውም።
ሌሊሴ ድጋፍ ብታገኝ ውስጧ ለሥራ ዝግጁ እንደሆነ ታውቀዋለች። የአቅም ጉዳይ ሆኖባት እንጂ የራሷን ሥራ ለመስራት ዝግጁ ነበረች። ሀሳቧም ውጥኗም ከልመና ወጥታ የራሷ ሥራ መስራት ነበር። ሀሳቧን ወደ ተግባር ለመለወጥ ግን እጅ አጠራት።
አንድ ቀን ዘወትር ቁጭ ብላ ከምትለምንበት አራት ኪሎ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በራፍ ላይ የድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች አጠገቧ መጡ። እዛው ስትለምን ያውቋታልና ‹‹ድርጅቱ ቦታ ቢፈቅድልሽ የራስሽን ሥራ ትጀመሪያለሽ ወይ?›› የሚል ጥያቄ አቀረቡላት። ይህ ጥያቄ አስቀድሞ በውስጧ ሲብሰለሰል የቆየ ነውና ለጥያቄው መልስ ለመስጠት ብዙ አላመነታችም። ወዲያው ተስማማች።
ከልመና ባፈራቻት አነስተኛ ገንዘብ ባለቤቷም ጨምሮላት የቺፕስ መጥበሻ፣ መክተፊያና ቢላ ገዛች። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ደግሞ ቦታና ኤሌክትረክ ፈቀደላት። ከዛም ድንች ገዝታ ቺፕስ እየጠበሰች መሸጥ ጀመረች። ብስኩት፣ ማስቲካ፣ ማስክና ሌሎችንም ሸቀጦች ከመርካቶ አምጥታ ከቺፕሱ ጎን ለጎን መሸጥ ቀጠለች።
ጠዋት ላይ ማስቲካ፣ የታሸገ ውሃ፣ ብስኩትና ሌሎችንም ሸቀጦች ትሸጣለች። ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽት አንድ ሰዓት ድረስ ደግሞ ቺፕሷን ትሸጣልች። ቀስ በቀስም ገበያው ደራላት፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሰዎችም በርቺ አሏት። ፊቷም በፈገግታ ተሞልቶ አልፎ አልፎ የሁለት አመት ከስድስት ወር ሴት ልጇን እያጫወተች ንግዷን አጧጧፈች።
ቺፕስና ሌሎች ማስቲካ፣ ከረሜላ፣ ብስኩት፣ የታሸገ ውሃና መሰል ሸቀጦችን መሸጥ ከጀመረች ገና ሁለት ወራትን እንኳን ያለደፈነችው ሌሊሴ፤ ዛሬ ከስድስት ኪሎ አካባቢ ከሚገኝ ገበያ ድንች ገዝታ በማምጣት ድንቹን ከትፋ ቺፕስ አድርጋ ለገበያ ታቀርባለች። ዘይቱን ደግሞ አንዳንዴ ከመርካቶ ሌላ ግዜ ከቀበሌ ሸማቾች ትገዛለች።
ለደምበኞቿ ከአስራ አምስት ብር ጀምሮ ቺፕስ ትሸጥላቸዋለች። ቺፕሱን አሳምራ ስለምተሰራው በርካታ ደምበኞችን አፍርታለች። አብዛኛው አላፊና አግዳሚ ቺፕስ፣ ማስቲካ፣ ብስኩት፣ ማስክና ሌሎችንም ሸቀጦችን የሚገዛውም ከእርሷ ነው።
ሌሊሴ ገቢዋ እየተሻሻለ በመምጣቱ የእለት ጉርሷን፣ የልጇንና የቤተሰቧን የቀለብ ወጪ መሸፈን ችላለች። እንጦጦ አካባቢ አንድ ክፍል ተከራይታ ከባለቤቷ ጋር እየኖረች የጎዳና ሕይወትን ተሰናብታለች። ባለቤቷም የቀን ሥራ እየሰራ የቤት ኪራዩን ወጪ በመሸፈን ያግዛታል።
ከቺፕስ ሽያጭ ብቻ በቀን ከሶስት መቶ አስከ አራት መቶ ብር ድረስ ታገኛለች። ከሌሎች ሸቀጣሸቀጦችም ከዚህ ያላነሰ ገንዘብ በቀን ታገኛለች። ከምታገኘው ገቢ ላይ የሚያስፈልጋትን ወጪ ሸፍና ቀሪውን በየወሩ ከሁለት አስከ ሰባት መቶ ብር ባንክ ታስቀምጣለች። ይህንንም ተከትሎ ኑሮዋ እየተሻሻለ በመምጣቱና ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አስተዋፅዖ ትልቅ በመሆኑ ምስጋናዋን ታቀርባለች።
አሁን ያላትን ትጋት በማስቀጠል ወደፊት የተሻለ ገቢ በማግኘትና ገንዘብ በመቆጠብ ከዚ የተሻለ ንግድ ውስጥ የመግባት ፍላጎት አላት። ልጇን አስተምራ የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ ትልቅ ሃሳብ ይዛለች። በሚቀጥለው አመትም ምኒልክ ትምህርት ቤት ልጇን ለማስመዝገብ ዕቅድ ይዛለች።
ሌሊሴ በልመና ውስጥ እያለች የደረሰባትን ችግር በሚገባ ታውቀዋለች። በልመና የሰው ፊት ገርፏታል። ስትለምን ውላ የሚመፀውታት አጥታ ፆሟን አድራለች። በገቢ ማነስ ለተወሰኑ ግዜያት ኑሮዋ ጎዳና ላይ ነበር።
በልመና ሕይወት ውስጥ ያሉ ሰዎችን ስትመለከት የቀደመው ሕይወቷን ያስታውሳታል። እናም የልመና ሕይወትን ስታስበው ስለሚዘገንናት ይህን ሕይወት ለማንም አትመኝም። በዚህ ሕይወት ውስጥ ያሉ ሰዎች ዛሬ ነገ ሳይሉ በሌላ ሥራ ላይ ተሰማርተው አዲስ ሕይወት እንዲጀምሩም ትመክራለች።
‹‹በልመና የሚገኝ ገንዘብ አይበረክትም፣ እኔ ለምኜ አይቼዋለሁ›› የምትለው ሌሊሴ፤ ከልመና ሕይወት ወጥቶ በሌላ ሥራ ላይ መሰማራት በራሱ ደስታ የሚሰጥና የሰው እጅ ከመጠበቅ የሚያላቅቅ ነው ትላለች።
ሌሊሴ የሄደችበት የሕይወት መንገድ ለብዙዎች አስተማሪ ነው። በተለይ ደግሞ ልመናን ሥራዬ ብለው የሙጥኝ ያሉ ሰዎች ከልመና ተላቆ በራስ ጉልበት ጥሮ ግሮ በመስራት ገቢ ማግኘት እንዲሚቻል ትምህርት የሰጠ በመሆኑ ብዙዎች ከርሷ ሕይወት ብዙ ቁምነገር ያገኛሉ ብለን እናምናለን። ሰላም!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥር 14/2014