የእኛ የራሳችን የሆነ ከሌሎች የሚለየን በራሳችን ጥበብ ተቃኝቶ የአኗኗር ዘይቤያችን ተቀድቶ ተጎናፅፈነው የሚያምርብን ጥበብ ተላብሰነው የምንደምቅበት የባህል ልብሳችን መለያችን ነው። በበዓል ወቅት እምር ድምቅ ብለን የምንታይባቸው የባህል ልብሶቻችን በተለይም በገናና ጥምቀት በዓላት ላይ የሁሉም ምርጫ ይሆናሉ።
ጥጡ ከማሳ ተለቅሞ፣ በእናቶች በጥንቃቄ ተፈልቅቆና ተፈትሎ ወደ ሸማኔው ይላካል። ሸማኔው ለዘመናት ባካበተው ልምዱ አቅልሞ ወድሮና በመወርወሪያው ሸምኖ ለገበያ ያቀርበዋል። ጥበቡን ተጠቅሞ ጥለቱን ያበጀዋል። የፋሽን ዲዛይነሩ ደግሞ ዘመኑ የሰጠውን እውቀትን ተጠቅሞ በልምድ ካገኘው ክህሎቱ ገር አዋዶ ጥበብ ላይ ጥበቡን ደርቦ ለልብስነት ያበቃዋል።
ዲዛይነሮቻችን ተለብሶ የሚያምር ተጎናፅፈውት የሚያስውብ ድንቅ የባህል ልብስ በታዘዙት መልክ ለደንበኞቻቸው ያዘጋጃሉ፤ እንደየፍላጎታቸው በሰውነታቸው ልክ አንዲያሳምራቸው አድርገው ያቀርባሉ። አላምደው በብዙዎች እንዲወደድ ያደርጉታል። ያኔ ፋሽን ይሆናል።
የሀበሻ ልብስ ዋንኛ መታያ ጊዜው የበዓል ወቅት ነውና አሁን ላይ ገናን በቀጣይ ደግሞ ሀበሻዊ አልባሳት የሚነግሱበት ጥምቀት በዓላት ላይ የሀገር ባህል አልባሳት ከተሞቻችንን ያጥለቀልቃሉ፤ አልባሳቱን የተጎናፀፉ ሰዎች መንገዶች ሞልተው ይታያሉ። የባህል አልባሳት ተጣጥፈው ከተቀመጡበት ሳጥን ይወጣሉ፤ ተሸጉጦ ከከረመበት ቅርጫት በማውጣት አጥበውና ተኩሰው ከሰው ጋር ይቀላቀሉበታል።
ወጣቶች እንደቀደመው ጊዜ የተዘጋጁ የውጪ አገር ልብሶች ከመልበስ የአገር ባህል አልባሳት በተለያየ መልክና በሚፈልጉት ዲዛይን አሰርቶ መልበስ ተላምደዋል። ይህ ደግሞ አገራዊ አልባሳት ወደገበያው በዝተው እንዲቀርቡ በማድረግ በኢኮኖሚና ባህል እድገቱ ላይ ታላቅ አዎንታዊ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል። በሙያው ዘርፍ ያሉ ተዋንያንም ተጠቃሚና በብዙ መልኩ ራሳቸውን የመለወጥ እድሉን ያሰፋላቸዋል።
ሳራ አየልኝ ጨርቆስ የገበያ ማዕከል ውስጥ የአገር ባህል አልባሳትና የሽፎን መሸጫ ሱቅ ባለቤት ናት። በበዓላት ወቅት የደንበኞቿ ቁጥር እንደሚጨምርና በአብዛኛው በትዕዛዝ የአገር ባህል ልብስና የተለያየ ጥልፎች እንደሚያሰሩ ትገልፃለች። በፊት ላይ በግምት ተሰርቶ በመስቀያዎች የተቀመጡ የአገር ባህል ልብሶች ሰዎች ገዝተው ይወስዱ እንደነበር ትናገራለች፤ አሁን ላይ ዲዛይነሮች በመበራከታቸውና የሰው ምርጫ እየጨመረ በመሄዱ ምክንያት አብዛኛው ሰው ቀደም ብሎ ትዕዛዝ አንደሚሰጥና በዚያው መሰረት እንደሚያዘጋጁ ታስረዳለች።
ይህ ወቅት ሰው ብቻ ሳይሆን ሱቁችም በባህል ልብሶች ይዋባሉ። የባህል ልብስ አልባሳት መሸጫዎች በዓላቱ የደንበኞቻቸውን ቀልብ አማለው ገበያቸው እንዲደራ ብርቱ ጥረት ያደርጋሉ። ያቀረቡት በሰዎች እንዲመረጥ የሚጥሩበት ወቅት ነውና የአገር ባህል አልባሳት በመስቀያዎች ቦታ ይዘው ተጠቃሚ አይቶ ይወዳቸው ዘንድ፤ ገዝቶ እንዲጠቅማቸው ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ። በዚያውም ገበያው ይደራል።
የበዓል ድባብ የሚስተዋልበት የሳራ ሱቅም በተዘጋጁ የባህል ልብሶች ሞልቷል። በሱቆቿ ውስጥ ከሁለት ሺህ አምስት መቶ እስከ 32 ሺ ብር ድረስ በተለያየ ዲዛይንና ቀለም የተዋቡ የአገር ልብሶች እንዳሉ የምትናገረው ሳራ፣ ከሁለት የልብስ ዲዛይን ባለሙያዎች ጋር እንደምትሰራና ከደንበኞቿ በምርጫቸው የተቀበለችው ዲዛይን በራስዋ ዲዛይነሮች እንደምታሰራ ትናገራለች።
ከእለት ወደ እለት እያደገ በሚሄደው የፋሽን እንዱስትሪ ውስጥ የአገር ባህል ልብሶች ተመራጭና በብዙዎች ተፈላጊ እንዲሆኑ የፋሽን ዲዛይን ባለሙያዎቻችን ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን የምትናገረው ሳራ፣ የገበያው ለውጥና የአገር ባህል ልብሶች ተፈላጊነት በራስዋ ማየት መቻልዋን በአስረጂነት ታቀርባለች።
ለአገር ባህል ልብሶቹ ተፈላጊነት ማደግና በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ መሆን የዲዛይነሮቹ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። ዲዛይነር ሮዛ ተስፋዬ የአገር ባህል ልብሶች በተለይም በበዓላት ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚለበሱና አሁን አሁን ደግሞ በአዳዲስ ዲዛይንና ተመራጭ ቀለሞች መቅረባቸው ለመልበስ ምቹ መሆኑ ምክንያት እንደሆነ ታስረዳለች።
በተለይም ከእናቶች እስከ ሸማው በጎጆ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተፈልቅቆ፣ ተባዝቶ፣ ተቀልሞና ተሸምኖ ከዚያም የዲዛይነሮች እሴት ታክሎበት ለገበያ የሚቀርበው የአገር ባህል ልብስ በተጠቃሚው ዘንድ ተፈላጊነቱ ማደጉ ለአገራዊ ዕድገቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ዲዛይነር ሮዛ ትገልፃለች።
በዚህም አገራዊ ኢኮኖሚን በመደገፍ የዘርፉን ተዋናዮች ገቢም ከፍ ማድረግ ያስችላል። ይህን ማድረግ ይቻል ዘንድ ደግሞ የዘርፉ ባለሙያዎች የዘመኑን ፋሽን ኢንዱስትሪ ጠንቅቀው የተረዱ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ውበት ጥራትና ወቅታዊነት በፋሽን እንዱስትሪው ወሳኝ ጉዳዮች መሆናቸውን የምትገልፀው ዲዛይነር ሮዛ፤ የፋሽን ዲዛይን ባለሙያዎች ህብረተሰቡ በሚፈልገው መልኩ አዳዲስ ፈጠራ የታከለባቸው አልባሳት አሰናድቶ ማቅረብ የሚኖርባቸው መሆኑን ትናገራለች።
በአገር ደረጃ ገና ታዳጊ የሆነው የፋሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ማደግ እንዲችል የባህል አልባሳትና በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች በተለያየ ዲዛይን አምርቶ ማቅረብ በህብረተሰቡም ተመርጠው እንዲለበሱ ማድረግ ይገባል የምትለው ዲዛይነር ዊንታ በልሁ ናት።
የዲዛይን ባለሙያዎች የተጠቃሚው ፍላጎት ቀስ በቀስ እየተረዱና አዳዲስ ፈጠራዎች ማከላቸው ጠቀሜታ እንዳለውም ትገልፃለች። በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን ጎን የሚገኘው ገበያ ማዕከል ውስጥ ከጓደኞችዋ ጋር የተለያዩ የልብስ ዲዛይኖችና ጥልፎችን በመስራት የምትተዳደረው ዲዛይነር ዊንታ፣ ማህበረሰቡ በተለይ በበዓላት ጊዜ የባህል ልብሶች ማዘውተር መጀመሩ የዲዛይነሮች አዳዲስ ፈጠራ ማከል እንደ ምክንያት ትጠቅሳለች።
በፋሽን ኢንዱስትሪው ብዙ መጓዝ የሚቀራት ኢትዮጵያ በራስዋ ልጆች ልዩ ጥበብ የሚመረቱት ባህላዊ አልባሳት በፋሽን መልክ ተወደው ተለምደውና ተመርጠው እንዲለበሱ ማድረግ ጥቅሙ እጅግ በጣም የበዛ ነው እንደ ባለሙያዎቹ። የራስን ባህል ከማስተዋወቅ ባለፈ የገቢ ምንጭን በማሳደግ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው። የአገር ባህል አልባሳት በፋሽን ገበያው አሁን ካለው የተሻለ ተቀባይነት እንዲያገኙና በስፋት ወደገበያው እንዲገቡ እንቅፋት የሚሆኑ ምክንያቶች ካሉ የጠየቅናቸው ባለሙያዎቹ የራሳቸውን ሀሳብ ይሰጣሉ።
ማህበረሰቡ በተለይ የአውዳመት ሰሞን አገር ባህል ልብሶች ለመልበስ ከፍተኛ ፍላጎት ያለው መሆኑን የምታስረዳው ዲዛይነር ዊንታ፣ ነገር ግን የሚዘጋጁ የባህል ልብሶች የሚፈጁት ጊዜና የሚወስዱት የጥሬ እቃ ብዛት ከፍ ማለት ዋጋው ውድ እንዲሆን እንዳደረገው ታስገነዝባለች። ይህ ደግሞ ማህበረሰቡ የአገር ባህል ልብሶች መልበስ ቢፈልግም አቅም ያላገናዘበ በመሆኑ ይተወዋል ስትል ታብራራለች።
አውዳመትን በልዩነት እንድንታይ የሚረዱን የሀገር ባህል አልባሳት በአገር ውስጥ ጥበበኞች በተለያየ መልክ ተሸምነውና ተሰርተው፤ ወደ ፋሽኑ ኢንዱስትሪ ተቀላቅለው ተመርጠው እንዲለበሱ በዲዛይነሮች ንድፍና ልዩ ክህሎት ተቀምረው በሰፊዎች ተሰናድተው የሚቀርቡበት ሁኔታ ይበልጥ መጠናከር ይኖርበታል። እነዚህ የአገር ባህል አልባሳት በአገር ውስጥ ገበያ አልያም ደግሞ በዓለም ገበያዎች ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ አሁንም የተጠናከረ ስራ መስራት ያስፈልጋል እንላለን። አበቃሁ! ቸር ያሰማን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥር 9/2014