አዲስ አበባ፡- የዘንድሮ የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሲከበር የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ያለም ፀጋይ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡
የዘንድሮ የሴቶች ቀን ሲከበርም እነዚህን ሥራዎች አጠናክሮ ለማስቀጠልበሚያስችል መልኩ እንዲሆን ታሳቢ ተደርጓል ብለዋል፡፡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጀማል በከር፤ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚቻለው በተለይም የኢኮኖሚ ተጠቃ ሚነታቸው ላይ ሲሰራ እንደሆነ ተናግ ረዋል፡፡
ለዚህም ሚኒስቴሩ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ከዳር ለማድረስ ሴቶች እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች ለገበያ እንዲያቀርቡ የሚረዷቸውን ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ ከዚህ ውስጥ ‹‹በሬ ለምኔ›› በሚል እንቅስቃሴ የተሠራው ማሳያ ይገኝበታል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰሀርላ አብዱላሂ በበኩላቸው፤ ቀኑን አስመልክቶ መጋቢት ሙሉ ወሩን የሚደረግ የነፃ ሕክምና መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ ሕክምናው በዋናነት የሚያተኩረው የማህፀን መውጣት ችግር ያጋጠማቸውን ሴቶች ሲሆን፤ በዚህም ከ100 ሺህ በላይ ሴቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ በአገሪቱ በመውለድ የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ 10 ሺህ ሴቶች መካከል 100 የሚሆኑት በማህፀን መውጣት ችግር ይጠቃሉ ሲሉ አመልክተዋል፡፡
ወይዘሮ ያለም እንዳሉት፤ ሕክምናውን ተከትሎ አንዱ ሊያጋጥም የሚችለውና እንደ ማነቆ የሚወሰደው የደም ልገሳ በመሆኑ በመጪው እሁድ ‹‹እኔም የመሪነት ሚናዬን እወጣለሁ›› በሚል መሪ ሃሳብ በሚደረገው ሩጫ ላይ የደም ልገሳ መርሐ ግብር ይከናወናል፡፡ ከሩጫው የሚገኘው ገቢም ለተመሳሳይ በጎ ዓላማ እንዲውል ይደረጋል፡፡
በቀጣይም በተጀመረው አግባብ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል፡፡ ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ108 በአገሪቱ ደግሞ ለ43ኛ ጊዜ ‹‹የላቀ ትኩረትና ቁርጠኝነት ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት›› በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2011
በፍዮሪ ተወልደ