ኑሮ የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ በችግር ወይም በምቾት፣ በሀዘን ወይም በደስታ በመከራ ወይም በፌሽታ የሕይወቱን ዘመን የሚያሳልፍበት ጊዜ ነው።ኑሮ መራራ ወይም ጣፋጭ ሊሆን ይችላል።የተሰጠውን ጊዜያዊ መተላለፊያ በር፣ እንደሚያልፍበት ሁኔታም ይወሰናል።ምክንያቱም ኑሮን የሚኖረው ሰው በአጭር ወይም በረጅም የሕይወት ጊዜያት ነው።ደስተኛ ወይም ችግረኛ ሆኖ ይታለፋል፤ ነገር ግን መሰረት እንዳለው ማመን ያስፈልጋል።ጣፋጭና መራር የሚያደርጉት ሰዎችና አጋጣሚዎች ናቸው።እነዚህን ሁለት ነገሮች ሕይወታችንን ይወስኑልናል፤ በልፋታችን ልክ ነገን እና ከነገወዲያን ያሳዩናል።
ሰው ዘላለማዊና አንድ ዓይነት ኑሮ አይኖርም።በተለይም እንደችግሩና ገጠመኛቸው ሁኔታ ኑሮ ልዩ ልዩ ይሆናል። መፍትሄ ለማምጣት የሚሄድበት ርቀትም እንዲሁ ይለያያል።ምክንያቱም በችግር ውስጥ ሆኖ ቀንና ሌሊት፤ ጥዋትና ማታ፤ ፀሐይና ጨረቃ፤ ብርሃንና ጨለማ ሳይገድበው የሚሠራ እንዳለ ሁሉ እያሰለሰ የሚሠራም ይኖራል።ይህ ደግሞ በሀገራችን የሚኖሩ ሰዎችን እንደችግራቸውና ጥረታቸው ሁኔታ ይለያያቸዋል።ከእነዚህ ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆኑና ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የቤተሰብን ጉሮሮ ለመድፈን ደፋ ቀና የሚሉ መካከል ደግሞ ለዛሬ የ‹‹እንዲህም ይኖራል›› አምድ እንግዳ ያደረግናቸው ብርቱዋ አዛውንት እማማ ሙሉነሽ ጀማነህ አንዷ ናቸው።
እማማ ሙሉነሽ ትውልዳቸው አሩሲ አካባቢ ነው።ግን አዲስ አበባ ከገቡ ረጅም ዓመታት ተቆጥረዋል።እንደውም ሕጻን ሆነው ወደ አዲስ አበባ እንደመጡ ያስታውሳሉ።በዚህም አክስታቸው ጋር ሆነው ብዙ ጊዜ አሳልፈዋል።ነገር ግን ከሰው ጫንቃ ላይ ለመውረድና በራሳቸው ሠርተው ለመለወጥ በማሰብ ‘አዲሱ ገበያ’ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በግለሰብ ቤት በቤት ሠራተኝነት ተቀጠሩ።በዚህ ሥራ ብዙ ዓመታትን ቢያሳልፉም ለእርሳቸው ግን ምቾት አልሰጣቸውም።በዚያ ላይ የራስ ነገር የሚጠራቀምበትና ለራሴ ተብሎ የሚሰራበት አይደለም።በእነኝህ እና መሰል ምክንያቶች ተነሳስተው ከቤት ሠራተኝነቱ ለቀው በዘመድ ቤት እየኖሩ የራሴ የሚሉትን ሥራ ጀመሩ።ይህም የጉሊት ላይ ንግድ ሲሆን፤ ብዙ ስቃይና መከራ ያሳለፉበት እንደነበርም አይረሱትም።
ይህንን ንግድ ሲጀምሩ ከፀሐይና ብርዱ በላይ የጉሊት ሸቀጣቸውን ለመሸጥ የሚቀመጡባትን ቦታ አትቀመጪም የሚለው የክስ ጋጋታ እርሳቸውን ያንገበግባቸው ነበር።ከዚያም አልፈው በግድ በአጠራቀሙት ገንዝብ የገዙት ሀብት ንብረት ወይ ይደፋል ወይም ደግሞ ይበላሻል።እናም ለሌላ ኪሳራ ይዳርጋቸዋል።በተለይ ቲማቲሙና ጎመኑ ወዲያው ስለማይሸጥላቸው ብዙ ኪሳራ አምጥቶባቸው እንደነበርም አጫውተውናል።ወደ ሌላ ሥራ የገቡትም በዚህና መሰል ምሬት በሚፈጥሩ ምክንያቶች እንደሆነ ያነሳሉ።
በጉዞዋቸው ብዙ ችግርና ሀዘን እንደሚፈራረቁባቸው ሁሉ፤ ብዙ የደስታ ጊዜያትንም አሳልፈዋል፤ ምክንያቱም እርሳቸው ባይታደሉና ልጅ ወልደው መሳም ባይችሉም፤ አብዛኞቹን የእህትና ወንድሞቻቸውን ልጆች ድረው ኩለዋል፤ ደግፈዋልም።ዛሬም እንዲህ ደክመው፤ ወገባቸው ጎብጦ እንኳን እነርሱን ከመደገፍ አልቦዘኑም።በአንድ ቀበሌ ቤት ውስጥ ከስምንት በላይ ቤተሰብን ያስተዳድራሉ።ቀደም ሲል አንዷ የእህት ልጃቸው ጽዳት እየሰራች ታግዛቸው ነበር።አሁን ግን ሥራው በመጠናቀቁ በቤት ውስጥ ትገኛለችና እርሷንም ከእነልጆቿ የሚደግፉት እርሳቸው ሆነዋል።ይሁን እንጂ አንድም ቀን ይህ በመሆኑ ተቆጭተው አያውቁም።“አቅም ኖሮኝ ከዚህ በላይ ባደርግላቸው ደስተኛ ነኝ” ይላሉም።
ወይዘሮ ሙሉነሽ መሥራትንና ሰው ማገዝን እንደ ጥንካሬና ኃይል ማግኛ መንገድ ይቆጥሩታል።ለሌሎች ሰዎች መምህርና አርኣያ መሆን ነው ብለውም ያስባሉ።ደከመኝና ሰለቸኝ ሳይሉ የቤተሰብም ሆነ የጎረቤትን ልጅ ይንከባከባሉ።ለእርሳቸው ተካፍሎ መብላት ልዩ ጣዕም እንዳለውም ያወሳሉ።ይህንን እንዲኖሩበት ያደረጋቸው ደግሞ ዕጣ ፋንታቸው እንደሆነ ይናገራሉ።ከችግር ወደ ድሎት ከደስታ ወደ ሀዘን ተገለባብጠው ዓመታትን አሳልፈዋል።እናም ሁሉንም በየአቅጣጫው አስተናግደዋልአሁንም እያስተናገዱ ይገኛሉ።
ባሳለፍኩት ፈተና ውስጥ አንድ ነገር ለዛሬ ሕይወቴ ጠቅሞኛል የሚሉት ባለታሪካችን፤ ሳይሰስቱ ለሰዎች መኖርና መስጠት በረከት እንዳለው ነው።ብዙ ለፍቶ ካልሰጡት ብዙ ይወሰዳል።ጥቂት ለፍቶ ግን ካካፈሉት ብዙ ይሆናል።ይህንንም ማድረጌ በሰፈሬ እንደተወደድኩ እና እንደተከበርኩ አቆይቶኛል።አሁንም እያኖረኝ ያለው ይኸው ልምዴ ነው ብለውናል።
‹‹የሥራ ዓይነቱ ቢለያይም እድሜ ግን አይገድበውም።ሁሉም ላይ ሆኖ መልፋትን ብቻ ነው የሚጠይቀው።ከዚያ ውጪ ከሆንን ግን ራሳችንን ጭምር ያቀለናል።አሁን ብዙዎች ሙሉዬ የሚሉኝ ሠርቼ እንጂ ለምኜ ስለማላውቅ ነው።ከኑሮዬና አኗኗሬ አንጻር ግን ይህ ግዴታዬ ነበር።ግን አላደረኩትም።ምክንያቱም ልመና ለእኔ አይመጥነኝም›› የሚል እምነት ያላቸው ወይዘሮ ሙሉነሽ፤ አሁን ኩበት ጠፍጥፈው፣ አድርቀው በመሸጥ በሚያገኟት ገቢ ነው ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት።የሁለት እህቶቻቸውን ልጆች ከአምስት የማያንሱ ተማሪዎች የማስተማር ኃላፊነት የእርሳቸው ነው።የቤት ወጪም ቢሆን የሚሸፈነው ከዚሁ የኩበት ሽያጭ በሚያገኟት ገቢ ነው።
‹‹እድሜ ሲገፋ የመሥራት አቅም ይዳከማል።በልካችን የሚሆኑ ሥራዎችም ውስን ናቸው።በተለይ ከጉልበት ሥራ ጋር ተያይዞ የሚከናወነው ሥራ እንደወጣትነት መቼም አይሆንም።ስለዚህ ገንዘብ አግኝቼ የቤተሰቤን ጉሮሮ የሚሞላልኝና ብዙ ጠቀሜታ ያለው የትኛው ሥራ ነው ብሎ መምረጥ ግድ ነው።ሥራው ፈታኝ ቢሆንም ዛሬ ላይ እያደረኩት ያለው ይህንን ነው ያሉን እንግዳችን፤ ሥራው ፊታቸውን ከማጨማደዱና አቧራ ከማልበሱም በላይ ዓይናቸውን አሳብጦት አጥቁሮታል።የእድሜ መግፋቱ ነገር እንዳለ ሆኖ የስራ ጫናው ወገባቸውን አጉብጦታል።ትንፋሻቸውም ቢሆን የተስተካከለ አይደለም።አሁን ላይ እየሰሩት ያለው ስራ የተለያዩ ህመሞችን እንደፈጠረባቸው በግልጽ ያሳያል።ምክንያቱም «አክ» ሲሉ አቧራ እንጂ ሌላ አይተፉም።ይህንን የሚያክሙበት ምንም አይነት ምግብም አያገኙም።ምክንያቱም የቤተሰቡን ጉሮሮ ለመድፈን እንኳን የሚገኘው ገንዘብ በቂ አይደለምና።
ይህም ቢሆን እንግዳችን የኑሮን ጣዕም ወይም ጣፋጭነቱንና መራራነቱን ለመለየት ሁለት ነገሮች ወሳኝ እንደሆኑ ያስባሉ።አንደኛው ሰው የፈለገውን ሲቀበል፣ የተመኘውንና ያየውን ሲጨብጥ ከመጠን በላይ ደስ ያሰኘዋል፤ ሕይወት ትጣፍጠዋለች፤ የሚፈልገውንም ወደማድረጉ ይገባል።ይህም ቢሆን ግን ጫፍ አያደርሰውም።ምክንያቱም ፍላጎቱ ከዚያም ይቀጥላል።ወደፊት የሚፈልጋቸው ነገሮች ይበረክቱና ስሜቱን ያቀሉታል፤ እርካታውም ይቀንሳል።እናም በዚህኛውም አለም ደስታ ጋር አይደረስም።ግን ጣፋጭነቱ ባለበት ልክ ይቀጥላል ሲሉ ያስረዳሉ።
ሌላውና ሁለተኛው ብለው ያነሱት ኑሮው አልሟላለት፤ ምኞቱ አልሳካለት ሲል የሚታየውን ሲሆን፤ አሁን እርሳቸው ያሉበትንና ጥረታቸውን ያስታውሳሉ።ትግሉና ልፋታቸው ለውጣቸው ላይ አላደረሳቸውም።ግን ከመልፋት መቆጠብ አልቻሉም።ምክንያቱም ነገን ለማየት ዛሬ ሆድን መሙላት ግድ ነው።ስለዚህም ተስፋ በመቁረጥ ሳይሆን መኖርን በማሰብ ልፋቱን ወደፊት እንዲገሰግስ አድርገውታል።አዕምሯቸውን በሐሳብ ወጥረው ቀን ከሌሊት ሳይሉ ይሠራሉ።ይህ ሲሆን ደግሞ ከሰውነት ጎዳና መውጣት አንዱ ችግር ይሆናል ባይ ናቸው።ለእርሳቸው እንዲህ መሆንም ምክንያቱ የሥራ ብዛትና የለውጡ ሁኔታ አለመመጣጠን መሆኑን ይናገራሉ።
‹‹ትናንት በውበቴ ያልተማረከ የለም።ለማግባትም ብዙዎች ጎትጉተውብኝ ነበር።ቤተሰብ ጭምር ከእኔ መለየትን አይፈልግም።ምክንያቱም ትንሽ ሠርቼ ቤቱ ሙሉ ይሆናል።ጉልበትና አቅሙ ስላለኝም ቁጭ ማለትን ስለማልወድ የተሻሉ የሚሆኑበትን መንገድም በስፋት አመቻቻለሁ።ዛሬ ግን የገባሁበት የኩበት መጠፍጠፍ ሥራ ባይጥለኝም እኔን አድክሞኛል።አቧራው በምንም የሚመከት አይደለም።ሁሉ ነገር በግዢ ቢመጣም ተግባሩ አቡክቶና ነፍቶ የሚከወን ስለሆነ፤ አይደለም በእድሜ ለገፋ ሰው ለወጣቱም አዳጋች ነው።ብናኙ ዓይንን ማጥፋት ብቻ ሳይሆን ሳንባ ላይ ችግር ይፈጥራል፤ ሥራው ደግሞ ጉልበትን ይበዘብዛል።እንዲህ ጎብጬ የምታዩኝም ያለምክንያት አይደለም።ከስድስት ዓመት በላይ በዚህ ሥራ ስለቆየሁ ብዙ አጎንብሻለሁ፡፡›› ይላሉ የዛሬ ሁኔታቸውን ከሥራው ከባድነት ጋር አዋህደው እያነሱ።
እማማ ሙሉነሽ ለራሳቸው ጎብጠው ቤተሰብን ቀና ማድረግ የቻሉ መሆናቸውን ከእህታቸው ልጅ ንግግር ሰምተናል።እርሷ እንዳለችን ልጆቿም ሆኑ እናቷ፤ እማማ ሙሉነሽ ባይኖሩ ኖሮ ዛሬን አያዩትም ነበር።እርሷም ብትሆን በእርሳቸው ብርታት ነው የቆመችው።ስለዚህም አክስቷ ብርቱ ብቻ ሳይሆኑ ስኬታማም እንደሆኑ ታስረዳለች።ሥራውን ለመከወን 11 ሰዓት ተነስተው 11 ሰዓት ያርፋሉ።ይህም ምሳ ለመብላትና የተለመደውን ቡናቸውን ለመጠጣት እንደሆነም ነግራናለች።
የልፋት ዋጋ ሳይገኝና ኑሮ ሲከብድ ይመራል፤ ዓለም ትጠላለች።ሕይወትን አጥፍቶ ማረፍንም ያስመኛል።መከራ የበዛበት ኑሮ የሚፈጥረውን ንዴት ለመወጣት፤ ራስን እንደማጥፋት፤ ያለምንም ድካም በአቅራቢያ የሚገኝ መፍትሄ የለም።ነገር ግን ይህ ትክክል አይደለም።ያችን ውድ ሕይወቱን ካጠፋ በኋላ ትርፍ ወይም ርካታ ማግኘት አይቻልም።እናም በዚህ ችግር ውስጥ ሆኖ ሁሌ መልፋትን ዋጋ መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ማመን ይገባል።ምክንያቱም ትዕግስት ካደረግን ዛሬን ያሻግረናል፤ ነገን እያለምን እንኖራለን ይላሉ እማማ ሙሉነሽ።
ይቀጥሉና የሰው ልጅ ሕይወቱን ካቆየ ሐዘንና ደስታ ጎን ለጎን እንደሚሄዱ አንድ ቀን ይረዳል።ትዕግስት ተስፋ እንዳላት፤ ነገን እንደምትሰጥ፤ ቤተሰብንም ሆነ ራስን ከሞት እንደምትታደግም ያውቃል።በተለይም ከሥራ ጋር ሲሆን ብዙ ነገርን እንደሚሻገርባት ያረጋግጣል።ስለሆነም ሰዎች ትዕግስተኛ መሆን መቻል አለባቸው።ለራሳቸው እንኳን መኖር ባይፈልጉ ለቤተሰባቸው ሲሉ መቆየት ይጠበቅባቸዋል።ምክንያቱም ተስፋ ባለመቁረጥ ውስጥ ፈውስና እድገት አለ።ስለዚህም ይህንን እያሰቡ መራመድ ያስፈልጋል ሲሉ ይመክራሉ።
የሰው ልጅ ማጣትና ማግኘትን አስቦ መንቀሳቀስ አለበት።ምክንያቱም ማንም ወደዚህ ምድር ሲመጣ ድሃ ሆኖ ወይም ሀብታም ሆኖ አይደለም።የእርሱ የልፋትና የትጋቱ መጠን ከአጋጣሚዎች ጋር ተዳምረው ነው ይህንን ባህሪ የሚያላብሱት።እናም በተሰጠን ጊዜ መሥራት ከዚያ ስናልፍ ደግሞ ሌሎችን ማገዝ ካልሆነልን ደግሞ ሌሎች ላይ ጣት ባለመቀሰር ልንደግፋቸው ይገባል ባይም ናቸው።
አንድ ሰው የኑሮን ጣዕም በትክክል ያውቃል የምንለው የእሱን መመቸት ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም አለመመቸት ወይም ሀዘናቸውንና ጭንቀታቸውን እንዲሁም ለኑሯቸው የጎደላቸውን ነገሮች በሙሉ ተገንዝቦ መረዳት ሲችል ነው።ስለሆነም ሁሉም ሰው ጊዜ ተለዋዋጭ እንደሆነ ማሰብ አለበት።ዛሬ ቢደላንና ሀብታም ብንሆንም ምናልባት ጓደኛችን ወይም ጎረቤቶቻችን ችግረኛ ሊሆኑ ይችላሉና እናስታውሳቸው።ምክንያቱም ነገ ከፋዮች እነርሱ ይሆናሉና ይላሉ።
ኑሮን በአንድ ጊዜ የተሻለ ማድረግ አይቻልም።ብዙ ልፋትና ትግልን ይጠይቃል።ከምንም በላይ ደግሞ ቁርጠኛ ሆኖ ወደፊት መጓዝና መሥራት አስፈላጊ ነው የሚሉት ባለታሪካችን፤ ዛሬ ከሰል አቡናኝና ኩበት ጠፍጣፊ ብሆንም ነገ ግን የተሻልኩ እንደሆንኩ አምናለሁ።ምክንያቱም መስራቴን አላቆምኩም።ካልሞትኩና ካልታመምኩም ይህ የማይሆንበት አጋጣሚ አይኖርም።ሀሳቤ በፈለኩት ጊዜ ላይሞላ ይችላል።ግን ጊዜ ይጠብቃል እንጂ ከሰራሁ አይሳካም ብዬ አላስብም።እናም ምኞታችን አንድ ቀን እንደሚሆንልን እያሰብን ሁልጊዜ ከሥራ ጋር እንቆራኝ የሚለው መልዕክታቸው ነው።
ጊዜ እድልን ይሰጣል።ለማቃናት ያላቋረጠ ትግል ከተደረገበት ደግሞ ችግርን ያጠፋል።ይህንን ግን የምንገነዘበው ካለፈ በኋላ ነው።እናም በተለይ እንደ እኔ በችግር ውስጥ ያሉ ሰዎች ኑሯቸው የቱንም ያህል ቢከብዳቸውም ጊዜያቸውን ከእድላቸው ጋር አድርገው በሥራ ሊያሳልፉት ይገባል።በየቀኑ ባይታያቸውም፤ ለችግራቸው መፍትሄ እየሰጣቸው እንደሚሄድ ማመን ግን አለባቸው።ብዙ ቤተሰብ የማስተዳድርበት ሥራው ቢከብድም ጊዜውን እየተጠቀምኩበት ስለሆነ መፍትሄ አግኝቼበታለሁ።ችግር በጊዜ ሂደት እንጂ በአንድ ጊዜ እንደማይቀረፍ ሰዎች ሊያምኑና በዚህም አስተሳሰብ የሚመሩ መሆን አለባቸው ሲሉ ከተሞክሯቸው በመነሳት ይመክራሉ።እኛም ምክራቸው መድኃኒት ይሁናችሁ እያልን ለዛሬ አበቃን።ሰላም!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 23/2014