ታኅሣሥ 14 ቀን 2014 ዓ.ም በሆቴል ዴሊ ኦፖል የተካሄደን የሙያና ቴክኒክ ትምህርት ዘርፉን የገመገመ፤ የተሻለ ሥራ አፈፃፀም ላሳዩትም እውቅና የሰጠን መድረክ አስመልክተን በዚሁ ገጽ ላይ ጽሑፍ ማስነበባችን ይታወሳል። ዘርፉ ያለበትን ሁኔታ በተመለከተም በዛሬው ዕለት እንደምናቀርብ በቀጠሮ መለያየታችንም ግልፅ ነው። በመሆኑም፣ በዚሁ መሠረት በዕለቱ ከቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች መካከል ከልምድ ልውውጥና አርአያነት አኳያ ይጠቅማል ያልነውን ይዘን ቀርበናል።
ጥናቱ የተዘጋጀውና የቀረበው መድረኩን ባዘጋጀው በአዲስ አበባ መስተዳድር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ሲሆን የጥናቱ አቅራቢም የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ማረጋገጥ ዳሬክቶሬት ነው።
ጥናቱ “በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት፣ የሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ባለስልጣን የ2013 በጀት ዓመት የግልና የመያድ [መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት] ኮሌጆች የውጭ ኢንስፔክሽን ትንተና ማጠቃለያ ሪፖርት” የሚል ሲሆን ከላይ በጠቀስነው መድረክ ላይ ጥናቱን ያቀረቡት ደግሞ በዳይሬክቶሬቱ የቴ/ሙ/ የኢንስፔክሽን ቡድን መሪ አብረሃም ምትኩ ነበሩ።
እንደ አቶ አብረሀም ማብራሪያ የኢንስፔክሽኑ የትኩረት መስኮች ግብዓት /Input/፤ ሂደት /Process/፤ እንዲሁም ውጤት/Outcome ሲሆኑ፤ የኮሌጆችን ደረጃ ምደባ ለማከናወን በመለኪያነት ለተቀመጡት ለእነዚህ የትኩረት መስኮች ክብደት በመስጠት የተከናወኑ ናቸው። ሂደቱም፤
• ኮሌጁ በኢንስፔክሽን አፈፃፀም ያገኘው ውጤት ከ50% በታች ከሆነ ደረጃ 1 (ስታንዳርድ የማያሟላ) ።
• ኮሌጁ በኢንስፔክሽን አፈፃፀም ያገኘው ውጤት ከ50%-69.99% ከሆነ ደረጃ 2 (በመሻሻል ላይ ያለ)። • ኮሌጁ በኢንስፔክሽን አፈፃፀም ያገኘው ውጤት ከ70%-89.99% ከሆነ ደረጃ 3 (ስታንዳርዱን ያሟላ)።
• ኮሌጁ በኢንስፔክሽን አፈፃፀም ያገኘው ውጤት ከ90%-100% ከሆነ ደረጃ 4 (ስታንዳርዱን በከፍተኛ ደረጃ ያሟላ)።
በማለት በጥናቱ አመልክቷል። ጥናቱ “አጠቃላይ የኢንስፔክሽን ውጤት በመቶኛ ሲገለፅ” በሚለው ስር የውጭ ኢንስፔክሽን ከሚሠራላቸው 87 ኮሌጆች ውስጥ 87ቱም የተሠራላቸው ሲሆን አፈጻጸሙ 100% መሆኑን ካስታወቀ በኋላ፤ በተሰራው የውጭ ኢንስፔክሽን ሥራ መሠረት የተፈረጁት 74 ኮሌጆች ሲሆኑ 6ቱ (8%) ደረጃ 1፣ 49ዱ (66%) ደረጃ 2፣ 19ቱ (26%) ደረጃ 3 ሲሆኑ፤ ደረጃ 4 የገባ ኮሌጅ የለም፡፡ በዚህ ትንተና መሠረት 74%ቱ ደረጃ 1 እና 2 ስለሆኑ ኮሌጆቻችን ብዙ መሥራት እንዳለባቸው ያሳያል፡፡
በማለት ዘርፉ ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ያሳያል። በመቀጠልም፤ “በዚህ መረጃ መሠረት 6 ኮሌጆች የጥራት እና የብቃት ችግር ስላለባቸው በኢንስፔክሽን መመሪያ ቁጥር 03/2012 ዓ.ም ገጽ 18 ተራ ቁጥር 16 ንዑስ ቁጥር 3 ላይ በተቀመጠው መሠረት አንድ ኮሌጅ ደረጃ 1 ሆኖ ከ40% በታች ውጤት ካገኘ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚዘጋ በማስቀመጡ ዳሎል ቢዝነስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ እና ባዮስ ቢዝነስ ኮሌጅ ደረጃቸው ከ40% በታች በመሆኑ በቀጥታ እንዲዘጉና ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረግ ይኖርበታል።” ይላል።
“በተጨማሪም በመመሪያው ገጽ 18 ተራ ቁጥር 16 ንዑስ ቁጥር 4 ላይ በተቀመጠው መሠረት አንድ ኮሌጅ ደረጃ 1 ሆኖ ከ40% – 49.99% ውጤት የሚያስመዘግብ ከሆነ ለመጀመሪያ ዙር ለአንድ ዓመት የሚቆይ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥና በቀጣዩ ዓመት በዳግም ኢንስፔክሽን ደረጃቸውን የማያሻሽሉ ከሆነ እንዲዘጉ ይደረጋል ብሎ በማስቀመጡ ካፒታል ሆቴል ማኔጅመንት ኮሌጅ፣ ኪዊንስ ኮሌጅ /ቄራ ካምፓስ/፣ አዲስ አበባ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እና ጠብታ ፓራሜዲክ ኮሌጅ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው መደረግ ይኖርበታል።
” ሲልም የውሳኔ ሀሳቡን ያቀርባል። “በ2013 በጀት ዓመት በውጭ ኢንስፔክሽን ውጤት መሰረት ከ80% በላይ ውጤት ያመጡ ኮሌጆች ዝርዝር”ን የሚገልፀው ይህ የባለስልጣኑ ጥናት ኮሌጆቹንም፤ ሰላም (መያድ)፣ 82.80፣ ደረጃ 3፤ አድማስ ኮሌጅ / መስቀል ካምፓስ/ (የግል)፣ 82.65፣ ደረጃ 3፤ እና አድማስ ኮሌጅ /መካኒሳ ካምፓስ/ (የግል)፣ 82.57፣ ደረጃ 3 በማለት ይዘረዝራቸዋል። “በዚህ መረጃ መሠረት 3 ኮሌጆች ከ80%
በላይ ውጤት በማግኘት የጥራት ስታንዳርዱን ያሟሉ በመሆናቸው ተሞክሮዎቻቸውን የሚያሰፉበትንና በላቀ ደረጃ ስታንዳርዱን እንዲያሟሉ የሚደገፉበትን አቅጣጫ ልንከተል ይገባል፡፡” ሲልም ይመክራል። ይህ በዓይነቱ የመጀመሪያ የተባለ ጥናት “ዝቅተኛ አፈጻጸም ካላቸው ስታንዳርዶች መካከል” በማለት ያስቀመጣቸው ተቋማት ያሉ ሲሆን እነሱም፤
• ስታንዳርድ 4፡- የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋሙ/ኮሌጁ ለደረጃው በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት የማሰልጠኛ ግብዓቶች፣ የመገልገያ ሕንፃዎች ፋሲሊቲ እና ለስልጠና የሚያገለግሉ መሣሪያዎች አሟልቷል በሚል ከተመዘኑ ኮሌጆች መካከል 55% በደረጃ 1፣ እና 30% በደረጃ 2፤ በድምሩ 85% ከደረጃ በታች፤
• ስታንዳርድ 5፡- የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋሙ/ኮሌጁ የተደራጀ የትምህርትና ስልጠና የቴክኖሎጂ ልማት ሠራዊት ፈጥሯል በሚል የተመዘኑ ኮሌጆች መካከል 54% በደረጃ 1 እና 8% በደረጃ 2 በድምሩ 62 % ከደረጃ በታች፤
• ስታንዳርድ 8፡- የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋሙ/ ኮሌጁ አሳታፊ ትኩረት የሚሰጣቸው የሰው ኃይል ፍላጎት መሠረት የትኩረት መስክ (Distinctive area of competency) እና ተቋማዊ ልማት እቅድ (Institutional Development Plan) አዘጋጅቷል በሚል ከተመዘኑ መካከል 19% በደረጃ 1፣ እና 53% በደረጃ 2፤ በድምሩ 72% ከደረጃ በታች ናቸው ። “የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው ስታንዳርዶች” ይልናም፤
• ስታንዳርድ 1፡- የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋሙ/ኮሌጁ ለደረጃው በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት የማሰልጠኛ ግብዓቶች የመገልገያ ሕንፃዎች ፋሲሊቲ እና ለስልጠና የሚያገለግሉ መሣሪያዎች አሟልቷል በሚል ከተመዘኑት ኮሌጆች መካከል 59% በደረጃ 3፣ 23% በደረጃ 4፤ በድምሩ 82% ደረጃቸውን ያሟሉ፤
• ስታንዳርድ 6፡- የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋሙ/ኮሌጁ ለማኅበረሰቡ ምቹ፣ የማያሰጋ እና ደህንነታቸውን የሚያረጋግጥ የማሰልጠኛ አካባቢ ፈጥሯል በሚል ከተመዘኑት መካከል 56% በደረጃ 3 እና 16% በደረጃ 4 በድምሩ 72% ደረጃቸውን ያሟሉ፤
• ስታንዳርድ 7- የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋሙ/ ኮሌጁ ራዕይ፣ ተልዕኮ፣ እሴቶች አሉት በሚል ከተመዘኑት መካከል 64% በደረጃ 3፣ 18% በደረጃ 4፤ በድምሩ 82% ደረጃቸውን ያሟሉ መሆናቸውን ከትንታኔው መረዳት ይቻላል፤ በማለት ያስቀምጣል። “በሂደተ ስታንዳርዶች ዝቅተኛ አፈጻጸም ካላቸው መካከል”ም የሚከተለውን ግኝት ያስቀምጣል።
ስታንዳርድ 9 የሰልጣኞች የውጤት ተኮር ስልጠና ተሳትፎ ጎልብቷል በሚል ከተመዘኑ ኮሌጆች መካከል 23% በደረጃ 1፣ 52% በደረጃ 2፤ በድምሩ 85% ከደረጃ በታች፤ ስታንዳርድ 10 አሰልጣኞችና ሰልጣኞች ችግር ፈቺ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን 100% የመቅዳት አቅም አዳብረዋል በሚል ከተመዘኑ መካከል 73% በደረጃ 1፤ 16% በደረጃ 2፤ በድምሩ 86% ከደረጃ በታች፤ ስታንዳርድ 12 የተቋሙ/የኮሌጁ አመራርና አሰልጣኝ ለሁሉም ሰልጣኞች ተስማሚና ዘመናዊ የስነ-ማሰልጠኛ ዘዴዎችን በመጠቀማቸው የሁሉም ሰልጣኞች የስልጠና ተሳትፎ ጎልብቷል በሚል ከተመዘኑት መካከል 38% በደረጃ 1፣ 35% በደረጃ 2፤ በድምሩ 73% ከደረጃ በታች፤ ስታንዳርድ 15 ሰልጣኞች በትክክል ተመዝነዋል፣ አስፈላጊው ግብረ መልስ ተሰጥቷቸዋል በሚል ከተመዘኑት መካከል 19% በደረጃ 1፣ እና 53% በደረጃ 2፤ በድምሩ 72% ከደረጃ በታች፤ ስታንዳርድ 16 የተቋሙ/ኮሌጅ አመራር የልዩ ልዩ አደረጃጀት ተጠሪዎች ያቀዷቸው እቅዶች በተያዘላቸው ጊዜ፣ ጥራትና መጠን መሠረት መፈጸማቸውን ይከታተላሉ በሚል ከተመዘኑት መካከል 47% በደረጃ 1፣ 32% በደረጃ 2፤ በድምሩ 79% ከደረጃ በታች መሆናቸው ተመልክቷል። በ”የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው ስታንዳርዶች” ስር ደግሞ፤
• ስታንዳርድ 11 አሰልጣኞች የሚሰጡት ውጤት ተኮር ስልጠና በአግባቡ የታቀደ፣ ለስልጠናው አስፈላጊ በሆኑ የስልጠና መሣሪያዎች የተደገፈ ሰልጣኞችን ብቁ፣ ተወዳዳሪና የሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ታልሞ የተዘጋጀ ነው በሚለው ከተመዘኑ ኮሌጆች መካከል 61% በደረጃ 3፣ 19% በደረጃ 4፤ በድምሩ80% የተሻለ አፈጻጸም፤
• ስታንዳርድ 17 ተቋሙ/ኮሌጁ የሰው፣ የገንዘብ እና የንብረትና ሀብት አጠቃቀም ሥርዓት ዘርግቶ ተግባራዊ አድርጓል በሚል ከተመዘኑ መካከል 66% በደረጃ 3፣ እንዲሁም 20% በደረጃ 4፤ በድምሩ 76% የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው እንደሆነ ያሳያል፤ ሲል ያስቀምጣል። “በዚህም መሠረት ዝቅተኛ አፈጻጸም ካላቸው ስታንዳርዶች መካከል” በሚለው ስር “ስታንዳርድ 17 ተቋሙ/ ኮሌጁ በከተማ ደረጃ የተቀመጠውን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተሳትፎና ስትራቴጂክ ግቦችን አሳክቷል በሚል ከተመዘኑ ኮሌጆች መካከል 29% በደረጃ 1፣ 51% በደረጃ 2፤ በድምሩ 80% ከደረጃ በታች የሆኑ እንደሆነ ያሳያል” ይላል።
“የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው ስታንዳርዶች” በሚለው ስር ደግሞ፤ ስታንዳርድ 23 በተቋሙ/በኮሌጁ አሰልጣኞች፣ አመራርና አስተዳደር ሠራተኞች መካከል ጥሩ ተግባቦት እና መስተጋብር ተፈጥሯል፣ ሌብነትና ብልሹ አሠራርን የመታገልና የተጠያቂነት ስሜት ዳብሯል በሚል ከተመዘኑ ኮሌጆች መካከል 57% በደረጃ 3፣ 18% በደረጃ 4፤ በድምሩ 75% የተሻለ አፈጻጸም፤
• ስታንዳርድ 24 ተቋሙ/ኮሌጁ ከአካባቢው ማኅበረሰብና ከአጋር ድርጅቶች ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠሩ ለተቋሙ/ለኮሌጁ ድጋፍ አስገኝቷል በሚል ከተመዘኑ መካከል 64% በደረጃ 3፣ እንዲሁም 20% በደረጃ 4፤ በድምሩ 84% የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው መሆኑን ያሳያል። “ከ24ቱ ስታንዳርዶች ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበባቸው” በሚል ርዕስ ስር፤
• ስታንዳርድ 24፡- ተቋሙ/ኮሌጁ ከአካባቢው ማኅበረሰብና ከአጋር ድርጅቶች ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠሩ ለተቋሙ/ለኮሌጁ ድጋፍ አስገኝቷል በሚለው ከተመዘኑት መካከል 64% በደረጃ 3፣ እንዲሁም 20% በደረጃ 4፤ በድምሩ 84% የተሻለ አፈጻጸም፤
• ስታንዳርድ 1፡- የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋሙ/ኮሌጁ ለደረጃው በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት የማሰልጠኛ ግብዓቶች የመገልገያ ሕንፃዎች ፋሲሊቲ እና ለስልጠና የሚያገለግሉ መሣሪያዎች አሟልቷል በሚል ከተመዘኑት መካከል 59% በደረጃ 3፣ 23% በደረጃ 4፤ በድምሩ 82% ደረጃቸውን ያሟሉ፤
• ስታንዳርድ 7፡- የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋሙ/ኮሌጁ ራእይ፣ ተልዕኮ፣ እሴቶች አሉት በሚል ከተመዘኑት መካከል 64% በደረጃ 3፣ 18% በደረጃ 4፤ በድምሩ 82% ደረጃቸውን ያሟሉ መሆናቸው ከትንታኔው መረዳት ይቻላል፡፡ በማለት ያሰፈረ ሲሆን፤ “ከ24ቱ ስታንዳርዶች እጅግ ዝቅተኛ ውጤት የተመዘገበባቸው” በሚለው ስር ደግሞ፤ \
• ስታንዳርድ 10፡- አሰልጣኞችና ሰልጣኞች ችግር ፈቺ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን 100% የመቅዳት አቅም አዳብረዋል በሚል ከተመዘኑት መካከል 73% በደረጃ 1፣ 16% በደረጃ 2 በድምሩ 86 % ከደረጃ በታች፤
• ስታንዳርድ 4፡- የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋሙ/ኮሌጁ ለደረጃው በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት የማሰልጠኛ ግብዓቶች፣ የመገልገያ ሕንፃዎች ፋሲሊቲ እና ለስልጠና የሚያገለግሉ መሣሪያዎች አሟልቷል በሚል ከተመዘኑት መካከል 55% በደረጃ 1፣ 30% በደረጃ 2፤ በድምሩ 85 % ከደረጃ በታች፤
• ስታንዳርድ 16፡- የተቋሙ/ኮሌጅ አመራር የልዩ ልዩ አደረጃጀት ተጠሪዎች ያቀዷቸው እቅዶች በተያዘላቸው ጊዜ፣ ጥራትና መጠን መሠረት መፈጸማቸውን ይከታተላሉ በሚል ከተመዘኑ መካከል 47% በደረጃ 1፣ 32% በደረጃ 2፤ በድምሩ 79% ከደረጃ በታች እንደሆኑ ያሳያል።
አሁን ወደ መፍሔው እንምጣ
ጥናቱ “ከኢንስፔክሽን ግኝቱ ትንተና በመነሳት ከቴክኒክና ሙያ ት/ስልጠና ስትራቴጂ አንፃር ሊስተካከሉ የሚገባቸው እርምቶች” በሚል ርዕስ ስር የመፍትሔ ሀሳብ ያቀረበ ሲሆን፤
ለኮሌጆች
በስታንዳርዱ መሠረት ደረጃውን የጠበቀ የማሰልጠኛ ወርክሾፕ ቢያደራጁ፣ • የማሰልጠኛ ወርክሾፕ ለስልጠናው አስፈላጊ በሆነ ግብዓት እንዲደራጅ ይደረግ፣
የመማር ማስተማር ማሠልጠኛ መሣሪያ /TTLM/ በሙያ ምደባና ስርዓተ-ስልጠናው መሠረት ይዘቱን ጠብቆ ሁሉንም ደረጃዎች እና የብቃት አሃዶችን ባካተተ መልኩ ሥራ ላይ ቢውል፣
• ስልጠና የሚሰጡ አሰልጣኞች ደረጃ በደረጃ እስከ ደረጃ 4 ቢመዘኑ ወይም የተመዘነ አሰልጣኝ ቢቀጠር፣
• ዲኖች፣ የተቋም መሪዎችና ስልጠና አስተባባሪዎች በቴ/ሙያ ዘርፍ እስከ ደረጃ 4 የተመዘኑና አሰልጣኞችን በዕውቀት መምራት የሚችሉ እንዲሆኑ ቢደረግ፣
• ተቋሙ/ኮሌጁ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የተመራቂ ሰልጣኞችንና አዲስ ተመዝጋቢ ሰልጣኞችን መረጃ ከቅበላ እስከ ምዘና በእያንዳንዱ ሰልጣኝ ማህደር መረጃውን መልሶ ቢደራጅ፣
• ደረጃውን የጠበቀ የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን በመዘርጋት ግልፅና የተደራጀ የመረጃ ፍሰት ሥርዓት ቢዘርጋ፣ • ተመራቂ ሰልጣኞችን ከሥራ ተቋማት ጋር ማስተሳሰር የተቋሙ/ኮሌጁ ተቀዳሚ ተግባር ቢደረግ፣
ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴ/ሙያ ት/ስልጠና ኤጀንሲ በከተማ አስተዳደሩ በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሠረት
በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚገኙ የግልና የመያድ ኮሌጆች ከተለያዩ መንግሥታዊ ከሆኑና ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ጥራት ያለው የትብብር ሥልጠና እንዲፈራረሙ ተገቢው ድጋፍና ክትትል ቢሰጥ፤ በከተማው ውስጥ ያሉ ሁሉም የግልና የመያድ ኮሌጆች ወጥ በሆነ የመማር ማስተማር ማሠልጠኛ መሣሪያ /TTLM or CBLM/ እንዲያሰለጥኑ በሁሉም የስልጠና ዘርፎች እገዛና ድጋፍ ቢደረግ፤ የተቋማትና ኮሌጆች በተዘጋጀው ቼክሊስት መሠረት የውስጥ ጥራት ኦዲት እንዲያደርጉ ድጋፍ ቢደረግ ፤
ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርትና ስልጠና ጥራት ሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጫ ባለስልጣን
የእውቅና ፍቃድ በሚሰጥበት ወቅት ደረጃውን ያልጠበቀ ሾፕና ግብዓት፣ ስታንዳርዱን ጠብቆ ባልተዘጋጀና ባልተሟላ ማሠልጠኛ መሣሪያ / TTLM/፣ የዲኖችና የአሰልጣኞች ፕሮፋይል በውልና ማስረጃ በተረጋገጠ አግባብ መደራጀቱ ሳይረጋገጥ እውቅና ፍቃድና እድሳት ባይሰጥ፣ • ሰልጣኞችን ሳያስመዝኑ ከደረጃ ወደ ደረጃ በሚያሸጋግሩና ያለምዘና አስመርቀው በሚበትኑ ተቋማትና ኮሌጆች ላይ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ፣
• የተቋማትና የኮሌጆች የመረጃ አያያዝ ሥርዓት እንዲሻሻል በመደገፍ የሰለጠኑና ያጠናቀቁ ሰልጣኞችን መረጃ ተቋሙ/ኮሌጁ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እንዲደራጅና አግባብነት የሌለው የስልጠና ማጠናቀቂያ ስርጭትን ለመከላከልም በባለስልጣን መ/ቤቱ መረጃው በየወቅቱ እንዲቀመጥ የሚደረግበትን ዘመናዊ አሠራር መዘርጋት፣
• ወጥ የሆነ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ሥርዓት አፈፃፀም እንዲኖር ለማድረግ ሕግና ሥርዓትን ተከትለው የማይሄዱ ተቋማትን በየጊዜው በመለየት አስተማሪ እርምጃዎች መውሰድ፣ እንደሚገባ ጥናቱ በምክረ ሀሳቡ አሳስቧል
በ”ማጠቃለያ”ውም፤
ኢንስፔክሽን የተቋማትን/የኮሌጆችን ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት ጠንካራ ጎኖችን በበለጠ ለማጠናከር፣ ክፍተቶችን ለማረም ወይም ለማስተካከል ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡
በ2012 በጀት ዓመት የቴ/ሙያ ት/ስልጠና ጥራት ማረጋጥ ቡድን በአዲስ መልክ ከተዋቀረ ጀምሮ የኢንስፔክሽን ማዕቀፍና የተለያዩ ቼክሊስቶችን የማዘጋጀት ሥራ ከተሠራ በኋላ የበጀት ዓመቱን እቅድ ለማከናወን ወደ ተግባር በመግባት በያዝነው ዓመት በ87 ኮሌጆች የውጭ ኢንስፔክሽን የተካሄደ ሲሆን 6 ኮሌጆች /8.11%/ቱ ደረጃ 1፣ 51ዱ /68.92 %/ቱ ደረጃ 2፣ 17ቱ /22% ቶቹ ደረጃ 3 ሲሆኑ የተቀሩት 13ቱ የደረጃ ፍረጃ ያልተደረገላቸው ሲሆኑ ኮሌጆቹ ያሉበትን ሁኔታ ያሳየ እና ጥንካሬዎችንና ክፍተቶችን ለይቶ ያመላከተ ሲሆን ግኝቶችም ተገኝተዋል።
በመሆኑም የቴ/ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት/ ኮሌጆች ላይ የውጭ ኢንስፔክሽን ሥራ መሠራቱ እንደ ከተማ ስትራቴጂውን በተገቢው ከመተግበር አኳያ ጠቀሜታው የላቀ ነው። ኮሌጆቹ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ከማፍራት አንፃር የሚታይባቸውን ችግሮች ነቅሶ በማሳየት ከችግራቸው የሚወጡበትን አቅጣጫ ከማመላከትና ከመሳሰሉት አኳያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል በማለት ይደመድማል። እኛም በዚሁ እንሰናበታለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጥር 2/2014