ተግባራቸው ሰቅጣጭ፣ዘግናኝ፣አገርና ሕዝብ አውዳሚ ሆኖብን እንጂ ንግግራቸው ግን በሳቅ እስከ ማፍረስ ያደርሳል፤ በተለይ ውሸታቸው ትልቅ ሰው ይህን ያህል ይዋሻል እንዴ ያሰኛል:: 27 ዓመታትን ሲዋሹን ነው የኖሩት ለካስ:: ሲዋሹ ለነገ አይሉም:: የሚናገሩትና መሬት ላይ ያለው እውነታ ሁሌም አራምባና ቆቦ ነው::
አንዳንዴ ሳስበው አጎታቸው ሰይጣን አባብሎዋቸው በሽብርተኛነት በተንኮልና በሴራ ጊዜአቸውን ፈጁ እንጂ በኮሜዲው ዘርፍ ቢሰማሩ የተዋጣላቸው በሆኑ ነበር:: ተግባርና ሥራቸው ያናደደንን ያህልም ባይሆን ፉከራቸው ከማናደድም አልፎ አስቆናል:: ማሽላ ሲያር ይስቃል እንደሚባለውም ይሁን ብቻ ውሸታቸው ያስቃል፤ያስፈግጋል፤ ያስገርማል::
የጁንታው አመራሮች የተዋጣላቸው ኮሜዲያን ሊሆኑ ይችሉ የነበረ መሆኑ አስቀድሞ ቢገባቸው ጥሩ ነበር:: ይህ ቢሆን ኖሮ ለእድገታችን ሳንካ ባልሆኑ ነበር:: አንድ ወቅት ላይ ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው ይል ነበር አንድ የጁንታው ዘባራቂ፤ ጦርነቱን ጀምረው በገዛ ሜዳቸው ተገርፈው ሲሸነፉ፣ ይሄው ሰው የኢትዮጵያውያንን ባህላዊ ምግብ አትብሉ ብሎ ይቀሰቅስ ገባ፤ አሉላ የተባለ ቀላማጅ:: ኢትዮጵያ በሚል የሚጠራውን ሁሉ አትጠቀሙ፤ አትጥሩ፣ ወዘተ. አለ:: ይህን ያለው ጁንታ ይሄኔ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያን የሚል ሆቴል ውስጥ ተቀምጦ፣ክትፎ እየበላ ይሆናል ::
የተዘጋጀላቸው ወጥመድ እንዳለ ሳይገምቱ ወይም የሆነች ድል የምትመስል ነገር ያዩና ቀልዳቸውን ይቀጥላሉ:: ልክ የዛሬ ወር ገደማ የእነዚህ ዘግናኝ ኮሜዲያን መሪ አይተ ደብረ ጽዮን ጉድጓዱ ውስጥ ሆኖ “ውጊያው አልቋል፤ ካሁን በኋላ የምታድነው ከተማ የለም፤ በከንቱ ከምትሞቱ ራሳቸሁ አድኑ” ሲል ተናግሮ ነበር:: ታጣቂዎቹ ግር ብለው ወሎ፣ ሸዋ ፣አፋር መግባታቸው ጮቤ አስረግጦት መሰለኝ:: አይይ … ወገን! ይሄ ሰውዬ ኢትዮጵያዊ መስሎ እንጂ ኢትዮጵያዊ ሆኖ አያውቅም ማለት ነው:: አሳምሮ አያውቀንም ነበር፤ ጦርነቱ ሲጀምር ያለቀ መስሎታል::
ለነገሩ አሜሪካኖቹም ሐሰተኛ መረጃ እየረጩ ቼ እያሉ እየጋለቡት ስለሆነና በደርግ ጊዜም የተጠቀመባት መንገድ ስላለች ነው ይህን ማለቱ:: እያሸበሩ ከተማ መያዝ፣ ሥልጣን መያዝ:: ዱባና ቅል ለየቅል ነው የተባለው:: ትህነግን ሰባብረን ለመጣል ቆርጠን መነሳታችን አልገባውም፤ ይህ ባይሆን ይህን አይነት ቀልድ ባልሞከረ ነበር፤ ጉደኛ ቀልድ ናት አኮ:: አዲስ አበባ ሲመኝ መቀሌ ተመለሰ::
ያን ሁሉ ቀረርቶ ረስቶት ሰሞኑን ደግሞ የድረሱልኝ ቀልድ ጀምሯል:: በቅርቡ በኢትዮጵያ ኃይሎች ተቀጥቅጦ ከተሸነፈ 50 ለሚሆኑ የውጪ መንግሥታትና ለተመድ በላከው የተማፅኖ ደብዳቤ ድሮንዋን አስቁሙልን፤ እስዋ ናት እንቅልፍ የነሳችን ብሏል::
ይቀልዳል አንዴ፤ እሷማ የቀረርቶው የእምቡር እምቡሩ ማርከሻ ናት፤ ዋጥ አርጋት ነበር የሚሉን ቤተሰቦቻችን ገርፈውን ማለቃቀስ ስናበዛ:: የዘንድሮ አጥፊ አርጩሜ ምረጡልኝ እያለ ነው:: ደጺ ይህችን ማለቃቀስ ተዋት፤ ዋጥ አርጋት!
እነዚህ ጉዶች የማይሉት የለም:: እንደ እባብ ተቀጥቅጠው መሸነፋቸውን ከማመን ይልቅ፣ ሰሞኑን ደግሞ ለሰላም ብለን ወደ ትግራይ ተመልሰናል አሉን:: ያኔ እናቶች ተንበርክከው ጭምር ተው! ሕዝቡን አታስጨርሱ! የሰላምን ጥሪ ተቀበሉ ሲሏቸው እሺ ቢሉ ኖሮ ዛሬ በቁም ነገር አዘል ቀልድ ሊያስቁን በቻሉ ነበር:: አሁን ግን ንግግራቸው ሁሉ ቀልድ ሆኖብን እያሳቀን ነው::
ያን ሰሞን አይተ ጌታቸው ረዳ “ለጠቅላላ እውቀት እንዲሆን…” ብሎ የጀመረው ንግግር ታወሰኝ:: “አዲስ አበባ አንገባም አላልንም፤ መቼም እንጦጦ ደርሰን አንመለስም…” ሲል ሕልሙን ነው ቅዠቱን ነገረን:: እኔ የምለው ጠቅላላ እውቀት የሌለው ሰው ለጠቅላላ እውቀት ብሎ ወሬ ይጀምራል እንዴ? መጀመር የለበትም:: ጠቅላላ እውቀት የሚባል አልተፈጠረበትም እኮ፤ መቀባጠር ብቻ!
ይልቅስ እኛ ከፈቅድንለት እሱ ራሱ አዲስ አበባ ይገባል:: የሚመጣውም ግን እጁ በካቴና ተጠፍንጎ፣ አንገቱን እንደ አጎቶቹ ደፍቶ፣ ፊቱ ገርጥቶና ጠቁሮ፣ ልብሱ ተልኮስኩሶ ነው:: ለእዚያውም እድለኛ ከሆነ:: ካልሆነ እንደ ባልደረቦቹ ምድርን ተቀላቀለ የሚል ዜና እንሰማለን::
ጌቾ በፉከራው አስፈግጎን በንቀቱም አናዶን ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ደግሞ ሌላ ኮሜዲ መሰል ቀልድ ይዞ ከተፍ አለ:: በጀግናው መከላከያችን ተደቁሶ መውጣቱን አላምን ብሏል:: ለእራሱም ለወዳጆቹም ትንግርት በሆነ ሁኔታ አሳፋሪ ሽንፈት ደረሰበት፤ ይህ የሆነው ደግሞ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ነው:: እንደተባለውም የአማራና አፋር ክልል መቀበሪያቸው ሆነ::
እነ እንጦጦ ደርሰን ዝም ብለን አንመለስም ባዮቹ ፣ መቀሌ ተመልሰው ገቡና አረፉት፤ ምን ‹‹ይዤ ልመለስን›› ለማንጎራጎርም ጊዜ ያገኙ አልመሰለኝም:: የተረፈውን ታጣቂ ወደ መቀሌ አስጠግቶ ሲያበቃ ደግሞ ይህ የማያልቅበት ጉድ “ለሰላምና ለድርድር ስንል ከያዝናቸው ቦታዎች ለቀን ወጥተናል ” ብሎ አስፈገገን:: ፈረንጅ ብላ! ብለናል::
መች በዚህ አበቅቶ፤ እኛ ከአማራና ከአፋር እንደለቀቅነው ሁሉ የኢትዮጵያ ኃይሎችም ከምዕራብ ትግራይ ለቀው ይውጡ ብሎም ቀልዱን ለማጣፈጥ ሞሯል:: ካፈርኩ አይመልሰኝ ነው ንግግራቸው ሁሉ:: እንደው የፈጠሩብን ሕመም ውስጣችን ባይኖር ቀልዳቸውን በጉጉት በጠበቅነው ነበር::
ኢትዮጵያን የምታህል ትልቅ አገር ለማፍረስ ሲኦል ድረስ እንደሚወርድ ሲነግረን የቆየው አንሶት፣ ትህነግ በአማራና አፋር ሕዝብ ላይ አይቀጡ ተቀጥቶ ተመልሶ መቀሌ በር ላይ በቆመበት ሁኔታ ለሰላም ብለን ወደ ትግራይ ተመልሰናል ይለናል::
በተለይ ጌታቸው ረዳ የሚናገረውና የሚፅፈው ሁሉ ይገርማል:: ሰው ሕግ ተምሬያለሁ ብሎ ከሕግ የራቀ ተግባርና እንዴት ይሰማራል፤ እንዴትስ ሕገ ወጥ ንግግር ያደርጋል:: እንዴትስ ያለሙያው የኮሜዲያንን ተግባር እኔ ሸፍኜ ከጦርነት የተረፈውን ሕዝብ በሳቅ ልግደል ይላል::
ሰላምን ያመጡት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ናቸው:: ለትህነግ ዘሎ መውጣት ዘሎ እንደ መግባት እንደማይቀል በማሳየት ከአማራና አፋር እንዳይወጣ አርገው ደቁሰውታል፤ ይህንንም በወረራ ይዟቸው የነበረ የአማራና አፋር አካባቢዎች ይመሰክራሉ:: የሥነምግባር ጉዳይ ይዞን እንጂ በምስል እያስደገፉ ጉዳቱን ማሳየት ይቻል ነበር::
ያ ኮስተር ብሎ የሚቀልደው ጄኔራላቸው ሌላው ኮሜዲያናቸው ነው፤ ፃድቃን:: እሱም ከወር በፊት “አሁን በድርድር የሚፈታ ነገር የለም፤ ከማን ጋር ነው የምንደራደረው፤ ጦርነቱ አልቋል.. ” ብሎናል :: ይሄ እንዴት ከት አርጎ አያስቅ:: ጄኔራል ፃድቃን ይቺን በጥቅምት ወር መጨረሻ ያደረጋትን ንግግር መልሶ ቢያዳምጣት ራሱም ከት ብሎ ሳይስቅ አይቀርም:: ለነገሩ ምን ሰዓት ኖሮት ያዳምጠዋል፤ ድሮኗ አላስወጣ አላስገባ አላስቆም አላስቀምጥ ብላቸዋለች፤ኮሜዲያኑን::
አንድ ቲኤምኤች በሚባል የእነሱ ሚዲያ ላይ እየወጣ እርስ በርሱ የሚጣረስ አስተያየት የሚሰጥ ስታሊን የተባለ ዘባተሎም አለ:: እሱን ስሰማ አይደለም ገና ብቅ ሲል ሳቄ ይመጣል:: ደሞ ዛሬ ምን ይዘባርቅ ይሆን እላለሁ:: በነገራችን ላይ እየሳቅኩበት እንጂ ስቄለት አላውቅም::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዘመቻ ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት ከሳምንታት በፊት ወደ ግንባር ሲዘምቱ ሕዝቤ ተከተለኝ ማለታቸውን ሰምቷል፤ ይሄው ስታሊን:: ይህን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የት ግንባር እንደዘመቱ ለነገረን ወይም መረጃ ላቀበለን 11 ሚሊዮን ብር እንሸልማለን” ማለቱ አስቆን ሳያበቃ ለካስ የዘመቱበትን ግንባር ለማወቅ የጓጉት በዚያ በኩል ለመፈርጠጥ አስበው መሆኑ ዘግይቶ ገባን::
ምን ዋጋ አለው እነዚህ የመሳሰሉ ቀልዶቻቸው እና አስቂኝ ተረኮቻቸው ሁሉ በማንደራደርባት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ላይ የተደረጉ ሆኑና አስመረሩን:: ያስመረሩንን ያህል አሁን የመከራ ፅዋ ተጎንጭተዋል:: ኢትዮጵያን የተዳፈረ ኢትዮጵያውያንን የነካ መጨረሻው ይሄው እንዲሆን ኢትዮጵያውያን ፈርደዋል:: ኢትዮጵያ ወደፊትም ታሸንፋለች፤ አበቃሁ፤ ቸር ያሰማን::
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 16/2014 ዓ.ም