የፋሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ ንዋይ የሚንቀሳቀስበትና በዓለም ደረጃ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ነው። አንዳድ አገራት ከአገራዊ ገቢያቸው ጋር በተስተካከለ መልኩ ረብጣ ዶላር ያፈሱበታል።ዘርፉን ቀድመው በመረዳት ለፋሽን ኢንዱስትሪው ትኩረት በመስጠት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላሮችን ወደ ካዝናቸው ማስገባትም ችልዋል። ይህ የሚያመላክተው የፋሽን ኢንዱስትሪ ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራበት ለአገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ነው።
ከዘርፉ በቢሊዮን ዶላር የሚያገኙት አገራት ፋሽንን ለአገራዊ ገቢያቸው ዋንኛ ዘርፍ አድርገውታል። እንደ አሮፓውያን አቆጣጠር በ2016 መጨረሻ ላይ በተሰራ አንድ ጥናት፤ ያደጉት አገራት ከአልባሳት ፋሽን ብቻ (ሌሎች የፋሽን ዘርፎች ሳያካትት) በዓመት ያገኙት ገቢ ለ1.26 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ መሆኑን ያመለክታል። ይህ የአንድ አመት ገቢ ብቻ ነው።
በተለይ እንደኛ ታዳጊ በሆኑ አገራት ላይ የስራ አጥነት ችግር ከፍተኛ ሆኖ ይስተዋላል። ፋሽን በትክክልና በተገቢው ሁኔታ ከሰሩበት ከፍተኛ የሆነ የስራ አጥ ችግር በመፍታት አገራት ያላቸው ሰዋዊ ሀብት በትክክል እንዲጠቀሙም ያደርጋል። የኢንዱስትውን ጠቀሜታ የተረዱት አገራት የፋሽን ኢንዱስትሪው ሰፊ ገበያ በማጥናት በሰጡት ከፍተኛ ትኩረት ገበያው የፋሽን ምርቶችን በማቅረብ ከፊት ተሰልፈዋለ። በተለይም በፋሽን ኢንዱስት እጅጉን ርቀው የሄዱት አገራት ዘርፉ ለገቢ ማግኛቸውና የህዝባቸው የስራ ዕድል መፍጠሪያ ብሎም ገቢያቸውን ማሳደጊያ አድርገው በመጠቀም ላይ ይገኛሉ።
በዚህ ዘርፍ አገራቱ ትኩረት ሰጥተው መስራታቸውና ገቢያቸውን ለማሳደግ በሰጡት ትኩረት ያገኙት ለውጥ ማሳያ ሊሆን ይችላል። በዘርፉ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኔዘርላድ፣ እንግሊዝና ስፔን በቅደም ተከተል ይጠቀሳሉ። እነዚህ አገራት የፋሽን ኢንዱስትሪውን ለማዘመንና የገቢ ምንጭ ለማድረግ ሲወጥኑ ቀድመው የሰሩት በሰለጠነና ዘርፉን ጠንቅቆ በሚያውቅ የሰው ሀይል ማፍራት ላይ ነው። በፋሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ከትምህርት ቤት እስከ ኮሌጅ ድረስ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሀይል አሰልጥነውና አብቅተው ለምርት ዝግጁ ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ በፋሽን ኢንዱስትሪው መስክ ገና ብዙ የሚቀራትና በጅምር ላይ ያለች አገር ስለመሆንዋ የመስኩ ባለሙያዎች ይመሰክራሉ። ለዚህ ደግሞ በርካታ ምክንያቶች ቢጠቀሱም በመስኩ በቂና የሰለጠነ የሰው ሀይል አለመኖር እንደ አንድ ምክንያት ይነሳል። እንደ አገር እዚህ ላይ ምን እየተሰራ እንደሆነ በስፋት በወደፊት የፋሽን ቅኝቶቻችን ውስጥ እናያለን። ለዛሬ በራስ ተነሳሽንት ዘርፉን ለማሳደግ እየሰሩ ያሉ ተቋማት ስራዎችን በወፍ በረር ዳሰናል።
ሄዋን የፋሽን ዲዛይን ትምህርት ቤት በአገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች የፋሽን ዲዛይን ትምህርት ቤቶችን በመክፈት ለኢትዮጵያ ፋሽን ዲዛይን ዕድገት የራሱን የሆነ አስተዋፅኦ እያደረጉ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች አንዱ ነው። ተቋሙ ከፋሽን ዲዛይን በተጨማሪ በውበት አጠባበቅና ሜካፕ እንዲሁም የፀጉር ስራ ስልጠናዎችን በአጭርና በረጅም ጊዜ ይሰጣል።
እንደ ተማሪዎቹ ፍላጎት ከ1 ወር እስከ 6 ወር ድረስ የተለያዩ ሙያዊ ስጠናዎችን የሚሰጠው ተቋሙ በርካታ ሙያተኞችን በማፍራት ለፋሽን ኢንዱስትሪው የራሱን አስተዋፅኦ እየበረከተ መሆኑን የምትናገረው በተቋሙ ውስጥ በአሰልጣኝነት የምትሰራው ህሊና ደስታ ናት። (እዚህ ላይ ህሊና እየተባለች የምትጠራው ባለሙያ ስምዋ መቀየሩ ልብ ይሏል)
በልብስ ስፌት ዲዛይን፣ በስነ ውበትና ሜካፕ፣ በጥፍር ስራ፣በፀጉር ስራና በዲኮር ስልጠና እንደሚሰጥና ተማሪዎችም ከተቋሙ ተመርቀው እየወጡ የራሳቸውን ስራ በመፍጠር ላይ መሆናቸውን ታስረዳለች። በተቋሙ ውስጥ ሰልጣኞች ሲመጡ እንደፍላጎታቸው ተለይተው ባሻቸው ሙያ በቂ የሆነ እውቀት ጨብጠው እንደሚወጡና በተለያዩ መድረኮች ላይም ውጤታማ ሆነው እንደሚታዩ በማሳያነት ትገልፃለች።
ሌላኛው መሰል ስልጠና የሚሰጠውና በከተማችን ከሚገኙ የፋሽን ዲዛይን ትምህርት ቤቶች መሀል ፐርፕል ተጠቃሹ ነው። ዚነት ሙሐመድ ዲዛይነርነት ናት በዚህ ስራ ሶስት ዓመታት ቆይታለች። የራስዋ ፐርፕል የተሰኘ የዲዛይን ፋሽን ት/ቤት ከፍታ እየሠራች ሲሆን አዲስ አበባ ቤተልና እንቁላል ፋብሪካ ሁለት ማሰልጠኛዎችም አሏት። በፋሽን ዲዛይን ትምህርት ቤቱ በፋሽን ዲዛይን የጋርመንት ዲዛይኖችንና የባህል አልባሳትን በተለይም የጥበብ ልብሶች ላይ በማተኮር በዲዛይንና ፋሽን ያስተምራሉ። ተቋሙ ከተመሰረተ ጀምሮ ለአራት ጊዜ ተማሪዎችን አብቅተው ማስመረቃቸውን ዲዛይነር ዚነት ትናገራለች።
በአካውንቲንግ እንደተማረች የምትናገረው ዲዛይነር ዚነት ቆይቶ የፋሽንና ዲዛይን ኮርሶችን ወሰደች ፤በፋሽን የወሰደችውን ሥልጠና ስታጠናቅቅ ቀጥታ ፐርፕል ፋሽንና ዲዛይን ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት በመክፈት ነው ስራን የጀመረችው። በተቋሙ ውስጥ በአሰልጣኝነት የሚሰሩ ባለሙያዎች በተመለከተ ጥያቄ ያነሳንላት ዚነት፤በራስዋ ተቋም ውስጥ ብቁና የሰለጠኑ ባለሙያዎች እንዳሏት ታስረዳለች። ነገር ግን በተለያዩ የፋሽን ዲዛይን ትምህርት ቤቶች በሚሰጡ ስልጠናዎች ላይ የጥራት ችግር እንዳለ እንደምትሰማና በራስዋ በኩል ይህ እንዳይነሳ ጥረት እንደምታደርግ ታስረዳለች።
ዲዛይነር የሺሀረግ በላይነህ የፋሽን ዲዛይን ትምህርት ቤቶቹ ጥራት ላይ ጥያቄ ታነሳለች። እንደ ዲዛይነርዋ የፋሽን ዲዛይን ትምህርት ቤቶቹ በአብዛኛው ስልጠና የሚሰጡት በልምድ እንጂ እውቀትና ክህሎትን በተላበሱ መምህራን አይደለም። ምን አልባትም ባሰልጣኝነት የሚሳተፉት ግለሰቦች ሙያውን ተምረውት ሳይሆን ፍላጎት ስላላቸው ብቻ የሚሰሩት ነው ሚመስለው በማለት አስተያየትዋን ትሰጣለች።
በእርግጥ ብቁና ሙያቸው ላይ ታታሪና ጎበዝ ብቃት ያላቸውም መኖራቸውን አትክድም። ለዚህም “እኔ በምማርበት ጊዜ እንደ አርዓያ የማያቸው ጎበዝ አስማሪዎችም ገጥመውኛል” በማለት ሌላኛው ገጠመኝዋንም ታካፍላለች። የፈለኩትን የፋሽን እና የዲዛይኒግ ትምህርት ለመማር ከ3 በላይ ትምህርት ቤቶች አንኳኩቻለው ነገር ግን የተሻለ ነገር ያገኘሁት አንዱ ላይ ነው በማለት ትምህርት ቤቶቹ ላይ ጠንከር ያለ ትችትዋን ትሰነዝራለች።
ህሊና ደስታ ከሄዋን የፋሽን የዲዛይን ትምህርት ቤት ውጪ በሁለት ፋሽን ዲዛይንና ስነ ውበት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በአሰልጠኝነት ታገለግላለች። ህሊና እየተዘዋወረች በምትሰራባቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ በአሰልጣኝነት የሚሰሩ ባለሙያዎች በአብዛኛዎቹ በልምድ ስራውን የሚሰሩ መሆናቸውን ትገልፃለች። ከጥቂት ባለሙያዎች በቀር ስራውን በትክክል እንደማያውቁት የምትገልፀው ባለሙያዋ የዘርፉን ዕድገት የተሻለ ለማድረግና ውጤት እንዲያመጣ የፋሽን ትምህርት ቤቶች ላይ ሊሰራ እንደሚገባ ትናገራለች።
በአብዛኛው ስልጠናዎች የሚሰጡት በልምድ እንደሆነና በተለይም በስነ ውበትና ሜካፕ እንዲሁም የፀጉር ስራ ስልጠናዎች የሚሰጡት በስራቸው ጎበዝ አዳዲስ ነገር ፈጣሪ በሆኑ ተማሪዎች መሆኑን ይናገራሉ። እርግጥ ሙያው ልምድ ወሳኝ ቢሆንም ይበልጥ የተሻለ ነገር ለመፍጠር በዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል የባለሙያዎቹ አስተያየት ነው።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 18 ቀን 2014 ዓ.ም