ሰሞኑን የእማሆይ ከሰፈር መታጣት ብዙዎችን አስጨንቋል። ለወትሮው አላፊ አግዳሚው የእሳቸውን ሰላምታ ለምዷል። እማሆይ ሁሌም ያገኙዋቸውን ሁሉ ሰላም እያሉ ስለደህንነታቸው ይጠይቃሉ። ስለከብቶቹና ፣ ስለ ልጆች፣ጤና ውሎ ማደር ይጨነቃሉ።
እማሆይን የሚያውቁ ሰፈርተኞች ጥያቄያቸውን በወጉ ይመልሳሉ። ሰላም መሆናቸውን፣ ቸር ውለው ማደራቸውን ይናገራሉ።እማሆይ ሁሉንም በወጉ መርቀው ለመንደር ሰፈሩ፣ለቀበሌ አድባሩ መልካሙን ይመኛሉ። ይህ እውነት ምዕራብ ጎጃም ዞን ፣ደጋ ዳሞት ወረዳ፣ አቅላት ‹‹ወይ በይኝ›› ቀበሌ ውስጥ ለዓመታት ዘልቋል፡፤ የጨፍጨፍ ጎጥ ነዋሪዎችና እማሆይ ምናሉ ውቤ በእናትና ልጅነት መከባበር ዕድሜን ቆጥረዋል።
እማሆይ ልጆች ወልደው ለወግ ማዕረግ አድርሰዋል።ልጆቹ ጎጆ ከቀለሱ በኋላ የተወለዱበትን ቀዬ ለቀው ከአካባቢው ርቀዋል።አንዳንዴ ብቅ እያሉ እናታቸውን ይጠይቃሉ።የሁሉ እናት የሆኑት እማሆይ ከብዙዎች ተግባብተው፣ ተስማምተው ያድራሉ።
ከልጆቻቸው አንደኛው አሁንም ከእሳቸው ጥግ አልራቀም። ጎጆ ቀልሶ ትዳር ከያዘ ጀምሮ አብሯቸው ይኖራል። እማሆይ ልጃቸው ወግ ማዕረግ ስላሳያቸው ደስተኛ ሆነዋል። አብሯቸው በመኖሩ እፎይታ እየተሰማቸው ነው። ሁሌም በጎውን ይመኙለታል ፣ መልካሙን ያስቡለታል፤ እንደ እናት የነገ ህይወቱ፣የወደፊት ዓለሙ ያስጨንቃቸዋል።
አንዳንዴ እማሆይ ራቅ ብለው ይሄዳሉ። አካሄዳቸው ቤተክርስቲያን ለመሳለም ፣ አልያም ገዳም ደርሶ ለመመለስ ነው። እንዲህ በሆነ ጊዜ ጉዳያቸው እምብዛም አይቆይም። የሄዱበትን ጨርሰው፣ በቶሎ ይመለሳሉ። ከቀዬው ደርሰው የትናንት ህይወታቸውን ይቀጥላሉ።መንደርተኛው የእማሆይ ሰላምታና ጸሎት ያበረታዋል።መልካምነታቸውን እያሰበ፣ምልጃቸውን ይናፍቃል።
ልጃቸው አበበ ጸጋው ሚስቱን ይዞ ከእናቱ ቤት መኖር ከጀመረ ዓመታት አልፈዋል። አንዳንዴ ባለቤቱና እናቱ እንደ አማትና ምራት ይሆናሉ። በየምክንያቱ የሚጋጩበት ሰበብ አይጠፋም። በየአጋጣሚው ነገር አንስተው ይቀያየማሉ፣ ይኮራረፋሉ። መልሰው ደግሞ እንደቀድሞ ይሆናሉ። ይህን የሚያውቀው አባወራ ጉዳዩን የለመደው ይመስላል። ከተማ ውሎ ሲገባ ሁኔታውን እንዳላየ ሊያልፍ ይሞክራል።
እናቱና ሚስቱ አልፎ አልፎ የሚያጋጫቸው ሰበብ በበዛ ጊዜ እማሆይ ያመራሉ።አንዳንዴ ድንገት ብድግ ብለው ለመሄድ ይነሳሉ። ውሎ ሲያድር ግን ችግሩ ይረሳል። ሰላም ይወርዳል። እንደገና ህይወት ቀጥሎም እንደበፊቱ መኖር ይጀመራል። ይህ ልማድ በልጅ አበበ ጎጆ መለስ ቀለስ ማለቱ ተለምዷል።
የእማሆይ መንገድ…
ሰሞኑን እማሆይ በሰፈሩ አልታዩም። ሁሌም ሰላምታቸውን በለመዱ መንደርተኞች ድምጻቸው እየተሰማ አይደለም። በርካቶችን ከመንገድ አቁመው ስለደህንነታቸው የሚጠይቁት እናት ከዓይን ቢታጡ አንዳንዶች ማሰብ መጨነቅ ይዘዋል። ቤተክርስቲያን ሲሄዱና ሲመለሱ ፣ ያላዩ ፣ ያላስተዋሉ ወዳጆቻቸው እየተነጋገሩ ነው። ሁሌም እማሆይ የት ጠፉ፣ በማለት መነጋገር ፣ መወያየት ይዘዋል ። ሰዎቹ መጨነቃችው ቢበረታ ወደቤታቸው ዘለቁ። ጠጋ ብለውም ስለእማሆይ ደህንነት ጠየቁ። ልጃቸው አበበ ለእናቱ ወዳጆች አሳማኝ ምላሽ ሰጠ። ሰዎቹ እማሆይ ከቀናት በፊት ማልደው መውጣታቸውን ሰሙ።
ጠያቂዎቹ ምላሽ ሲያገኙ እፎይታ ተሰማቸው። እስካሁን እማሆይ ድንገት ከሰፈሩ መጥፋታቸው የተለመደ አልነበረም። ከልጃቸው አንደበት ሰላም መሆናቸውን ባወቁ ጊዜ ግን መንደርተኞቹ ተንፈስ አሉ። ሰላምተኛዋ፣ ቅን አሳቢዋ እናት ከዓይን መጥፋታቸው ሲያስጨንቃቸው ሰንብቷል።
ሰዎቹ ጥቂት ቆዩና እማሆይ ወዴት እንደሄዱ ጠየቁ። ከልጅ አበበ ስለ እናቱ ከዓይን መራቅ ማብራሪያ አላጡም።እማሆይ ከቀናት በፊት ራቅ ወዳለ ገዳም መሄዳቸውን አረጋገጡ። ጠያቂዎቹ ይበልጥ ተረጋጉ። እማሆይ በድንገት የመሄዳቸው እውነት በምክንያት እንደሆነ ገባቸው።
እማሆይ ሰፈር ቀዬውን ለቀው ገዳም ከሄዱ ቀናት ተቆጠረ። ወዳጅ ዘመድ ይመለሳሉ በሚል በናፍቆት ጠበቀ። በጉጉት ደጁን ቃኘ። እማሆይ ከሄዱበት መንገድ አልተመለሱም። አሁን መንደሩ ጠዋት ማታ በሰላምታ እየተጎበኘ አይደለም።የተለመደው የእማሆይ በረከት ከጠፋ ጊዜያት ተቆጥረዋል። መመለሳቸውን የሚናፍቁ ወዳጆች አሁንም ያለመታከት ጠበቁ። እማሆይ እንደታሰበው በጊዜው አልመጡም።
አሁንም የመንደሩ ሰዎች ተጨንቀዋል። ወዳጅ ቤተሰቡ የእማሆይ ድንገት ወጥቶ መቅረት እያሳሰባቸው ይነጋገራሉ። ዛሬም አንዳንዶች ከልብ ቢጨነቁ ወደልጃቸው ቤት ሄደው ጥያቄ አንስተዋል። የእማሆይን መመለስ፣አንስተው ጤናቸውን ጠይቀዋል።
አንድ ቀን ወደ እማሆይ ቤት ማልደው የገሰገሱ የቅርብ ዘመዶች የልጃቸውን ሚስት ደጋግመው ጠየቋት። የልጅ ሚስትም ልክ እንደ እነሱ ተጨንቃለች። የእማሆይ አወጣጥ እንደቀድሞ አለመሆኑን እያነሳች ትነግራቸው ይዛለች። እሳቸው ወደገዳሙ ሲሄዱ ለመመለስ አስበው አይደለም። ይቺን ዓለም ንቀው፣ልብሳቸውን አቃጥለዋል። ላለመመለስ፣ ቆርጠው ከቤታቸው ርቀዋል።
ሰዎቹ በእማሆይ ቁርጥ ውሳኔ ደነገጡ። ይህ አይነቱ ሃሳብ የራሳቸው ምክር ብቻ ሆኗል። እንዲህ መደረጉ በሁሉም ሳይሆን በአንዳንዶች ዘንድ የተለመደ ነው። ለዕምነታቸው ያሰቡ፣ በዚህ ጽኑ መንገድ ይጓዛሉ። ይቺን ዓለም ንቀው፣ ዓላማቸውን ከገዳም፣ከምናኔ ያደርጋሉ ።
የእማሆይ መታየት…
የእማሆይ ከቀዬው ድንገት መጥፋት ከተወራ ጥቂት ጊዚያት በኋላ ገዳም መኖራቸውን የሚያረጋግጥ ዜና ተሰማ። በወረዳው ካለውና ‹‹ዋንታ ማርያም ›› ከተባለ ገዳም መኖራቸው ታወቀ ። እሳቸውን ‹‹ አይተናል›› ያሉ ሰዎችም ወሬውን እየተቀባበሉ አደረሱት። ይህኔ ወዳጅ ዘመድ በእፎይታ ተነፈሰ። እማሆይ እንደ ልቦናቸው፣ የእምነታቸውን ፈቃድ ይፈጽሙ ዘንድ ጉዳዩን በይሁንታ ተቀበለ።
ወዳጅ ዘመድና ልጆቻቸው የእማሆይን መመለስ እየናፈቁ ዓመታትን ጠበቁ። እማሆይ እንደታሰበው ሆኖ ብቅ አላሉም። ከቀናት በአንድ ቀን የሚወዱት ወንድማቸው ከዚህ አለም በሞት ተለየ። የእሱን መሞት ተከትሎ ብዙዎች መንገደኛዋ እንደሚመጡ አሰቡ። የሟችንና የመነኩሴ እህቱን ፍቅር የሚያውቁ ዘመዶች እማሆይ ለቅሶውን ሰምተው እንደማይቀሩ ገመቱ። ጠዋት ማታ ደጅ ደጁን እያዩም መምጣታቸውን ጠበቁ። እማሆይ አሁንም ብቅ አላሉም። ናፋቂዎቻቸው በሰቀቀን ዋተቱ።
አሁን እማሆይ ምናሉ እንደዋዛ ከቤት ከወጡ ሶስት ዓመታት ተቆጥረዋል። የእሳቸው ጉዳይ የሚያሳስባቸው ልጆች እንቅልፍ እያጡ ነው። እናታቸው ያለ ዓመል ያለ ልምዳቸው ወጥተው የመቅረታቸው ጉዳይ ሰላም ነስቶ ያስጨንቃቸው ይዟል።እማሆይ አልፎ አልፎ ከቤት ቢወጡም እንዲህ ጨክነው አያውቁም። ዓመታትን የሚያቆይ፣ ከቤት አውጥቶ የሚያዘልቅ ጉዳይም ሊኖራቸው አይችልም።
ምክክር …
ወዳጅ ዘመድ ይበልጥ መጨነቅ ይዟል። እስካሁን በሃሳብ ሲባዝን ለቆየበት እውነት መፍትሄ ሊያበጅለት ምክር ጀምሯል። ሰዎቹ በጉዳዩ መነጋገር መመካከር ሲጀመሩ ስለ እማሆይ ሽው የሚሉ ወሬዎች መሰማት ያዙ። ስለ መነኩሴዋ እናት አጠራጣሪ ጉዳዮች ይናፈስ ጀመር። ይህ ወሬ ደግሞ ከፖሊስ ጆሮ ለመድረስ ውሎ አላደረም።
የወረዳው ፖሊስ በአካባቢው የሚወራውን ጉዳይ እንደዋዛ አላለፈውም። በሰፈሩ ጉምጉምታ ተመርኩዞ ሰዎችን ጠያየቀ። እንደ ጓደኛ፣ ወዳጅ ዘመድ ቀረብ ብሎም መረጃ መያዝ ጀመረ። የፖሊስ መርማሪው ሹም ባዶ እጁን አልተመለሰም። ትኩረት የሚስብ፣ ሚዛን የሚደፋ እውነት ይዞ ተመለሰ።
መጋቢት 2 ቀን 2006 ዓ.ም …
እማሆይና ምራታቸው እንደወትሮው በቤታቸው ተቀምጠው ያወጋሉ። የዛሬ ጨዋታቸው መልካም አይመስልም። እንደዋዛ የተጀመረው ንግግር ካለመግባባት ደርሶ ያጨቃጭቃቸው ይዟል። ከሁለቱ እማሆይ አምርረዋል። የልጃቸው ሚስትም ጉዳዩን በቀላሉ አልተወችውም። እያረፉ ይጨቃጨቃሉ፤ እየተጨቃጨቁ ክፉ ደግ ይነጋገራሉ።
ከከተማ ማልዶ የወጣው የእማሆይ ልጅ በቤቱ የለም።አጋጣሚው ያመቻት የሚመስለው ባለቤቱ ድምጽዋን ከፍ አድርጋ የልቧን ትናገራለች።እማሆይና የምራታቸው ጭቅጭቅ አይሏል። ከምሽቱ ሶስት ሰአት ሲል ድንገት ከወደውጭ የእግር ኮቴ ተሰማ። እሱን ተከትሎም ሌላ ድምጽ ጭቅጭቁን ሰብሮ ገባ።የእማሆይ ልጅ አበበ ነበር። አበበ እግሩ ከግቢው እንደረገጠ የሁለቱ ንግግር የጠብ እንደሆነ አወቀ።ከውጭ ተንደርድሮ ወደውስጥ ሲዘልቅ ፊቱ ላይ ንዴትና ብስጭት ተነበበ ።
ከቤት እንደገባ እናቱንና ሚስቱን ማስማማት አልፈለገም።ፊቱን ወደ እናቱ አዙሮ ጮኸባቸው። ክፉኛ ደነገጡ። ሚስቱን ሁለተኛ እንዳይናገሯትም በሀይለ ቃል አስጠነቀቃቸው። እማሆይ ከእሱ ይህን አልጠበቁም። ልጃቸው እያመናጨቀ፣ መቆጣቱ አስደንግጦ ሆድ ባሳቸው። በገዛ ቤታቸው እንዲህ መደረጉን ፈጽሞ አላመኑም።
እማሆይ የልጃቸውንና የምራታቸውን ድርጊት መቋቋም አልቻሉም። የወሰኑትን ሊያደርጉ ራሳቸውን አዘጋጁ።ልብሳቸውን ጠቀለሉ፣ መቋሚያቸውን አነሱ። ጨለማው አላስፈራቸውም።በሩን ከፍተው ወደውጭ ወጡ። ልጃቸው ይመለሱ ዘንድ ጠየቀ። እማሆይ ቃሉን መስማት አልፈቀዱም።
አበበ ከተል ብሎ ልብሳቸውን ጎተተው።አልተመለሱም። ተናደደ፣ ቀኝ እግሩን አንስቶ በእርግጫ ሲመታቸው ከመሬት ወደቁ። አልራራም። በያዘው ሽመል አናታቸውን ብሎ ጣላቸው።እማሆይ በግንባራቸው ድፍት አሉ።አበበ ደነገጠ። እየተንቀጠቀጠ፣ትንፋሻቸውን አዳመጠ። ጸጥ፣ዝም ብለዋል።
ባልና ሚስቱ መሀላቸው የወደቁትን እማሆይ ውቤን እያዩ ተደናበሩ።ከደቂቃዎች በፊት አብረዋቸው የነበሩ እናት አሁን ላይመለሱ ሄደዋል። አይናገሩም፣ አይተነፍሱም፣አይላወሱም። አበበ ደጋግሞ እናቱን እያገላበጠ አያቸው። ለውጥ የለም። ራሱን ይዞ ለመጮህ ዳዳው። የሰራውን ሲያስብ ቃሉ ከአንደበቱ ተወተፈ። በጭንቀት ወዲያ ወዲህ እያለ ተራወጠ። ወዲያው ራሱን ለማጥፋት በገመድ ለመታነቅ ወሰነ።
ሁኔታውን ያየችው ሚስቱ እጁን ይዛ ልታረጋጋው ሞከረች። ይህ ሁሉ የሆነው ከእሷ ጋር በተፈጠረው ጠብ ምክንያት ነው።እናም መላ ልትፈጥር ፣መፍትሄ ልታመጣ ግድ ነው።ሚስት ፈጥና አሰበች። አሁን የሆነው ሆኗል። የፈሰሰ አይታፈስም። የተሰበረ አይጠገንም። ራስን ማጥፋት እንደማይገባ ቀስ ብላ አስረዳችው። ሚስቱ የምትለውን ተረጋግቶ አዳመጠ። ጥቂት ቆይቶም ራስን የማጥፋት ሃሳቡን አስወገደ። ሚስቱ ባመጣችው ድንቅ ዕቅድ ለመስማማት ዓይኑን አላሸም።
ከሦስት ዓመታት በኋላ …
አሁን የወረዳው ፖሊስ በአቅላት ‹‹ወይ በይኝ›› ቀበሌ ደርሷል። ‹‹ጨፍጨ›› ከተባለችው ጎጥ መመላለስ የጀመረው መርማሪ ሳጂን በላይነህ ላቀው ለጆሮዎቹ አዲስ መረጃ እየደረሰው ነው። ውሎ ሳያድር በእማሆይ ግቢ ደርሶ ልጃቸውን ፈለገ። ልጅዬው በአካባቢው መኖር ከተወ ዓመታት መቆጠራቸውን ሰማ። ሳጂን የመነኩሴዋ ልጅ ከመንደሩ የራቀበትን ጊዜ ቆም ብሎ አሰላው። ወቅቱ እማሆይ መንገድ ወጥተው አልተመለሱም ከተባለበት ጊዜ ጋር እኩል ገጠመለት።
የፖሊስ ምርመራ …
የወረዳው ፖሊስ ያዋቀረው የምርመራ ቡድን በስፋት ስራውን ጀምሯል። የእማሆይ ልጅ አበበ ካለበት ተፈልጎ ተጠይቋል።ልጅ እናቱ ከቤታቸው ከወጡ በኋላ ከተማ እየኖረ መሆኑን እየተናገረ ነው። ፖሊስ የሚናገረውን አላመነም። በጥያቄዎች እያጣደፈ እውነቱን መጠየቅ ጀምሯል ።
አበበ አሁንም በእናቱ ገዳም መግባት ከአካባቢው መራቁን እያስረዳ ነው። ፖሊስ የሰማውን መረጃ እያጣቀሰ እውነቱን እንዲናገር መወትወቱን ይዟል ። በእጁ ያለውን አስተማማኝ ማስረጃ አንድ በአንድ ማስረዳት የጀመረው መርማሪ ከአበበ እውነታውን ለመረዳት አልተቸገረም። እናቱን ስለመግደሉ ያመነው ልጅ ከሶስት ዓመታት በፊት ስለሆነው እውነታ አንድ በአንድ ማስረዳቱን ቀጠለ።
ሰላሳ ስድስት ወራት ወደኋላ …
የዛን ቀን ምሽት የእማሆይን መሞት የተረዱት ጥንዶች ሟችን በለበሱት ልብስ ጠቅልለው ራስና እግራቸውን በመያዝ ከቤት አወጧቸው። ርምጃቸው አልተሰማምም።በግቢው ከሚገኝ የሽንት ቤት ጉድጓድ አጠገብ ሲደርሱ ቆም ብለው አስከሬኑን ከዳር አቆዩት። ጊዜ አልፈጁም። በጥልቅ ከተቆፈረው ጉድጓድ ቁልቁል ወርውረው አፈር አለበሱት። ሚስት ድንጋይ እያቀበለች፣ ባል ጠጠርና ጓል እያለበሰ፣ ጉድጓዱ መንገድ እስኪመስል ደፈኑት። ስራቸው ሲጠናቀቅ እፎይታ ተሰማቸው።
ጥንዶቹ ከቤት ሲገቡ የእማሆይ ቀሪ ልብሶች ከተቀመጡበት አገኟቸው።በጋራ መክረው ከውሳኔ ለመድረሰ ቋንቋቸው አልተለያየም። ልብሶቹን ለቃቅመው በእሳት አቃጠሉ።እሳቸውን የሚያስታውሱ ትዝታዎችን አስወግደው ሚስጥር ለመጠበቅ ተማማሉ።
ከቀናት በኋላ ሁለቱም እማሆይ ገዳም ሄደው በቶሎ አለመመለሳቸውን በየፊናቸው አወሩ። ምናኔያቸውን የሰሙ ብዙዎች ያሉትን ሁሉ አመኑ። ቆይተው የተጠራጠሩ ጥቂቶች ያሰቡትን ለፖሊስ ጠቆሙ። ፖሊስ በመንደሩ ደርሶ ተጠርጣሪው ወላጅ እናቱን ገድሎ የቀበረበትን ቦታ እንዲጠቁም አዘዘው። አበበ የተባለውን ለማድረግ ወኋላ አላለም።ከሶስት ዓመታት በፊት ከሚስቱ ተባብሮ እናቱን የቀበረበትን የሽንት ቤት ጉድጓድ መማስ መቆፈር ያዘ። የሟች ልጆች፣ መላው ወዳጅ ዘመድ፣ የአቅላት ‹‹ወይ በይኝ›› መንደርና የጨፍጨፈ ጎጥ ነዋሪ አስከሬኑ በልጃቸው እጅ ተቆፍሮ መውጣቱን ባየ ጊዜ በመረረ ጨኸትና በከባድ ለቅሶ አነባ። ፖሊስ የሟችን አካል በቤተክርስቲያን አጸድ በክብር እንዲያርፍ አደረገ።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወላጅ እናቱን በጭካኔ ገድሎ አስከሬኑን ከሽንት ቤት ጉድጓድ በጨመረው ግለሰብና በወንጀሉ በተባበረችው ባለቤቱ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት በችሎቱ ተገኝቷል። ፍርድ ቤቱ ከዓቃቤ ህግና ከፖሊስ የምርመራ መዝገብ በአግባቡ ተጣርቶ የቀረበለትን ክስ መርምሮ የጥንዶቹን ጥፋተኝነት አረጋግጧል። ፍርድ ቤቱ ህዳር 9 ቀን 2012 ዓ.ም ባሳለፈው ብይንም።አንደኛ ተከሳሽ አበበ ፀጋው በሃያ አንድ ዓመት ጽኑ እስራት፣ እንዲሁም ባለቤቱ ይመኝ አንተነህ በአስራ ዘጠኝ ዓመት ጽኑ እስራት ይቀጡልኝ ሲል ወስኗል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 16/2014 ዓ.ም