አምቦ፦ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል በ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የማስፋፊያ ግንባታ እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል የማስፋፊያ ግንባታ ማድረጉ የመማር ማስተማሩን ሂደት የተሻለ ከማድረጉ ጎን ለጎን በአካባቢውና በምዕራብ ኦሮሚያ ለሚገኙ ሪፈራል የህክምና አገልግሎቶችን ያሳልጣል፡፡
ሆስፒታሉ ዞናል ሆኖ የተገነባ የነበረ ቢሆንም አምቦ ዩኒቨርሲቲ መረከቡን ገልፀው ተቋሙ የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደራሱ አስተዳደር ያሸጋገረበት መንገድ ህጋዊ ሥርዓቱን የጠበቀ ነው ብለዋል፡፡ ከአራት ዓመት በፊት የዞናል ሆስፒታሉ ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲጠቃለል ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ከኦሮሚያ ጤና ጥበቃ እና ከትምህርት ሚኒስቴር ፍቃድ ማግኘቱን አመልክተዋል።
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነት ሥራዎች አስተባባሪ አቶ ሙለታ ዱጉማ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ከተረከበው ከዓመታት ቆይታ በኋላ ሆስፒታሉ የነበረውን አቅም ለማሳደግ የማስፋፊያ ግንባታ መጀመሩን ገልጸዋል። ሆስፒታሉ ለዩኒቨርሲቲ የሪፈራልነት ቁመናን ሙሉ ለሙሉ እንዲላበስ ከማድረግ በተጓዳኝ ፣የአገልግሎቱን አድማስ በማስፋት የምዕራብ ኦሮሚያ የህክምና ማዕከል እንዲሆንም መታሰቡን ይናገራሉ፡፡
እንደ አቶ ሙለታ ገለፃ የማስፋፊያ ግንባታው አገልግሎቱን በማሳደግም ጭምር ነው፤ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ስፔሻሊስት ሀኪሞችን መቅጠር ፣አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ማሟላት ተከናውኖ ወደ ተሟላ ደረጃ ለመሸጋገር እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡ ከሦስት ወር በፊት ማስፋፊያ የጀመረው ዩኒቨር ሲቲው ግንባታውም በቲ ኤን ቲ ኮንስትራክሽንና ንግድ ድርጅት እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ግንባታው ከአምስት ዓመት በኋላ ተጠናቆ አገልግሎት የሚሰጠው ሪፈራል ሆስፒታሉ ሙሉ ወጪውም በፌዴራል መንግሥት የሚሸፈን ነው፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2011
በዳንኤል ዘነበ