ኢትዮጵያ በ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ 1ወርቅ፣ 1ብር እና 2 ነሃስ በጥቅሉ 4 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ በደረጃ ሰንጠረዡ 56ኛ ሆና ማጠናቀቋ ይታወሳል። በወቅቱ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ለውጤቱ መበላሸት ትልቅ ሚና እንደነበረው በግልፅ ከመታየቱ ባሻገር የስፖርት ቤተሰቡን ቅር ያሰኘና የአትሌቶችን ስነልቦና ጭምር በእጅጉ መጉዳቱ አይዘነጋም።
ከውድድሩ በኋላም ሁለቱ ተቋማት በየፊናቸው ጉዳዩን ለሕዝብ ለማሳወቅና አንዱ አንዱን ለመውቀስና ኃላፊነቱን ለማሸከም ከመጣር የዘለለ ለጠፋው ነገር በዘላቂነት የተወሰደ ርምጃ ሳይኖር ጉዳዩ ተዳፍኖ ወራትን አስቆጥሯል። ይህ ጉዳይ አሁንም ድረስ ከስፖርት ቤተሰቡ ህሊና ያልጠፋ እና በወደፊቱ የኦሊምፒክ ጉዞ ላይ ስጋትን ያሳደረ ነው።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም በሐዋሳ ባካሄደው 25ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ይህ ጉዳይ በጉባኤው ተሳታፊዎች በተደጋጋሚ ተነስቷል። በመድረኩ የቀረበውን የ2013ዓም የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ተከትሎ የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውጤትና አጠቃላይ ክስተት መፍትሄ የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑን ጉባይተኞቹ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ፤ በቶኪዮ ኦሊምፒክ የተከሰቱ ችግሮችን ፌዴሬሽኑ በራሱ በኩል መገምገሙን ይጠቁማሉ። እንደ ዋና ፀሐፊው ገለጻ፤ ፌዴሬሽኑ በግምገማው ጠንካራና ደካማ ጎኖች የለየ ሲሆን፤ የውስጥና የውጪ አደናቃፊ ጉዳዮች ያላቸውንም በተመሳሳይ ተመልክቷል። ከአትሌት መረጣ ጀምሮ፤ በዝግጅት፣ በአመራር ብቃት፣ የአሠልጣኞች አቅም፣ የህክምና ቡድን፣ የመሳሰሉት በውስጥ ግምገማው ተካተዋል።
ከውጪ ደግሞ ጣልቃ ገብነቶችና ተናቦ ባለመሄድ የተነሳ የተፈጠሩ ችግሮች መኖራቸው ተጠቁመዋል። በመሆኑም እንደ መንግሥት እንዲሁም እንደ ሕዝብ ያሉትን ችግሮች አንጥሮ ገምግሞ በማየት አቅጣጫ ይሰጥበታል በሚል ፌዴሬሽኑ እየተጠባበቀ መሆኑን አብራርተዋል።
የግምገማ ሪፖርቱ እስከ ኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት የደረሰ እንደመሆኑ፤ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም ይህንኑ ፈትሾ በ100 ቀናት እቅዱ ውስጥ አካቶና አቅጣጫ ተቀምጦለት የወደፊት የሃገሪቱ ስፖርት መስመር ይዞ በፌዴሬሽኖች እና በኦሊምፒክ ኮሚቴው መመራት ያለባቸው ጉዳዮች መለየት እንደሚኖርባቸው ተጠቁሟል።
በ የ ት ኛ ው ም ዓለም ሰዎች ሊጋጩ እንደሚችሉ የሚጠቁሙት አቶ ቢልልኝ፤ በሰዎች ግጭት ሃገር መጎዳት እንደሌለባት አስረድተዋል። ጥፋት ያለበት አካል ታርሞ ሃገርን በማስቀደም የሃገርን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል። ይህንን አስተካክሎም የሚመራ አካል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። በመንግሥት በኩልም ይኸው ጉዳይ አጽንኦት በመሰጠቱ ደስተኛ መሆናቸውን አቶ ቢልልኝ ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ በኦሊምፒኩ ውጤት ላለመገኘቱ የተለያዩ ምክንያቶች የሚነሱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በአመራሩ በኩል ችግር እንደነበረ ተናግረዋል። ችግሩን በግልጽ ተመልክቶ መፍትሄ መስጠትና አስተማሪ እንዲሆን ማድረግም በዚህ ዓመት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተያዙ ዕቅዶች መካከል መካተቱን ጠቁመዋል።
ከዚህ ባለፈ ግን ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ሁለቱን አካላት ለማካሰስ፣ ለማወነጃጀል አሊያም ለዳኝነት የተቀመጠ ተቋም አለመሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል። ለዚህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት የስፖርት ማህበራትና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በሚያደርገው ክትትል፤ ችግሩ ለምን ተፈጠረ፣ ከዚህ በላይ ውጤት ሊመዘገብ አይችልም፣ ላለመመዝገቡስ ምክንያቱ ምንድነው፣ በሚለው ላይ ውይይት በማድረግ ልምድ እንደሚወሰድበት አስረድተዋል። ችግሩ እንዳይደገምም መፍትሄ የሚቀመጥበት እንደሚሆንም አስታውቀዋል።
ሚኒስትር ድኤታው እንዳስታወቁት፣ ስፖርት ስኬትም ውድቀትም አለው፣ በመሆኑም አፈጻጸሙን በመመልከት ልምድ መውሰድ ካለበት ልምድ መውሰድ ያስፈልጋል። በኦሊምፒኩ እንደ ሃገር የሚጠበቀው ውጤት አልተገኘም፤ በዚህ ምክንያትም ኢትዮጵያ ተጎጂ ሆናለች። ይህንንም እንደ መንግሥት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያምንበታል፤ ይህ ችግር እንዳይደገም በአሠራሩና በህጉ መሰረት ተቋማዊ ነጻነትን በማይነካ ነገር ግን መንግሥትና ሕዝብ ሊያገኙት ከሚገባቸው ጥቅም አንጻር ታይቶ ልምድ የሚወሰድበትንና ሐገርም ውጤታማነቷን የምታስቀጥልበትን ዕድል ለመፍጠር ይሰራል። ከዚህ ባለፈ የስፖርት አመራሩ ሊጠይቅ የሚችለው የስፖርቱ ጠቅላላ ጉባኤ አለ፤ ጉባኤው የመሻርም ሆነ የመሾም መብት እንዳለውም አብራርተዋል።
በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ተገኝተው በተመለከቱትም ሕዝብን ያስቆጣውን የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ውጤት በማስመልከት ፌዴሬሽኑ አስቀድሞ ስራዎችን ማከናወኑ እና ከሁሉም በላይ እንደ ስፖርቱ ባለሙያ የራሱን ችግር ለመመልከት ያደረገው ቁርጠኝነት የሚያስመሰግነው ነው ብለዋል። ከሁለት ዓመት በኋላ በሚካሄደው የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ፤ የቶኪዮ 2020 ውጤትን ሊክስ የሚችል ውጤት ማስመዝገብ ሕዝቡ የሚጠብቀው እንዲሁም የመንግሥትም ፍላጎት እንዳለውም አሳስበዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም