የሰው ልጅ ስነ ውበትን ከሚለካባቸው ነገሮች አንዱ ጸጉር ነው:: የጸጉር መኖር አለመኖር ፤ የጸጉር አይነት እና ቀለም ፤ ርዝማኔ እና እጥረት የግለሰቡን ውበት እንደሚወስኑ ይነገራል::
በዚህም የተነሳ ሰዎች በተቻላቸው መጠን ለጸጉራቸው ጥንቃቄ ያደርጋሉ:: ይህ በእንዲህ እንዳለ ሳይንሳዊ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከጠቅላላው ወንዶች 60 በመቶ ከጠቅላላ ሴቶች ደግሞ 50 በመቶው ጸጉር የመሳሳት ችግር ያጋጥማቸዋል::
በዚህም የተነሳ ብዙዎች ውበታቸው የጎደለ ስለሚመስላቸው የመሸማቀቅ እና የራስ መተማመን የመጉደል ችግር ያጋጥማቸዋል:: ይህን ለማስተካከል በሴቶች በኩል ሰው ሰራሽ ጸጉርን (ሂውማን ሄር) መጠቀም አሁን ተለምዷል::
ዋጋውም በብዙ ሺ የሚቆጠር ብር ሆኗል:: በወንዶች በኩል እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ይህ ነው የሚባል መላ ያልነበረው ሲሆን አሁን ላይ ግን የጸጉር ንቅለ ተከላ ተጀምሯል::
የጸጉር ንቅለ ተከላ ታሪክ
የታሪክ ጸሐፍት እንደሚሉት የጸጉር ንቅለ ተከላ የተጀመረው በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ነው::እ.ኤ.አ በ1930ዎቹ በጃፓን የአይን ሽፋሽፍቶችን ለማስተካከል እንደተጀመረ የሚነገረው ይህ ቴክኒክ በ1950 እ.ኤ.አ በአሜሪካዊው የቆዳ ሐኪም ኖርማን ኦረንትሪየች ዘመናዊነትን ተላብሷል::በዚህ መልኩ እያደገ ሄዶች ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል::
በቴክኒክ ደረጃ ስናየው የጸጉር ንቅለ ተከላ የሚደረገው በራስ ቅል ላይ የጸጉር መሳሳት ወይም መመለጥ በሚያጋጥምበት ወቅት በሚጠፋው ጸጉር ምትክ ሌላ አዲስ ጸጉር ለመተካት ነው:: ሥራው የሚከናወነውም በቂ ጸጉር ካለበት የራስ ቅል ክፍል ላይ ጸጉር ወስዶ በሳሳው ወይም በተመለጠው የራስ ቅል ክፍል ላይ በመትከል ነው::
ሄልዝ ላይን የተባለ ድረ ገጽ እንደሚያመለክተው ከሆነ ከ80 እስከ 90 በመቶ ያሉ የጸጉር ንቅለ ተከላዎች ስኬታማ ሲሆኑ አብዛኛው ጸጉር ንቅለ ተከላው በተካሄደ ከሶስት እስከ አራት ወር ባለ ጊዜ ውስጥ ያድጋል:: በጎንዮሽ ጉዳትነት የሚነሳው በአንዳንድ ሰዎች ላይ የሚያጋጥመው የቆዳ መቆጣት ፤ ማሳከክ ፤ መልሶ መርገፍ እና መሰል ክስተቶች ናቸው::
የጸጉር ንቅለ ተከላ የሚደረገው እንዴት ነው?
በጣም ቀላል በሆነ አገላለጽ ለማስቀመጥ ያህል የጸጉር ንቅለ ተከላ ማለት በራስ ቅላችን ቆዳ ላይ ጸጉር ካለበት ክፍል ጸጉር ነቅሎ በመውሰድ በራስ ቅላችን ቆዳ ጸጉር በሌለበት ክፍል ላይ መትከል ወይም ማስገባት ማለት ነው::
ይህ ሲባል ግን በአብዛኛው ጸጉር የሚወሰደው ከራስ ቅላችን ቆዳ በተለይም ከኋለኛው የራስ ቅል ቆዳ ላይ ነው ለማለት እንጂ ከሌላ የሰውነት ክፍል ላይም ጸጉር ሊወሰድ ይችላል:: የንቅለ ተከላው ሂደት ከመጀመሩ በፊት ሐኪሙ ጸጉር የሚወሰድበትን የራስ ቅል ክፍል ካጸዳ /ስቴራላይዝ ካደረገ/ በኋላ ሕመም እንዳይሰማ ያደነዝዘዋል::
ታካሚው ሂደቱ ተሠርቶ እስከሚያበቃ ድረስ መተኛት የሚፈልግ ከሆነም ሐኪሙን መጠየቅ ይችላል:: ከዚህ በኋላ ሐኪሙ በFUE ስልት ማለትም በቆዳ ስር የሚገኘውን የጸጉር ቋት ከነቆዳው አንስቶ በማዘዋወር ወይም በFUE ስልት ማለትም በቆዳ ስር የሚገኘውን የጸጉር ቋት ቆዳው ሳይነሳ አውጥቶ በማዘዋወር ንቅለ ተከላውን ያከናውናል:: ለምሳሌ ያህልም ከሁለቱ መንገዶች አንዱ የሆነው በቆዳ ስር የሚገኘውን የጸጉር ቋት ቆዳው ሳይነሳ አውጥቶ በማዘዋወር የሚከናወን ንቅለ ተከላ / FOLLICULAR UNIT EXTRACTION – FUE/
እንዴት እንደሚከናወን እንመልከት:: በቆዳ ስር የሚገኘውን የጸጉር ቋት ቆዳው ሳይነሳ አውጥቶ በማዘዋወር ለሚከናወነው ንቅለ ተከላ / FUE/ ባለሙያው ከዚህ በታች የተመለከቱትን ቅደም ተከተሎች ይጠቀማል፡- በራስ ቅል ጀርባ ክፍል ያለው ጸጉር ይላጫል::
ሐኪሙ ከራስ ቅል ቆዳ ላይ በቆዳው ስር የሚገኙትን የጸጉር ቋቶች /follicles/ አንድ በአንድ የሚወስድ ሲሆን ይህ በተወሰደበት ቆዳ ላይ ጥቃቅን ምልክቶች ይታያሉ:: ከላይ ከተጠቀሰው አሠራር ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ሐኪሙ መርፌ ወይም ምላጭ በመጠቀም ጸጉር በሚተከልበት የራስ ቅል ክፍል ላይ ቀዳዳዎችን ካበጀ በኋላ ከቆዳ ስር የወሰዳቸውን ቋቶች /follicles/ ይተክላል:: በመጨረሻም ሥራው የተሰራበት የራስ ቅል ክፍል በፋሻ እና በባንዴጅ እንዲሸፈን ይደረጋል፡፡
የጸጉር ንቅለ ተከላ በኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ የጸጉር ንቅለ ተከላ በቅርብ ጊዜያት እየተለመደ የመጣ ሲሆን አንዳንድ ታዋቂ ግለሰቦችም የዚህ አዲስ ግኝት ተጠቃሚ ሲሆኑ ታይቷል::ከነዚህ መሐከልም ተዋናይ ይገረም ደጀኔ ፤ ጋዜጠኛ ሰመረ (ሰመረ ባርያው) ፤ የሳክስፎን ተጫዋቹ እዮብ እድሉ እንዲሁም እግር ኳስ ተጫዋቹ አህመድ ረሺድ ይገኙበታል::እነዚህ ታዋቂ ግለሰቦች ንቅለ ተከላውን ያከናወኑበት ቦታ ደግሞ
ትሬቢያን የጸጉር ስፔሻሊቲ ክሊኒክ ይሰኛል::ባለቤቱ አቶ ፍቅር ሽፈራው ከባለቤትነታቸው ባለፈ የጸጉር ንቅለ ተከላው ተጠቃሚም ናቸው::ጸጉራቸው ከንቅለ ተከላው በኋላ በአዲስ መልክ ማደግ መጀመሩን እና በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ይገልጻሉ::ሌላኛው የጸጉር ንቅለ ተከላውን ያካሄደው ጋዜጠኛ ሰመረም በአንድ ቪዲዮ ላይ የጸጉር ንቅለ ተከላ ማካሄዱ የበለጠ ወጣትነት እንዲሰማው እንዳደረገው ሲናገር ይሰማል::
በክሊኒኩ የንቅለ ተከላ ሥራውን የሚያከናውኑት የቆዳ ሐኪሟ ዶ/ር ቅድስት የኔነህ ንቅለ ተከላው ከመካሄዱ በፊት የጸጉር መሳሳቱ መንስኤ ምን እንደሆነ እንደሚጣራ ይናገራሉ::” በቅድሚያ የምክክር እና የምርመራ ስራ እናካሂዳለን:: ከሕክምና ጋር በተያያዘ ጉዳይ ለምሳሌ በካንሰር ሕክምና ምክንያት ወይም መሰል ጉዳዮች ጋር የሚመጣ የጸጉር መሳሳትን በንቅለ ተከላ ማስተካከል ያስቸግራል:: የሰውየው የእድሜ ሁኔታም እንደዚያው ተጽዕኖ ይኖረዋል:: የጸጉሩ አይነት ፤ የቆዳው አይነት እና ሌሎችም አብረው ይታያሉ ይላሉ ዶ/ር ቅድስት::
ከዚያ ባለፈ ንቅለ ተከላውን ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ መሟላቱ ሲረጋገጥ ሥራው ይከናወናል::” ብለዋል::
ደንበኛው የሚከፍለው ክፍያም በተደረገው ምርመራ መሠረት እንደሚተመን ገልጸዋል::ደንበኛው ያን መክፈል ከቻለ ንቅለ ተከላው በባለሙያ ይደረጋል::ከዚያም ለቀጣይ ስድስት ወራት በክሊኒኩ ክትትል ይደረጋል::ባለቤቱ አቶ ፍቅር እንደሚሉት ባስመዘገቡት ውጤት የተነሳ ወደ ሁለት አመት ገደማ እየተቃረበ በመጣው ክሊኒካቸው ንቅለ ተከላውን የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር እየበረከተ ነው::
በእያንዳንዱ ዘርፍ ባለሙያዎች ስራዎን እንደሚያካሂዱ የሚናገሩት አቶ ፍቅር የሚመለከተው የመንግሥት ቢሮም ክትትል እንደሚያደርግ ይገልጻሉ::
አሁን ላይ አዲስ አበባ ውስጥ ከትሬቢያን በተጨማሪ ይህን አገልግሎት የሚሰጡ ጥቂት ተቋማት ያሉ ሲሆን ይህም የሚመለክተው በኢትዮጵያ የኮስሞቲክ ሰርጀሪ (የውበት ቀዶ ጥገና) ዘርፍ እያደገ መሆኑን ነው::መንግስት ለዘርፉ ተገቢ ትኩረት ቢሰጠው ለከርሞው ይህን ፍለጋ ወደ ሌሎች አገራት የሚሄዱ ዜጎች ካሉ ማስቀረት ያስችላል::
(አቤል ገብረኪዳን)
አዲስ ዘመን ጥር 2/2014