ስንሻው የቤቱን በር ከፍቶ ሲገባ ከምሽቱ ስድስት ሰዓት አለፍ ብሏል። ከሚሰራበት ቦታ በጊዜ ቢወጣም ወደ ቤቱ የሚገባው ግን አምሽቶ ነው። መብራት ሳያበራ ሄዶ አልጋው ላይ ዘፍ አለ። ጆሮዎቹን ወደ ውጪ ወረወራቸው፤ ከዝምታ በቀር ምንም አላዳመጠም።
ትናንትና የመንደሩ ሰዎች ሰፈሩን ይልቀቅልን ሲሉ የቀበሌው አስተዳዳሪ ጋ ሄደዋል። በእሱ ያልተማረረ አንድም ሰው ሰፈሩ ውስጥ የለም። ለምን ካላችሁኝ እንዲህ እላችኋለሁ፤ ስንሻው ውሸታም ነው፤ ከውሸቱ በላይ ብድር በመጠየቅ ተወዳዳሪ የለውም። በእነዚህ መንታ ድርጊቶቹ የተነሳ የሰፈሩ ሰው ሁሉ ጠላው። ከዚህ አካባቢ ይራቅልን ሲሉም አመጹበት። ከመንደሩ ሰው ለመሸሽ ሲልም አምሽቶ ወደ ቤት መግባትን ልማድ አደረገው።
ስንሻው የኃጢያት ጠቢብ ነው፤ እውቀቱን ለእኩይ ነገር የተጠቀመ ሰው ቢኖር ስንሻው ብቻ ነው። ከአንድ ሰው የሆነ ነገር ከፈለገ መጀመሪያ ያን ሰው ማሞገስና ማድነቅ ይጀምራል። ሰፈሩ ውስጥ የተበደራቸውን ሰዎች ሁሉ በአድናቆትና በሙገሳ ጀምሮ ኪሳቸውን አራቁቷቸዋል። እሱ ሲናገርና ቅዱስ ጳውሎስ ሲሰብክ አንድ ናቸው። አፉ ጅብ ያጠላ ያህል ነው፤ አፍዝ አደንግዝ አለው።
ብድር ወስዶ ከከለከላቸው የመንደሩ ሰዎች መካከል እማሆይ ምንትዋብ አንዷ ናቸው። ደጀ ሰላም ድረስ ሄዶ ነበር ‹ነገ እመልሳለሁ አዛኝቷ ምስክር ትሁነኝ ብሎ ገንዘቡን የተቀበላቸው። ሁሌም ከእሳቸው ይበደራል፤ አንድም ቀን ግን መልሶላቸው አያውቅም፤ እሳቸውም አንድም ቀን ከልክለውት አያውቁም።
ብዙ ጊዜ ተበድሮ ካስቀረበቸው ሰዎች መካከል እማማ ባንቺ ይርጉ ሌላዋ ናቸው። ሽሮና በርበሬ ወደ ሚሸጡበት የጉልት ገበያ ይሄድና ‹እናት አለሜ ! ይላቸዋል፤ ከአዳፋ ሻሻቸው ያመለጠ ነጭ ሽበታቸውን ወደ ማደሪያው እያጎረ። ከዛም አሳዛኝ አይኑን በእርጅና በሞጨሞጨው አይናቸው ላይ ያስለመልመዋል። ያኔ ወላድ ሆዳቸው ቦጭ..ቦጭ ይላል።
ለምን እንደሚመጣ እያወቁም፤ ‹ምነው..ምን እግር ጣለህ? ይሉታል..። እንደ ሻሻቸው ያደፈ አሮጌ ጃንጥላቸውን ከጸሐዩ ሊከልሉት ወደ እሱ እያዩ።
‹‹ድሀ ምን ማረፊያ አለው፤ ይሄው እባክናለሁ። ‹አይዞህ! ሁሉም ያልፋል፤ መበርታት ነው ይሉታል። እውነት፣ እምነት፣ ደግነት በሚያውቁ አዛውንት አይናቸው እያስተዋሉት።
‹እርሶ እኮ ገነቴ ኖት፣ እርሶ ባይኖሩ ኖሮ ውሻም በጨው አይቀምሰኝ ነበር። ሳይደግስ አይጣላ እርሶን ጥሎልኛል› ሲል ወደ ሰማይ ይመለከታል። ቀጥሎም ‹እንዳው..ነገ የምመልሰው ጥቂት ገንዘብ ካለዎት› ይላቸዋል ፊቱን፣ ነፍሱን አሳዝኖ፣ ባዘነ በተራቆተ ባዶ ሰውነት።
መቀነታቸውን ፈትተው ‹እንካ ይቺናት ያለችኝ፤ ዛሬ ምንም አልሸጥኩም። ይሉታል ከእሱ ባልተናነሰ ኅዘን ውስጥ ወድቀው። በመጣ ቁጥር እንደሰጡት ነው። ካላቸው ከመቀነታቸው ላይ ፈትተው፣ ከሌላቸው ደግሞ አጠገባቸው ከምትሸጠው ወጣት ሴት ላይ ተበድረው ይሰጡታል።
እማማ ባንቺይርጉ ነገን አያውቁትም፤ እርጅና ነው መሰለኝ፤ ነገ መቼ እንደሆነ ዘንግተውታል። ስንሻውም ይሄን ደካማ ጎናቸውን ሰበብ አድርጎ ሁሌ ማታ ማታ ነገ እመልሳለሁ እያለ ገንዘብ ይወስድባቸዋል።
እሳቸው ነገን አያውቁትም፤ አጠገባቸው መጥቶ ገንዘብ ሲላቸው ትናንት የወሰደውን መልሶ የሚጠይቃቸው ነው የሚመስላቸው። ብዙ ቀን ነገ እመልሳለሁ ብሎ የሸጡትን ሁሉ ወስዶባቸው ያውቃል። ብዙ ቀን ነገን ስለማያውቁ በእርጅናቸው ተጫውቶ ያውቃል። ብዙ ቀን በእውነታቸው ላይ ተረማምዶ ዋሽቷቸው ያውቃል። እማማ ባንቺ ይርጉ ቀን ሙሉ የሸጡትን ለእሱ አበድረው ቤታቸው ባዶ እጃቸውን ገብተው ያውቃሉ። ነገ እመልሳለሁ አበድሩኝ ብለው ጎረቤት ሄደው ያውቃሉ።
አሁንም ሰጡት፤ በእውነት፣በእምነት። ሰላላ እጃቸውን ወደ መቀነታቸው ሲሰዱ የተረፈ አንዳችም ገንዘብ አልነበራቸውም። ከመቀነታቸው ላይ ቀና ሲሉ ስንሻውን ካጠገባቸአው አጡት። በርቀት እሱን የሚመስል ሰው አዩ። በምን ፍጥነት ከዚህ እስከዛ እንደሄደ አላውቅ አሉ። ሁሌ ሳያዩት ነው የሚሄደው፣ ሁሌ እንዲህ እንደ አሁኑ ገንዘብ ሊሰጡት የፈቱትን መቀነታቸውን ለማጥበቅ ጎንበስ ባሉበት ነው ትቷቸው የሚሄደው።
ሲመጣ እንጂ ሲሄድ አይተውት አያውቁም። ሲመጣ፣ አጠገባቸው ሲቆም መልአክ ሆኖ ነው፣ ሲሄድ ግን እንደ ሰይጣን ነው.፤ ሳያዩት ሳይሰሙት ብን ብሎ ይጠፋል። ደግሞ አንድም ቀን አመስግኗቸው አያውቅም።
የስንሻውን እግር ተከትሎ አንድ ችግረኛ ‹ስለ ምንተ ስለማርያም..› ሲል ተጠጋቸው። ምን ይስጡት? መቀነታቸው ባዶ ነው። ሻሼ ላይ ካለ ብለው አዳፋ ሻሻቸውን ፈተሹ ለምስኪኑ የሚሆን አንዳች አላገኙም። ወደ ድሀው አዩ፤ እጁን ዘርግቶ እየጠበቃቸው ነው። ከበርበሬው አራት ማንኪያ፣ ከሽሮው አራት ማንኪያ አድርገው በፔስታል ጠቅልለው እንካ አሉት።
‹ይቅርታ እናቴ! የምገዛበት ምንም ፍራንክ የለኝም፤ ልለምን ነው ፊትዎ የቆምኩት፤ በልገሳ የሚሰጡኝ ከሆነ ልቀበልዎት› አለ..ስጦታ መሆኑን ባለማመን።
‹እጄ ላይ የምሰጥህ ሳጣ ነው ሽሮና በርበሬ የሰጠሁህ። የሚያስከፋህ ከሆነ ትንሽ ቆይተህ ናና በገንዘብ እቀይርልሀለሁ› አሉት።
እጃቸውን ስሞ ተቀበላቸው። ከእናት አንደበት ያን ያህል ትህትና ሰምቶ አያቅም። በዘመኑ ለምኖ ካገኘው ሁሉ የያንእለታው በለጠበት። በዘመኑ ከተቀበለው ሁሉ በዛን ቀን ከእኒያ እናት የተቀበለው ላቀበት።
ሰው ለካ እያለው ከሚሰጥ ከሌለው ላይ ቢሰጥ ይበልጥ ኖሯል። ብዙዎች ካላቸው ላይ ነው የሚሰጡት፤ ካላቸው ላይ ካልሆነ ከሌላቸው ላይ ተቀብሎ አያውቅም። ያላቸው ካልሆኑ የሌላቸው ሰጥተውት አያውቁም።
ሰው ገንዘብ ኪሱ ከሌለ የሚሰጠው ያለው አይመስለውም። እኛ ኪሳችንን ብቻ ስለምንፈትሽ እንጂ ልባችንን መፈተሽ ብንችል የምንሰጠው ብዙ ነገር ነበር። እኚህ እናትም ያስተማሩት ይሄን ነው። መቀነታቸው ሲነጥፍ ወደ አዳፋ ሻሻቸው ማተሩ በዛም አንዳች ሲያጡ እነሆ ካላቸው ላይ አካፈሉት። እሳቸው ለእሱ መስጠት ከሰሰቱ ባለጸጋና ከበርቴ መካከል ከመቀነቷ ላይ ፈትታ ያላትን አንድ ሳንቲም ለጌታ እንደሰጠችው ድሀ ሴት ናቸው።
እማማ ባንቺ ይርጉ ስለ ማርያም ተብለው አጥተው አያውቁም። ድሀ ፊታቸው ቆሞ የለኝም ብለው አያውቁም። መስጠት የማይሰለቸው እጅ፣ ማዘን የማይሰለቸው ልብ፣ ጸጋና በረከት የተሞላ ሴትነት። ሁሉን የሚያውቁት ቤት ሲደርሱ ነው፤ አሸቦ በማሰሮው ውስጥ እንደሌለ ቤት ሲደርሱ ነው የሚያውቁት። ሌማቱ ባዶ እንደሆነ፣ ቦሀቃው ሊጥ እንደሌለው የሚያውቁት ማታ ነው፤ ቤት ሲደርሱ ግን ሁሉ እንዳለው ባለጸጋ ናቸው።
ያን ቀን ስንሻው ወደ ቤቱ አልተመለሰም፤ ከእማማ ባንቺ ይርጉ እንደተለየ ከየት መጣ የማይባል መኪና ገጭቶ ገደለው። ደባና ፍርድ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 15/2014