አዳማ :- በኢትዮጵያ በተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ለአርአያነት የሚበቁ ሴቶች ማፍራት መቻሉን የኦሮሚያ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ። «የተደራጀ የሴቶች ነቅናቄ ለዘላቂ ልማት» በሚል መሪ ቃል ትናንት በአዳማ ገልማ አባገዳ አዳራሽ ከዘጠኙም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ሴቶች ደም በመለገስና በተለያዩ ዝግጅቶች ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን አክብረዋል።
በወቅቱም የኦሮሚያ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን እንዳሉት፣ የዘንድሮው ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን ተስፋ ባለመለመው የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ መከበሩ ለየት ያደርገዋል ። በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ የጾታ እኩልነት እንዲረጋገጥ መልካም ዕድል መፍጠሩንና ለአርአያነት የሚበቁ ሴቶችን ማፍራት ያስቻለ መሆኑንም አመልክተዋል። በቅርቡ የተከበረው 123ኛው ዓመት የአድዋ ደል በዓል የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ያረጋገጠ እንደነበር ያወሱት ወይዘሮ ጠይባ ሴቶች አሁን በተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ የውሳኔ ሰጪነት ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የለውጥ ጅምሩ ከግብ ሊደርስ የሚችለው ሴቶች ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ተደራጅተውና ተጋግዘው የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ጥረት ሲያደርጉ እንደሆነም ገልጸዋል ። ለሁሉም መሰረት የሆነውን ሰላም በማስጠበቅ ረገድም ሴቶች ያላቸውን የተፈጥሮ ጥበብ በመጠቀም ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባና በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚደረግ ጥረትን በማጋለጥ፣ ለመልካም አስተዳደር መስፈንና ለአገራዊ ልማት መረጋገጥ መረባረብ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ አጸደ አይዛ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ 35 ለሴቶች የሰጠውን መብት በተለይም የንብረት ባለቤትነትን የሚያረጋግጠው አንቀጽ ለሴቶች መብት መጎናጸፍ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አውስተው ሴቶች ተደራጅ ተውና ተጋግዘው ይህንን መብታቸውን ከግብ ማድረስ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። ፌዴሬሽኑ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ለሴቶች ተጠቃሚነት እንዲሁም ከሰላም ጋር በተያያዘ ሰፊ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አስካለ ለማ እንዳሉት በዓሉ የሴቶችን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ለመሄድ አቅም የሚፈጥር ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አገሪቷን የሚፈታተነውን የሰላምና የልማት ተግዳሮቶች በጋራ ለመፍታት እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል። አንዳንድ የበዓሉ ታዳሚዎችም ዕለቱን ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከተውጣጡ ሴቶች ጋር ማክበራቸው እንዳስደሰታቸው የገለጹ ሲሆን፣ በመድረኩ ላይም ዶክተር አምባሳደር ትዝታ ሙሉጌታ «ሴቶችና ሰላም» በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ አቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2011
በለምለም መንግስቱ