አዲስ አበባ፡- በየደረጃው ያሉ እናቶች ለሀገር ሰላም እያደረጉ ያለውን የሰላም ጥሪ አጠናክረው ሊገፉበት እንደሚገባ የሰላም ሚኒስቴር አሳሰበ።ሚኒስቴሩ የሰላም አምባሳደር እናቶችን በመያዝ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ቢያደርግም ውጤቱ መጠነኛ መሆኑን ገለጹ፡፡ በሚኒስቴሩ የሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ዳይሬክተር ወይዘሮ አበባ ተገኝ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ እናቶች ለሰላም መስፈን ላቅ ያለ ሚና አላቸው፡፡ ከየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል ሴቶችና ህፃናት ደግሞ በሰላሙ መስፈን ተጠቃሚ እንደመሆናቸው እናቶች በሰላም ጥሪ ላይ አጥብቀው ሊሰሩ ይገባል፡፡
ይህንንም በተግባር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንደ ወይዘሮ አበባ ገለፃ፤ በኢትዮጵያ በየጊዜው በየቦታው እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን በሰላም ለማለፍ የእናቶች ሚና ጉልህ ነው፡፡ ህዝቡ ‹‹የሰላም ጉዳይ ይመለከተናል›› እንዲል በሰላሙ ጉዳይ መንቀሳቀስ ግድ ይላቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ በብሄር መከፋፈል አብቅቶ፣ በጋራ፣ በመተሳሰብ እና በአንድነት መኖር እንዲጀምር የሴቶች አስተዋጽኦ ወሳኝ በመሆኑ፤ በዚህ ላይ በስፋት መስራት ይገባል። የሰላም ሚኒስቴር የሰላም አምባሳደር እናቶችን በመያዝ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እንቅስቃሴዎችን ቢያደርግም ለውጡ ግን መጠነኛ መሆኑን ያመለከቱት ዳይሬክተሯ፣ ቅድሚያ ተሰሚነት ያላቸው ሴቶች ይህንኑእንቅስቃሴ አጠናክረው ማስቀጠል እንደሚኖርባቸው ገልፀዋል፡፡
‹‹የሰላም አምባሳደር እናቶች ለሰላም መስፈኑ የማይተካ ሚና እንዳላቸው በቅርቡ በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተደረገው እንቅስቃሴ አመላካች ነው፡፡›› ያሉት ወይዘሮ አበባ፣ በወቅቱም በዩኒቨርሲቲ ያሉ ተማሪዎች እንዲሁም ስለሰላም ግድ የሚላቸው ወጣቶች ምላሻቸው መልካም መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ ጥረት ግን አስተማማኝ ውጤት እስኪገኝበት ድረስ ተጠናክሮ መሄድ እንዳለበት አሳስበ ዋል፡፡
‹‹በዩኒቨርሲቲዎች የሚፈጠረው ግጭት ማስቆምና ለውጥ ማምጣት የሚቻለው እንደነዚህ ዓይነት እንቅስቃሴዎች መጠንከር ሲችልና ሴቶቹም በዚያው ልክ ሲሰሩበት ነው፡፡›› ያሉት ዳይሬክተሯ፣ ጥረቱ መልካም ጅማሮዎችን እያሳየ በመሆኑ ሴቶች ፍሬ ማፍራታቸውን አምነው ሊሰሩበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የሰላም ሥራም በአንድ ጀምበር የሚፈታ አለመሆኑንም በመገንዘብ በየደረጃው ያሉ እናቶች ሁሉ ይህንን ጥረት ማጠናከር እንዳለባቸው አብራርተዋል፡፡ ከሁሉም ክልል የተውጣጡት የሰላም አምባሳደር እናቶች ዋነኛ ዓላማ በአገር ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ማድረግ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በዚህ ጉዳይ ላይ ለነገ ሳይሉ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ወይዘሮ አበባ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2011
በጽጌረዳ ጫንያለው