አንድ ላይ ከቆምን ሰላምና ጸጥታችንን ማረጋገጥ እንደምንችል ትምህርት ያገኘንባቸው አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል። ኢትዮጵያ በውጭና በውስጥ ጠላቶቿ ህልውናዋ አደጋ ላይ በወደቀ ጊዜ የቁርጥ ቀን ልጆቿ የተለያዩ አደረጃጀቶችን ፈጥረው ሊያድኗት ሲረባረቡ አይተናል። ከመንደር እስከ ግንባር ባለው አደረጃጀት ሴቶችም የራሳቸውን ሚና ተወጥተዋል። ከሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ጋር ተያይዞ በመዲናችን በሁሉም ክፍለ ከተሞች እየተሠራባቸው የሚገኙ የሴቶች ብሎክ አደረጃጀቶች የፋይዳው አንዱ ማሳያ ናቸው።
አደረጃጀቶቹ የሕወሓት ጁንታ ቡድን ከሚያደርሰው ማንኛውም ዓይነት ጥቃት አካባቢን ለመጠበቅ ዓይነተኛ መፍትሄ እየሆኑ ነው። በተለይ የከተማዋ እንብርት በሆነው አራዳ ክፍለ ከተማ ሴቶች ለሰላም መስፈን እያደረጉት ያለው አስተዋጽዖ የጎላ ነው። እኛም ለዛሬ አዲስ አበባ ከተማ ባሉ ብሎክ አደረጃጀቶች ዙርያ የሚመለከታቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎችና የሥራ ኃላፊዎች አነጋግረን ያዘጋጀነውን ጽሑፍ ልናስነብባችሁ ወድደናል።
‹‹አራዳ ክፍለ ከተማ እንደ ስፋቱ ችግሩም ብዙ ነው›› ያለችን የክፍለ ከተማው ብሎክ 17 ነዋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣት እመቤት ካሳ ነች። የከተማዋ ዋነኛ እምብርት የሆነው ፒያሳ እንደዚሁም የፈረሰው የቀድሞው አትክልት ተራ፣ ሶማሌ ተራ፣ የመርካቶ ገበያ አዋሳኝ ሀብተ ጊዮርጊስ ድልድይና አምባሳደር ቲያትር አካባቢ፣ እሪ በከንቱና ሌሎች ቀደም ባሉ ጊዜ ስማቸው በአደገኝነት የሚጠራ አካባቢዎች በዚሁ ክፍለ ከተማ መገኘታቸውን ትጠቅሳለች።
እንደ እመቤት ገለጻ አምባሳደርና ሀብተ ጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ ከፍተኛ ችግር የነበረባቸው ናቸው። የሰው እንቅስቃሴ የሚበዛባቸው እንደመሆናቸው በቀንና በማታም ሆነ በሌሊት ሁከትና ግርግር አያጣቸውም። አራዳ ህንፃና ፑሽኪን አካባቢም ተመሳሳይ ሁከትና ግርግር ያለባቸው ናቸው።
በነዚህ አካባቢዎች ሳንጃ፣ ጩቤና ገጀራ በመያዝ ዝርፊያና ቅሚያ ይከናወን እንደነበር እመቤት ታስታውሳለች። የሴቶች ቦርሳና ሞባይል መንትፎ መሮጥም የተለመደ ተግባር ሆኖ መቆየቱን ታወሳለች። ብዙ ሴቶች በዚህ ምክንያት ባዷቸውን ይቀሩ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነውም ትላለች።
በተለይ ፑሽኪን አካባቢ ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት እስከ ሁለት ሰዓት ባለው ጊዜ በጩቤ የሚወጉ፣ የሚታረዱና ማጅራታቸውን የሚመቱ እንደነበሩም ትገልፃለች።
እንደ በጎ ፈቃደኛዋ ወጣት አገላለጽ ሴቶች በብሎክ ተደራጅተው አካባቢያቸውን መጠበቅ ከጀመሩ በኋላ ችግሮቹ ተቀርፈዋል። እነዚህን አካባቢዎች ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ ሌሊቱ ስምንት ሰዓት በንቃት ይጠብቃሉ። በመሆኑም ነጣቂዎቹ ስለሚፈሩ አይመጡም። ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ጀምሮም እስኪነጋ ድረስ በወጣት ወንዶች ስለሚጠበቅ ችግሩ ቆሟል ማለት ይቻላል። በክፍለ ከተማው ያሉት አደገኛ ቦታዎች ቀንም በተለያየ መንገድ የሚጠበቁበት ሁኔታ ቢኖርም ፑሽኪን አካባቢ ሞባይልና ቦርሳ መንትፎ የመሮጡ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ቆሟል ማለት አይቻልም ብላናለች።
የሕወሓት ጁንታ ቡድን ለሀገሪቱ ሥጋት የማይሆንበት ደረጃ እስኪደርስ ድረስ አካባቢን በሴቶች አደረጃጀት መጠበቁ ዓይነተኛ መፍትሄ ሆኖ እንደሚቀጥልም ታረጋግጣለች። በሁሉም የክፍለ ከተማዋ አካባቢዎች በተለይም በነዚህ በአደገኞቹ ቦታዎች መብራት እንዲበራ መደረጉ ለጥበቃ ሥራው እገዛ ማድረጉን ትገልጻለች።
ሌላዋ የሶማሌ ተራ ቀበሌ 14 ነዋሪ ወይዘሮ ሸምስያ ቱሉ በብሎክ አደረጃጀቱ የመቶ መሪ ናቸው። ወደ አደረጃጀቱና መሪነቱ የገቡት አግባብ ያለው ስልጠና ወስደው ነው። በስልጠናው ስለ ችግር አፈታት፣ ስለ መረጃ ልውውጥ፣ ስለ ደህንነት ስጋት እንዲሁም ከማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ጋር ተናብቦ ስለሚሠራበት ሁኔታ ዕውቀት ቀስመዋል። ለዚህም የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል። ባጅና የደንብ ልብስም አላቸው።
ከሰኞ እስከ እሁድ በምሽት፣ በቀንና በሌሊት አካባቢያቸውን የሚጠብቁ ሴቶችን ጠርንፈው (አስተባብረው) ይመራሉ። እርሳቸውም በፊናቸው እንዲሁ ወጥተው አካባቢቸውን ይጠብቃሉ። ጥበቃው በተለይ አሸባሪው የሕወሓት ጁንታ ቡድንና የቡድኑ ደጋፊዎች በአካባቢው ሊያደርሱት የሚችሉትን ጥፋት ቀድሞ ለመከላከል አስችሏል።
የጥፋት ኃይሎችን ቤት ለመፈተሽ ወይም ጥቆማ ሰጥቶ ለማስፈተሽም ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። ጥርጣሬ ወይም ጥቆማ ካለ የጥፋት ኃይሉ ደጋፊዎችም ሆኑ የሌሎች የማንኛቸውንም ሰዎች ቤት ምስክር አቁመው እንደሚፈትሹ ያወሳሉ። አንዳንዴም በአካባቢው እንግዳ የሆኑ ሰዎችን ሲያዩ መታወቂያቸውን በማሳየት እንዲተባበሯቸው ይጠይቃሉ።
ሶማሌ ተራ አካባቢ አሁንም ሆነ ቀድሞ ለሁከትና ወንጀል መንስዔ የሚሆኑ መሸታ ቤቶችና መኝታ ቤቶች አለመኖራቸውን ይጠቁማሉ። በምትኩ ትላልቅ ህንፃዎችና መኖርያ ቤቶች በመኖራቸው እምብዛም የፀጥታ ችግር እንደሌለ ይናገራሉ። እስከ ተክለሐይማኖትና ጎላ ሚካኤል ድረስ በመዝለቅ የሰላም ስጋት ናቸው የሚሏቸውን ነገሮች ሁሉ እየተከታተሉ ስርዓት በማስያዝ አስተዋጽዖ እያበረከቱ መገኘታቸውን ነግረውናል።
‹‹ሶማሌ ተራ የቀድሞ ስሙ በጥሩ አይጠራም ነበር›› ያሉን ወይዘሮ ሸምሲያ የተሰረቀ መኪና መጥቶ የሚበለትበት እንደሆነም ይጠቀሳሉ።
ከቅርብ ወራት ወዲህ በሴቶች በሚደረገው አካባቢን የመጠበቅ ዘመቻ ይሄ ታሪክ መለወጥ ችሏል ብለዋል። እንደውም መኪኖች አስፋልት ዳር ደህንነታቸው ተጠብቆ ማደር እንደጀመሩና፤ ምሽት ሲሆን የሚፈሩ ሰዎችም ያለምንም ስጋት መንቀሳቀስ እንደቻሉ ተናግረዋል። ይህ አዲስ ጅምር ለሁሉም ማህበረሰብ ጥቅም እየሰጠ እንዳለና በተለይም ቀዳሚ ተጎጂ ለሚሆኑት ሴቶችና ህፃናት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰዋል።
የቅድመ ጥንቃቄ ሥራ የሚከወንበት ተግባር እንደመሆኑ በአዲስ አበባ ከተማ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ሊሰነዝር ከሚችለው የትኛውም ዓይነት ጥቃት አስቀድሞ ለመከላከል ይረዳል ብለዋል።
ወይዘሮ ዘርፌ ንጉሴ የዚሁ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ነዋሪ ናቸው። እርሳቸውም በአደረጃጀቱ ውስጥ የመቶ መሪ ናቸው። ያገኘናቸው ምሽት ሁለት ሰዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አካባቢ በጥበቃ ሥራ ላይ ተሰማርተው ባሉበት ጊዜ ነው። አካባቢው በመደበኛ ወታደር የሚጠበቅ ቢሆንም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና ለሀገሪቱ ደህንነት ሲሉ በብሎክ በተደራጁ ሴቶች ጭምር እንዲጠበቅ ማድረጋቸውን አጫውተውናል። አካባቢው ታላላቅ የዓለምና የሀገር ውስጥ እንግዶች ከሥራ ጋር በተያያዘ የሚጎበኙት ቦታ በመሆኑ የጥበቃ ትኩረት ያስፈልገዋል ይላሉ። ስለሆነም በየቀኑ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ቅኝት ይደረግበታል። ከጸጥታ ሥራው ባሻገር የጽዳት ዘመቻም እያከናወኑ የሴቶች አደረጃጀትን የአካባቢያቸውን ንጽህና ለመጠበቅ እንደሚጠቀሙበት ይናገራሉ።
ወይዘሮ ቦጋለች ቦንኬ ነዋሪነታቸው ከዚሁ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ብዙም በማይርቀው በቀበሌ 18 ነው። ወይዘሮዋ ይሄ ቀበሌ ቀድሞ ወጣቶች በግሩፕ የሚደባደቡበትና ብዙ ግርግርና ሁከት የሚበዛበት መሆኑን ያወሳሉ።
አሁን በሴቶች አደረጃጀት በመጠበቁ ችግሩ መቀረፉንም ይጠቁማሉ። እርስ በእርስ ይጋጩ የነበሩ ወጣቶችም በበጎ ፈቃደኝነት ተደራጅተው ከአራት ሰዓት ተኩል በኋላ እስከ ሌሊቱ ስምንት ብሎም እስከ ንጋት አካባቢያቸውን የሚጠብቁ ሠላማዊ ዜጎች መሆናቸውን ይናገራሉ።
ወይዘሮ ሁሉአገርሽ አዘዝ የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት እንደሚገልጹት በብሎክ አደረጃጀት ገብተው መዲናችን አዲስ አበባ ከተማን ከአሸባሪው የጁንታ ቡድን ጥቃት የሚከላለኩ ከ18 ሺህ 700 በላይ ሴቶችን ያቀፉ የብሎክ አደረጃጀቶች አሉ። ሴቶቹ አካባቢያቸውን ከአሸባሪውና ወራሪው ጠላት የሚጠብቁት በቀንና በሌሊት የፀጥታ ሥራ ላይ በመሰማራት ነው። ከ41 ሺህ በላይ የወንድ ተባባሪ አባላትም በተግባሩ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ይገልፃሉ። 6 ሺህ 50 ያህል በጎ ፈቃደኞችም መሳተፋቸውን ያክላሉ። በአጠቃላይ ከ450 ሺህ በላይ የማህበሩ አባላት በመቶ፣ በሻምበልና በጓድ አደረጃጀት ገብተው በቀንና በሌሊት የፀጥታ ሥራ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ። በጓድ አደረጃጀት ብቻ 412 ሴቶች አሉ።
አሸባሪው ጁንታ ቡድን በከፈተው ጦርነት ያጠቃው ሴቶችና ህፃናትን መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቷ ከዚህ አንጻር የሰላሙ ተጠቃሚ የበለጠ ሴቶችና ህፃናት መሆናቸውንም ያወሳሉ። በአደረጃጀት ገብተው አካባቢያቸውን መጠበቃቸውና ቡድኑንና ደጋፊዎቹን አጋልጠው ለሕግ ማቅረባቸው በአዲስ አበባ ከተማ ሊፈጠር የታሰበውን ሽብር ቀድሞ ለመከላከልና ሴቶችና ህፃናትን ብሎም ሕብረተሰቡን ከዚሁ ጥፋት ለመታደግ ማስቻሉን ይጠቅሳሉ።
አባላቱ ሥራውን ከማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ጋር ተቀናጅተው እየሠሩ መሆናቸውንና ለዚህ የሚያበቃቸውን ስልጠናም ቀደም ብለው በየክፍለ ከተማው መውሰዳቸውን ወይዘሮ ሁሉአገርሽ ገልጸዋል።
ማህበሩ የሴት አደረጃጀትን ከፀጥታ ሥራው ጎን ለጎን በህልውና ዘመቻው ከአሸባሪው ኃይል ጋር እየተፋለመ ለሚገኘው የመከላከያ ሠራዊትና በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ማሰባሰብ ለሚያስችል ሥራና ለደም ልገሣ የተጠቀመበት መሆኑንም ነግረውናል።
አቶ በቀለ አበበ በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ አንድ የሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት መረጃና ግጭት አፈታት ቡድን መሪ ናቸው። እርሳቸው እንዳወጉን በወረዳው 32 ብሎክ አደረጃጀቶች አሉ። አደረጃጀቶቹ ሀገራችን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ተንተርሰው ሻምበል፣ መቶና ጓድ በሚል አደረጃጀት መዋቀራቸውን ይጠቅሳሉ። በእያንዳንዱ የመቶ አደረጃጀት ሥር የሻምበል አደረጃጀቶች አሉ። በጓድ አደረጃጀት ውስጥ 117 የሴት አደረጃጀቶች አሉ። ከ810 አደረጃጀት ውስጥ 417ቱ የሴቶች አደረጃጀቶች ናቸው። በመቶ አደረጃጀት ሥር 27 ሰዎች ሲኖሩ 10ሩ ሴቶች ናቸው። እንዲሁም በ81 የሻምበል አደረጃጀት 39ኙ ሴቶች ናቸው። በአጠቃላይ በ810ሩ አደረጃጀት ውስጥ 417ቱ የሴት አደረጃጀት ሲሆን የወንድ አደረጃጀት 393 መሆኑንም ይናገራሉ።
አደረጃጀቱን የበለጠ እየተጠቀሙበት የሚገኙት ከፀጥታና ከወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ ጋር በተያያዘ በሮንድ/ጥበቃ/ መልክ፣ መረጃ ልውውጥ ለማድረግ እንደሆነም ይገልፃሉ። እያንዳንዳቸው ጠርናፊ አካላት እንዳላቸውና፤ መረጃ በመለዋወጥ ዓይነተኛ መፍትሄ የሚሆን ተግባር እያከናወኑ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
‹‹የውጭ መብራት አገልግሎት በወረዳው ሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ሆኗል›› የሚሉት ቡድን መሪው ለአብነት አምባሳደር፣ ቦርደኔ ንዑስ ቀበሌ 14፣ ፑሽኪን ንዑስ ቀበሌ 11፣ አትክልት ተራ ለመልሶ ግንባታ የፈረሰው አካባቢ ግልጽ ብሎ እንዲታይ የውጭ መብራት አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ እንደተቻለ ተናግረዋል። በዚህም በጭለማ ምክንያት ይከሰታል ተብሎ የሚታሰብ የፀጥታ ችግር እንዳይኖር ተደርጓል።
በወረዳው ሰባት ቦታዎች የስጋት ሥፍራዎች ተብለው መለየታቸውንም ጠቅሰዋል። እነዚህም ፑሽኪን፣ ሀብተ ጊዮርጊስ ድልድይ፣ አትክልት ተራ፣ አራዳ ህንፃ አካባቢ ከተለዩት መጠቀሳቸውንም ይናገራሉ። በእነዚህ ሥፍራዎች የነበረው አደገኛ ችግር በሴቶች ብሎክ አደረጃጀት ተሳትፎ መቀረፍ መቻሉን አውስተዋል።
አራዳ ህንፃ አካባቢ የቦርሳና የሞባይል ቅሚያ ይዘወተር እንደነበር የጠቀሱት አቶ በቀለ የሴቶች አደረጃጀት ከተፈጠረ በኋላ ከሊስትሮ፣ ጀብሎና ፓርኪንግ ሠራተኞች ጋር በመቀናጀት ጭምር ችግሩን መቅረፍ እንደተቻለ ተናግረዋል።
በወረዳው ሦስት ሽፍት እንዳለና የመጀመሪያው ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽት ሦስት ሰዓት በሴቶች እንደሚሸፈን፤ ከሶስት ሰዓት እስከ አምስት ሰዓት በጎልማሳ ወንዶች እንደሚጠበቅና፤ ከአምስት ሰዓት ተኩል እስከ ንጋት ያለው አስቸጋሪ ጊዜ ደግሞ ትኩስ ኃይል በሆኑ በበጎ ፈቃደኛ ወንድ ወጣቶች እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
በዚሁ መሰረት የወረዳው አመራሮችም አካባቢያቸውን የሚጠብቁበት ሽፍት እንዳላቸው ገልጸዋል። አምስት አምስት አመራሮች በየቀጠናው እየተሰማሩ ሥራው ውጤታማ እንዲሆን ከአራዳ ክፍለ ከተማ ማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ጋር እየተናበቡ የመሥራቱን ሂደት ያመቻቻሉ። በዚሁ መሰረት ሴት አደረጃጀቶችም በወረዳው ካሉ አምስት የቀጠና የፖሊስ ኮሚዩኒቲዎች ጋር በመቀናጀት ይሠራሉ።
በየቀኑ ሌሊት ምን ተከሰተ? እናንተ ጋር ምን ተመዘገበ? የሚል የመረጃ ልውውጥ ሲኖር ወረዳው ጣቢያው ተጠሪነቱ ለሠላምና ፀጥታ ስለሆነ ከጣቢያው በየቀኑ የ24 ሰዓት መረጃ ይወስዳል። መረጃው የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት ዓይነተኛ እንደመሆኑ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢ ያሉ አደረጃጀቶች የሴት አደረጃጀቶቹን ተሞክሮ በመቅሰም ያሰፉት ዘንድ በመጠቆም ጽሑፋችንን ደመደምን!!!
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 19/2014