የተወለዱት ጅባትና ሜጫ አውራጃ ደንዲ ወረዳ አቤቤ ቄሬንሳ የሚባል ቀበሌ ውስጥ ነው። ስድስት ዓመት ሲሞላቸው ወደ አዲስ አበባ የመጡ ሲሆን ልዑል ሳህለ ስላሴ ትምህርት ቤት ገብተው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ተማሩ። በዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ተከታትለዋል። በመቀጠልም ከኢትዮጵያ መብራት ሃይል ማሰልጠኛ ተቋም በኤሌክትሪክ ቴክኖሎጂ ዲፕሎማቸውን አግኝተዋል።
ሥልጠናቸውን እንዳጠናቀቁ ሰቲት ሁመራ ስራ ተመድበው ለሦስት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ 1981 ዓ.ም በወያኔ ሃይሎች ባደረጉት የመስፋፋት ወረራ ምክንያት ጥለው ለመውጣት ተገደዱ።
በኋላም ደብረ ማርቆስ ተመድው ለጥቂት ወራት የሰሩ ሲሆን በጥያቄያቸው መሰረት አዲስ አበባ ደቡብ ዞን ተመድበው ማገልገል ቀጠሉ። በአገሪቱ የመንግስት ለውጥ ከመጣ በኋላም እኚሁ ሰው በሚሰሩበት ተቋም ውስጥ በነበራቸው ቅልጥፍና ታታሪነት በሰራተኛ ማህበር ውስጥ ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ተመረጡ። ሆኖም እንግዳችን ያመኑበትን በድፍረት የሚናገሩና ለእውነትም የሚሞግቱ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ከሕወሓት አመራሮች ጋር መግባባት አቃታቸው።
በተለይም በሰራተኞች ላይ የሚፈፀመውን ግፍ በማጋለጣቸውና በመቃወማቸው ምክንያት በወቅቱ ከነበሩት የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር መላተም ያዙ። ይህ አለመግባባት እያደገ መጣና ከስራ እስከመባረርና ከአገር እስከመውጣት ደረሱ። ላለፉት 24 ዓመታት በአውስትራሊያ ኑሯቸውን ያደረጉት እንግዳችን ካሉበት ሃገር ሆነውም ከፋፋዩን ስርዓት ሲቃወሙና ሲያጋልጡ ነው የኖሩት።
የለውጡን መምጣት ተከትሎ ደግሞ ከሁለት አስርተ ዓመታት የስደት ኑሮ በኋላ ሃገራቸው መግባት የቻሉ ሲሆን ለውጡ እንዳይቀለበስና ለተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ቀጣይነት በገንዘብ ሲደግፉና ዲያስፖራውን ሲያስተባብሩ ቆይተዋል።
ሕወሓት በከፈተው ጦርነት የተጎዱ ዜጎችን ለመርዳት በማለምም ዳግመኛ ወደ አገራቸው የመጡት እኚሁ ሰው በተለይም በአፋርና አማራ ክልሎች በአሸባሪ ቡድኑ የደረሱትን ጉዳቶች ተዘዋውረው ተመልክተዋል። በተጨማሪም ከአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ያሰባሰቡትን 225 ሺ ዶላር ለሚመለከተው የመንግስት አካል አስረክበዋል።
የዛሬው የዘመን እንግዳችን በአውስትራሊያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተቋቋመው ኢትዮጵያን እንታደግ (save Ethiopia) የተሰኘ የበጎ አድርጎት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አያሌው ሁንዴሳ ናቸው። በህይወት ተሞክሯቸውና በሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከጋዜጣችን ጋር ያደረጉትን ውይይት እነሆ ብለናል።
አዲስ ዘመን፡-ከአገር የወጡበትን አጋጣሚ ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ አያሌው፡- እንደሚታወቀው ሕወሓት አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ካደረጋቸው ተግባራት አንዱ የነበሩትን ተቋማት ማፍረስ ነበር። ደርግ ይገለገልበት የነበሩት የይስሙላ ማህበራት በሙሉ አፈረሰና እንደገና በራሱ አምሳል ሊጠፈጥፍ ሞከረ። የኢሰፓን ሰራተኛ ማህበር አፍርሶ በኢህአዴግ ሰራተኛ ማህበር ለመተካት ሲሞክር ብዙ ቦታ አልተሳካለትም ነበር። ካልተሳካላቸው መስሪያ ቤቶች አንዱ መብራት ሃይል ነበር።
በአጋጣሚ ደግሞ መብራት ሃይል የሰራተኛ ማህበር ሲቋቋም እኔ በሰራተኛ ማህበሩ ስራአስፈጻሚነት ተመረጥኩኝ። በሌላ በኩል ፎርም ማስሞላት ጀምረው ነበር። ፎርሙ ሲሞላ ደግሞ ብሔር ይጠይቅ ነበር። እኔም ‹‹ብሔር›› በሚለው ጥያቄ ላይ ኢትዮጵያዊ ብዬ ሞላሁ። ይህ ነበር የመጀመሪያ የፀባችን መነሻ። ‹‹ዜግነትህን ሳይሆን ብሔርህን ነው የተጠየከው›› ሲሉኝ ብሔሬ ኢትዮጵያዊ መሆኑን አስረግጬ ነገርኳቸው።
ሆኖም ፎርሙን ሲያስሞላ የነበረው ተላላኪ የነበረ ልጅ ከበርሃ የመጡ ዘመዶቹ ባለስልጣን አደረጉትና እኔ ኢትዮጵያዊ በማለቴ ሊቆጣኝና ሊያስፈራራኝ ሞከረ።
እኔ ግን ብሔር ማለት አገር ማለት እንደሆነ እሱም ኢትዮጵያ ብቻ መሆኑን ነገርኩት። ጎሳ ከሆነ ኦሮሞ ነኝ አልኩት። ሊቀበለኝ ስላልፈለገ ወረቀቱን ቀደድኩና አባረርኩት። በዚህ ሁኔታ የተጀመረው ክርክር እያደገ መጣ። በተለይም የሰራተኛ ማህበሩ ስራአስፈፃሚና የኦዲት ኮሚሽን ሰብሳቢ ስለነበርኩኝ ከእነሱ ጋር የሚያነካካኝ ነገር እያደገ መጣ። በወቅቱ ደግሞ የንግድ ባንክ ሰራተኞች የሥራ ማቆም አድማ አድርገው ነበር። ግን የነበረው መንግስት ጥያቄያቸውን ከማድመጥ ይልቅ በአሳፋሪ ሁኔታ ወዲያውኑ እነሱን አባሮ በምትካቸው ሌሎችን ቀጠረ።
በዚያ ምክንያት የተባረሩትን የባንክ ሰራተኞች የእኛ ማህበር ድጋፍ አደረገላቸው። ይሁንና ድጋፋችን ‹‹በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ መንግስትን ጠልፎ ለመጣል የተደረገ ሙከራ ነው!›› ተብሎ ነው የተገለፀው። እነሱ ‹‹ያደረጋችሁት ፀረ መንግስት እርዳታ ነው›› ቢሉንም እኛ ግን ለአቻ ማህበር አባል የሆኑ ዜጎች ከነቤተሰቦቻቸው ችግር ውስጥ ወድቀው ዝም ብሎ ማየት ተገቢ ባለመሆኑ ነው የሚል ምላሽ ሰጠናቸው። ጉዳዩ እየተካረረ ወደ ሚዲያ መውጣት ጀመረ። ብዙ ሰው ደፍሮ የሚናገርበት ጊዜ ቢሆንም እኛ የመብት ጥያቄያችንን በአደባባይ እናቀርብ ነበር።
በመሆኑም ማህበራችንን አገዱት፤ በዚህም አልተወሰኑም፤ ከ100 በላይ ሰራተኞችና የማህበሩን አባላት በአንድ ቀን አባረሩ። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተወሰነ ውሳኔ ታምራት ላይኔ ነው ያባረረው። እኔን ከእነዚህ ሰራተኞቸ ጋር አላባረሩኝም ነበር። ይሁንና እኔን ወደማባበልና ወደ ማስፈራራት ገቡ። ‹‹አፍህን ዝጋና እንሹምህ›› የሚባል ነገር መጣ። ታምራት ላይኔ ጠርቶ አስፈራራኝ።
እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልጄ ሳድግ ደርግ 17 ዓመት ዝም በሉ ብሎን ዝም ብዬ ኖሪያለሁ፤ አሁን በአደባባይ ስለመብት ማውራት የጀመርኩት የዲሞክራሲ መብቶች ይከበራሉ ስላላችሁ ነው። ስለሆነም በአደባባይ አፋችሁን ዝጉ በሉንና አፌን ዘግቼ ልቀመጥ፤ አልያ ግን በአደባባይ ተናገር እያላችሁኝ ፤ ቢሮ እያስጠራችሁ አፍህን ዝጋ የምትሉኝ ከሆነ አልቀበልም አልኳቸው።
አቶ ታምራት ‹‹ዝናህን ሰምቻለሁ፣ ደፋርነህ›› አሉኝ። እኔ ግን እውነቱን መናገር እንጂ ድፍረት እንዳልሆነ ስነግራቸው ‹‹የፈለግነውን ማድረግ እንደምንችል ታውቃለህ?›› ሲሉኝ አውቃለሁ፤ እኔ ብሞት የሚቀርብኝ እከክና ችግር ነው፤ እናንተ ለመኖር ብትሰጉ አይፈረድባችሁም፤ እኔን ግን ስቃዬን ነው የምትገላግሉኝ አልኳቸው። ያንጊዜ ‹‹ውጣ ከቢሮዬ›› ብለው አባረሩኝ። በመሰረቱ እኔ 1986 ዓ.ም ተባርሬ ከአገር እስከወጣሁበት 1989 ዓ.ም ድረስ ሞራሌን ለማላሸቅ ብዙ ሙከራዎችን አድርገውብኛል። አንድ ቀን የማልረሳው ላምበረት የሚገኝ አንድ ሆቴል ከጓደኛዬና ልትወልድ ከደረሰች ሚስቱ ጋር ሆነን ሳለ መሳሪያ ጠምደው መጡብንና ከበቡን። ያቺ እርጉዝ ሴት እኔን ሲያስጨንቁኝ በድንጋጤ የማህፀን መድማት አጋጠማት።
ብዙዎቻችሁ ስርዓቱ መበላሸት የጀመረው ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነ ነው የምታስቡት፤ ነገር ግን ከጅምሩም ትክክል ያልነበረ ስርዓት ነው። አንድ ነፃና ምንም አይነት የፖለቲካ ስልጣን ፍላጎት የሌለውን ሰው በከባድ መሳሪያ የሚያስፈራራ ስርዓት ነው። በመጨረሻ ወደ ግድያ እንደሚሄዱ ምልክቶችን አየሁኝ። ከዚያ በፊት ግን ድብደባና ፍንከታ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበር ኮንፌዴሬሽንም አገዱ፤ ቢሮውን አሸጉና እዚሁ ሀገር ውስጥ ስደተኛ ማህበር አደረጉት። በመጨረሻ ሀገር ጥለን ወደ ኬኒያ ተሰደድን። ኬኒያ ስደተኛ ሆኜ ወደ አውስትራሊያ ሄድኩኝ። ይህም ማለት ከ1990
ዓ.ም ጀምሮ አውስትራሊያ የገባሁ ወደ ሀገሬ መግባት የቻልኩት ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን በመጡበት ዓመት ፋሲካ በዓል ላይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚያ በኋላ ወደ አገርዎ ሲገቡ ምንአይነት ስሜት ተፈጠሮቦት?
አቶ አያሌው፡- ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ነው የተፈጠረብኝ። እሱን በቃላት ለመግለፅ ይቸግረኛል። አገር ማለት ቤተሰብ ማለት ነው። ይሁንና እኔ ወደ አገር ቤት ስመለስ ብዙ የቤተሰብ አባል በህይወት አላገኘሁም። እንዲሁ ዝም ብዬ ከመምጣቴ በፊት ኢትዮጵያ ለእኔ ለቅሶ ቤት ናት ብዬ አስብ ነበር። ለማልቀስ እንደምመጣም አውቀው ነበር። የሆነውም ይኸው ነው።
ገጠር ወንድሞች አሉኝ፤ ባለፈው ስመጣ እነሱ ጋር እንድቆይ ብዙ ተማፅነውኛል። እኔ ግን እንድሞት አልያም እንዳብድ ትፈልጋላችሁ ወይ? ነው ያልኳቸው። ልክ እዛ ስሄድ በዚያ አስከፊ ስርዓት እናቴ ፤ አባቴ እንዲሁም ሌሎች የቤተሰብ አባላትን መቅበር እንኳን ያለመቻሌ ጉዳይ ያበሳጨኛል።
እናም በዚህ ምክንያት አይደለም አምቦ ከቡራዩ አልፌ መሄድ ህመም ነው የሚፈጥርብኝ። እርግጥ ነው፤ እኔ ብቻ አይደለሁም የዚህ እጣፈንታ ተካፋይ የሆንኩት። ብዙዎች የእኔ አይነት በደል የደረሰባቸው አሉ። ግን ደግሞ የማንም ሽፍታ ቡድን ተነስቶ ከተወለድሽበት አገር እንዳትኖሪ ተከልክለሽ ወላጆችን ያህል ማጣትና ሳይቀበሩ መቅረት የዘላለም ፀፀት ነው የሚፈጥርብሽ።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ በመነሳት ይህ ስርዓት አገሪቱንም ሆነ ህዝቦቿን ምን ውስጥ ከቷል ማለት ይቻላል? በተለይ ከዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አኳያ?
አቶ አያሌው፡- ስለምን የዲሞክራሲ ስርዓት ነው የምናወራው? ለእኔ ከሕወሓት ዲሞክራሲ መጠበቅ ሰይጣንን በቅዱስ ስፍራ እንደመፈለግ ነው። አንድ ጎጠኛ እና ጠባብ ቡድን ስለዲሞክራሲ ምን ሊያውቅ ይችላል?። ለእኔ አብዮታዊ ዲምክራሲ የለየለት አምባገነን ስርዓት ነው።
ስለዚህ በምንም መንገድ ስለዲሞክራሲ ልናወራ አንችልም። ደርግም ተመሳሳይ አምባገነን መንግስት ነበር፤ ሆኖም ኢትዮጵያዊ ስርዓት ነው። ሕወሓት መራሹ መንግስት ግን ይከተል የነበረው ኢትዮጵያዊ ስርዓት አልነበረም።
ለምን ጉዳይ እንደሆነ እስካሁንም ባላውቅም ቀን ከሌሊት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲተጋ የነበረ መንግስት ነው። በመሰረቱ ሕወሓትን ለመተርጎም የሚሞክር ሰው በራሱ ለማበድ የወሰነ ነው። ምክንያቱም ምንም ሎጅክ ከጀርባው የለውም። እነሱን እርኩስ መንፈስ ነው ለማለትም የቸገረ ነገር ነው። ምክንያቱም እርኩስ መንፈስ ለእሱ እንድትገዢ ያደርጋል እንጂ ከተገዛሽለት በኋላ ሊያጠፋሽ አይሞክርም። የሕወሓት ክፋት ጥግ ከእርኩስ መንፈስም በላይ ነው። 27 ዓመት በቤተመንግስት ሲኖር ሸፍቶ የኖረ እና ጉዞውን ሽፍትነት ላይ የጨረሰ ቡድን ነው።
ከሁሉ በላይ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ብሎ መከላከያውን አፈረሰ። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ የቆመችባቸው ዋና ዋና ምሰሶዎች እንደመከላከያ ያሉ ተቋሞቻችን ናቸው። ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ብትሄጂ አንድም ስለውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚያውቅ የለም። ዲፕሎማቶቻችንን ኢትዮጵያዊ በመሰለልና በመበታተን ስራ ላይ ተጠምደው ነው የኖሩት። ገንዘብ እየከፈሉ ሰዎችን በቤተሰብ እስከማስፈራራት ድረስ ይደርሱ ነበር። በአጠቃላይ የወያኔ ስርዓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ በደንብ ተግቶ ሰርቶ አሁን በቆምንበት የጎሳ ማንነት ላይ ጥሎናል።
እነሱ እኮ በሙሉ አፋቸው ኢትዮጵያ ብለው ለመጥራት ስለሚከብዳቸው ‹‹ሃገሪቱ›› ነበር የሚሉት። ስለዚህ ስርዓቱ ሙሉ ዘመኑን ሲዘርፍ፤ ሲገድል ነው የኖረው። በመጨረሻ ሲበቃው ኢትዮጵያን እንዴት እንደሚያፈርስ ሲያመቻች ቢቆይም እነሱ እንዳሰቡት ሳይሆን ቀርቶ ኢትዮጵያ ሳትፈርስ የሽፍታ ቡድኑ ራሱ ቀድሞ ፈረሰ።
አዲስ ዘመን፡- ያንን ሁሉ በደል ፈፅመው ሳለና በይቅርታ እንዲኖሩ እድሉ ተፈጥሮላቸው ሳለ መከላከያውን ከጀርባው መምታቸውንና ንፁሃንን በግፍ መጨፍጨፋቸው ከምን የመነጨ ነው ይላሉ?
አቶ አያሌው፡- አስቀድሜ እንደገለፅኩት የሕወሓት የክፋት ተግባር ከባህሪው ነው የሚመነጨው። ሕወሓት እሱ ካልገዛ በቀር ሌላው ሊቀጥል እንደማይችል በግልፅ ተናግሯል። ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው የሚገዛውን ሃገር ‹‹እኔ ካልገዛሁ ትፈርሳለች›› ብሎ ማለትን ምንአመጣሁ?።
ኢትዮጵያ በትውልድ ቅብብሎሽ እዚህ የደረሰች ሃገር ነች። ብዙ ስርዓቶች ተቀያይረዋል። እነሱ የመግዛት ዘመናቸው ሲያልቅ ተፈጥሯዊ ነውና ደግሞ ሌላ ገዢ ይመጣል ብሎ ለማሰብ ፈቃደኞች አይደሉም። ሕወሓት በክፋትና በቅንዓት ያበዱ ሰዎች ስብስብ ነው። ስለዚህስለእኩልነት በፍፁም ማሰብ አይችሉም። በመሰረቱ እኔ ለውጡ መጥቶ የኢትዮጵያ ችግር በእርቅና በይቅርታ ሊዘጋ ይገባል ከሚሉ ሰዎች አንዱ ነኝ።
ይህንኑ አቋም ይዤ ለዓመታት ሰዎችን ለማስገንዘብ ሞክሪያለሁ። ሕወሓት ግን ይቅርታ ሊጠይቅ ፍቃደኛ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ነበረኝ። ለውጡ መጥቶ ዶክተር አብይ ይህንን አቋም ሲያራምዱት እንዴት ይሆናል? የሚል ስጋት ነበረኝ። ምክንያቱም ይቅርታ የሚጠይቅ ቡድን አይደለም።
መከላከያውን ከመውጋታቸው በፊት በሃገሪቱ የፖለቲካ ስርዓት የሆነው ነገር ተዓምር ነው የሚመስለው። ብዙ ሰው ልብ የማይለው ነገር አለ። ሕወሓት የሃገሪቱን የደህንነት ተቋም፤ የውጭ ግኑኝነቱን ሁሉ ተቆጣጥሮ የሃገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈው በመሸጥ ምዕራባውያንን ከጎኑ አሰልፎም ነበር።
አሁን የምናየውም የዚያ ስራ ውጤት ነው። የነበረውም መከላከያ ኢትዮጵያዊ አልነበረም፤ በጎሳ የተከፋፈለ ነው። ስለዚህ ይሄ ሁሉ በሆነበት እንዴት ነው የለውጡ መንግስት መዝለቅ የሚችለው የሚል ስጋት ነበረኝ።
አንድ ቦታ ላይ ለውጡ ይገለበጣል የሚል ፍራቻ ነበረኝ። ይህንን ለውጥ በጣም የተለየ የሚያደርገው ሁሉም ነገር በጥንቃቄና በሂሳብ የተሰራ መሆኑ ነው። የማደንቀው ለዚህ ነው። እነሱ ምንም ሳያውቁና ሳይነቁ ብሎኑ ተፈቶ መቀሌ ተጠራርገው መሄዳቸውን በቀላሉ ልናየው አይገባም።
እዚህ ቢሆኑ ኖሮ በአገር ላይ የበለጠ አደጋ ይፈጥሩ ነበር ብዬ አምናለሁ። በተለይ መከላከያው ሪፎርም ሳያደርግ ቢቀርና እነሱም እዛው ቢሆኑ ኖሮ ተጨማሪ ችግር ይፈጥርበት ነበር። ምክንያቱም ሁሉም ነገር በእጃቸው ስለነበረ ነው።
እነሱን በጥበብ ወደ መቀሌ እንዲከትሙ ካደረገ በኋላ በፍጥነት የተሰሩት ስራዎች ለውጡን ትንግርት ያደርገዋል። እርግጥ ‹‹የሰፊው ህዝብ የማስታወስ ብቃት አጭር ነው›› እንደሚባለው ሁሉ ሁሉንም ነገር ረሳነው፤ አሁን ላይ በቅንጦት ጉዳዮች ላይ እንጣላለን። በመሆኑም ቀድሞውንም ቢሆን ሕወሓት ጥፋት እንደሚያደርስ እርግጠኛ ነበርኩኝ።
ኢትዮጵያን ሊበትናት የሚችል ጥፋት ሲያደርስ የለውጥ ሃይሉ ያንን የሚመጥን ዝግጅት ላይኖረው ይችላል የሚል ስጋት ነበረኝ። ግን ፈጣሪ ይመስገንና የደረሰው ጉዳት ከባድ ቢሆንም ከስጋቴ አኳያ የለውጡ ሃይል በበቂ ሁኔታ መመከት ችሏል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- በአውስታራሊያ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ለውጡን ተከትሎ እያደረጋችሁ ስላለው የድጋፍ እንቅስቃሴ ያጫውቱን?
አቶ አያሌው፡- እንዳልሽው እኛ በአውስታራሊያ የምንኖር ኢትዮጵያውያን ለውጡ ከመጣ ጀምሮ የምንችለውን ሁሉ ድጋፍ ስናደርግ ቆይተናል። በቀን አንድ ዶላር የድጋፍ መርሃ ግብር ጀምሮ፤ ህዳሴ ግድብ ቦንድ ግዢ፤ በወለጋ፣ ምዕራብ ኢትዮጵያ፤ ቤኒሻንጉልና አጣዬ ለተፈናቀሉ ሰዎችና ለደረሰው ጉዳት፤ በኮረና፤ በአንበጣና በሌሎችም ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በርካታ ተሳትፎ አድርገናል።
ይሄኛው ጦርነት ሊጀመር ሲል ግን ማለትም ሰራዊቱ ከተጠቃ በኋላ የሚሆነውን ነገር አሰብን። ኢትዮጵያ ጦርነቱን እንደምትወጣው ጥርጣሬ አልነበረንም፤ ግን ደግሞ ከጦርነቱ መልስ ትልቅ የኢኮኖሚ ችግር እንደሚያጋጥማት መተማመን ላይ ደረስን። ጦርነቱ ብቻ ሳይሆን የምዕራባውያኑ ተፅዕኖ ሊያመጣ የሚችለውን ችግር አስቀድመን ለመተንበይ ሞክረን ነበር።
ምዕራባውያኑ በኢኮኖሚ ካደቀቁን በኋላ የፖለቲካ ስልጣኑን እንዲቀማ ሊያደርጉ ይችላሉ የሚል ስጋት ስለነበረን ከአስር ወር በፊት በመላው ዓለም የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ማድረግ ስለሚችለው ነገር ተነጋገርን። በገንዘብ ሃገሪቷን መርዳት አለብን የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስን።
በተለይ ውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቀነስ ያስችል ዘንድ ‹‹ኢትዮጵያን እንታደግ›› የሚባል ቡድን አቋቋምን። ከዚያ በኋላ በየወሩ ለቀጣይ አስር ዓመት ምንአልባት ኢትዮጵያ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ነፃ እስከምትወጣ ድረስ መርዳት አለብን ብለን ሃሳቡን በዓለም አቀፍ ደረጃ እየሸጥን በአውስታራሊያ ደረጃ አንድ ብለን ጀመርን። አሁን ህጋዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት አቋቁመን በአውስትራሊያ የአሰራር ማዕቀፍ አስመዝግበናል። ምክንያቱም በኋላ ላይ ገንዘብ መላክ ሊከለከል ይችላል የሚል ስጋት ስለነበር ነው።
በወቅቱ ደግሞ ምዕራባውያኖቹ ‹‹የሀገሪቱ መንግስት ሽብርተኛ ነው፤ ሃብት እናግዳለን›› የሚል ነገር አምጥተው ነበር። አሁን ላይ በየወሩ የሚያወጣው ዲያስፖራ ብቻ 162 አካባቢ ደርሷል። እናም ገንዘቡን በየወሩ እየላክን እንዲቀመጥ እናደርጋለን። ይህም በህዝቡ ውሳኔ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ያስችለን ዘንድ ነው። ዝም ብለን ለመንግስት ጥሬ ገንዘብ መስጠት አልፈለግንም። ምክንያቱም መንግስት ሁልጊዜ መንግስት ነው፤ የፖለቲካ ፍላጎት አለው። ‹‹ብፁዕ፤ ቅዱስ›› የሚባል መንግስት የለም።
ስለዚህ መንግሰት የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን እንዲቀርፍ ሊረዳ ይገባል፤ የተመነዘረውን የኢትዮጵያ ብር ደግሞ ለልማት እናውላለን የሚል ትልም ይዘን እየሰራን ነው ያለነው። እዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ህጋዊ ሰውነት እንዲኖረው እናስመዘግበዋለን።
በጦርነት የተጎዱትንም ሆነ የተፈናቀሉትን ለመደገፍ እየሰራን ሳለ ግን ጦርነቱ ፈነዳና ሰፋ ያለ አውስትራሊያ አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር አዘጋጅተን 225 ሺ ዶላር ድጋፉን ለሚመራው መንግስታዊ ተቋም አስገብተናል። ከዚህ በተጨማሪም በጦርነቱ የተጎዱ ሰዎችን በአፋርና አማራ ክልል በሙሉ ዞረን ጎብኝተናል። እኔ እነዚያን አካባቢዎች እየተዘዋወርኩ ከመጎብኘቴ በፊት ፕሮፖጋንዳ ሊኖረው ይችላል ብዬ ፍራቻ ነበረኝ። ግን እንዳየሁት ከሆነ ገና አልተነገረም። ዜናው ሁሉ ተጋኖ የቀረበ ነበር የሚመስለኝ።
ሄጄ ሳየው ግን ምንም እንዳልተነገረ ነው የተረዳሁት። ምንአልባትም ህዝብ እንዳይቀያየም በሚል ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ህዝብን በስሜት መንዳት የሚያመጣው ችግር በራሱ የከፋ ሊሆን ይችላል። በሩዋንዳ ሁቱና ቱትሲ ላይ የሆነው ነገር ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። ስለዚህ ሃላፊነት በተሰማው መንገድ የተያዘ ይመስለኛል።
አሁንም አለመናገር ጥሩ ነው። ምክንያቱም የሆነው ነገር ያማል፤ ለመግለፅ ይቸግራል፤ ግን ደግሞ ሊመጣ የሚችለውን የባሰ ችግር ማሰቡ የተሻለ ነው። እነዚህ ሰዎች ለምሳሌ በደሴ ዩኒቨርሲቲ የፈፀሙትን ግፍ ስታይ መግለፅ እንኳን ይከብድሻል። ያ ዩኒቨርሲቲ ካሉት ተቋማት በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠቀሱት መካከል ነበር። ምንም ሳያስቀሩ የቻሉትን ዘርፈው ያልቻሉትን አውድመው ነው የሄዱት። በጣም የሚያሳዝንሽ መጫን ያልቻሉትን ንብረት ዳግመኛ እንዳይሰራ አድርገው ማውደማቸው ነው።
በዲጂታል መሳሪያ የሚቆለፉ የምርምር ማዕከላትን በር መክፈት ሲያቅታቸው ግድግዳ አፍርሰው ነው የገቡት። ይህንን ካደረጉት ሰዎች መካከል ደግሞ የዚያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረ ሰው ይገኝበታል። የተማረ የዩኒቨርሲቲ ምርቁ በጥፋት ሴራ ላይ ሲሳተፍ ማየት የበለጠ የሚጎዳ ነገር አለ ብዬ አላምንም። ከብቶቹን ረሽነዋል፤ ዋናው የዩኒቨርሲቲው በር ላይ መቃብር ቆፍረዋል፤ በየግድግዳው ላይ የተፃፈውን ነገር አትጠይቂኝ!። ይሄንን ለመረዳት ይከብዳል።
ሕወሓት ብልግና ወይም ክፋት ነው የሰራው የሚለው ቃል በራሱ አይገልፀውም። እንደእኔ እምነት ሊጠና የሚገባው የሕወሓት ክፋት ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ሕወሓትን 27 ዓመት እንዴት ሊሸከመው እንደቻለ ነው።
እንዴት ይህንን ሁሉ ዓመት ከሕወሓት ጋር መኖር እንደቻላችሁ ለእኔ እንቆቅልሽ ነው። ፕሮፌሰር መስፍን እንደሚሉት የኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ የደነደነ ነው። በአለም ላይ እንደዚህ አይነት ግፍ የተሸከመ ህዝብ ያለ አይመስለኝም። በህይወቴ በጣም ደስ የሚለኝ ነገር ለሕወሓት አለመገዛቴን ነው። በኢትዮጵያዊነቴና በነጻነቴ አለመደራደሬ ሁሌም ያኮራኛል።
አዲስ ዘመን፡- ዲያስፖራው ከያለበት ሆኖ የምዕራብውያኑን ጫና ለመከላከል ያደረገውን እንቅስቃሴ እንዴት ይገልፁታል?
አቶ አያሌው፡- በሀገራችን ‹‹ረሃብ ሲገባ ብልህ እማወራ እሳት ታዳፍናለች እንጂ እንዲጠፋ አታደርግም›› ይባላል። ምክንያቱም አንድ ቀን ረሃቡ ያልፍና እሳት ያስፈልጋል፤ ኢትዮጵያዊነት እንደሱ ነው።
የኢትዮጵዊነት ጠኔ ገብቶ 27 ዓመት ኢትዮጵያዊነት ጥምብ ርኩሱ ወጥቶ ነው የኖረው። እነሱ ‹‹ኢትዮጵያዊነትን ከነጭራሹ አጥፍተነዋል›› ብለው ነበር፤ ግን ኢትዮጵዊነት ዝም ብሎ የሚጠፋ አይደለም፤ ልክ እንደብልኋ እማወራ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ተዳፍኖ ነው የኖረው። አንድ ቀን ግን ያ ሁሉ ግፍ ሞልቶ ሲፈነዳ ያ ኢትዮጵያዊነት ተግ አለና ይሄን ፈጠረ። ሌላ ምንም ተዓምር የለውም። ኢትዮጵያ የሶስት ሺ ዘመን ታሪክ ያላት ሃገር ሆና ሳለ ኢትዮጵያዊነት እንዲሁ እንደሻማ እፍ ተብሎ የሚጠፋ አይደለም።
ለወደፊቱም ሌሎቹም ከዚህ ሊማሩ ይገባል። ስቃያችን፤ መከራችን ይበዛል፤ እንሞታለን፤ እንሰደዳለን ኢትዮጵያዊነት ግን ገና ይቀጥላል። ሚስጥሩ ይሄ ነው። ዲያስፖራው በዚህ ደረጃ በአንድነት የቆመበት ምክንያት ሌላ ሚስጥር ኖሮት ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ኢትዮጵያ ስለነበረች ነው።
አሁንም ቢሆን እኮ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ውስጥ ነው ኢትዮጵያ የተገኘችው!። ዶክተር አብይ ይህ ሁሉ ድጋፍ ያገኘው ኢትዮጵያ ብሎ በመነሳቱ ነው። እኔ በራሴ በጣም ግርም ያለኝ ወያኔ ሲገባ የ15 ዓመት ታዳጊ የነበሩ ሰው ውስጥ ኢትዮጵያ በቀለች። ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት ጊዜው ደረሰና ፈነዳ። ጎሰኝነትን አፈር አበላ። ከዚህ ቀደም የወያኔ ባለስልጣት ላይ የምንጮኸው ኢትዮጵያን ክብር ስላወረዱ ነው። አሁን ኢትዮጵያ ላይ የሚጮሁ ምዕራባውያን ላይ ተነሳንባቸው፤ አቁሙ አልናቸው፤ አቆሙ። አሁን ሊደራደሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡-የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎ አገር ውስጥ ከገባው ዲያስፖራው በቀጣይ ምን ይጠበቃል?
አቶ አያሌው፡- መጀመሪያ ደረጃ ልንገነዘብ የሚገባው ነገር የመጣነው ለጉብኝት ሳይሆን እናት ኢትዮጵያ ለቅሶ ላይ በመሆንዋ ለቅሶ ልንደርስና ህዝባችንን ልናፅናና ነው። የወገኖቻችን ችግር ልንካፈልና ልንደግፍ ነው። ወጥተሸ ብታይ የሚዝናና ዲያስፖራ አታገኚም። በመሰረቱ ምን የሚያዝናና ነገር አለ። በነገራችን ላይ እኮ በዚያም ወገን ቆመው የሚሞቱት በእነዚህ እርኩሳን ተመርተው በልተው የጠገቡ ልጆች አይደሉም። እነሱም ኢትዮጵያውያኖች ናቸው።
ትግራይን ጨምሮ የወደመውን አካባቢ መገንባት የእኛ የኢትዮጵያውያኖች እዳ ነው። ሁላችንም ድርሻ ድርሻችንን መሸከም ይጠበቅብናል። ከለቅሶ በመለስ ኢትዮጵያ ከገባችበት ችግር የምትወጣበትን መፍትሄ የመፈለጉ ስራ የሁላችንም ነው። ለዲያስፖራው ብቻ የሚተው አይደለም።
መንግስትና ህዝቡ ሀገሪቷ መልሳ እንዲህ አይነት አዘቅት ውስጥ እንዳትገባ ሁሉንም ባማከለ መልኩ መስራት አለብን። ለእኔ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ከዘመነ መሳፍንት ቀጥሎ በጣም አስቀያሚ ጊዜ ነው የሚመስለኝ። የዚህ የለየት የሚያደርገው ዋና አላማው ኢትዮጵያን ማፍረስ መሆኑ ነው። ኢትዮጵያን እየጠላ ኢትዮጵያን የገዛ ቡድን ነው። ቤተመንግስት 27 ዓመት ሙሉ ‹‹ነፃ አውጪ ነኝ›› ብሎ የኖረ ደፋር ቡድን ነው።
አዲስ ዘመን፡- መንግስት እስረኞችን መፍታቱ ለአገር ዘላቂ ሰላም ምን ፋይዳ ይኖረዋል?
አቶ አያሌው፡- ይሄ ጉዳይ እንዳልሽው የተደበላለቀ ነገር ፈጥሯል። አንደኛ የዲሞክራሲ ባህል እጥረቱ የጎዳንም ይመስለኛል። በመሰረቱ ብዙ ህዝብ ቅር ብሎታል ለማለት መለኪያችን ሊታወቅ ይገባል።
በየማህበራዊ ሚዲያው የሚጮኸውን ብቻ አይተን ብዙ ህዝብ ቅርብሎታል ልንለው አንችልም። አየሽ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። እንደዚህ የምናስብ ከሆነ ችግሩን ተደራሽ ለማድረግ ጥሩ ግብዓት አይደለም። ምክንያቱም የተነሳንበት መለኪያ የተሳሳተ በመሆኑ ነው። እርግጥ ነው፤ በስሜታዊነት ቅር የተሰኙ ወገኖች አሉ። ገና ቁስሉ አልዳነም፤ የተደረገው ነገር ያማል። ግን ቁስል እየነካካን እንዲመረቅዝ እያደረግን ወደ ሌላ ችግር ውስጥ ባንገባ ጥሩ ነው። ሕወሓት ያደረሰውም ሆነ የሚያደርሰው ጉዳቱ ቀላል አይደለም። ግን ከዚህ ውስጥ ለመውጣት የይቅርታ ልብ አስፈላጊ ነው። ይቅርታው መቼ ?እንዴት? የሚለው ነገር ግን የሕዝብን ስነልቦና ማጤን ያስፈልጋል።
የህዝብን ቁስል በጣም በማይጎዳ መልኩ መደረግ አለበት። ይሄ ሲደረግ ቅድም እንዳልኩት መንግስት በእጁ ላይ ያሉትን ወርቅ የሆኑ ሃብቶችና እድሎች መመንዘር መቻል አለበት። በተጨማሪም ስሜታዊነት በሂደት ለምክንያታዊነት ቦታውን እየለቀቀ ይመጣል። እናም በምክንያት ማሰብ ስትጀምሪና ስሜታዊነት ሲለቅሽ አጥርተሽ ማሰብ ትቺያለሽ።
በፍቅር ዓለም እንኳን ልብስን አውልቆ ተቃራኒ ፆታ ጋር መቆም ስሜት እንጂ ፍቅር አይደለም ይባላል። ልብን ገልጦ ማሳየት ግን ትክክለኛ ፍቅር ነው ይባላል። ስለዚህ ስሜት ብዙ ጊዜ ልብስ አስወልቆ ሊያቆምሽ ይችላል፤ ግን ልብ ከፍቶ እውነታውን አያሳይሽም። ስለዚህ ብሽቀቱ ቀስ በቀስ ይረጋጋል። ይህም ሆኖ መንግስት ግን በግሉ ማረም ያለባቸው ነገሮች አሉ። ስለብሄራዊ እርቅ ሲጮሁ የነበሩ ሰዎች ሲቆጡ አይቻለሁ።
ብዙዎቹም ጊዜው አይደለም ነው የሚሉት። ጊዜውን ደግሞ የሚወሰነው በሪፈረንደም አይደለም። የሚወሰነው በፖለቲካ ስርዓቱ ነው። ህዝብ ቅር ብሎታል፤ ግን ህዝብ የሚሾፈረው በሊሂቃኑ ነው፤ እነዚህ ሊሂቃኖች ደግሞ እዚህ ጋር መስራት መቻል አለባቸው።
ለመሻገር ሃገሪቱ እንደሃገር እንድትቀጥል መደረግ ይገባቸዋል። ይህ ጉዳይ ተደራሽ የሆነበት መንገድና ምክንያት በመንግስት ሊብራራ ይገባል። ህዝቡን የማስገንዘብና የማሳመን ስራው በተከታታይነት መሰራት አለበት የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ አያሌው፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጥር 7/2014