በዛሬ ዕትም በሰነድ መለያ ቁጥር 78470 ሚያዝያ 7ቀን 2005 ዓ.ም አምስት ዳኞች በተሰየሙበት እስከ ፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ደርሶ ውሳኔ የተሰጠበትን የወንጀል ሁኔታ ያስቃኛል።
በዕለቱ አመልካቾች አቶ ታሪኩ ጫኔ እንዲሁም ተጠሪ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ሕግ የቀረቡ ባይሆንም መዝገቡ ተመርምሮ ፍርድ መሰጠቱንም ያትታል። መነሻው ጉዳዩ አንድ ሰው በፍትሐ ብሔር ጉዳይ ተከሶ ኃላፊነት የለበትም ተብሎ የመጨረሻ ፍርድ ከተሰጠ በጉዳዩ ላይ በወንጀል የሚጠየቅበት ሕጋዊ አግባብ መኖር ያለመኖሩን የሚመለከት ነው።
አመልካች ላይ ተጠሪ ክስ ያቀረበው በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀ(ለ)) እና 413(ሀ) እና (ለ)) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ነሐሴ 20 ቀን 2001 ዓ/ም በኢትዮጵያ ጨረር መከላከያ ባለስልጣን የአካባቢና ምግብ ጨረር መጠን ክትትል ባለሙያ ሆነው በሚሰሩበት ጊዜ የማይገባ ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት እና በመንግስት ሀብት ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ከመስሪያ ቤቱ ፈርመው የተረከቡትን የቀረጥና የማጓጓዣ ዋጋ ሳይጨምር ግምቱ ብር 76.867.34 የሆነን ዩኒቨርሳል ሰርቬየር ሜትር ሞዴል አር፣ጂ፣ኤስ የሆነ የጨረር መጠን መከላከያ መሳሪያ (Universal servey meter) RGS- 200 እና የርቀት መቆጣጠሪያ ያለው በባትሪ የሚሰራ ባለ ብዙ ዘርፍ አገልግሎት ዲጂታል የራጂ ማሽነሪ፣ የጥፋት መቆጣጠሪያ ኪት (digital diagnostic quality control)(RADCheck plus model p6 526 multifunction meter with remot control model Rmt 240 A and collimation test too) የተሰኙ መሳሪያዎችን አመልካቹ በአዳማ ከተማ የአዳማ ሆስፒታል የራጅ መሳሪያዎችን ፍተሻ እንዲያከናውን ታዞ በተጠቀሰው ቀን በስር ሁለተኛ ተከሳሽ ከነበረውና ከመስሪያ ቤቱ ሹፌር በሆነው በአቶ አረጋዊ ታደገ በሚሽከረከር መኪና በመጫን ወደ ናዝሬት ከወሰዱ በኋላ በተጠቀሰው ሆስፒታል ተገኝተው የምርመራ ስራቸውን ማከናወናቸውን ተከትሎ እነዚህን መሳሪያዎች ለመስሪያ ቤቱ ማስረከብ ሲገባቸው ያለአግባብ ለመበልጸግ ንብረቶችን ባለመመለሳቸውና በመሰወራቸው የመውሰድና የመሰወር የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ነው። የክርከሩ ሁኔታ እና ውሳኔ አመልካች ክደው ተከራክረው አቃቤ ሕግ አሉኝ ያላቸውን ማስረጃዎችን ያሰማ ሲሆን አመልካችም የመከላከያ ማስረጃዎቻቸውን አሰምተዋል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍ/ቤትም አመልካች የወንጀል ድርጊቱን መፈፀማቸውን ያለመከላከላቸው ተረጋግጧል በሚል ምክንያት በክሱ ተጠቅሶ በቀረበው ድንጋጌ ጥፋተኛ አድርጎ በስድስት ወር ጽኑ እስራትና በአንድ ሺህ ብር እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል።
አመልካች ይግባኛቸውን ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ ቤት አቅርበውም ተቀባይነት አላገኘም።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።
የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም አመልካች በንብረቱ ላይ የፍ/ ብሔር ክስ ቀርቦባቸው ሃላፊነት የለባቸውም ተብሎ መጨረሻና አስገዳጅ የህግ ትርጉም ለመስጠት ስልጣን ባለው የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰሚ ችሎት ውሳኔ በተሰጠበት ሁኔታ ጥብቅ የሆነ ማስረጃ ምዘና በሚጠይቀው የወንጀል ጉዳይ ላይ ጥፋተኛ መባላቸው በወንጀል ጉዳይ የማስረጃ ምዘና መርህን ያላገናዘበ መሆኑን ጠቅሰው መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው። አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ ሊታይ የሚገባው መሆኑ ታምኖበት ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎለት ቀርቦ ግራ ቀኙ በጽሁፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለ መልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።
እንደመረመረውም ጉዳዩ ለሰበር ሰሚ ችሎት ሊቀርብ የቻለው አመልካች በፍ/ብሄር ጉዳይ ተጠያቂነት የለባቸውም ተብሎ ተወስኖ እያለ በወንጀል ተጠያቂነት አለባቸው ተብሎ
በእስር እንዲቀጡ መወሰኑ ተገቢ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል ነው። አመልካች በንብረቶቹ መሰወርና መውሰድ በፍትሐ ብሔር ተከሰው ተጠያቂነት የለባቸውም ተብሎ በሰ/መ/ቁጥር 69179 የተወሰነ መሆኑን፣ በፍትሐ ብሔር ጉዳይ የተሰሙት ማስረጃዎች በወንጀል ጉዳዩም የተሰሙ መሆኑ ግራ ቀኙን ያላከራከሩ ነጥቦች ሲሆን አከራካሪው የሕግ ጥያቄ በፍትሐ ብሔር ጉዳይ ነፃ የተባለ ሰው በወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ የሚጠየቅበት ሕጋዊ አግባብ አለ? ወይም የለም? የሚለው ነው።
ተጠሪ የወንጀል ችሎት በፍትሐ ብሔር ችሎት ውሳኔ ሊገደድ የሚችልበት ሕጋዊ አግባብ የለም በማለት የሚከራከር ሲሆን አመልካች በበኩላቸው በወንጀል ጉዳይ የማስረጃ ምዘና መርሁ በፍትሐ ብሔር ጉዳይ የማስረጃ ምዘና መርህ የጠበቀ በመሆኑ በፍትሐ ብሔር ጉዳይ ነፃ የተባለ ሰው በተመሳሳይ ጉዳይና ማስረጃ በወንጀል ተጠያቂ የሚሆንበት ሕጋዊ አካሄድ የለም በሚል የሚከራከሩ መሆኑን ተረድተናል።
በመሰረቱ በወንጀል ጉዳይ የተሰጠ ውሣኔ በዚያው ጉዳይ በፍትሐብሔር በማስረጃነት አግባብነት እና ብቃት የሚኖረው ስለመሆኑ የፍ/ብ/ ሕ/ቁ 2149 ድንጋጌ ተቃራኒ ንባብ ያስገነዝበናል።
በዚህ ድንጋጌ መሰረት በወንጀል የተሰጠ ውሣኔ በፍትሐብሔር ለቀረበው ክስ በማስረጃነት አግባብነት የሚኖረው በወንጀል ክሱ በወንጀል ፍ/ ቤት ተከሣሹ ጥፋተኛ ተብሎ ከተወሰነ ስለመሆኑ እና ለዚህም የሚሰጠው ምክንያት የወንጀል ክስ ማስረጃ አመዛዘን መርህ ከፍትሐብሔር የበለጠ ጠንካራና የማያሻማ ማስረጃ የሚጠይቅ መሆኑ ነው።
ወደዚህ ድምዳሜ ለመድረስም በወንጀሉ ጉዳይ የተሰሙት ማስረጃዎችም በፍትሐብሔሩ ጉዳይም የቀረቡና የተሰሙ ሊሆኑ ይገባል። በወንጀሉና በፍትሐብሔር ጉዳይ የተሰሙት ማስረጃዎች የተለያዩ ከሆነ እና በወንጀል ጉዳይ ክስ የቀረበበት ነጥብም ከፍትሐ ብሔሩ ክስ ጋር ግንኙነት የሌለው ከሆነ በወንጀል ክስ ተጠያቂ መሆን ሁል ጊዜ በፍትሐብሔሩ ክስ ኃላፊነትን የማያስከትል ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2149 ድንጋጌ ይዘት፣ መንፈስና ዓላማ ያስገነዝበናል።
ይህ ስለመሆኑም ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁጥር 46386 እና በሌሎች በርካታ መዛግብት በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(1) መሰረት በየትኛውም እርከን የሚገኝ ፍ/ቤትን የሚያስገድድ የሕግ ትርጉም ሰጥቶበታል።
በመሆኑም የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2149 ድንጋጌ አጠቃላይ ይዘትና መንፈስ የሚያስገነዝበን በወንጀል ጉዳይ የቀረበ www.chilot.me ማስረጃ ክብደት ያለው መሆኑ ከተረጋገጠ ለፍትሐብሔሩ ክርክር ብቃት ያለው ማስረጃ መሆኑና በፍትሐብሔር ክብደት ሊሰጠው አይገባም የተባለ ማስረጃ ለወንጀሉ ክስ ሲቀርብ ክብደት የሚሰጥበት አግባብ የሌለ መሆኑን ነው።
ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም አመልካች በጉዳዩ በፍትሐብሔር ክስ ቀርቦባቸው ኃላፊነትን የሚያስከትል ድርጊት አልፈጸሙም፤ ንብረቶቹን በጥንቃቄ አስቀምጠው እያለ ከራሳቸው ቁጥጥር ውጭ በሆነና በሌላ ሰው በተፈፀመ የስርቆት ተግባር ንብረቶቹ መጥፋታቸው ተረጋግጧል በማለት በሰ/መ/ቁጥር 69179 በሆነው አስገዳጅና የመጨረሻ ፍርድ ተሰጥቶ ባለበት ሁኔታ አመልካች በጉዳዩ በሙስና ወንጀል ተከሰው በፍትሐብሔር የቀረቡት ተመሳሳይ ማስረጃዎች በቀረበበትና በተሰሙበት እንዲሁም ተመሳሳይ ፍሬ ነገር በተረጋገጠበት ሁኔታ ጥብቅ የሆነ የማስረጃ ምዘና በሚጠይቀው የወንጀል ጉዳይ አመልካች የወንጀል ድርጊት ፈፅመዋል፣ አድራጎቱም ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘትና በመንግስት ንብረት ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ የተፈፀመ ነው ተብሎ ድምዳሜ መያዙ መሰረታዊ የሆነ የወንጀል ማስረጃ ምዘና መርህን ባልተከተለ ሁኔታ የተሰጠ ውሳኔ በመሆኑ አግባብ ሆኖ አላገኘነውም።
ሲጠቃለልም ለክርክሩ መነሻ የሆነው ድርጊት አመልካች በፍትሐብሔር ተከሰው ነጻ ከተባሉበት ድርጊት ጋር ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይነት ያለው በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የተሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔ የወ/መ/ህ/ሥ/ሥ/ሕ/ ቁጥር 141 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ከፍ/ብ/ሕ/ ቁጥር 2149 ድንጋጌ ተቃራኒ ንባብ ጋር የሚጣረስና መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሆኖ ስላገኘነው ተከታዩን ወስነናል።
ውሳኔ
1. በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 94166 ነሐሴ 20 እና 23 ቀን 2003 ዓ.ም ተሰጥቶ በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 73873 ጥር 02 ቀን 2004 ዓ.ም የፀናው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁጥር 195(2(ሐ) መሰረት ሙሉ በሙሉ ተሽሯል።
2. አመልካች የወንጀል ድርጊት ስለመፈጸማቸው በወ/መ/ሕ/ሥሥ/ቁጥር 141 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ አልተረጋገጠባቸውም ብለናል።
3. መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል። የመስማሚያ ሀሣብ እኔ ስሜ በሦስተኛው ተራ ቁጥር የተሰየምኩት ዳኛ አብላጫው ድምጽ በሰጠው ውሣኔ እስማማለሁ።
ነገር ግን አብላጫው ድምጽ በወንጀል የተሰጠ የጥፋተኝነት ውሣኔ በፍትሐ ብሄር ጉዳይ በማስረጃነት ሲቀርብ ሰለሚኖረው ውጤትና በፍትሐ ብሄር የተሰጠ ውሣኔ በወንጀል ጉዳይ ስለሚኖረው ውጤት የፍታብሄር ሕግ ቁጥር 2149 ድንጋጌ በሰጠው ትርጉም የማልስማማ መሆኔ ይህንን የመስማሚያ ሀሣብ ጽፌያለሁ።የፍትሐ ብሄር ሕገ ቁጥር 2149 በወንጀል ተከስሶ በነጻ መለቀቅ የፍትሐ ብሄር ኃላፊነትን የማያስቀር መሆኑን የሚደነግግ ድንጋጌ ነው።
ይህ ድንጋጌ ቀድሞ በፍትሐ ብሄር ተከሶ ኃላፊነት የለበትም የተባለ ሰው በወንጀል ጉዳይ ሲከሰስ ማስረጃዎቹ ተመሣሣይ ሲሆን ከወንጀሉ ክስ በነጻ የሚሰናበት መሆኑን የሚደነግግ አይደለም።ድንጋጌው የራሱ የሆነ ልዩ ባህሪና ዓላማ ያለው በመሆኑ የተቃርኖ አተረጓጎም “Acontrario Interpretation” ተግባራዊ ሊሆንበት የሚችል አይደለም።
በፍትሐብሄር ጉዳይ ተከራካሪዎቹ ግለሰቦች በመሆናቸው በራሳቸው ችሎትና ያለጠበቃ ተከራክረው በወንጀል የተጠረጠረው ወይም የተከሰሰው ሰው የፍትሐ ብሄር ኃላፊነት የለበትም ተብሎ ሊወሰን የሚችልበት ሁኔታ አለ።
በወንጀል ጉዳይ በፍትሐ ብሄር የተሰሙትን ምስክሮችና ማስረጃ በተጠናከረ ሁኔታ በማቅረብ ዕውነቱን እንዲያወጡም ማድረግና የተከሣሹ ማስረጃ ዕምነት የማይጣልበት መሆኑን በማሳየት በወንጀል የተከሰሰው ሰው ወንጀል መፈፀሙን በሌላ ሁኔታ ለማስረዳት ከተቻለ ተከሣሹ በፍትሐ ብሄር ተከሶ ኃላፊነት የለበትም በመባሉ ብቻ ከወንጀል ክሱ በነጻ እንዲሰናበት የፍታብሄር ሕግ ቁጥር 2149 ድንጋጌ ሊተረጎም አይገባውም።
በያዝነው ጉዳይ አመልካች ላይ በፍትሐ ብሄር ከተረጋገጠው ፍሬ ጉዳይ በተለየ ሁኔታ በወንጀል በቀረበው ማስረጃ ተጠሪ አላረጋገጠም።
ይህም የተጠሪ መልስ አመልካች ወንጀል የፈፀመ መሆኑን በበቂ ሁኔታ የማስረዳት ግዴታውን ያልተወጣ መሆኑን ያሳያል።ስለዚህ አብላጫው ድምጽ አመልካች በነጻ እንዲለቀቅ መወሰኑ ተገቢ ነው ብየ በምክንያቱ ላይ ብቻ ተለይቻለሁ ሲል ሃሳቡን ይደመድማል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 30/2014