በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን በ1970 አ.ም ታኅሳስ ወር ከወጡ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ እትሞች ዜናዎችን ይዘን ቀርበናል፡፡ ዜናዎቹ ተስፋፊው የሶማሊያ መንግስት በሀገራችን ላይ የከፈተውን ወረራ ለመቀልበስ ይደረግ የነበረውን ርብርብ፣ እየተገኘ ያለውን ድል፣ የዘማች ቤተሰብ እንክብካቤንና የመሳሰሉትን የሚያስታውሱን ናቸው፤ አሁን በሀገራችን ካለው ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ጋር በእጅጉ የሚመሳሰሉም ናቸው፡፡ መልካም ንባብ፡፡
ወራሪው የሶማሊያ ጦር በመደምሰስ ላይ ነው
ሐረር፤(ኢ-ዜ-አ-)፡- አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት ብሎ ለውድ ሀገሩ አንድነትና ነፃነት ቃል ኪዳን የገባው የምሥራቅ ጦር ግንባር ሠራዊት ጠላቱን በማርበድበድና በማጥቃት ላይ መሆኑን ትናንት ከሥፍራው የተላፈው ዜና ገልጧል፡፡ ከተላለፈው ዜና ለመረዳት እንደተቻለው ሠራዊቱ በጃርሶ ወረዳ ሰሞኑን በወሰደው የማጥቃት ርምጃ በሙዳ ጀሐታ ቀበሌ መሽጐ የነበረውን የአድኃሪውን የሞቃዲሾ መንግሥት ጦር ደምስሶ በርከት ያሉ መሣሪያዎችን ማርኳል፡፡ ከማረካቸው መሣሪያዎች ውስጥ ሞርተሮች፤ መድፎች፤ ታንኮች፤ ከባድና መለስተኛ የጭነት ተሽከርካሪዎች፤ በርከት ያሉ ልዩ ልዩ ጥይቶችና ፈንጂዎች ይገኙበታል፡፡ ከዚህም ሌላ ከሶማሌ ጭቁን ሕዝብ ጉሮሮ እየተነጠቀ ለአድኃሪው ዚያድ ባሬ ወታደሮች ስንቅ እንዲውሉ በብዛት የተላኩ እንደ ሩዝ፤ ስኳር፤ ቴምርና ሲጋራ የመሳሰሉ ምግቦች ተማርከዋል፡፡ የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች ቡድን ከኤጀርሳ ጎሮ ከተማ 25 ኪሎ ሜትር ርቆ መደበኛውና ሚሊሺያው ጦር «አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት! እናሸንፋለን!»
እያለ የአባቶቹን ወኔ በአብዮታዊ ስሜት አድሶ የፋሺስቱን የዚያድ ባሬ ቅጥረኞች ለመደምሰስ ወደፊት እንደ ዳልጋ አንበሳ ሲወረወር ለመመልከት ችሏል፡፡ ከዚህም ሌላ በድሬዳዋ ከተማ የሚገኙ ፭፻ መምህራን አብዮታዊ የሥራ ዘመቻ ለማድረግ ጠዋት ትናንት በልዩ ልዩ ተሽከርካሪዎች ወደ ጦር ግንባር ተሰማርተዋል፡፡ እነዚህ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች መምህራን ከድሬዳዋ ከተማ ከ፵ እስከ ፷ ኪሎ ሜትር ርቀት ጀልዴሳ ወደ ተባለው ቀበሌ ተሰማርተው ከጦሩ በሚሰጣቸው መመሪያ መሠረት የሶማሊያ ጦር ጥሎት የሸሸውን መሣሪያ ለመሰብሰብና የአካባቢውም ነዋሪዎች መልሶ ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት ተካፋይ ለመሆን እንደሆነ ቃል አቀባዩ ገልጧል፡፡ የድሬዳዋ መምህራን በግምባር ዘምቶ ከጠላት ጋር በመዋደቅ ላይ ለሚገኘው ሠራዊት ስንቅ የወር ደመወዛቸውን ከ፹ሺህ ፭፻ ብር በላይ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከፍለው ለመጨረስ በተስማሙት መሠረት ከታኅሳስ ወር ፸ ዓ.ም ጀምሮ የየወሩን ክፍያ መጀመራቸው ቀደምብሎ መገለጹ የሚታወስ ነው፡፡ መምህራኑ ትናንት ጠዋት ጎዞአቸውን በጀመሩበት ወቅት የአድኃሪውን የሶማሌ መንግሥት የሚያወግዙ ልዩ ልዩ መፈክሮች አሰምተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ሰሞኑን የድሬዳዋ ከተማ የልዩ ልዩ ጋራዥ ሠራተኞችና በድሬዳዋ ከተማ የሚገኙ ወዝ አደሮች እንዲሁም በድሬዳዋ አካባቢ የሚገኙ በማኅበር የተደራጁ አርሶ አደሮች ባለፉት ሦስት ቀናት ተመሳሳይ የሥራ ዘመቻ አድርገው ትብብራቸውንና ድጋፋቸውን ገልጠዋል፡፡
(የካቲት 5 ቀን 1970 አም)
በወራሪዎች ቤት ንብረታቸው የፈረሰ በመቋቋም ላይ ናቸው
ሐረር፤ድሬዳዋ፤(ኢ.ዜ.አ) በሐረርጌ ክፍለ ሀገር በአድኃሪው የሶማሊያ መንግሥት ወራሪ ወታደሮች ቤት ንብረታቸው ፈርሶባቸው የተሰደዱት በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የኤሬሮ የአዋሬ የሁንደኔ የኩርፋ ጨሌ
ወረዳዎችና ምክትል ወረዳዎች አርሶ አደሮች በአሁኑ ጊዜ ወደ ቤታቸው በመመለስና በመቋቋም ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ አርሶ አደሮች የአድኃሪውን የሞቃዲሾን መንግሥት አመራር ውድቀት የተገነዘቡ በመሆናቸው ከመደበኛው መለዮ ለባሹና ሚሊሺያው ሠራዊት ጎን በመሰለፍ የወራሪውን ጠላት ኃይል በመከላከልና በመደምሰስ ላይ ናቸው፡፡ ቁጥራቸው በርከት ያሉ እነዚሁ ገበሬዎች በሰጡት አስተያየት፤ ወራሪዎቹ የሶማሌ ወታደሮች በሸሪፍ ካሌድሶና በፈዲስ ከተሞች በኢትዮጵያ ተከላካይ ጦር በከባድ ሁኔታ የተመቱ በመሆናቸው የጦር መሣሪያቸውን በያለበት እየጣሉ ወደ መጡበት በመፈርጠጥ ላይ ሲገኙ፤ አብዛኛዎቹም እጃቸውን በመስጠት ላይ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ እንደገና በመቋቋም ላይ ለሚገኙት ለነዚሁ አርሶ አደሮች የአካባቢው ሚሊሺያ ሻለቃ አዛዥና አንድ የፖለቲካ ካድሬ ስለኢትዮጵያ አብዮት ሂደት፤ ስለጊዜው ተጨባጭ ሁኔታ፤ ስለብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት መለስተኛ ፕሮግራም ገለጣ አድርገውላቸዋል፡፡
( የካቲት 2 ቀን 1970 አ ም )
የመድኃኒዓለም ተማሪዎች በሰብል ስብሰባ ተሰማሩ
፩ሺ፫፻ የሚሆኑ የመድኃኒዓለም ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህራንና ተማሪዎች ሁለት ቀን የሚቆይ የሰብል አሰባሰብ ዘመቻ ለመሳተፍ ትናንት በወልቂጤ ወረዳ ወደ ጠደሌ እርሻ ጣቢያ ሄደዋል፡፡ ተማሪዎችና መምህራኑ በዘመቻው የተሳተፉት በመምህራን የውይይት ክበብ አማካይነት በሰፊው ተነጋግረው ባሳለፉት ውሳኔ ነው፡፡ በዚሁ ጊዜ የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር አቶ ሰለሞን አስፋው ባደረጉት ንግግር ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ይህ ትምህርት ቤት የፀረ አብዮተኞች መጠራቀሚያ እንደነበረ አስረድተው በአሁኑ ዓመት ግን አቋሙን ለውጦ ለአገሪቱ ድጋፍ ለመሆን በአዲስ መንፈስ ቆርጠው መነሳታቸውንና ይህንን በአሁኑ ወቅት በተግባር ለመተርጎም መብቃታቸው የሚያስደስት መሆኑን ገልጠዋል፡፡
(ጥር 20 ቀን 1970 አም)
ለእናት ሀገር ጥሪ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር ከ228 ሺህ ብር በላይ ገቢ አደረገ
የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር ለእናት አገር ጥሪ ርዳታ ለመሰብሰብ ባደረገው ቅስቀሳና አስተዋጽኦ እስካሁን ፪፻፳፰ሺህ፶፫ብር ከ፵ ሳንቲም ገቢ ማድረጉን የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ኰሚቴ ለጓድ ሻለቃ ደበላ ዲንሳ የአዲስ አበባ አጠቃላይ የአብዮት ዘመቻ አስተባባሪ ኰሚቴ ሊቀመንበር ትናንት አስታወቁ፡፡ በዚሁ መሠረት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር ካሁን በፊት ሰፊው የአዲስ አበባ ሕዝብ ለዘመን መለወጫ ከለገሳቸው የእንስሳት ቆዳዎች ሽያጭ የተገኘውን ፩፻፷፮ ሺህ ፩፻፺፱ብር ከ፵ ሳንቲም ቀደም ሲል ገቢ ማድረጉን የማኅበሩ የሥራ አስኪያጅ ኰሚቴ ካመለከተ በኋላ፤ ማኅበሩ ጥቅምት ፮ ቀን ፲፱፻፸ ዓ/ም/ በአዲስ አበባ ስታዲየም ለእናት ሀገር ጥሪ ካዘጋጀው በዓል ከተገኘው ፶፰ ሺህ ፰፻፹፩ ብር ከ፷፭ ሳንቲም ውስጥ ፵፰ሺህ አራት ብር ቼክ በትናንትናው እለት ለጓድ ሻለቃ ደበላ ዲንሳ አስረክቧል፡፡ ማኅበሩ ከጥቅምት ፮ ቀን ዝግጅት ካስገኘው ገቢ ውስጥ የአንድ በሬ ጨረታ ሽያጭ ፲፪ ሺህ ብር ቀደም ሲል ገቢ ማድረጉን የሥራ አስኪያጁ ኰሚቴ አስታውቆ፤ ለበዐሉ ዝግጅት ቀርበው የነበሩ ግምታቸው ፩ሺህ ፰፻፶ ብር የሆኑ ሁለት በሬዎች አንድ የበግ ሙክት ለታጠቅ ጦር ሠፈር መሰጠታቸውን አመልክቷል፡፡ የሥራ አስኪያጁ ኰሚቴ ስለዚሁ ጨምሮ በሰጠው ማብራሪያ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር ለእናት ሀገር ጥሪ ገንዘብ በመሰብሰብ ብቻ ሳይወሰን፤ ካለው አነስተኛ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ የማኅበሩ ጠቅላላ ጉባኤ በወሰነው መሠረት ሃምሳ በመቶ ወጪ በማድረግ ፪ሺህ፱፻፸፪ ከ፴፭ ሳንቲም መስጠቱን ለጓድ ደበላ ዲንሳ አስረድተዋል፡፡ (ታኅሳስ 14 ቀን 1970 አም
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 12/2014