የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን(ዋልያዎቹ) የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታቸውን ከትናንት በስቲያ ምሽት ከቡርኪና ፋሶ ጋር አከናውኖ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት አጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ቡርኪና ፋሶ ወደ ቀጣዩ ዙር በአራት ነጥብ ስታልፍ ኢትዮጵያ በአንድ ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ ከምድቧ ሳታልፍ ቀርታለች።
ዋልያዎቹ ከጨዋታ ጨዋታ ያሉባቸውን ሰፊ ክፍተቶች እያረሙ፣ ከመጀመሪያው የኬፕቨርዴ ጨዋታ በካሜሩኑ ጨዋታ የተሻሉ ሆነው እንደቀረቡት ሁሉ በቡርኪናፋሶውም ጨዋታ የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። ለክብር ተጫውተውም በክብር የዘንድሮውን የአፍሪካ ዋንጫ ጉዞ በዳዋ ሆጤሳና ጌታነህ ከበደ ሁለት ግቦች አንድ ነጥብ ይዘው ደምድመዋል።
አብዛኛው የዋልያዎቹ ስብስብ በወጣት ተጫዋቾች የተሞላና በመድረኩ ልምድ የሌለው እንደመሆኑ ያሳዩት ተጋድሎ ሊመሰገንና ለወደፊት ሊበረታታ ይገባል። ዋልያዎቹ በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ያላቸውን ሁሉ ለአገራቸው ሰጥተዋል፣ በዚህም ምስጋና ይገባቸዋል።
ይህ የአፍሪካ ዋንጫ ለዋልያዎቹ እንዲሁም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ እንጂ ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም። በጥቅሉ ኢትዮጵያ የእግር ኳስ ደረጃዋን ያየችበት፣ አቅሟንም የፈተሸችበት ነው። የዋልያዎቹ ስብስብም በርትቶ ከተሰራ የተሻለ ውጤት ማሳየት እንደሚቻል ትምህርት ሰጥቷል።
ከዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ዋልያዎቹ መማር ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች በዝርዝር ተጠንተው ስለቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ማሰቢያ ጊዜው ነገ ሳይሆን አሁን ነው። ዋልያዎቹ ከዚህ በኋላ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ብርቅ ሊሆንባቸው አይገባም። በአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ እንዳለፉት ዓመታት ስምንትና ከዚያ በላይ ዓመት የመጠበቅ ምዕራፍ እዚህ ላይ ተዘግቶ በመድረኩ ዘወትር ከመሳተፍ ባለፈ ከምድብ ስለማለፍና ከዚያ በላይ ስኬት ስለማስመዝገብ የቤት ሥራው ዛሬውኑ ይጀመር።
ከቡርኪናፋሶው ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ፣ በውድድሩ ቡድናቸው ምን መልክ እንዳለው ለማሳየት መጣራቸውን አስታውቀዋል፡፡ ” ከመጀመሪያው ጨዋታ አንስቶ ነበር ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ እየሆኑብን የመጡት››ሲሉ ጠቁመው፣ ‹‹ያም ሆኖ ዛሬም ማሸነፍ አልቻልም ፤ ብናሸንፍም ለማለፍ በቂ አልነበረም። በጨዋታው እድሎች ለመፍጠር ጥረናል ፤ ግብም አስቆጥረናል። ይህ ግን በቂ አልነበረም። እንደ አጠቃላይ ከውድድሩ ብዙ ትምህርት እንወስዳለን።››ሲሉ አብራርተዋል፡፡
‹‹ልምድ ሲያገኙ ጥሩ ነገር ሊፈጥሩ የሚችሉ አሉ። ለቀጣዩ ውድድርም እንደምንመለስ ተስፋ አለኝ።” ሲሉ ተናግረዋል። ከሞላ ጎደል ከአገር ውስጥ በተመረጡ ተጫዋቾች የተዋቀረው ቡድን የልምድ እጥረት እንዳለበት ያወሱት አሰልጣኝ ውበቱ፣ ”ከዚህ የተሻለ ለመራመድ ደግሞ ልምድ ያስፈልገን ነበር። ያ ልምድ ደግሞ በአንድ ምሽት አይመጣም።” ሲሉም አስረድተዋል።
ቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ በኮትዲቯር አስተናጋጅነት የሚካሄደው ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ነው። በዚህ አፍሪካ ዋንጫ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያንም በቀጣይ የመሳተፍ እድል ይኖራቸዋል። ይህም አሁን ትልቅ ክፍተት ሆኖ የታየው የልምድ ጉዳይ ነገ መነሳት የሚችል ሰበብ አይሆንም። ለዚህ ደግሞ አሰልጣኝ ውበቱ የጀመሩት የቡድን ግንባታ ተጠናክሮ መቀጠሉ ትልቅ ዋጋ ይኖረዋል።
እንዳለፉት ዓመታት ፌዴሬሽኑ አሰልጣኝ በየጊዜው የመቀያየር ልማዱን ካላጤነው ግን ነገም እንደ አዲስ በአዲስ አሰልጣኝ አዲስ የቡድን ግንባታ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ እንዳይሆን ሊታሰብበት ይገባል። የገነቡትን እየናዱ አዲስ ለመገንባት ከመጣር ይልቅ ጊዜ መስጠትና አሁን ያሉ ክፍተቶችን ማረም የተሻለው አማራጭ እንደሚሆን ይታመናል።
በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈው የዋልያዎቹ ስብስብ ቀጣዩን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲያልፍና የቡድኑን ግንባታ ለማጠናከር ያሉትን አማራጮች ሁሉ በአግባቡ መጠቀምም ያስፈልጋል። ለዚህም በአገር ውስጥ ሊጎች ብቻ የሚሳተፉ ተጫዋቾች የሚፋለሙበት የአፍሪካ ዋንጫ(ቻን)፣ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ(ሴካፋ) እንዲሁም የተለያዩ የማጣሪያና የወዳጅነት ጨዋታዎች ትልቅ ግብዓት እንደመሆናቸው በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 11/2014