(የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጥር 1 ቀን 2014 ዓ.ም በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የህንፃ ምረቃ ሥነስርዓት ላይ ተገኝተው ያደረጉት ንግግር)
ክቡር የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ
ክቡር የፌዴሬሽንና የሕዝብ ተወካዮች አፈ ጉባኤዎች
ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን
ክቡር ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
ክቡር ጄነራል አበባው ታደሰ
የተከበራችሁ እንግዶች፣ሚኒስትሮች የክልል አመራሮች ፤ ከሁሉ በላይ የኢትዮጵያ ኩራት የሆናችሁ የጦር መኮንኖች! በቃላችሁ በመዝሙራችሁ የማንጨበጥ ነበልባል እሳት ነን ለጠላታችን፤ ፍሙ ከርቀት ይፋጃል ብረት ያቀልጣል ክንዳችን፣ ኢትዮጵያ በእኛ ደም ደምቃ በአፅማችን ፍላጻ ተማክራ እንደታፈረች እንድትኖር ከዘመን ዘመን ተከብራ ከመሞት በላይ እንሙት ደማችን ሺህ ጊዜ ይፍሰስ አየር አፈሯ ይባረክ ሁልጊዜም ስሟ ይታደስ፡፡ እንዳላችሁት ስሟን ለማደስ እጅግ ከፍተኛ የሆነውን ጀግንነት፣ ማሰብ የሚከብደውን ብቃት ስላሳያችሁ ኢትዮጵያ አብዝታ ታከብራችኋለች።
በአገራችን ባህል ላሸነፈ ሽልማት፣ ለተሸነፈ ምህረት መስጠት የታሪካችን ክፋይና ኢትዮጵያ የሚለው ስም ብያኔ አካል ሆኖ የቆየ ነው። እኛ የዛሬ ትውልድ የኢትዮጵያ ልጆች ከአባቶቻችን ልንማር የሚገባው ቁልፍ ጉዳይ ዘላቂ ድል ለማረጋገጥ በጀግንነት ተዋግቶ ደምን አፍስሶ፣አጥንትን ከስክሶ፣ሕይወትን ገብሮ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ከእኔ ይቅር ብለው ለጠላት፣ ለተሸነፈ፣ እጅ ለሰጠ ምህረት ማድረግም ጭምር የአባቶቻችን የማንነት መገለጫና የወረስነው የጀግንነት አካል መሆኑ ሁልጊዜም በልባችን ሊኖር ይገባል።
አባቶቻችን በጦርነትም በሰላምም እያሸነፉ ነው አገር ያፀኑት፡፡ ኢትዮጵያን ለሺህ ዘመናት ሳትገዛ በነፃነት እንድትኖር ያደረጉት በአውደ ውጊያ ብቻ ሳይሆን በሰላም መድረክም አሸናፊ ሐሳቦች እያፈለቁና ቀድመው እየተገኙ ነው። በጥቂቱ ወደ ኋላ መለስ ብለን ታሪካችንን ገለጥ ገለጥ ብናደርግ ራስ ወልደ ጎርጊስና የከፋው ንጉሥ ጋኪ ሸረኮ ሲዋጉ በነበረው ውጊያ ራስ ወልደ ጎርጊስ ያሸነፉ ቢሆንም ንጉሥ ጋኪ ሸረኮ ከማረኩ በኋላ እንደ ምርኮኛ ሳይሆን እንደ ንጉሥ ነበር ወደ ሸዋ ያመጧቸው።
በእምባቦ ጦርነት ንጉሥ ምኒልክና ንጉሥ ተክለኃይማኖት በገጠሙት ውጊያ ንጉሥ ምኒልክ ንጉሥ ተክለኃይማኖትን ያሸነፉ ቢሆንም የቆሰሉትን ንጉሥ ተክለኃይማኖት ወንድሜ ብለው አቅፈው አክመው ወደ ጎጃም እንደመለሷቸው ታሪክ ይናገራል።በዓደዋ ጦርነት እርስ በእርሱ ብቻ ሳይሆን ከውጭ በተደረገው ጦርነት ፊትአውራሪ ገበየሁ ጉርሙ ያጡት ንጉሥ ምኒልክ በሺህ የሚቆጠር ወታደር የሞተና የቆሰለባቸው ቢሆንም በአውደ ውጊያ በጀግንነት ተዋግቶ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ሲያሸንፉም ከእኔ ይቅር ማለትን ለእኛ ለልጆቻቸው አስተምረውን አልፈዋል።
ትላንት ክስ የተቋረጠላቸው የተሸነፉ ኃይሎች ክስ እንዲቋረጥና ከሥር ቤት እንዲወጡ ሲደረግ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል።ይህ ቁጣ የተቀሰቀሰው በሁለት ቡድኖች ነው።አንደኛው ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ ጭር ሲል የማይወድ ሁልጊዜ እያጋጨ በሰበር ዜና ብር የሚሰበስብ ፣የት እንዳለ የማይታወቅ፣ካለበት ሆኖ ስንዋጋ ጦርነት አቁሙ የሚል ስናቆም ተዋጉ የሚል አጓጉል ብልጣብልጥነት የሚያጠቃውና እንብዛም ጆሯችንን የማንገልጥለት ቡድን ነው።
ሁለተኛው ቡድን ግን በዜናው ድንገተኝነት የደነገጠ ፤ በነበረው ተጋድሎና ሁኔታ ጊዜውን ገንዘቡን ሕይወቱን ለመስጠት የወሰነ ከያለበት አገርና ክልል ተሞ ከአገርና ከሕዝብ ጋር የዘመተ ይሄንን እኩይ ጠላት አምርሮ የሚጠላና ከዚህ እኩይ ጠላት ጋር የሚደረግ ማንኛውም ንግግር ኢትዮጵያን ይጎዳል ብሎ የሚያምን ቅን ተቆጪ ነው። የዚህን ቅን ተቆጪ ኃይል መንግሥት ሙሉ በሙሉ ያደንቃል፣ይረዳል፣ለማስገንዘብም ጥረት ያደርጋል። እነዚህን ቅን አገር ወዳድ ኢትዮጵያን በውስጥም በውጪም የሚገኙ የአንዳንዶችን ከእኛ ይቅር ማለት አምርረው የጠሉና የደነገጡ ወንድምና እህቶቻችን እንዲገነዘቡልን የምንፈልገው ይሄ ጉዳይ እኛም መጀመሪያ ስንሰማው ያስደነገጠን መሆኑ ነው።
ነገር ግን ደጋግመን ስናመነዥከው ግራ ቀኙን ስንፈትሽ ለኢትዮጵያ የሚበጅ፣ለኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም የሚያግዝ፣ የኢትዮጵያን ጠላቶች የሚቀንስ፤ በአውደ ውጊያ ያገኘነውን ድል በሰላሙ መድረክ እንድንደግም የሚያደርግ፤ የአባቶቻችንን ልጆች መሆናችንን የሚያረጋግጥ በመሆኑ እየመረረን የዋጥነው ሁነት ነውና እናንተም ለአገራችሁ ዘላቂ ድል ስትሉ ፣ለአገራችሁ ክብርና አሸናፊነት ስትሉ ደጋግማችሁ በማሰብ ይሄንን ውሳኔ እንድትቀበሉ በትህትና እጠይቃችኋለሁ።
ውሳኔውን ለምን ለምትሉ ይህ ውሳኔ የተወሰነው ኢትዮጵያን በጠንካራ አለት ላይ ለማኖር ነው። ጠላቶቿን ለመቀነስ ነው። ጉልበት ለመሰብሰብ ነው። ያልገባውና የሚከተል ማህበረሰብ ካለ ዓይናቸውን ገልጠው ማየትና ከጥፋት ጎዳና እንዲመለስ ለማድረግ ነው። ሌላም በርካታ ምክንያቶች አሉት። ነገር ግን ትላንት ክስ አቋርጠን ከሥርቤት እንዲፈቱ ያደረግናቸው ግለሰቦች ሁሉም በሚባል ደረጃ የመንግሥት ስልጣን ይዘው በዚህ ሁኔታ ውስጥ የተሳተፉ በቀጥታ የሚወስኑ በቀጥታ የሚያዙ አይደሉም።
አንዳንዶች በታሪካቸው ምክንያት አግዝፈን የምናያቸው ቢሆንም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከሁሉም የውሳኔ ሰጪነት መድረክ በቀጣይ የማይሳተፉ ኃይሎች ናቸው። ከዚህም በላይ ኢትዮጵያዊ ማንነታችንና ጀግንነታችን ሽማግሌዎች በእሥር ቤት እንዲሞቱ የሚፈልግ የሚፈቅድ አይደለምና ጀግኖች ስለሆንን አዛውንቶች ሲቻል ወደ ገዳም አልያም ወደ ቤታቸው እንጂ በእስር ቤት እንዳይቆዩ ወስነናል። ይህ ውሳኔ ዛሬ የሚመርረን ቢሆንም እንኳን ውሎ ሲያድር ልጆቻችንን የሚያኮራ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያፀና መሆኑን ቅንጣት አንጠራጠርም ።
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከውስጥም ከውጪም ለዚህ ጉዳይ የተሰለፋችሁ ዜጎች ይቅር ከእኛ ብለን የለቀቅናቸው ሰዎች በማሸነፋችን ያገኘነው ፀጋ መሆኑን አትዘንጉ ።አሸንፈን ይቅር ለማለት ያበቃን ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን። ለአንድ አፍታ ከሳምንታት በፊት ወደነበረው ሁኔታ መልሻችሁ ደብረ ሲና የደረሰው ኃይል አዲስ አበባን ተቆጣጥሮት ቢሆን ኖሮ እኛ ተሸንፈን ይሄ ኃይል አሸንፎ ቢሆን ኖሮ ምህረት ለመስጠት ሳይሆን ምህረት ለመቀበል የሚያበቃ ዕድል ማግኘት እንችል ነበር ወይ ?
ምህረት መስጠት ከማሸነፍ ጋር የተያያዘ ነው። ምህረት መቀበል ግን መሸነፍ ብቻ ሳይሆን የአሸናፊው ልብን የሚጠይቅ ነው።ፈጣሪ ለእኛ ድል የሰጠን ብናሸንፍ እንደማያሰክረንና ይቅር እንደምንል ስለሚያውቅ ጠላቶቻችን ደግሞ ቢያሸንፉ ኢትዮጵያን ማፍረስ ብቻ ሳይሆን የምህረት ልብ እንደሌላቸው ስለሚያውቅ ነው። ጀግኖች፣አሸናፊዎች፣ምህረት ሰጪዎች ስላደረገን ፈጣሪያችንን እናመሠግናለን።ለነገሩ ይቅር የሚል እኮ መበቀል እየቻለ፣ማሰር እየቻለ፣መግደል እየቻለ የሚተው ነው።ይቅር ያልነው እየቻልን መሆኑን ልንገነዘብ ያስፈልጋል።ያሸነፍከውን ማሰር፣የበደለህን መቅጣት የተለመደ የምናውቀውና ማንም ሰው ሊያደርገው የሚችለው ተግባር ነው።
የእኛ ተግባር ከዚህ እንዲለይ የተፈለገበት ዋና ምክንያት የጠላቶቻችንን ባህሪ፣የጠላቶቻችንን ጠባይ እኛን እንዲወርሰን አንፈልግም፡፡ ዘራፊነት፣ሌብነት፣ነፍሰ ገዳይነት፣አገርን አፈርሳለሁ ብሎ በአደባባይ በኩራት መናገርን የመሳሰሉ ጥዩፍ ጸባዮች እኛን እንዲወርሱን አንፈቅድም አንሻም።በዚህም ምክንያት ጠላቶቻችን በለመዱት መንገድ ሳይሆን በተለየ መንገድ በመሄድ ኢትዮጵያን ለማፅናትና ለማላቅ ምንም እንኳን በድንገት ሲሰማ ለመቀበል የሚያስቸግር ቢሆንም በዘላቂነት አገራችንን የሚያቆይ የሚያፀና የሚያፅናና ሆኖ ስላገኘነው የተወሰነ መሆኑንና በዚህ ውሳኔ ክስ የተቋረጠላችሁ ወገኖች ስላሸነፍን መበቀል እየቻልን ይቅር ማለትን ስለመረጥን ክስ አቋርጠን እናንተን ሳይሆን ከእናንተ ጀርባ ያለውን ሕዝብ አክብረን የወሰነው መሆኑን አውቃችሁ ይሄን ዕድል ሳታበላሹ እንድትጠቀሙበት ላሳስባችሁ እፈልጋለሁ።
ክስ ማቋረጥ ማለት ምህረት መስጠት ማለት አይደለም።ክስ የተቋረጠለት ሰው በአግባቡ መጠቀም ካልቻለ መልሶ የክስ መዝገቡን መምዘዝ የሚቻል ስለሆነ፡፡ በዚህ ጉዳይ ያዘኑ የተቆጡ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች እንዲገነዘቡ የምንፈልገው ነገር የወሰድነው መድኃኒት ማስታገሻ አይደለም። የወሰድነው መድኃኒት ፈዋሽ በመሆኑ የጎንዮሽ ጉዳት አለው። ይጎረብጣል፣ያማል።ለማዳን ብቻ ሳይሆን ከጎንም የመጎርበጥ ባህርይ አለው።ለጊዜው የሚያስታግስ ሳይሆን ለልጆቻችን የድልና የአሸናፊነት መንፈስ የሚያላብስ ስለሆነ እንደኛ ደጋግማችሁ ስታስቡት ጠቀሜታው መቶ በመቶ ይታያችኋልና ደግማችሁ በማሰብ ልባችሁና አዕምሯችሁ ቢከፈት ዋናው ዓላማ የምትወድዋትን ኢትዮጵያ አንድ አድርገን ለማጽናት ካለን ፍላጎት ብቻ የመነጨ መሆኑን እንድትገነዘቡ ቢያንስ ቢያንስ ጉቦ በልተን እንዳለቀቅናቸው እንድታስቡ ላሳስባችሁ እፈልጋለሁ።
እነዚህ በሰዓቱ ሙሉ ስንናገርላቸው የቆየን የኢትዮጵያ ጠላት የኢትዮጵያ የጥፋት ምልክት በቅርበት ሁላችንም የምናውቃቸውና የምናያቸው ብቻ ሳይሆኑ ከአፍንጫችን ስር ዘወር አድርገን ስንመለከት ኢትዮጵያ በአቀማመጧ ለነጻነት ባላት ክብርና በማንነቷ የተነሳ ከሩቅም ከቅርብም በርካታ ጠላቶች ያሏት ናት ። በመንግሥት የሚወሰነው እያንዳንዱ ውሳኔ አርቆ ማሰብና ኢትዮጵያን በማጽናት ብቻ ላይ የሚመሠረት መሆኑን ዜጎች እንዲገነዘቡ እጠይቃለሁ፡፡ አርቀንና አሻግረን በማየት ኢትዮጵያን ማጽናት የሚያስፈልግበት ምክንያት በጥልቀት አስበን ካልሠራን በስተቀር በጠላቶቻችን የተሰለፉ ሐይሎች ባላቸው ትጥቅ፣ ጉልበትና ሐብት መጠን ከሆነ ኢትዮጵያ ማሸነፍ አትችልም።
ኢትዮጵያ በሐብትና በጉልበት የሚበልጧት አገሮች ተቃርነዋት ቆመው እያሉ እንድታሸንፍ ያደረጋት የመሣሪያ ሳይሆን የልብ ብልጫ ነው። ቀድማችሁ እንደሰማችሁኝ እጅግ ብዙ በዚህ ዘመን እንደዚህ አይነት ጀግኖች አሉወይ ተብሎ ለማሰብ የሚያስቸግሩ ወጣቶች እናቶቻቸውን ያለጧሪ አስቀርተው ሚስትና ልጆቻቸውን ያለደጋፊ አስቀርተው በሚያስደንቅ ጀግንነት ፈንጂ ላይ ተረማምደው አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍስሰው ሕይወታቸውን ገብረው የሰጡን ድል እንጂ እንደ ጠላቶቻችን ፉከራማ ቢሆን ኖሮ ዛሬ በዚህ ባማረ ሁኔታ ተገናኝተን ድልን ለማወደስ ባልበቃን ነበር።
ኢትዮጵያ ከአንድ ወር በፊት ከካዛጊታ ወደ ባቲ በተደረገው እልህ አስጨራሽ የትጥቅ ትግል ውጊያ ሽንታቸውን እየጠጡ የሚጓዙ ጀግኖች ነበሯት፤ ኢትዮጵያ የጭፍራን ምሽግ ሰብሮ ብሬ ዶቃ ላይ ለቁጥር በሚያታክት ደረጃ የተደረገባቸውን ማጥቃት በቂ ድጋፍ ሳያገኙ ለብዙ ሳምንታት ብቻቸውን ገትረው መያዝ የሚችሉ ጀግኖች ያላት አገር ነች። ኢትዮጵያ ቡርቃ ከተያዘ በኋላ 80 ና 90 ኪሎ ሜትር በአገር ተጉዞ ሀርቡ ላይ በጥልቀት መቁረጥ የሚችል ጀግና ሠራዊትና የጦር መሪ ያላት አገር ናት። ኢትዮጵያ ኮምቦልቻ ተይዞ ጠላት በደሴ ዙሪያ በሚንቀሳቀስበት ወቅት ብዙ በረሃን በማቋረጥ ቆርጦ ዞብልን መያዝ የሚችል ጀግና ሠራዊትና መሪ ያላት አገር ናት።
እነዚህ ጀነራሎች ለድል ያበቁን በትጥቅ ብዛት ሳይሆን በልብ ነው፡፡ ጠላቶቻችን በሳተላይት ምስል ሁሉ ሲታገዙ እንደነበር ሁላችሁም የምትገነዘቡት ነው። አርቀን ማሰብ የኢትዮጵያን መጽናት በጥልቀት ማየት የሚያስፈልገን ዋና ምክንያት በተቃራኒ የቆሙ ሐይሎች በብዙ ሙያተኞች በጥልቀት አስበው ሊበታትኑን ተነስተው ነበርና ፈጣሪያችንን ይዘን ሕይወታችንን ሳንሰስት ለመስጠት ተዘጋጅተን ባገኘነው ድል ውስጥ አርቆ ማሰብና ብልሀት ከጀግንነቱ እኩል ትርጉም ነበራቸው።
አንድ አባት ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ታላቁ ልጅ ታታሪ፣ ታዛዥና የዋህ ቢሆንም ብልሀት ይጎለዋል ፤ ነገር ግን ታናሹ እንደ ታላቁ አይነት ባህርይ ያለው ቢሆንም በብልሀትና አርቆ በማሰብ ይልቅ ነበርና አባት ኃላፊነት የሚሰጠው ለታናሹ ነበር፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ ታላቁ አባቱን ቁጭ አድርጎ እኔ ታላቅ ሆኜ እያለሁ እድሜዬን ሙሉ ካንተ ጋር እየለፋሁ እየሠራሁ ኃላፊነት የምትሰጠው ለታናሽ ወንድሜ ነው፤ ለምን ይህንን ታደርጋለህ ብሎ አባቱን ጠየቀው?
አባትየውም መልሱን ከመመለሴ በፊት አንድ ቦታ ልላክህ ይለዋል፡፡ አቶ አበበ ጋር ሂድና እንቁላል ለመጣል የደፈረሱ ዶሮዎች ካሉ ጠይቀህ ና እነሱን በማርባት ትርፍ ማግኘት ይኖርብናል ይለዋል፤ ልጁም በታዘዘው መሰረት ሄዶ ጥያቄውን ጠይቆ ይመለሳል ፤ አባትም ጠየቀ፤ ሰንት ዶሮ አለው፤ አምስት፤ ዋጋቸው ስንት ነው? እሱንማ አልጠየኩም፤ በል ተመልሰህ ጠይቅ፤ እሺ ብሎ ተመልሶ ይጠይቃል፤ ሰንት አሉህ? መቶ ሀምሳ ብር፤ መቼ ሊያቀርብልን ይችላል? እሱንማ አልጠየኩም፤ ተመልሰህ ጠይቅና ና፤ ጠይቆ መጥቶ ነገ ሊያቀርብ ይችላል ይለዋል፡፡ ታላቁን ከጎኑ ያስቀምጥና ታናሹን አቶ አበበ ጋር ሂድና እንቁላል ለመጣል የደረሱ ዶሮዎች ካሉ ጠይቀህ ና፤ እነሱን በማርባት ትርፍ ማግኘት ይኖርብናል ይለዋል፡፡
ልጁም በታዘዘው መሰረት ሄዶ አቶ አበበ 5 ዶሮዎች አሉት፤ እያንዳንዳቸው 150 ብር ናቸው፤ የምንገዛ ከሆነም ነገ ሊያቀርበልን ዝግጁ ነው፤ ነገር ግን አንድ ሳምንት ብንሰጥህስ ስለው እንዲያማ ከሆነ አስር ዶሮዎች 150 ሳይሆን 120 ብር አድርጌ ላቀርብላችሁ አችላለሁ ብሎኛል፤ ተጨማሪ ጊዜ ብንሰጥህስ ስለው እንደዛማ ከሆነ ዶሮዎቹን ወደ 25 ከፍ አድርጌ ዋጋቸውንም በ75 ብር ላቀርብላችሁ እችላለሁ ሲለኝ በዚህ ዋጋ ተስማምቼ መጥቻለሁ ፤ አሁን ለእነዚህ ዶሮዎች የሚሆን ቦታ እናዘጋጅ ይላል።
አየህ ልጄ አንተ አንድ ጉዳይ ጨርሰህ ለመምጣት ሦስት ጊዜ ስትመላለስ እርሱ ግን ለተመሳሳይ ጉዳይ ሄዶ ትርፋማ የሚያደርገንን መንገድ ተስማምቶ ተመልሷል። እናም ለዚህ ነው ኃላፊነት የምሰጠው አለ። እናም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለይቶ ለመንግሥት ኃላፊነት የሚሰጠው አርቀን አስበን መጀመር ሳይሆን እንድንጨርስ ስለሆነ ይህንን ኃላፊነት የሰጠን ሕዝብ ለምንወስናቸው አንዳንድ ውሳኔዎች ለእሱ ጥቅም ሲባል የተደረጉ መሆናቸውን ማመን መገንዘብ ያስፈልጋል።
አሰላስለን ተመልክተን ለዘላቂ ድል የሚያበቁን ታክቲኮች ቀይሰን ኢትዮጵያን የሚያጸና ዘላቂ ድሏን ለማረጋገጥ የሚወሰዱ መራር እርምጃዎች ካሉ ለመረጠን ሕዝብ ጥቅም ሲባል መሆኑን መገንዝብ ያስፈልጋል። የአገራችን የህልውና አደጋ ጨርሶ አልተወገደም፤ ጊዜው አሁን ነወይ? ጥቃት ደርሶብን ሲያበቃ የሚሉ ድምጾችም ይደመጣሉ። እውነት ነው፤ የአገራችን የህልውና አደጋ ጨርሶ አልተወገደም፤ ለዚህም ነው ሐይል መሰብሰብ የዝግጅት የስትራቴጂ ብልጫ ማድረግ ከሁሉም በላይ ሳይገነዘብ የተበተነ ሕዝብ ካለ አገሩን ለመታደግ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ለማድረግ የተወሰነበት ዋናው ምክንያት የህልውና አደጋው ጨርሶ ያልተወገደ በመሆኑ ነው። ነገር ግን እኛ አስረን ነው ክስ የሰረዝነው፤ አባቶቻችን ግን ወዲያው ማርከው ነው ፈረሶቻቸው ላይ ጭነው አንዲያገግሙ አድርገው የመለሱት፤ ኢትዮጵያዊ ከሆንን እንደ አባቶቻችን ይቅር ማለትንና በሰላም መድረክ ማሸነፍን የታሪካችን አካል አድርገን ልጆቻችንን ማውረስ እንደሚገባ ማመን ከሁላችን ይጠበቃል።
ጦርነት መልከ ብዙ ነው፤ በሁሉም ግንባር የመዘጋጀት ብልጫ ያስፈልጋል፤ በባለፈው ውጊያ የነበሩ ድክመቶች ዋጋ ያስከፈሉንን ድካሞች ማረም ይጠይቃል፤
የተከበራችሁ መኮንኖች
ዜጎችና በዚህ ስፍራ የምትገኙ እንግዶች፤ ከሕወሓት ስህተቶች ስድስት ነገሮችን እንድንማር እጠይቃችኋለሁ፤ ሕወሓት የያዘው ከፋፋይ ሃሳብ ያነሳው የሰፈር አጀንዳ የተጠናወተው ክፋት፣ ጥላቻ፣ ሌብነት ለከፍተኛ ሽንፈት ያበቁት ወደፊትም ድል በሰፈሩ እንዳይደርስ የሚያደርጉት እኩይ ባህርይዎቹ ቢሆኑም ከዚህ ሁሉ ግን ባለፈው አንድ ዓመት ገደማ ምናልባትም ዘለግ ብለን ሦስት ዓመት ገደማ ብንመለከት ሕወሓት በትክክል ማሰብ ባለመቻሉ በሕዝቡ ላይ ያደረሰውን ጫና ለማየት ስለሚያግዝ አንደኛ ለውጡ እንደመጣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ እንዲያደርግልን ጠይቀን ሕዝቡም በደሉን ረስቶ በዳዮቹን አቅፎ ለመኖር ሲሰናዳ ያን የለውጥ ጉዞ ተቀብሎና ደግፎ መቆም ያልቻለው ሕወሓት የመጀመሪያውን ታሪካዊ ስህተት ሰርቷል። ያገኘውንም ይቅርታ እንዲያጣና ከፍተኛ ጥፋት እንዲደርስበት ሆኗል።
ሁለተኛው ብልጽግና ሲመሰረት ሕወሓት ከራሱ ክብርና ስም ዘሎ ለትግራይ ህዝብ ቢቆረቆር ኖሮ ከብልጽግና ለመውጣት ምናልባት የከፋ እንኳን ከሆነ ለሁለት ተከፍሎ ከፊሉ ብልጽግና ጋር መቆየት ቢችል ኖሮ በርካታ ዜጎቹን መታደግ ይችል ነበር። ይህንን ማድረግ ባለመቻሉ የሌብነት ጥጉ ተከፍቶ እንዲታይና የክፋቱ ጥግም ተከፍቶ እንዲታይ ስላስቻለ ብዙውን ነገር አበላሽቷል።
ሦስተኛ ብልጽግና በትግራይ ክልል ውስጥ ለመወዳደርና ለማሸነፍ ብዙም ዝግጁ ባልነበረበት ወቅት ራሱ በጻፈው ህገ መንግሥት በፌዴራል መንግሥት የሚተዳደሩ የአገር መከላከያ ሠራዊት የምርጫ ቦርድ መኖር አለበት ብሎ ሲያበቃ የምርጫ ቦርድን ጥሶ የምርጫ ኮሚቴ በመሰየም የሄደበት ሁኔታ ዋጋ አስከፍሎታል። በጊዜውም የፌዴራል መንግሥት ወጪ ሸፍኖ የሚያካሄደውን ምርጫ ራሱ ዋጋ ከፍሎ የጨረቃ ምርጫ ለማድረግ ተገዷል። የዚህም ውጤት ብዙ መዘዝ አምጥቶበታል።
አራተኛ የሰሜን እዝ ጥቃት በብዙ መንገድ ተገልጿል።በአንድ መንገድ ብቻ እንመልከተው፤ በሺ የሚቆጠሩ መኮንኖች ለ20 ዓመትና ከዛ በላይ መከላከያን ያገለገሉ በዘር አደራጅቶ ከመከላከያ ውጡ ማለት ሕዝቡንም ራሱንም በእጅጉ የሚጎዳ ነገር ነበር፤ እያጠቃን አንኳን እነዛን ሃይሎች በውስጡ አቆይቶ ቢሆን ኖሮ በሶስት ሳምንት ማሸነፍ የሚቻል አልነበረም። የወጡት ሃይሎች በከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ሀብት ያላቸው ይሆናሉ፤ በዝቅተኛ ደረጃ ያሉት ደግሞ ቢያንስ ለአንድ ዓመት ደመወዝ ጡረታ አልባ አገር ከሃዲ ይሆኑና ከሚያሸንፈው አገር መከላከያ ተነጥለው ከሚሸነፈው ሽፍታ ጎራ እንዲሆኑ ያስገደደ ደካማ ውሳኔ ነበር።
አምስተኛ ከመቀሌ ስንወጣ ወጡልኝ ብሎ ከሚከተል ደጋግሞ ቢያስብ ኖሮ የብዙ ወጣቶችን ህይወት ከመቀጠፍ ያድን ነበር።
ስድስተኛ ወደደሴ የሚያደርገው ጉዞ ቁልቁለት ሆነልኝ ብሎ ሳይዘጋጅ ሳያስብ ራሱን በበቂ ሁኔታ ሳያዘጋጅና እድል ቢቀና እንኳን እንዴት አድርጎ አገር አንደሚመራ ሃሳብ ሳይነደፍ በእውር ድንብር መጓዙ ስላሸነፍክ ብቻ ከግብህ በላይ መጓዝ ተገቢ እንዳልሆነ በእጅጉ የተማርንበትና በመልሶ ማጥቃቱ ከአፋርና ከአማራ ክልል ካስወጣን በኋላ ተጨማሪው ጉዞ አያስፈልግም ያልነው የእውር ድንብር ጉዞ ውጤቱ አደገኛ መሆኑን ከሕወሓት በመማር ጭምር ነው።
ሰባተኛ አሁን ወደ ትግራይ ክልል የማንገባበት በርካታ ምክንያቶች ያሉን ቢሆንም አንገባም ብለን ከቆምን በኋላ ነገሩን በተለየ መልኩ ለማየት ጥረት እያደረግን ባለንበት በዚህ ወቅት ሕወሓት አሁንም አላረፈም፤ አሁንም በግራ በቀኝ ሊነካካን ይፈልጋል። ለሰባተኛ ስህተት የሚጓዘው ሕወሓት በፍጹም ድል ማግኘት የማይችል እንኳን ቢሆን በወጣት የትግራይ ልጆች ህይወት የመቀጠፍ የመቁሰል አደጋ የሚያስከትል ስለሆነ ሰባተኛው ስህተቱ መስመር ስቶ ሳይሄድ መማር የሚችልበትን እድል መፍጠር የራሱ ቢሆንም አንኳን እንደ ባላንጣ አትንኩን እረፉ ለማለት እወዳለሁ። የነካካችሁን እንደሆነ በተለመደው መንገድ የከፋ ቅጣት ይደርስባችኋል።
ትላንት እንኳን ክስ አቋርጠን እስረኞች ይውጡ ስንል የሕወሓት ጀሌዎች የአማራና የኦሮሞ አካውንት በመክፈት እኛን ለማባላት ሳይተኙ አድረዋል፤ በእርግጥ አማራና ኦሮሞ በትናንሽ ጉዳይ የመኳረፍ ባህርይ አላቸው። ነገር ግን ኢትዮጵያ ስትነካ አጀንዳዎቻቸውን ወደኋላ ጥለው በአንድ ጉድጓድ ሞተው የኢትዮጵያን ነጻነት እንደሚያጸኑ ባለፉት ጥቂት ወራት ተመልክተናል። በመሆኑም ይህ ከንቱ ሙከራ ሊከፋፍለንም ሆነ ሊያስቆመን እንደማይችል ተገንዝበው እኛን ከመነካካት እንዲቆጠቡና ሰባተኛውን ስህተት እንዳይፈጽሙ እመክራለሁ።
የተቀረው አለምም ዓይኑን እንዲከፍት እውነት እንዲፈልግ በባለፈው አንድ ዓመት ለነበረው ጦርነት የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ሰላም እየፈለገና ለሰላም እጁን እየዘረጋ በተደጋጋሚ ጥቃት የተፈጸመበትና በዓለም መድረክ ፍትህ ያጣበት መሆኑን የምናውቅ ቢሆንም አሁንም የዘረጋነውን የሰላም አጅ ባለመቀበል ትንኮሳ የሚያደርገውን ሃይል ዓለም አይኑን ገልጦ እንዲያይ እውነት አንዲፈለግ ለማሳሰብ እፈልጋለሁ።
የትግራይ ሕዝብ ባለፈው አንድ ዓመት በኢኮኖሚ በዲፕሎማሲ በፖለቲካ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። አሁን አይኑን መግለጥ ያለበት ጊዜ ይመስለኛል። ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ እናቶች አሁንም ለአገራቸው ሰላምና አንድነት ወደላይ ማንጋጠጥና ፈጣሪያችሁን መማጸን አታቁሙ። ሁለተኛ ወጣቱ በተለይም የአገር መከላከያ ሚኒስቴርና በየክልል ያሉ ልዩ ሃይሎች ክንዳቸውን ማበርታትና መናበብ እንዳያቋርጡ። ሶስተኛ ከሁሉ በላይ የድላችን ሚስጥር አንድነት መጠበቃችን ነውና አንድ መሆን መደመር በጋራ መቆም ለዘላቂ ድል ስለሚያበቃን ኢትዮጵያውያን ሆይ፤ አገራችሁን መታደግ የምትሹ ከሆነ አሁንም በመደመር አንድ መሆንን አበክራችሁ ፈልጉ።
እኛ ነጻ አገር ተረክበናልና ይህንን ለልጆቻችን ለማስረከብ ከፍላጎቶቻችን ባሻገር የሌሎችንም ፍላጎት መገንዘብ ይኖርብናል። ትላንት በነበረው ውሳኔ እንኳን አንደኛው የኢትዮጵያ ጫፍ ሲያዝን ሌላው ደግሞ ሲስቅ ማየት የቻልነው ኢትዮጵያውያን በአንዳንድ ውሳኔዎች ላይ ስለወንድማችን ስንል በጋራ የመቆምና የማለፍ ልምምድ ገና ብዙ እንደሚቀረን ያመላክታል ።
እኛ ስንጠቃ ብቻ ለውጊያ እንድ የምንሆን ሳይሆን ስለወንድሞቻችን ደስታ የራሳችንን መሻት የምንቆጥብ ስለሌሎች ፍላጎት የእኛን ፍለጎት የምንተውና በጋራ መቆም አንዲሁ በነጻ የማይገኝ መሆኑን የምናስብ ሕዝቦች መሆን ይኖርብናል። ከዚያም ባሻገር የወደመብን በርካታ ሀብት አለና ይህንን በመገንባት የሕዝቦቻችን በደል እንዲሽር ለማድረግ መሰብሰብ አመራር መስጠት ወደሌላ ግንባር ማተኮር ስለሚኖርበን ኢትዮጵያውያን በጀመርነው መንገድ ብቻ ሳይሆን በሌሎች መንገዶች መጓዝ እንዳለብን አንድታስቡ ከአደራ ጭምር ላሳስብ እወዳለሁ።
የአገር መከላከያ ሚኒስቴር፤ እናንተ ጀግኖች ኢትዮጵያን የሚመጥን ዘመን የሚሻገር የአንድነታችን ምልክት የሚሆን የህልውናችን ምሰሶ የሆነ ለሁላችን ኩራትና መመኪያ የሆነ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር እንድትገነቡ መንግሥት በታላቅ ኃላፊነት ሊያስገነዝባችሁ ይፈልጋል። የሕወሓትን መንገድ ሳንከተል ኢትዮጵያዊ የሆነ ተቋም ብንገነባ ልጆቻችን በሰላም እንዲኖሩ የሚያመቻች ስለሆነ ዛሬን ሳይሆን ነገን እያሰባችሁ ተቋሙን እንድትገነቡ የሰላም ጊዜ የሚባል ለመከላከያ የለምና በሰላም ጊዜ ሰፊ ዝግጅት በማድረግ ድል እንድትጎናጸፉ እንዳትዘናጉ አደራ እላለሁ።
በዚህ አስከፊ ጦርነት ኢትዮጵያን እናፈርሳለን ብለው የተነሱ ሃይሎች ኢትዮጵያ ዛሬም አንደትላንቱ የማትፈርስ መሆኗን በድጋሚ ለማረጋገጥ ህይወታቸወን የገበሩ አጥንታቸውን የከሰከሱ ደማቸውን ያፈሰሱ ጀግኖችና የጦር መሪዎችን ኢትዮጵያ አብዝታ ታመሰግናለች። ዛሬ ባለንበት በመከላከያ ዋናው መስሪያ ቤት የተገነባው ግንባታ ኢትዮጵያን የሚመጥን ሲሆን ይህ ስራ አሁን ባለበት ደረጃ እንዲደርስ በርካታ ሰዎች የተለየ ሚና የነበራቸው ሲሆን በዲዛይን፣ በግንባታ እንዲሁም ወጣቶች ግቢውን በማስዋብ አመርቂ ስራ ስለሰሩ ከሁሉ በላይ የቀድሞውን የመከላከያ ሚኒስቴር ዶክተር ቀነዓንና ዴኤታውን ዶክተር ጌታቸውን አብዝቼ ማመስገን እፈልጋለሁ።
አሁን ያሉ ሚኒስትርና ሚኒስትር ዴኤታዎች ይህንን ግቢ ባለበት ሁኔታ የመጠበቅ እና የማልማት ኃላፊነት አንዳለባቸው እያስገነዘብኩ ተቋም መገንባት ሃይል መገንባት ማባዛት ማዘመን መዋጋት ሳይሆን ውጊያ ማስቀረት የሚችል የአገር መከላከያ ሚኒስቴር መንግሥት በቅርበት ይገነባል። የኢትዮጵያ ነጻነት፣ አንድነትና ሉአላዊነት ዛሬም አንደትላንቱ በልጆቿ ደምና አጥንት ተከብሮ ይኖራል። ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ትኑር። ለዚህ ቀን ለዚህ ማዕረግ ላበቃን ፈጣሪያችን ምስጋና ይሁን። ለእናንተም ልቦና ይስጣችሁ፤ አመሠግናለሁ።
አዲስ ዘመን ጥር 3/2014