በኤርትራ የሁለት ቀናት ጉብኝት ያደረጉት የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በኤርትራ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ አወገዙ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአንድ ፓርቲ በብቸኝነት በምትተዳደረውና በምዕራባውያን ዘንድ በተገለለችው ኤርትራ ያደረጉትን ጉብኝታቸውን ረቡዕ ከሰዓት በኋላ አጠናቀዋል።
ዋንግ ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር መወያየታቸውን እና “ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን” ለማጠናከር ፕሬዚዳንቱ በቻይና ጉብኝት እንዲያደርጉ መጋበዛቸውንም የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከስብሰባው በኋላ በጋራ በሰጡት መግለጫ “በዲሞክራሲና በሰብአዊ መብት ሰበብ በሌሎች አገራት የውስጥ ጉዳይ የሚደረግ ጣልቃገብነትን” አውግዘዋል። “ቻይና በኤርትራ ላይ የተጣለውን ማንኛውንም
ማዕቀብ ትቃወማለች” ማለታቸውም ተገልጿል። በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ የአሜሪካ መንግሥት በአራት የኤርትራ ተቋማትና በሁለት ኤርትራውያን ላይ በያዝነው ዓመት ማዕቀብ ጥሏል።
ማዕቀቡ የኢትዮጵያን መረጋጋትና አንድነት እያናጋ ነው ባለው ቀውስና ግጭት ውስጥ አስተዋጽኦ አላቸው ያላቸውን የኤርትራ ተቋማትና ዜጎችን ኢላማ ያደረገ መሆኑን የአሜሪካ የፌዴራል ግምጃ ቤት በወቅቱ አመልክቷል።
በዚህም መሠረት ዕቀባው የተጣለባቸው ተቋማት የኤርትራ መከላከያ ኃይል፣ የኤርትራ ገዢ ፓርቲ ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ለፍትህ፣ ህድሪ ትረስ እና ሬድ ሲ ትሬዲንግ ኮርፖሬሽን ሲሆኑ ግለሰቦቹ ደግሞ አብረሃ ካሳ ነማሪያም እና ሐጎስ ገብረሕይወት ወልደኪዳን የተባሉት ናቸው።
ምንጭ ቢቢሲ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 29/2014