እንደመግቢያ
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የሰጠባቸውን ውሣኔዎች ለፍርድ ቤቶች፣ ለሕግ ባለሙያዎች፣ ለሕግ ትምህርት ቤቶችና በአጠቃላይ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ጥናቶችን ያደርጋል፡፡ ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጥናትና የሕግ ድጋፍ ዳይሬክቶሬት መስከረም 26 ቀን 2007 ዓ.ም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ውሣኔዎች በሚል የሰጠውን ውሳኔ የተመለከተ ይሆናል፡፡ በዛሬው የተዘጋው ዶሴ አምድ የሰነድ መለያ ቁጥር 98052 ሐምሌ 14 ቀን 2006 ዓ.ም አመልካች፡-በርሄ ሐጎስ ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ እና በነገረ ፈጅ ስዩም ረጋሳ ቀርበው እና አምስት ዳኞች ተሰይመው መዝገብ ተመርምሮ ፍርድ የተሰጠበት ውሳኔ ለማስቃኘት ወደድን፡፡
ፍሬ ጉዳዩ
ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን የተጀመረውም በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከሳሽ የነበሩት የአሁኑ ተጠሪ በአሁኑ አመልካች ላይ ባቀረቡት ክስ ነው፡፡ በ30/08/2005 ዓ.ም. አዘጋጅተው ያቀረቡት ክስ ይዘትም ባጭሩ ይህን ይመስላል፡፡
ከሳሽ ከ16/07/2005 ዓ.ም ጀምሮ በተከሳሽ ድርጅት ውስጥ በጀማሪ ነገረ ፈጅነት የሥራ መደብ ላይ ተቀጥረው አንድ ወር ከ15 ቀናት የሰሩ መሆኑን፤ የ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ እንዲኖር የተደረገ ስምምነት ሳይኖር ተከሳሽ ድርጅት የስራ አፈጻጸምህ ዝቅተኛ ነው፣ ሰዓት አክብረህ ሥራ አትገባም የሚል እና መሰል ምክንያቶችን በመዘርዘር የስራ ውላቸውን አላግባብ እንዳቋረጠ የሚገልጽ ሆኖ ስንብቱ ሕገ- ወጥ ነው ተብሎ ተከሳሽ ድርጅት ከሕገ-ወጥ የሥራ ስንብት ጋር የተያያዙ ክፍያዎችን እንዲፈጽምላቸው እና ቅጥሩም ቋሚ ቅጥር ነው ተብሎ ይወሰን ዘንድ ዳኝነት የተጠየቀበት ሲሆን፤ ተከሳሽ ድርጅት በበኩሉ በ13/10/2005 ዓ.ም በሰጠው መልስ ከሳሽ የተቀጠሩት ለ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ መሆኑን፣ በዚህ የሙከራ ጊዜ ውስጥ በፍርድ ቤት ቀጠሮ በጊዜ ሳይቀርቡ ቀርተው መዝገቦች እንዲዘጉ በማድረግ፣ በሰዓት ስራ ባለመግባት እና የመሳሰሉ ጥፋቶችን ከመፈፀማቸውም በላይ ማስጠንቀቂያ እና መልሶችን ራሳቸውን ችለው የማዘጋጀት ውስንነት የታየባቸው መሆኑን እና ማስጠንቀቂያ መስጠት ሳያስፈልግ እንዲሰናበቱ የተደረገውም የሙከራ ጊዜያቸው ባለማጠናቀቁ መሆኑን በመግለጽ ክሱ ውድቅ ሊደረግ ይገባል በማለት ተከራክሯል፡፡
ከሳሽ እና ተከሳሽ በፍርድ ቤት
ፍርድ ቤቱም የተከሳሽን ምስክሮች ከሰማ እና ከሳሽ ፈርመው ተቀብለዋል በተባለው ለ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ የተቀጠሩ መሆኑን በሚገልጸው ደብዳቤ ላይ የተመለከተው እና በከሳሽ የተካደው ፊርማ ተመርምሮ ውጤቱ እንዲቀርብለት ካደረገ በኋላ ከሳሽ የተቀጠሩት ለ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ መሆኑን በሚገልጸው ደብዳቤ ላይ የተመለከተው እና በከሳሽ የተካደው ፊርማ የከሳሽ መሆኑ በፎረንሲክ ምርመራ የተረጋገጠ ቢሆንም በአዋጅ ቁጥር 377/1996 በአንቀጽ 11(3) በተመለከተው መሰረት ግራ ቀኙ በ16/07/2005 ዓ.ም ባደረጉት የቅጥር ውል ላይ የሙከራ ጊዜ እንዲኖር ስለመስማማታቸው ውሉ የማያመለክት መሆኑን፤ የሙከራ ጊዜ እንዲኖር ግራ ቀኙ ስለመስማማታቸው በውሉ እስካላረጋገጡ ድረስ ቅጥሩ የተፈጸመው ለ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ ስለመሆኑ የሚገልጸውን ደብዳቤ ከሳሽ ፈርመው መቀበላቸው ብቻውን ከሳሽ በዚህ የውል ሁኔታ ስለመስማማታቸው የሚያረጋግጥ አለመሆኑን፤ የሙከራ ጊዜ እንዲኖር ግራ ቀኙ በውሉ ያልተስማሙ መሆኑ ከተረጋገጠ ደግሞ ከሳሽ በተከሳሽ የተጠቀሱትን ድክመቶች አሳይተው ቢሆን እንኳ ተከሳሽ የከሳሽን የሥራ ውል ማቋረጥ ይገባው የነበረው በማስጠንቀቂያ ሆኖ ሳለ ያለማስጠንቀቂያ ማቋረጡ ስንብቱ የተከናወነው ከሕግ አግባብ ውጪ እንደሆነ የሚያመለክት መሆኑን በዝርዝር በመግለጽ ተከሳሽ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ብር 2 ሺህ 500፣ የስራ ስንብት ክፍያ ብር 273.97 እና የካሳ ክፍያ ብር 15ሺህ በድምሩ ብር 17 ሺህ 773.97 (አስራ ሰባት ሺህ ሰባት መቶ ሰባ ሶስት ብር ከዘጠና ሰባት ሣንቲም) የገቢ ግብር ቀንሶ ለከሳሽ እንዲከፍል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
አመልካች አቤቱታውን ለዚህ ችሎት ያቀረበው፤ ይግባኝ ሰሚው ከፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔን በማጽናቱ ሲሆን፤ የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ የቅጥር ውሉ በተደረገበት በዚያው ቀን ተጠሪ የተቀጠሩት ለ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ ስለመሆኑ የሚገልጸውን ደብዳቤ ፈርመው መቀበላቸው በተረጋገጠበት ሁኔታ፣ ለሙከራ ጊዜ መቀጠራቸው የተገለጸበት ደብዳቤ በአመልካች ብቻ የተዘጋጀ ነው ተብሎ የአመልካች ክርክር በስር ፍርድ ቤቶች ውድቅ የመደረጉን አግባብነት ተጠሪው ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል፡፡የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር መርምረናል፡፡
በዚህም መሰረት አመልካች አጥብቆ የሚከራከረው ለሙከራ ጊዜ የተቀጠረ ሰራተኛ ለስራው ተስማሚ አለመሆኑ ሲረጋገጥ አሰሪው የሥራ ስንብት እና የካሳ ክፍያ ለመክፈል ሳይገደድ የሰራተኛውን የስራ ውል ያለማስጠንቀቂያ ሊያቋርጥ የሚችል ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 11(5) በግልጽ የተመለከተ ሆኖ እያለ፤ እና ተጠሪውም ለ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ የተቀጠሩ ስለመሆኑ በቅጥሩ ዕለት በአድራሻቸው የተጻፈውን ደብዳቤ ፈርመው በመቀበል ያረጋገጡ ሆኖ እያለ፤ አሰሪው ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ውሉን ያቋረጠው አላግባብ ስለሆነ ሕገ ወጥ የሥራ ስንብት የሚያስከትላቸውን ክፍያዎች እንዲፈጽም በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ አግባብነት ያላቸውን የአዋጁን ድንጋጌዎች መሰረት ያደረገ አይደለም በማለት መሆኑን ተገንዝበናል ይላል፡፡
እንደተባለው ተገቢ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ለሙከራ ጊዜ የተቀጠረ ሰራተኛን በሙከራ ጊዜው ውስጥ አሰሪው ያለማስጠንቀቂያ ማሰናበት የሚችል ስለመሆኑ አዋጁ የሚደነግግ ቢሆንም የአዋጁ አንቀጽ 11(5) ድንጋጌ ተፈጻሚ ከመደረጉ አስቀድሞ ግን ተዋዋዮቹ የሙከራ ጊዜ እንዲኖር በቅጥር ውላቸው የተስማሙ መሆኑ በቅድሚያ መረጋገጥ እንዳለበት የአዋጁ አንቀጽ 11(3) በግልጽ ያመለክታል፡፡ በተያዘው ጉዳይ የቅጥር ውሉ የተደረገውም ሆነ ተጠሪው የተቀጠሩት ለ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ ስለመሆኑ አመልካች ለተጠሪው በደብዳቤ የገለጸው በተመሳሳይ ቀን ነው፡፡
ተጠሪ የተቀጠሩት ለ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ የመሆን አለመሆኑ ጉዳይ ደግሞ መረጋገጥ ያለበት በአዋጁ አንቀጽ 11(3) መሰረት በቅጥር ውሉ እንጂ አመልካች በተናጠል ለተጠሪው በሚሰጠው ማስታወቂያ ባለመሆኑ ተጠሪው የሙከራ ጊዜውን የቅጥር ሁኔታ በውሉ ላይ በግልጽ የተቀበሉ መሆኑ እስካልተረጋገጠ ድረስ በአመልካች የተጻፈላቸውን የቅጥር ደብዳቤ ፈርመው የተቀበሉ መሆኑ መረጋገጡ ብቻ የሙከራ ጊዜውን የቅጥር ሁኔታ ተስማምተው ተቀብለዋል ከሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የሚያስችል አይደለም፡፡ በመሆኑም ተጠሪ የተቀጠሩት ለ45 ቀናት የሙከራ ጊዜ በመሆኑ እና የተሰናበቱትም በስራ ላይ የተለያዩ ድክመቶችን በማሳየታቸው በመሆኑ ስንብቱ ሕጋዊ ነው በማለት አመልካች የሚያቀርበው ክርክር ሕጋዊ መሰረት ያለው ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም፡፡
ሲጠቃለል የሥራ ውሉ የተቋረጠው ከሕግ አግባብ ውጪ መሆኑን በማረጋገጥ አመልካች ለተጠሪው ተገቢ ክፍያዎችን እንዲፈጽም በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ ስላልተገኘ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
ውሳኔ…
በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከሳሽ ተከሳሽ የተለያዩ መረጃዎችን እያቀረቡ ብሎም የህግ አንቀጾችን እያጣቀሱ ሲከራከሩ በነበረው ሁኔታ አምስት ዳኞች በሰበር ውሳኔው ለመቀመጥ የተወሰነ ሲሆን በዚህ ግራ ቀኙን የተመለከተው ሰበር ችሎት ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ በዚህ ውሳኔ መሰረትም የሚከተሉት ነጥቦች ተካተዋል፡፡
1. በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመለያ ቁጥር 83708 በ21/02/2006 ዓ.ም ተሰጥቶ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ.ቁ. 139206 በ06/06/2006 ዓ.ም በውሳኔ የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 348(1) መሰረት ፀንቷል፡፡
2. የውሳኔው ቅጂ ለስር ፍርድቤቶች ይላክ፡፡
3. በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመለያ ቁጥር 86397 የተያዘው አፈጻጸም ታግዶ እንዲቆይ በዚህ መዝገብ በ10/07/2006 ዓ.ም ተሰጥቶ የነበረው ትዕዛዝ ተነስቷል፡፡
4. የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡
5. ውሳኔ ያገኘ ሰለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል ሲል ደምድሟል፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 23/2014