አዲስ አበባ፡- የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ‹‹ደራሽ›› ፕላትፎርም የተባለ ሀገር አቀፍ የተቀናጀ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ አገልግሎት ሥርዓት የሙከራ ጊዜ አጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ፡፡ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የተቀናጀ ፕላትፎርም ዲቪዥን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዮናታን አያሌው ትናንት በተቋሙ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት ‹‹ደራሽ›› የተቀናጀ የክፍያ ፕላትፎርሙ በባንክ፣ በተንቀሳቃሽ ስልኩ፣ በበይነ መረብ (ኢንተርኔት) እና በሌሎችም አማራጭ ክፍያ ለመፈጸም የሚያስችል ዘዴ ሲሆን፣ ደህንነቱ በተጠበቀ ከአንዱ ወደ ሌላው በማድረስ አገልግሎት የሚሰጥ አዲስ ቴክኖሎጂ ነው፡፡
እንደ አቶ ዮናታን ገለጻ የግብር፣ የኪራይ፣ የውሃ፣ መብራት፣ የስልክና የተለያዩ አገልግሎት ሰጪዎች እንዲሰበሰብላቸው የሚፈልጉትን ክፍያ ወደ ‹‹ደራሽ›› ይልካሉ፡፡ ደራሽ ደግሞ አብረውት ለሚሰሩ ባንኮች ዳታውን ወይንም መረጃውን በማድረስ የአገልግሎት ክፍያው እንዲፈጸም ይደረጋል፡፡ ደምበኞችም ለተጠቀሙበት አገል ግሎት ባንኮች በሚያስከፍሉበት የክፍያ አማራጮች ሁሉ በመጠቀም ክፍያቸውን ይፈጽማሉ፡፡
ኤጀንሲው ቴክኖሎጂውን ለአንድ ዓመት ሲያለማ መቆየቱን የጠቆሙት አቶ ዮናታን በሙከራ ጊዜውም በፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር በተመረጡ የግብር ከፋዮች የክፍያ ሥርዓቱን ተግባራዊ በማድረግ ባለፉት ስምንት ወራት ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ የሐረሪ ክልልም በተመሳሳይ ካለፈው ወር ጀምሮ የውሃ አገልግሎት ክፍያውን ‹‹ደራሽ›› ፕላትፎርም በተባለው አገልግሎት መጠቀም መጀመሩን አመልክተዋል፡፡
አሁን በሥራ ላይ ካለፈው ‹‹ለ ሁሉ›› ከተባለው የክፍያ አገልግሎት በምን ይለያል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ደራሽ›› ፕላት ፎርም ማንኛውንም የክፍያ አገልግሎት የሚሰ በስብ ተቋምን ተደራሽ የሚያደርግ መሆኑን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ዓላማውም በአገልግሎት ላይ የሚገኝ ተቋምን መተካት እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
ማንኛውም ተገልጋይ ሳይንገላታ እጁ ላይ ባሉ አማራጮች እንዲጠቀም ማስቻል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ የማስፋፊያ ሥራ ሲጠናቀቅ ህጋዊ የሆኑ የግልና የመንግሥት ባንኮች የ‹‹ደራሽ››ፕላትፎርም አካል ሆነው የሚሰ ሩበት ሁኔታ እንደሚመቻች አስታውቀዋል፡፡ ለደንበኞቹ ተደራሽ የሆነውን መርጦ መጠቀም የተገልጋዩ ምርጫ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2011
በለምለም መንግሥቱ