ማልዶ ከቤት የወጣው ልጅ አሁንም አልተመለሰም። ከበር ቆመው አሻግረው የሚቃኙት እናት ተስፋ አልቆረጡም። መምጣቱን ናፍቀው ድምጹን ጠበቁ። መድረሱን እያሰቡ የወጣበትን ጊዜ አሰሉት። እንደዛሬው ቆይቶ አያውቅም። ተጨነቁ።
አንጀታቸው ሲንሰፈሰፍ ልባቸው ሲመታ ተሰማቸው። የነሐሴ ዝናብ መጣሁ እያለ ነው። ቀኑን አኩርፎ የዋለው አየር ማምሻውንም ቀጥሏል። አስፈሪው ድምጽ በነጎድጓድ ብልጭታ ታጅቦ ጨለማውን ይሰነጥቃል። ማካፋት የጀመረው ዝናብ ሀይሉን ጨምሯል። ደጁ በእርጥበት እየራሰ፣ እየረሰረሰ ነው።
እናት እየወጡ፣ እየገቡ በደጁ ተመላለሱ። አዲስ ነገር የለም። የውሾች ጩኸት እየበረታ፣ ጨለማው እየገፋ በሄደ ጊዜም ተስፋ አልቆረጡም። የምሽት ጨረቃ ደምቃ እስክትታይ ዓይኖቻቸውን ከአንድ አቅጣጫ ተከሉ። ኮቴ እያዳመጡ፣ ድምጽ እየለዩ አዲስ ነገር ጠበቁ። አሁንም አንድዬ ልጃቸው ብቅ አላለም።
በትካዜ የሚብሰለሰሉት እናት ልጃቸው በዓይናቸው እየዞረ፣ በዓይምሯቸው ሲመላለስ ቆም ብለው አሰቡት። እሱን ለማሳደግ ብዙ ለፍተዋል፣ ደክመዋል፣ ያለ አባት፣ ያለአጋር ጎጆ ማቆም፣ ልጅ ማሳደግ ቀላል አልነበረም። ልጃቸውን በስርዓት ለማነጽ፣ ከእኩዮቹ ላለማሳነስ ጉልበት፣ ዕድሜያቸውን ከፍለዋል።
ጥሪታቸውን አፍሰዋል። አንዱ ፍሬ ‹‹የሴት ልጅ›› እንዳይባልባቸው ሌት ቀን ለፍተዋል። አሁን ህልማቸው መና አልቀረም። የደከሙበት ተሳክቶ፣ ያሰቡት ዕውን ሆኗል። ልጁ ከጉርምስና ዕድሜ ደርሷል። ብዙዎች ስለሴትዬዋ ልጅ መልካሙን፣ በጎውን ይናገራሉ። እሱ ያለ አባት እንደማደጉ ፈጽሞ አይቀብጥም፣ አንዳንዶች እንደሚሉትም ‹‹የሴት ልጅ›› ሆኖ አያውቅም።
ሰው ቤት አይሄድም፣ ርቆ አይላክም፣ እንደእኩዮቹ ከመጠጥ ቤት መታየት ልምዱ አይደለም። ከልጅነቱ እስከ አሁን ዕድሜው ሥርዓት ይዞ ቀጥሏል። እናት ይህን ሁሉ ሲያስቡ ግራ ገባቸው። ጨዋ የተባለው ልጅ ያለልምዱ ውሎ ማምሸቱ አዲስ ሆኖ ያስጨንቃቸው ያዘ። አሁንም ያለመታከት መጠበቃቸውን ቀጠሉ። ሌቱ ተጋምሶ ንጋት እስኪቃረብ ተስፋ አልቆረጡም። ከጨለማው አፍጥጠው፣ ከደጁ እንደቆሙ የወፎች ድምጽ ተሰማ።
ነሐሴ 7 ቀን 2009
በሳር ጎጆው ዙሪያ የተሰበሰቡት ነዋሪዎች ባዩት በሰሙት ጉዳይ አዝነዋል። ምሽቱን በስፍራው የተፈጸመው ድርጊት የብዙዎችን ልብ እንደሰበረ ነው። አብዛኞቹ ደረታቸውን እየደቁ ያለቅሳሉ። ጥቂት የማይባሉት ራሳቸውን በእጃቸው ይዘው ከወዲያ ወዲህ ይላሉ። ጎጆው ቀን ከገበያ ለሚውሉ ሰዎች የጠላ መሸጫ ሆኖ ነው። በዚህ ስፍራ ሁሌም ገዥና ሻጭ አረፍ ይላሉ። ባለጠላዎቹ ከሚቀዱላቸው እየተጎነጩም የልባቸውን ያወጋሉ። ጀንበር አዘቅዝቃ ወደመጡበት እስኪመለሱ ስፍራው የብዙዎች ድካም ማሳረፊያ ነው። ዛሬ ግን የጎጆው ልማድ እንደወትሮው አልሆነም። በውስጡ የሚታየው እውነት ለተመልካች ሰቀቀን ሆኖ በርካቶችን እያስለቀሰ ነው።
ትናንት ምሽት ከስፍራው የደረሱት ፖሊሶች ጎጆውን ከፍተው ሲገቡ የተባለው ጥቆማ እውነት መሆኑን ተረዱ። አንድ ወጣት በአቧራማው የጎጆው ወለል ተዘርግቷል። ጠጋ ብለው ትንፋሹን አዳመጡ። ሕይወቱ ካለፈ ሰዓታት ተቆጥረዋል። ዙሪያ ገባውን እየቃኙ አካባቢውን አጤኑ። ከሟች አጠገብ የተቀመጠው የብረት ከዘራ በአንድ ጎኑ ተወላግዶ ይታያል።
ፖሊሶቹ አስቀድሞ ሀይል የተመላ ድርጊት እንደተፈጸመበት ገመቱ። ከወደጫፉ በቆዳ የተለበጠው ከዘራ ባለቤት እንዳለው ያሰቡት ፖሊሶች እርስበርስ ተያዩ ። ከዘራው በትክክል በአንድ ሰው እጅ ላይ ይታወቃል። ፖሊሶቹ ያስተዋሉትን በማስታወሻቸው መዝግብው ወደቀጣዩ አመሩ። ሟች በቀኝ ግንባሩ ላይ ያረፈበት ምት ክፉኛ ጎድቶታል። አንገቱ በስለት በመታረዱ ስፍራው በደም ርሷል። ከአቧራው ላይ የወደቀውን ሰው ማንነት በወግ ያላወቁት ፖሊሶች ተገቢውን ምርመራ እንዳጠናቀቁ ስለማንነቱ ጠየቁ። ስምና አድራሻውን
ለማወቅ አልተቸገሩም። የአካባቢው ተወላጅና የመንደሩ ነዋሪ መሆኑ ተነገራቸው። አሁን ፖሊሰ የሟች ሰም ወጣት አስፈሪ ገበየሁ መባሉን አውቋል። ዕለቱን ከቤት እንደወጣ ያለመመለሱን ከቤተሰቦቹ ጠይቆ ተረድቷል። በስፍራው አስፈላጊ መረጃዎች ከተሰነዱ በኋላ የተሟላ የምርመራ ቡድን ተዋቀረ። ሀሳቦች እየተመዘዙ፣ ጉዳዮች እየተነሱ ውይይት፣ ምክክሩ ተጀመረ። በሰሜን ሸዋ ዞን የአገረ ማርያም ከሰም ወረዳ ፖሊስ አባላት ሰብሰብ ብለው እየመከሩ ነው።
እስካሁን በ ‹‹ቁም ድንጋይ›› ቀበሌ በአንድ የሳር ጎጆ ውስጥ ስለሆነው ድርጊት ፍንጭ አልተገኘም። ከሟች ማንነት በቀርም ስለወንጀሉ ሁኔታ የጠቆመ አልተገኘም። ፖሊሶች ተጨንቀዋል። የአካባቢው ሰው በሀዘን አንገቱን ደፍቷል። ይህን አስከፊ ወንጀል ማን ፈጸመው ? ይሉት ጥያቄ ለሁሉም ራስ ምታት ሆኗል። አሁን የሟች አስከሬን ከወደቀበት ተነስቶ በክብር አርፏል።
ሀዘንተኞች በቤታቸው ሆነው ጉዳዩን ማብሰልሰሉን ቀጥለዋል። አንዳንዶች ከመላ ምት ተነስተው ያሻቸውን ይገምታሉ። የፖሊሶቹ ዓይንና ጆሮዎች የሚመጡ መረጃዎችን አይንቁም። የሚሰማውን ሁሉ በአግባቡ ያስቡታል። የሚያጠራጥራቸውን መዝገብ ከፍተው በስልት ይመረምሩታል። የፖሊስ ምርመራና ክትትሉ ቀጥሏል። በወጉ የተዋቀረው ቡድን ሌት ተቀን ዕንቅልፍ የለውም። ፍንጭ ለማግኘት፣ መረጃዎችን ለመጨበጥ ሲሮጥ ይውላል። ‹‹የእከሌ ነው›› የሚል አስረጂ ባይመጣም የብረት ከዘራውን ባለቤት ለማግኘት አሰሳው ቀጥሏል። ቀናት ያስቆጠረውን አሰቃቂ ወንጀል የሚጠቁም ቀዳዳ ግን አልተገኘም። የምርመራ ቡድኑ አባላቱ አሁንም ፈታኝ መንገዶችን እያለፉ ነው።
የሟች ቤተሰብና የመንደሩ ነዋሪ የሚፈልገውን እውነት ለማስጨበጥ እልህ አስጨራሹን ትግል ቀጥለዋል። እስካሁን የሟች ገዳይን የሚጠቁም ፍንጭ አልተገኘም። ያም ሆኖ ተስፋ አልቆረጡም። በጀመሩት ጥረት ፍለጋቸውን ተያያዙት።
ፍንጭ …
ከዕለታት በአንዱ ቀን ከፖሊሶች ጆሮ የደረሰው አዲስ መረጃ የተለየ ትኩረት አገኘ። ስለ ወንጀሉ መፈጸም ያውቃል የተባለ ሰው በመንደሩ እንዳለ ተሰማ። የቡድን አባላቱ ጊዜ አላጠፉም። ይህን እውነት ያውቃል የተባለውን ሰው በፍጥነት ጠርተው በጥያቄ ያጣድፉት ያዙ። ፖሊስ በሰው ማስረጃነት የቀረበውን ሰው ስለግድያው ሁኔታ ደጋግሞ ጠየቀው። ሰውዬው ለምላሹ ጥቂት አንገራገረ።
ሰውዬው ከዚህ ቀደም ለሕይወቱ በመፍራት ጥቆማ መስጠት አልቻለም። አሁን በሕግ ጥላ ስር ነው። ፖሊስ እውነታውን ያስረዳ ዘንድ በትዕግስት ጠበቀው። ተጠያቂው እምብዛም ሳይቆይ አየሁት ያለውን ድርጊት አንድ በአንድ ማስረዳት ጀመረ። ወንጀሉ በተፈጸመበት ምሽት ከጎጆው በር ላይ ያየውን እውነት አልዘነጋም።
ቅድመ- ታሪክ…
ወጣቱ ለዓመታት ሲሰማው የቆየው ታሪክ ሲረብሸው ቆይቷል። እውነታው ውስጡ ውሎ ባደረ ቁጥር ሰላም አልሰጠውም። ተኝቶ ሲነሳ፣ ተቀምጦ ሲራመድ ሁሉ ጉዳዩን ያሳስበዋል። በየቀኑ የሚብሰለሰልበትን ታሪክ ከብዙዎች ሰምቶ አረጋግጧል።
ጉዳዩን ባወቀ ጊዜ ዓይኖቹ ከአንድ አቅጣጫ አርፈዋል። ደሞዝ ተሰማ ከዓመታት በፊት በሞት ያጣውን ወንድሙን ረስቶት አያውቅም። ባስታወሰው ቁጥር ዕንባ ባይኑ ይሞላል፤ ቁጭት ንዴትና ብስጭት ይይዘዋል። ከሞቱ የአሟሟቱ ሚስጥር ሰላም አይሰጠውም። የእሱን ማለፍ ተከትሎ በአካባቢው የሚናፈሰው ወሬ ደግሞ ይበልጥ ስር ይዞ ውስጡን ሲሞግተው ኖሯል።
ደሞዝ የወንድሙ ገዳይ ነው የተባለውን ሰው ለይቶ አውቋል። ሁሉም በየቤቱ ጉዳዩን ባወራው ቁጥር ብሽቀት ይይዘዋል። እሱ እያለ የወንድሙ ደም መና እንደማይቀር በገባው ጊዜም ከስሜቱ ጋብ ብሎ ቀጣዩን ዕቅድ ያስባል። አዎ! ‹‹እኔ እያለሁ የወንድሜ ደም መና አይቀርም›› ሲል ለራሱ ይነግረዋል። ከውስጡ በተሰማማ ቁጥር አሻግሮ እያሰበ፣ አጥብቆ እያቀደ የሚሆነውን ይወጥናል። ፈገግ፣ ኮስተር እያለም ራሱን ከሌሎች፣ ሌሎችን ከራሱ ያናብባል። ደሞዝ ለዕቅዱ መሳካት ካሰባቸው ባልንጀሮቹ ሁነኛ ያላቸውን መርጦ ለይቷል። የተመረጡት አጋሮች ከሌሎች ልቀው ሚስጥር እንደሚጠብቁ እርግጠኛ ነው። በእሱ ዕምነት ባልንጀሮቹ የዓመታት ቋጠሮውን ይፈታሉ። እልሁን ይወጣሉ፣ ዕንባውን ያብሳሉ።
ደሞዝ አስፈሪ ከተባለው የሰፈሩ ልጅ ጋር አፈር ሲፈጭ፣ ውሃ ሲራጭ አድጓል። ሁለቱ ከልጅነታቸው ጀምሮ የተለየ ቅርበትና ፍቅር አላቸው። በጎጥ በመንደሩ እንደአካባቢው ልጆች ሲቦርቁ፣ ሲደሰቱ ኖረዋል። ደሞዝ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በአስፈሪ ላይ የተለየ ስሜት ይታይበት ይዟል። ባየው ቁጥር ውስጡ ይበሽቃል፤ ፊቱ ይለወጣል ። ደሞዝ የአስፈሪ አባት ወንድሙን እንደገደለበት ካወቀ ወዲህ ውስጡ እየጎሸ ተቸግሯል። ለማስመሰል የሚያሳየው ፈገግታ ለጊዜው የውስጥ ትኩሳቱን ቢያበርድም አብሮት ሊቆይ አልቻለም። ጠዋት ማታ ያሰበውን ለመፈጸም መላና ዘዴ ይቀይሳል። የወንድሙን ገዳይ በአብሮ አደጉ ለመበቀልና ደሙን ለመወጣት ጊዜ እያመቻቸ ቀን እየቆጠረ ነው።
ለዚህ ዓላማው በአጋርነት ያሰባቸው ሁለቱ ሰዎች ሀሳቡን ካጸደቁለት ቆይተዋል። ሟች ወንድሙ ከሌሎች ህሊና ተረስቷል። ከእሱ ልቦና ግን ለአንድም ቀን ጠፍቶ አያውቅም። ሞቱን የሚበቀልለት ደሙን የሚወጣበት ደግሞ የገዳዩን ወንድ ልጅ በመግደል ብቻ ነው። ለዚህ ዕቅዱ ዕውን መሆን የታጨው አስፈሪ የቅርብ ጓደኛውና አብሮ አደጉ እንደሆነ አላጣውም። ያም ቢሆን ከሟች ወንድሙ አይበልጥም። ቂምና እልሁን ሊወጣበት ደሙን ሊከፍልበት ቤዛ ይሆናል።
ውሎው …
ደሞዝና ሁለቱ ጓደኞቹ በቀጠሯቸው ቀን ተገናኝተዋል። ደሞዝ ወደ እነ አስፈሪ መንደር ማልዶ ገስግሷል። ባልንጀራው ስለስራ ጉዳይ የነገረውን ሁሉ ስላመነው ደስ ብሎታል። አስፈሪ ጓደኞቹ ባገኙለት ስራ ጥቂት ገንዘብ ቢቆጥር አይከፋውም። እነሱን ተከትሎ ከመንደሩ ሲርቅ ልቦናው አንዳች አልጠረጠረም።
ደርሶ የሚመለስበትን ጊዜ እያሰላ ከጎናቸው ተራመደ። አስፈሪ ሶስቱን ባልንጀሮች ተከትሎ ‹‹ሾላ ገበያ›› ከተባለ ከተማ ደረሱ። በደሞዝ ጋባዥነት የተጀመረው ቁርስ እስከ ምሳ ዘልቆ በስፍራው ሲዝናኑ ቆዩ። ከቀትር በኋላ በከተማው እየተዘዋወሩ ሻይ ቡና ማለታቸው አልቀረም።
ሶስቱ ምክክራቸውን ለመተግበር ጊዜው መድረሱን ባወቁ ጊዜ ወደ መንደራቸው መመለስ እንዳለባቸው ተናገሩ። አስፈሪም ቢሆን ከሀሳባቸው አልተነጠለም። የተባለው ስራ እንደታሰበው ባይገኝም በጊዜ ቤቱ ለመግባት አብሯቸው ተነሳ። ከተማውን ለቀው የመንደራቸውን አቅጣጫ ሲጀምሩ ጊዜው ለዓይን መያዝ ጀምሮ ነበር። ደሞዝ በጨዋታ መሀል ጓደኞቹን ወግደረስንና ካሳን አስተዋላቸው። ሁለቱም ለጉዳዩ ዝግጁ መሆናቸው አረጋገጡለት። አራቱ ሰዎች ፊትና ኋላ ሆነው መጓዛቸውን ቀጥለዋል። አሁን የምሽት ጨረቃ በደመና ተሸፍና እየወጣች ነው።
መንገደኞቹ ጉዟቸውን ቀጥለው ‹‹ቁም ድንጋይ›› ከተባለ ስፍራ ደርሰዋል። ባሻገር በገበያ ቀን ጠላ የሚሸጥበት የሳር ጎጆ ይታያል። ሶስቱ ሰዎች ጎጆው አጠገብ ሲቃረቡ ሊያልፉት አልፈለጉም። አስፈሪን ከፊት አስቀድመው ተከታትለው ገቡ።
ከአቧራማው የሳር ጎጆ እግሩ የቀደመው አስፈሪ ወደውስጥ ከመዝለቁ ከቀኝ ግንባሩ ላይ በብረት ከዘራ ከባድ ምት ሲያርፍበት ተሰማው። በድንጋጤ እየጮኸ እንዲተውቱ ተማጸናቸው። ማናቸውም ለቅሶና ጨኸቱን ሊሰሙ አልፈለጉም። ተረባርበው ከመሬት ጣሉት። ደሞዝ የሟችን እግሮች ጠፍሮ እንደያዘ ወግደረሰ ፈጥኖ እጆቹን በመያዝ ተባበረው።
ይሄኔ ካሳ የተባለው ጓደኛቸው በያዘው ጩቤ የአስፈሪን አንገት መገዝገዝ ጀመረ። የሰላ ስለት ያረፈበት የወጣቱ አንገት በደም ለመጥለቅለቅ አልዘገየም። ይህን ያስተዋሉት ባልንጀሮች በያዙት መደቀኛ የሚፈሰውን ደም በመቅዳት ከሁለት ሊትር ተኩል በላይ ደም አጠራቀሙ። የቀዱትን ደም በጥንቃቄ ይዘውም ለመሸጥ ተስማሙ። ባልንጀሮቹ የብረት ከዘራውን ትተው የገደሉበትን ትልቅ ጩቤ ይዘው ከስፍራው ራቁ። እንደበግ ያጋዳሙትን የሟች አስከሬን ከጎጆው ጥለው ወደሾላ ገበያ ከተማ ሲመለሱ ከምሽቱ አንድ ሰዓት እያለ ነበር።
የፖሊስ ተጨማሪ ምርመራዎች…
ቃል ሰጪው በሰጠው ፍንጭ መሰረት የብረት ከዘራው ካሳ አድነው የተባለ ግለሰብ ንብረት መሆኑ ታወቀ። ፖሊስ ከሶስቱ ተጠርጣሪዎች የአንደኛውን ማንነት እንዳረጋገጠ አሰሳውን በስፋት ቀጠለ። በውጣውረድ የተፈተነ፣ በታላቅ ጥረት የታገዘ ውጤት ተከተለ።
ከቀናት በኋላ የምርመራ ቡድኑ ሶስቱን ተፈላጊዎች ከእጁ አስገባቸው። ሁሉንም ከያሉበት አድኖ በቁጥጥር ስር አዋላቸው። የዞኑን ዓቃቤ ሕግ ጨምሮ መላው የጸጥታና የፖሊስ አካላት የተሳተፉበት የምርመራ ሂደት በአመርቂ ፍሬ ተጠናቀቀ። ዋና ኢንስፔክተር አለማየሁ ሀይሌና ሳጂን ሳለሁ አላዬ ከሌሎች አካላት ጋር የተሳተፉበት የወንጀል ምርመራ በበቂ ማስረጃዎች ተሰንዶ ወደዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተላለፈ።
ውሳኔ…
በዕለተ ቀጠሮው በችሎቱ የተሰየመው የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቂም በቀል መነሾ የወጣቱን ሕይወት በግፍ የነጠቁ ተከሳሾችን ጉዳይ ማየት ጀምሯል።
የተሰየመው የመጨረሻ ችሎት ውሳኔ የሚሰማበት በመሆኑም በርካቶች ታድመዋል። ፍርድ ቤቱ ሶስቱ ተከሳሾች በፈጸሙት ከባድ የግድያ ወንጀል ጥፋተኝነታቸውን በበቂ ማስረጃዎች አረጋግጧል።
በዕለቱ በሰጠው ብይንም አንደኛ ተከሳሸ በዕድሜ ልክ እስራት፣ እንዲሁም ሁለተኛና ሶስተኛ ተከሳሾች በሃያ ሁለትና ሃያ ሶስት ዓመት ጽኑ እስራት ይቀጡልኝ ሲል ወስኗል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጥር 7/2014